የእለት ዜና

የክተቱ ዘመቻ መዳረሻ

Views: 164

በኢትዮጵያውያን ዘንድ ክተት ዐዋጅ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው የጦርነት ጥሪ ነው። ለዚህም ነው ሰሞኑን በአማራ ክልል መሪነት ለቀረበው የክተት ዐዋጅ ከየኹሉም አቅጣጫ ድጋፍና የድጋፍ ሰልፍ የተካሄደው። ስለክተት ዐዋጁ መነጋገሪያ የሆኑ በርካታ ጉዳዮች የነበሩ ቢሆንም ለዛሬ የመዳረሻውን ጉዳይ መርጠናል።

ከጥንት ጊዜ ጀምሮ አንድ የአገር መሪ ወይም የአውራጃና የአገር ግዛት አስተዳዳሪዎች ክተት ብለው ሕዝቡን በዐዋጅ ሲያዙት የታወቀ ልዩ ቦታና የጊዜ ገደብ ያስቀምጡ ነበር። ይህ ልማድ ከስርዓቱ ጋር አብሮ ባይቋረጥም ስሙን የሚወክለው ተግባሩ ግን እንዳልተሟላ የሚናገሩ አሉ። ክተት ዐዋጅ ይነገር የነበረው እረፍት ላይ ሆኖ እያረሰ ለሚኖረው ለመደበኛው ጦርም ጭምር ነበር። ጭፍራ የሚባለው በመደበኛው ዕዝ ውስጥ ገብቶ በማያውቀው አዛዥ የሚዋጋ ሳይሆን የራሱን መርጦ የሚታዘዝበት ነው። ተመልሶ ቢሄድም እንደክህደት ስለማታይበት ነጻነት እንደነበረው የሚናገሩ አሉ።

የዘመኑ ከታች እንደድሮዎቹ የማረከውን አስፈቅዶ የማይወርስበት ጊዜ ላይ እንገኛለን። ይህ ብቻ ሳይሆን እቴጌ ጣይቱ ቃል ገብተው እንደነበረው በጦርነቱ ቢሰዋ ልጆቹን መንግሥት ኃላፊነት ወስዶ ሊያሳድግለትና ሊያስተምርለት እንደሚችል አምኖ አይገባበትም። ለአገር ቢሆንም ዘመቻውም ሆነ የሱ መዝመት የቤተሰቡን ዕጣ ፈንታ እንዳያበላሸው፣ ቢያንስ እርሻው መንደር በቀሩት ተራ ወጥቶ እንዲታረስለትም ይደረግ ነበር።

ሌላው ክተት ሲባል የት እንደሆነ በግልጽ እንዲታውቅ ይደረግ ነበር። ስልጠና ማዕከል ይሁን ቀጥታ ወደ ጦር ግንባር ተበጣጥሶ እንዳይደርስና ለአሰናካዮች ሲሳይ ሆኖ አላስፈላጊ ሰለባ ከሚሆን የታወቀ ቦታ እንዲገኝ መደረግ ነበረበት የሚሉ ሰዎች ሐሳባቸውን ይሰነዝራሉ። በሌላ በኩል እስከመቼ ድረስ ከትቶ መጨረስ እንዳለበት ከቦታው ርቀትና ከዘመቻው አጣዳፊነት አኳያ ተገምግሞ መነገር ነበረበት የሚሉ አሉ። ይህ መሆኑ የዘመቻውን ጊዜ ለማቀላጠፍ፣ ስንቅ ለማዘጋጀትና አላስፈላጊ ድካምንና ወጪን ለመቀነስ እንደሚያግዝ የሚሞግቱም ነበሩ።

ያም ሆነ ይህ፣ የክተት ዘመቻው አላማ ስለታወቀ በየአካባቢው እየተመዘገበ በጋራ እንዲሄድ የመኪና ባለሀብቶችም ዝግጁ እንዲሆኑ መደረጉ ግልጽ ቢሆንም፣ የክተቱን ታሪክም ሆነ ባህል በማያበላሽ፣ አገርንና ሕዝብን በሚጠቅም መልኩ፣ እንዲሁም አላስፈላጊ ደም መፋሰስን በሚያስቀር መልኩ ቢሆን እንደሚመረጥ ብዙዎች ይስማሙበታል። “የቸኮለች አፍሳ ለቀመች” እንደሚባለው፣ እንደነ “ቶሎ ቶሎ ቤትም ግድግዳው ሰንበሌጥ” እንዳይሆን ማን ከየት እንደመጣ ሊታወቅ ይገባል። የሚሞትን ሰው ብዛት ቀንሶ ድል ማድረግ እንጂ፣ የብዙዎች ሕይወት ጠፍቶ ማንም ድል አድራጊ ስለማይባል መጠንቀቁ አይከፋም። ድል የሚነሳው የሚለየው በሔደበት መንገድ እንጂ፣ ባደረሰው የጥፋት መጠን ስለማይሆን ክተቱ ተገቢ መዳረሻ ሊቀመጥለት እንደሚገባ ብዙዎች ይናገራሉ።


ቅጽ 3 ቁጥር 143 ሐምሌ 24 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com