የእለት ዜና

የኮቪድ ወረርሽኝን የዘነጉት የአደባባይ ላይ ሰልፎች

Views: 147

ኮቪድ-19 ኢትዮጵያ ውስጥ የገባበት ጊዜ አገሪቱ ትልቅ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ ውስጥ የነበረበችበት ወቅት ነበር። አገሪቱ ምርጫ የሚደረግበትንም ወቅት በማራዘም ባሳለፍነው ሰኔ ወር ላይ የመጀመሪያውን ዙር አካሂዳለች። ምርጫ ቢካሄድም እንደ አገር ደግሞ ትልቅ ፈተና ውስጥ የተገባበት አንድ ጉዳይ አለ። ይህም በመከላከያ ሠራዊትና አሸባሪ ተብሎ በተፈረጀው ሕወሓት መካከል እየተካሄደ ያለው ጦርነት ነው።
ይህን ያነሳንበት ዋነኛ ምክንያትም የአገርን ኢኮኖሚ ሲያተራምስ የከረመው ኮቪድ-19 ወረርሽኝ አሁን በጦርነት ሳቢያ ትኩረት ተነፍጎት እየተመለከትነው ስለሆነ ነው።

አዲስ አበባ ለኮቪድ-19 እየሰጠች ያለችው ምላሽ የተዘበራረቀ ነው። አብላጫው ገጠር ነዋሪ በሆነባትና 110 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት አገር ውስጥ የጦርነት አዙሪትና መሰላቸት የበሽታው ስርጭት ትኩረት እንዲያጣ ያደረጉ ይመስላል። አዲስ አበባ የሚገኘውን መስቀል አደባባይ ሰበብ እየፈለጉ በሕዝብ ማጨናነቅ ከተጀመረ ብዙ ጊዜያት ተቆጥረዋል። ባሳለፍነው ሳምንትም የተስተዋለው ይህ ነው። ከመከላከያ ጎን እቆማለሁ በሚል በርካታ ወጣት የአዲስ አበባ የሕብረተሰብ ክፍል ታድሞ ነበር። በወቅቱም እንኳን የኮሮና ወረርሽኝ ጉንፋን እንኳን የገባ አይመስልም ነበር። እንደዚህ አይነት ትላልቅ የኮሮና ወረርሽኝ መተላለፊያ መንገዶች እያሉ ትኩረት በመንፈግ የሚያልፉ በርካታ የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የግል መገልገያ ስፍራዎችን የኮቪድ ጥንቃቄ ባለማድረጋቸው ሲያስፈራሩ ይስተዋላሉ።

ኹላችንም እየተመለከትን ያለነው አንዱ የታክሲ አገልግሎት ነው። የታክሲ ሹፌሮች የጫኑዋቸው ሰዎች ማስክ የማያደርጉ ከሆነ እና ተራርቀው የማያስቀምጡ ከሆነ ቅጣቱ አይጣል ነው።
በተለይ ደግሞ ወቅቱ ክረምት እንደመሆኑ መጠን የመንገድ መዘጋጋት እና የትራንስፖርት እጥረት የሚታይ ሆኖ ሳለ አንድ ሰው እንኳን ትርፍ የሚጭን ታክሲ ከተገኘ የቅጣት ደረሰኝ ሲያከናንቡት ይስተዋላል። እውነት ይህ ቅጣት ኮቪድ ወረርሽኝ ለመከላከል ተብሎ የወጣ መመሪያ ነው ወይንስ ቅጣት ላይ ሲሆን ሁሉም ተረባርቦ ኮቪድ-19ኝን የማሸነፍ ሥራ እየሠራ ነው? መልሱን የሚመለከተው አካል ይመልሰዋል።

ከዚህ ውጭ የተለያዩ ለሕብረተሰቡ አገልግሎት ይሰጣሉ የሚባሉ ተቋማት እንደ ሞሎች፣ ሆቴሎች እና ባንኮች ማስክ ሳያደርጉ እና ሳኒታይዘር ሳያስደረጉ አገልግሎት መስጠት አይችሉም።
መንግሥት ሰበብ እየፈለገ ሕዝብ ለሕዝብ በሚያደረገው መተፋፈግ ያልተከላከለውን የኮሮና ወረርሽኝ፣ በመገልገያ ተቋማት እና አገልግሎት ሰጪዎች ላይ ሕግ በማጥበቅ ለመፍታት መሞከሩ የተቃረነ አሠራር መኖሩን ያሳያል።
እንደ መንግሥት የኮሮና ወረርሽኝ መከላከል ይመለከተኛል በማለት መመሪያዎችንና ክልከላዎችን የሚያስተገብረው የጤና ሚኒስቴር የመከላከል ሥራውን በኹሉም ቦታ ዕኩል ማስፈጸም ይገባዋል።
መመሪያ ተብሎ እንደ መንግሥት የሚወጣውም ቢሆን ጊዜና ቦታ በመለየት ለመተግበር ሳይሆን ለኹሉም አኩል የማስፈጸም ተግባር ሲያከናውን ነው ተገቢ የሚሆነው።

ከላይ የተነሳንበትም ከመከላከያ ሠራዊት ጎን እቆማለሁ የተባለው መሰባሰቢያም ቢሆን ትኩረት ሊሰጠው ያስፈልጋል። ማንም ለአገሩ የሚሰራው ጤናው ተጠብቆ መንቀሳቀስ ሲችል ነው። ስለዚህ የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ በጦርነቱ ለሚሳተፉ የአገር ልጅ በሙሉ አስፈላጊውን የመከላከያ ቁሳቁስ ማሟላት ይጠበቅባቸዋል።

እንደ አገር የውጭ አጋሮች ኢትዮጵያ እነዚህን ተግዳሮቶች መፍታት እንድትችል መርዳት ይችላሉ። የዓለም ባንክ በርካታ ሚሊዮን ዶላር የሚገመት የዓይነት አስቸኳይ ድጋፍ በማድረግ እንደጀመረው መንግሥት የኮሮናን ስርጭት ለመቆጣጠር ለሚያደርገው ጥረት ድጋፍ ከማድረግ በተጨማሪ፣ እነዚህ አጋሮች መጪውን ወቅት መንግሥት ለብቻው የሚወስዳቸውን ዕርምጃዎች ለመቀነስ ምቹ ሁኔታዎችን ለመፍጠር የሚያግዙ ተጨማሪ ሥራዎችን በመሥራት መጥቀም አለባቸው።

ከኹሉም በላይ ልንረዳው ያልቻለነው ጉዳይ ቢኖር ኮሮና ወረርሽኝ ቦታ እና ጊዜ የማይመርጥ በሽታ መሆኑን ነው። የኮቪድ-19 በሽታ እስከ አሁን ድረስ በዓለም ዙርያ ከፍተኛ ሞት እና ጉዳት አስከትሏል። እስካሁን ካደረሰው ጉዳት ሁሉ የከፋ ጉዳት ገና ወደፊት ሊመጣ ይችላል። ከኢትዮጵያ ተጋላጭነት አንጻር ደግሞ በሽታው በሕዝቦቿ መካከል በስፋት ቢሰራጭ አገሪቱ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ አለመረጋጋት ሊገጥማት ይችላል። በሌላ በኩል ቀውሱ አንዳንድ መልካም አጋጣሚዎችንም ፈጥሯል። ወረርሽኙ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ጉልህ ለውጥ በማምጣት ወደ ከፍተኛ ደም መፋሰስ ሊያመራ የነበረውን የምርጫ የጊዜ ሰሌዳውን ለማራዘም በቂ ምክንያት እንዲኖር አድርጓል።

መንግሥት ማስክ መጠቀምን ግዴታ ካደረገ የሰነባበተ ቢሆንም አሁንም ድረስ በርካታ መሰባሰቦች እና ማስክ ያለመጠቀም ልማዶች ከዛም አልፎ የመጨባበጥ እና የመተቃቀፍ ድርጊቶች ተበራክተዋል።
ለኮቪድ -19 መስፋፋት ቸልተኛ የሆነው ሕብረተሰቡ ብቻ ሳይሆን መመሪያን እንዲጣስ የፈቀዱ ሕግ አስከባሪዎች፣ በየሰበቡ ሕዝብ እንዲሰባሳብ የሚያደርጉ የመንግሥት መዋቅር ውስጥ ያሉ ግለሰቦች ተጠያቂ ናቸው።
የጤና ሚኒስቴር ሕብረተሰቡን ማስክ ለመጠቀም ቸልተኛ ሆነ ብለው የሚወነጅሉ ቢሆኑም፣ መንግሥት ግን ራሱ በሚያስተባብራቸው ሰልፎች የበሽታውን የማስተላለፊያ መንገዶችን እያስፋፋ በመሆኑ ሀይ ሊባል ይገባዋል።


የኮቪድ-19 ወረርሺኝ ክትባት ዙሪያ የሚሰራጬ አሉታዊ ዘገባዎችን መከላከል እንደሚገባ ተገለጸ
የኮቪድ -19 ክትባቶችን ተደራሽ ለማድረግ ትክክለኛ መረጃዎች በአግባቡ ማድረስ እንደሚገባ ተገለጸ።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ክትባትን በሚመለከት የሚሰራጩ አሉታዊ ዘገባዎችን ለመከላከል እና ትክክለኛ መረጃዎችን ለማሰራጨት ሚዲያዎችን መጠቀም እንደሚገባ የጤና ሚኒስቴር የእናቶች እና ህጻናት ጤና ዳይሬክተር መሰረት ዘላለም (ዶ/ር) ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የክትባት ስራዎች ከተጀመሩ ረጅም ዓመታት የተቆጠረ ሲሆን በዚህም የክትባት ፕሮግራም በሚሊየን የሚቆጠሩ ህጻናትን መታደግ ተችሏል ሲሉ መሰረት ገልጸዋል።
እንደ ሃገር በኮቪድ-19 ወቅት 15 ሚሊዮን ህፃናትን የኩፍኝ ክትባት ተከትበው ዓለም አቀፍ ዕውቅና ማግኘቱን መሰረት አክለው ገልጸዋል።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ስርጭትን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ህብረተሰቡን ከፍተኛ የማነቃቂያ ስራዎችን መስራት እንደሚያስፈልግ በጤና ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና ኮምኒኬሽን ዳይሬክተር ተገኔ ረጋሳ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
ከኮቪድ 19 ክትባት ጋር ተያይዞ በተለያዩ አካላት እየተስራጩ ያሉ የተዛቡ መረጀዎች መኖራው የታወቀ ሲሆን መረጃዎችን ከጤና ሚኒስቴር ብቻ በመውሰድ መጠቀም እንደሚገባ ተገኔ አሳስበዋል።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝ እና ክትባቱ ላይ ትኩረቱን ያደረገ ስለጤና መረጃዎች ላይ የሚመክር የውይይት መድረክ ከጤና ሚኒስቴር የእናቶች እና ህጻናት ጤና ዳይክቶሬት ፣ የህዝብ ግንኙነት እና ኮምኒኬሽን ዳይሬክቶሬት፣ የሕግ ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት እንዲሁም ጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም ዳይሬክቶሬት እና ከተለያዩ አጋር ድርጅቶች ከተውጣጡ ተወካዮች ጋር ተካሂዶ ነበር።


የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኮቪድ-19 የተዘጉ ትምህርት ቤቶች በድጋሚ እንዲከፈቱ ጥሪ አቀረበ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በኮቪድ-19 ምክንያት የተዘጉ ትምህርት ቤቶች እንዲከፈቱ ጥሪ ማቅረቡ ተገለጸ።
የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ተከትሎ በትምህርት ቤቶች መዘጋት ምክንያት 600 ሚሊዮን ተማሪዎች የመማር ሕልወናቸው አደጋ ላይ መውደቁን ድርጅቱ አስታውቋል።
የመንግስታቱ ድርጅት የሕጻናት ፈንድ (ዩኒሴ) ቃል አቀባይ ጄምስ ኤሌደር ከጄኔቭ እንደገለጹት፣ መንግሥታት የኮሮና ቫይረስ ቀውስና የበሽታውን ስርጭት፣ ሊያጋጥማቸው የሚችለውን ችግር በማሰብ ትምህርት ቤቶችን መዝጋታቸው ከባድ ውሳኔ መሆኑን በመረዳት ሊቀጥል እንደማይገባው ገልጸዋል።
“ኮቪድ 19 ወረርሽ ሆኖ ከተከሰተበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ባለ መረጃ ትምህርት ቤቶችን መዝጋት የመንግሥታት የመጀመሪያ ውሳኔ እንደነበር ሁሉ፣ በድጋሚ መክፈትም የመጀመሪያ ውሳኔያቸዉ መሆን ይገባው ነበር“ ሲሉም አሳስበዋል።
ከትምህርት ቤቶች በፊት መጠጥ ቤቶችን እና ሌሎች አገልግሎቶች መጀመሩን አስከፊ ስህተት እንደሆነም ቃል አቀባይዋ ተናግረዋል።
ትምህርት ቤቶችን ለመክፈት ሁሉም መምህራንና ተማሪዎች ክትባት እስኪወስዱ መጠበቅ አይቻልም ያሉት ቃል አቀባዩ፣ አክለውም ወረርሽኙ ያስከተለው ኢኮኖሚያዊ ችግር ቢኖርም መንግሥታት የትምህርት በጀታቸውን ጠብቀዉ እንዲቆዩም ጥሪ አቅርበዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 143 ሐምሌ 24 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com