የእለት ዜና

በቶኪዮ የክብር ሸማችንን የገፈፈን ማነው?

Views: 164

አብይ ወንድይፍራው እንደአዲስ ማለዳ ጋዜጣና መጽሔት በቻምፒየን ኮሚኒኬሽን ሥር ከሚታተመውና ትኩረቱን በምጣኔ ሀብት ዙሪያ ካደረገው Ethiopian Business Review የእንግሊዝኛ መጽሔት የስፖርት ቢዝ (Sport Biz) ዓምድ አዘጋጅ ሲሆን፣ የቶኪዮ 2020 የኦሊምፒክ ዝግጅቶችን ለመዘገብ እና ለመተንተን በስፍራው ከተገኘ ሳምንት አስቆጥሯል። አብይ ለአዲስ ማለዳ ተደራሲያን ይመጥናሉ ያላቸውን ግላዊ ትዝብቱን፣ እንዲሁም ማራኪ ናቸው የሚላቸውን የኦሊምፒክ ታሪኮች ሊያጋራን እነሆ የመጀመሪያውን ጽሑፉን ልኮልናል።

ኦሊምፒክ ትልቅ ነው፤ በይዘቱም በዝግጅቱም ብሎም በትርጉሙም በእጅጉ ይሠፋል። ሆኖም ትልቁ ኦሎምፒክ ያለ አትሌቲክስ ምንም ነው ሊባል ይችላል። ውበቱም ድምቀቱም በአመዛኙ የአትሌቲክስ፣ የፊልድ እና የትራክ ውድድሮች ናቸው። የአትሌቲክስ ከዋክብት የኦሊምፒክ መልክ ናቸው። ይህንን እውነታ ዓለም ዐቀፉ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን ብቻ ሳይሆን የኦሊምፒክ ደጋሹ ኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ ይስማሙበታል።

በኦሎምፒክ መንደርም ይሁን ለጋዜጠኞች ብቻ ተለይቶ በተዘጋጀው የሚዲያ ማዕከል የሚታየው ድባብም ይህንን ያረጋግጣል። ከሐምሌ 16 አንስቶ ሲካሄድ የቆየው የቶኪዮ ኦሊምፒክ ድምቀቱ እየጨመረ መጥቷል። በቶኪዮ ኹለቱ የአውሮፕላን ማረፊያዎች በየዕለቱ የሚደርሱ እንግዶች ቁጥርም በእጅጉ ጨምሯል። እነዚህ ድግሱ ሲሞቅ ጊዜ ጠብቀው የሚመጡት ናቸው። በእርግጥም አትሌቲክስ የኦሊምፒክ ጣዕም እጅግ አስፈላጊው ክሬም እንደማለት ነው።

ይህ እውነታ ኹለቱንም ማለትም የዓለም ዐቀፉን ኦሊምፒክ ኮሚቴ እና አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን ያግባባቸዋል፤ እንደአስፈላጊነቱ በጥምረት አብረው እንዲሠሩም ምክንያት በመሆኑ። ይሄንን እውነታ በተመሳሳይ ወደ ኢትዮጵያ ዓውድ ስንገለብጠው ትርጉሙም ውጤቱም ሌላ ነው። ኹለቱን ዓለም ዐቀፍ ተቋማትን ያግባባቸው ተመሳሳይ ምክንያት በኢትዮጵያ ላሉት የኹለቱ ተቋማት ተወካዮች ያለመግባባት ዋነኛ ሰበብ ሆኖል። ላለፉት ኹለት ዓመታት ገደማ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሜቴውና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ተቋማዊነታቸውን ያጡና አብረው መሥራት የተሳናቸው ሆነው ታይተዋል። በይበልጥ ኦሊምፒኩ ሲቃረብ ደግሞ በቀደሙት ወራት በደብዳቤ ልውውጦችና በስብሰባዎች ሲቀጣጠል የቆየው ቁርሾ በአደባባይ ፈንድቷል። ከአደባባይም በትልቁና በዓለም ዙሪያ ሚሊዮኖች በሚታደሙበት የኦሎምፒክ መድረክ ገመናቸው ራቁቱን አደባባይ ተሰጥቷል።

እንዳለመታደል ሆኖ በኦሊምፒክ መክፈቻው ሥነ ስርዓት የተፈጠረው ተቋማቱን ወደ በለጠ ብሽሽቅ መራቸው እንጂ ባልተገባ መስዋዕትነት እንደተገኘ ትምህርት እንኳን አልተወሰደም። ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስም ሆኑ የፌዴሬሽኑ ፕሬዝደንት ሌተናል ኮሎኔል ደራርቱ ቱሉ በሰዓታት ውስጥ በሚዲያ ቀርበው ተወነጃጅለዋል። የኦሎምፒክ ኮሚቴ መሪ ብልጠት በተሞላበት አገላለጽ ጥፋቱን ሁሉ ወደ ቀድሞዋ አትሌት ደራርቱ ቱሉ እና በእርሷ ወደሚመራው ተቋም እንዲሁም ሌሎች ተወካዮቻቸው ሲያላክኩ፣ ደራርቱም በእምባም ጭምር በታጀበ ስሜት ተመሳሳዩን አድርጋለች። የኦሊምፒክ ኮሚቴና የፌዴሬሽኑ ፌስቡክ ገፆች ከሚያሰራጯቸው መረጃዎች አንስቶ እስከሚጠቀሟቸው ፎቶግራፎች ተቋማቱ በወንድማማችነት፣ በመደጋገፍና በጨዋነት ሠላማዊ እና የተሻለች ዓለምን ስለመፍጠር ከሚሰብከው የኦሊምፒክ ተልዕኮ ጋር የተጣሉ ያስመስላቸዋል።

የልዩነት ምክንያት…
በኹለቱ ግዙፍ የስፖርት ተቋማት ወይም በተቋማቱ መሪዎች መካከል ያለውን ልዩነት ብዙዎች የሚገነዘቡበት መንገድ ትክክል አይመስልም። በማኅበራዊ ሚዲያው ላይ የሚስተዋሉ አስተያየትና ትችቶች ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስን ተፈጥሯዊ ግትርና ‹ሀይ ባይ ያጣ በጥባጭ› ብቻ አድርገው ይስሏቸዋል። ተወዳጇን ደራርቱንም በቅን ልቧ ልትፋለመው የማትችለውን ግብ ግብ ውስጥ ድንገት ራሷን ያገኘች አድርገው ይመስሏታል። ሌሎች ደግሞ የቀድሞዋ አትሌት የአስተዳደራዊ ክህሎት ላይ ያላቸውን የብቁነት ጥያቄ እያነሱ የድርሻዋን ተጠያቂነት ልትወስድ እንደሚገባ ይሟገታሉ። በአጭሩ ለብዙዎች ከአዲስ አበባ ጽ/ቤቶቻቸው ወጥቶ ቶኪዮ የደረሰውን የኹለቱ ተቋማት የተካረረ የአቋም ልዩነት የዶክተር አሸብር እና የደራርቱ ወይም ከጀርባ ያሉ ሌሎች ግለሰቦች ጉዳይ ብቻ ያደርጉታል።

በተቋማቱ መካከል በተፈጠረው እና እየተባባሰ ለመጣው ልዩነት ግለሰባዊ እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ስሜት ቦታው ከፍ ያለ ቢሆንም፣ የሁሉም ችግር መነሻ ግን አይደለም። ኦሊምፒክ ኮሜቴና አትሌቲክስ ፌዴሬሽን እጅግ የተራራቀ ሊባል የሚችል የሥራ ድርሻ እና የኃላፊነት መደበላለቅ ችግር ገጥሟቸዋል። በተለይ ኦሊምፒክን በተመለከተ አትሌቶች የት ሆቴል ይረፉ ከሚለው አንስቶ አገሪቱ በየትኞቹ አትሌቶች ትወከል እስከሚለው ውሳኔ ሒደት ድረስ መግባባት አልቻሉም። ሌላው ቀርቶ በአትሌቶች የትጥቅ እደላ ላይ እንኳን በቀላሉ መግባባት የዳገት ያህል ፈታኝ ሆኖባቸዋል።

ፌዴሬሽኑ ኦሊምፒክ ኮሚቴውን ‹‹ቴክኒካዊ በሆኑ ጉዳዮቼ ጭምር በሥራዬ ጣልቃ ይገባብኛል›› ሲል በመጨረሻዎቹ የቶኪዮ የጉዞ ዝግጅቶች ወቅት ያለ ይሁንታው በብሔራዊ ቡድኑ ስብስብ ውስጥ እንዲካተቱ የተደረጉ ወይም ሙከራ የተደረገባቸውን የአትሌቶች ዝርዝር ለውጦች እንደማስረጃ ያቀርባል። ኦሊምፒክ ኮሚቴ በበኩሉ ፌዴሬሽኑን ‹‹አትሌቶችን እንደመያዣ እየተጠቀመ እጅ ለመጠምዘዝ የሚሞክር›› አድርጎ ይወቅሰዋል። ሆኖም እስካሁን በተዘጋጁ የጋራ መድረኮችም ይሁን የተናጠል የሚዲያ ቃለ ምልልሶች ከተቋማዊ ሥልጣንና አንፃር በኹለቱ መካከል ያለ ግልፅ አለመግባባት ሲነገር አልተደመጠም። የማያባራው መወነጃጀል ቶኪዮ ዘልቆ በተለይ የማኅበራዊ ሚዲያውን ትኩረት ይዟል:፡ የኦሊምፒክ ኮሚቴና የፌዴሬሽኑን መሰረታዊ ያለመግባባት ምክንያት ቀርቦ ለሚመለከት ሰው ጉዳዩ የተቋማዊ አቋም እና ድንበር መደበላለቅ መሆኑ በግልፅ ይታየዋል።

ቢዘገይም እንኳን በግልፅ ንግግር ተደርጎበት ልዩነቱ ካልተፈታ ጉዳዩ ቶኪዮ ላይ የሚቋጭ አይሆንም። ዶ/ር አሸብር እና ደራርቱ ቦታቸውን ለቀው ቢሄዱም እንኳን ችግሩ በተተኪዎቻቸው መቀጠሉ አይቀሬ ይመስላል።

ገላጋይ የለም?
ይሄ የብዙዎች ጥያቄ ነው። ስፖርቱን ከውድቀት አገርን ከውርደት ደርሶ የሚታደግ ሽማግሌ ከወዴት አለ ሲሉ የሚማፀኑ አልጠፉም። ለዚህ ሚና በግንባር ቀደምነት የሚታጨው ኃይሌ ገ/ሥላሴ ነው። ኃይሌ ከስፖርቱም አልፎ አገራዊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የሚሳተፍ እና እጅግ ተፅእኖ ፈጣሪ ግለሰብ ቢሆንም፣ ለኦሊምፒክ ኮሚቴና ለፌዴሬሽኑ ግን በገለልተኝነት በሽምግልና ለመቆም የሚያስችል አቋም ላይ መገኘቱ አጠራጣሪ ነው። በአሁኑ ወቅት የኦሊምፒክ ኮሚቴው ም/ፕሬዝደንት ከመሆኑ ሌላ ከአንዳንዶቹ አከራካሪ ውሳኔዎች ጀርባ ሊኖር እንደሚችል ግምት አለ። በሌላ በኩል ከጥቂት ዓመታት በፊት ከፌዴሬሽኑ ፕሬዝደንትነት በፈቃዱ የለቀቀበት በሆድ ይፍጀው የቀረ ምስጢርም በአገሪቱ አትሌቲክስን ለሚመራው ተቋም በገለልተኝነት እንዲቆም የሚያስችለው አይመስልም።

ሌላው ለሽምግልና ተጋባዥ መንግሥት ነው። ደራርቱ ውዝግቡ ሲካረር በተደጋጋሚ ጊዜ በግልፅ ቋንቋ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጣልቃ ገብተው ስፖርቱን እንዲያድኑ ጥሪ አድርጋለች።
ነገር ግን፣ ይሄ በራሱ አከራካሪ ብቻ ሳይሆን በእጅጉ ጥንቃቄ የሚፈልግ ጉዳይ ነው። ቢያንስ እስከአሁን ድረስ በመንግሥት በኩል በውስጥ የሚደረጉ ግፊቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ መገመት ቢቻልም፣ በአደባባይ የሚታይ ይህ ነው የሚባል ተፅእኖ ወይም ግልፅ አስተዳደራዊ ጣልቃ ገብነት አልተስተዋለም። በመንግሥት አካላት በኩል የሚስተዋለው ዝምታ ዓለም ዐቀፋዊ በሆኑ የስፖርት አስተዳደራዊ መዋቅሮች ውስጥ እጅን ማስገባት የሚያስከተለውን መጥፎ ውጤት በማጤን የመጣ ስለመሆኑ በእርግጠኝነት ለመመስከር ያስቸግራል። ቢያንስ ግን እስከአሁን በተቋማቱ መካከል ባሉት ልዩነቶች ላይ መንግሥት በግልፅ ሸንጎ አልተቀመጠም።

ውዝግቦቹና አትሌቶቻችን
የኦሊምፒክ ኮሚቴና ፌዴሬሽኑ ውዝግብ አሁን አትሌቶቹን ተከትሎ ኦሎምፒክ መንደር ገብቷል። በተቋማቱና በባለሙያዎቻቸው ከመግባባት ላይ ሳይደረስ ‹‹በሥልጣን›› የተላለፉ የአትሌቶች ምርጫ ውሳኔዎች ችግር አምጥተዋል። ላለፉት ወራት ተከባብረው አብረው ሲለማመዱ በቆዩ እና በተመሳሳይ የውድድር ዓይነቶች ለአንድ ባንዲራ በሚወዳደሩ ከዋክብት መካከልም ልዩነት አምጥቷል። ለወትሮው ጓደኛሞች በነበሩ አሰልጣኞች እና የአትሌት ማኔጀሮችም መካከል በጥርጣሬ መተያየትን ወልዷል። ያለመግባባት ማዕበሉ ሽፋኑን እያሰፋ መጥቶ የስፖርት ጋዜጠኞችን ወደ ግብግቡ ጋብዟል። በሳምንታት ውስጥ በተፈጠረ መካረር መካከለኞቹ ፅንፍ ሲይዙ፥ ገለልተኞቹ ጎራ ለይተው ጠቡን ተቀላቅለዋል። በዚሁ ሁሉ መካከል በታላቁ ኦሊምፒክ ድል ለማምጣት አእምሮዊ እና አካላዊ ዝግጅት የሚያስፈልጋቸው አትሌቶቻችን የሚገኙበትን ሁኔታ መረዳት አያስቸግርም። በየዕለቱ የሚወጡት ደስ የማያሰኙ ዜናዎች ትኩረታቸውን እንዲሰበስቡ የሚያግዟቸው አይደሉም። እያንዳንዱ ቀን ሰዐት ተዘርዝሮ ለወራት ብሎም ለዓመታት ዝግጅት በሚደረግበት ኦሊምፒክ የኢትዮጵያ አትሌቶች ስለእያንዳንዱ ቀን እርግጠኞች እንዳይሆኑ ተፈርዶባቸዋል። ከወራት ዝግጅት በኋላ ከሆቴል ወደ ኤርፖርት ሲጓዙ እንኳን ከቦሌ አጥር ስለማለፋቸው እርግጠኞች እንዳይሆኑ ሆነዋል። በአውሮፕላን ተሳፍረው ቶኪዮ ከደረሱም በኋላም ቢሆን የኦሊምፒክ መንደርን ስለመርገጣቸው መተማመኛ የሚሰጣቸው አያገኙም። በዚህ ሁሉ ሒደት አልፈው ውጤት ባይሆንላቸው የሚከተላቸውን በማኅበራዊ ሚዲያ የሚቀጣጠል የሕዝብ ቅሬታና ቁጣም ይታሰባቸዋል።

ሆኖም በቶኪዮ ሰማዩ ጭጋግ የወረሰው አይደለም። ተስፋቸውም ደብዝዞ እንደሆነ እንጂ ጨርሶ የጠፋ አይደለም። አትሌቶቻችን በግል ሮጠው እንደ አገር ማሸነፍ ያውቁበታል። በተቋማዊ ብቃት እዚህ አልደረሱምና፥ በተቋማዊ ምስቅልቅል እንደማይሰበሩ ተስፋ ማድረግ እንችላለን። ከአበበ ቢቂላ ጋር በነገስንባት በቶኪዮ በመክፈቻው ዕለት ማዕረጋችን ተገፍፎ ራቁታችንን ወጥተናል። በዚያው አደባባይ ደግመን ቀና ብለን ለመታየት ተስፋ አለን። በአትሌቶቻችን ተስፋ አለን! እንደሁልጊዜውም ብቻቸውን ታግለው ይዘውን ይወጣሉ። ጥርሳቸውን እያፋጩ፣ አምጠው፣ ቃተው የለመድነውን የክብር ሸማችንን ይደርቡልናል። በዓለም ኹሉ ፊት ወርቅ ያለብሱናል። በአትሌቶቻችን ዛሬም ተስፋ አለን!


ቅጽ 3 ቁጥር 143 ሐምሌ 24 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com