የእለት ዜና

የመሪ ያለህ!

በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ወታደራዊ ዘመቻ ከተጀመረ አንስቶ በርካታ ስህተቶች እንደተፈፀሙ የሚናገሩ አሉ። ከእነዚህ መካከል መከላከያ ትግራይን ለቆ የወጣበትን ምክንያት የማይቀበሉ ድርጊቱን ሲተቹት ይሰማል። ይህን ተግባር ደርግ ትግራይን ለቆ ከወጣበት ሂደት ጋር እያነፃፀሩ ግዛቸው አበበ እንዲህ ያስነብቡናል።

ቤኒሻንጉል ክልል አንዴ ወያኔዎች፣ ሌላ ጊዜ ሱዳኖች አንዳንዴም ግብጾች በስተጀርባ አሉበት እየተባለ ሰበብ በሚሰጥባቸው ጥቃቶችና ግጭቶች ብዙዎች በአረመኔያዊ ግፍ ተገድለዋል፣ ተሰንክለዋል፣ ተሰድደዋል። ክልሉ በወታደራዊ ዕዝ ስር ገብቶም ችግሩ የሚቆም አልሆነም። ወታደራዊ ዕዙን የሚመሩ የጦር መሪዎች ‘ችግሩን መቅረፍ ያልተቻለው ለምንድን ነው?’ ተብለው ሲጠየቁ ‹አካባቢው በጥቅጥቅ ደንና በጫካ የተሸፈነ ስለሆነ ለወታደራዊ ዘመቻዎች አመች አልሆነም፣ ታጣቂዎቹ ጥቃቶችን አድርሰው ወደ ጫካው እየገቡ ስለሚሰወሩ እነሱን መቆጣጠሩ ከባድ ሆኗል› የሚል መልስ ሰጥተዋል።

ሰኔ 2013 ‹ሕግን ለማስከበር› በተባለለት ዘመቻ ወደ ትግራይ የዘመተው ጦር ሳይታሰብ ትግራይን ሙሉ በሙሉ ለቅቆ ወጥቷል። ይህን ማፈግፈግ ያስከተለ ተብሎ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ምክንያት የተሰጠው የትግራይ ሕዝብ በሙሉ ለኢትዮጵያ ጦር ጠላት ሆኖ ስለተሰለፈ፣ ከበርበሬና ገጀራ ጀምሮ በተገኘው መሳሪያ ሁሉ ጦሩን እያጠቃ መሆኑንና የትግራይ ሕዝብ ለኢትዮጵያ ጦር ደጀን ስላልሆነ ከትግራይ መውጣቱን ተገቢነት ለማሳየት ተሞክሯል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ ጦር ውስጥ ሕዝቡ በጅምላ ጠላት እየሆነብን ነው የሚል ስሜት እየተፈጠረ መሆኑንና ጦሩ ሕዝብን አጥቅቶ መጥፎ ታሪክ እንዳይጽፍ ለመጠንቀቅ ጦሩን ከትግራይ ማውጣት ማስፈለጉን ተናግረዋል። አያይዘውም ትግራይ ውስጥ መዋጋትን ከደጀን ሕዝብ ርቆ እንደመዋጋት አድርገው ከመግለጽ አልፈው፣ በመቀሌ አካባቢ መዋጋትን በባድመ ጦርነት ወቅት በኤርትራ ውስጥ በምትገኘው በቶኮምቢያ ከሻዕቢያ ጋር ከማዋጋት ጋር አነጻጽረውታል።

የትግራይ ሕዝብ የ15 ቀናት ወይም የወራት ዕድሜ ያለው የጽሞና ጊዜ ቢሰጠው ሐሳቡን ሊቀይር እንደሚችል፣ የትግራይ ሕዝብ ከሕወሓትና ከብልጽግና መንግስት የሚበጀው ማን መሆኑን ልብ እንዲል ያደርገዋል በማለት፣ ትግራይን ጥሎ የመውጣቱን ተገቢነት ለማሳየት የሞከሩ በርካታ የብልጽግና ባለስልጣናት ብቻ ሳይሆኑ እነ ዶ/ር አረጋዊ በርኸን የመሳሰሉ የትግራይ ተወላጆችም ጭምር ናቸው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ መቀሌ እንደ ዓብይ ዓዲ፣ እንደ ሸራሮ፣ እንደ በሻሻ የሆነችበት ሥራ ስለተሠራ ሕወሓት እንደ ስጋት ሊታይ አንደማይገባው የተናገሩ ቢሆንም፣ የጦሩ በትግራይ መቆየት በደርግ ዘመን ሲሆን እንደነበረው ወያኔ የጦሩን መሳሪያ፣ ቀለብና የሰው ኃይል እየማረከ እንዲደራጅ ማድረግን ሊያስከትል እንደሚችል፣ በኤርትራ ምድር አገርን የማዳን ጦርነት ለብዙ ዓመታት ቢደረግም ኤርትራን ከመገንጠል እንዳላዳናት በማውሳት ትግራይን ለሕወሓት ትቶ ለመውጣቱ የተሰጠውን ምክንያት አነጋጋሪና የተምታታ እንዲሆን አድርጎታል። ይህ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አነጋገር ሕወሓት ትግራይን ሊገነጥል እንደሚዋጋና ይህን የግንጠላ ዘመቻ በጦር ኃይል ለማምከን መሞከር ኪሳራ እንጅ ትርፍ እንደሌለው አድርገው እንደተናገሩ ተደርጎ እየተተረጎመ ነው።

ይህን መሰል ምክንያት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ይሰጥ እንጅ፣ የኢትዮጵያ ጦር ከትግራይ ይውጣ ብሎ ጥያቄ አቀረበ የተባለለት የትግራይ ብልጽግና ቡድን የሰጠው ምክንያት ከዚህ የተለየ ነበረ። ትግራይን እያስተዳደረ ነው ሲባልለት የነበረው የትግራይ ብልጽግና ቡድን የትግራይ ገበሬዎች እፎይ ብለው የእርሻ ሥራቸውን እንዲያካሂዱ ታስቦ መሆኑን የሚያሳይ፣ ማፈግፈጉም የእርሻ ሥራው እስኪጠናቀቅና ገበሬዎች ምርታቸውን እስኪሰበስቡ የሚራዘምና የእርሻው ሥራው ሲጠናቀቅ የኢትዮጵያ ጦር ወደ ትግራይ እንደሚመለስ የሚጠቁም እንደምታ ያለው ነበረ። ኢትዮጵያ ከሌላ አቅጣጫ ችግር ሊጋረጥባት ስለሚችል ጦሩ በትግራይ መቆየቱ ተገቢ አይደለም የሚል ምክንያት በወታደራዊ ባለሥልጣናት መሰንዘሩም የሚዘነጋ አይደለም።

የኢትዮጵያ ጦር የትግራይን ግዛት ለቅቆ መውጣቱን ተከትሎ ሕወሓት በአማራ ክልል ላይ ጦርነት ከፍቷል። ጦርነቱ ኮረምንና ግራካሶን አልፎ አላማጣ፣ በሌላ በኩል ደግሞ እስከ አበርገለና ማይጸብሪ አካባቢዎች ተስፋፍቷል። ‘ይህን የሕወሓት መስፋፋት መከላከል ያልተቻለበት ምክንያት ምንድን ነው?’ የሚል ጥያቄ ከሕዝብ ዘንድ ሲነሳ በአማራ ብልጽግና ቡድን የተሰጠው ምክንያት ቡድኑ ሕጸናትን፣ ሽማግሌዎችን፣ ቀሳውስትንና መነኩሴዎችን ከፊት ለፊት እንደ ሰብዓዊ ጋሻ እያሰለፈ ስለሚመጣ መከላከል ውጊያ ማድረጉ ኢሰብዓዊ የሆነ ተግባር ለመፈጸም የሚያስገድድ ስለሆነ ማፈግፈግ ተመራጭ ሆኗል የሚል ዓይነት ነው። ሕወሓት በአፋር በኩል ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎም የአፋር ክልል ብልጽግና ተመሳሳይ ምክንያት ሰጥቷል።

የቤኒሻንጉልን ጥቃቶችና ጭፍጨፋዎችን ለማስቆም ያልተቻለበት፣ ትግራይን ለመልቀቅ ግድ የሆነበት፣ የራያን ምድር ለሕወሓት ለማስረከብና የአፋርን ምድር መወረር መከላከል ያልተቻለበት ምክንያት ሆነዋል ተብለው የተሰነዘሩት ሰበቦች የገዘፈ የአመራር ችግር መኖሩን የሚጠቁሙ ናቸው። ሕወሓት ይህን የአመራር ችግርና ክፍተት ተጠቅሞ በጥቂት ወራት ውስጥ ራሱን እንደ አዲስ አደራጅቶ ለብልጽግና ቡድን የራስ ምታት እየሆነ መምጣቱንም የሚያሳይ ነው። ከዚህ ሌላ የአንዳንድ ኃያላን አገሮች ስውር ጫና ምን ዓይነት ሚና እንዳለው በግልጽ የታወቀ ነገር ባይኖርም፣ ኃያላኑ እጃቸውን አጣጥፈው እንደማይቀመጡ ግን መገመት ይቻላል።

በእርግጥ የብልጽግና ቡድን ፖለቲካዊ አመራር በጣም የተዝረከረከ፣ ስህተቶችን በጭብጨባና በፉጨት እንዲሸፋፈኑ የሚጥር፣ በአገርና በሕዝብ ላይ የሚደርሱ ዘርፈ ብዙ ችግሮችን በአብለጭላጭና በአንጸባራቂ የመዝናኛ ግንባታዎች ሸፋፍኖ ለማለፍ የሚሞክር፣ አጠያያቂ ስህተቶችና ክፍተቶች ሲያጋጥሙ ሰበብ በመደርደርና ተጠያቂ በማፈላለግ ራሱን ሸፋፍኖ የኖረ ነው። ይህ የብልጽግና ቡድን የአመራር ዝርክርክነት ጦርነቱ እንዲካሄድ በተፈለገበት ስትራቴጂ ላይም አሻራውን አሳርፎ ኢትዮጵያ ኹለት ገጽታ ያላት ሆና እንድትታይ እያደረገ ነው። የአዲስ አበባዋ ኢትዮጵያና የባህር ዳሯ ኢትዮጵያ።

የባህር ዳሯ ኢትዮጵያ የክተት ጥሪ አውጃለች። የባህር ዳሯ ኢትዮጵያ ሕዝቤ የሕልውና ጥያቄ ተጋርጦበታል ብላ የእናት አገር ጥሪዋን እያሰማች ነው። በውትድርና ሙያ ላይ የነበሩ ዜጎቿን ወደ ጦር ካምፕ እንዲመለሱ ብቻ ሳይሆን ገበሬዎችንና ሚሊሻዎች የራሳቸውን ስንቅና ትጥቅ ይዘው ወደ ፍልሚያ ቦታዎች እንዲዘምቱ እየወተወተች ነው። ለወታደራዊ ፍልሚያው ገንዘብና ስንቅ የማሰባሰብ ዘመቻውን በሰፊው ተያይዛዋለች።

በአዲስ አበባዋ ኢትዮጵያ ደግሞ ነገሩ ሌላ ነው። ከስምንት ወራት ግብግብ በኋላ በሰኔ 2013 ዓም የብልጽግና መንግስት የተናጠል የተኩስ አቁም ማድረጉን ተከትሎ ወታደሩ ዕረፍት ማድረግ እንደሚገባው ሲነገር ተሰምቷል። በእርግጥ ኢትዮጵያ ከጥቅምት 2013 ዓም መጨረሻ ጀምሮ በትግራይ ምድር በአየርና በምድር ኃይል የተቀናጀ፣ በኤርትራ ረዳትነትና በዩናይትድ ዓረብ ኢምሬትስ ዘመናዊ ሰው አልባ አውሮፕላኖች የታገዘ ከፍተኛ ግብግብ እያካሄደች የቆች ብትሆንም፣ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ይህን ግብግብ ጦርነት ብሎ መጥራት እንደ ወንጀል፣ እንደ ኃጢያትና እንደ ተቃዋሚነት የሚያስቆጥር ሆኖ ነበረ የቆየው። እናም ጦርነት ሳይኖር ተኩስ አቁም ታወጀ ሲባል ነገሩ ግራ አጋቢ ይሆናል።

የጦሩን ከትግራይ መውጣት ተከትሎ የአዲስ አበባዋን ኢትዮጵያ የሚመሩት ሰዎች አማራ ክልልን ዘሎ የሚመጣ ጠላት አይኖርም ባዮች ሆነው በአማራው ሕዝብ ደምና አጥንት እፎይ ሊሉ መሞከራቸው ከማንም የተሰወረ አይደለም። ነገሩ በዚህ ይብቃ ሳይባል የብልጽግና ቡድን ተቀላቢዎች ናቸው ተብለው በሚጠረጠሩ አክቲቪስቶች በኩል አማራውን ሕዝብ ለጦርነቱ ተጠያቂ አድርጎ የመወንጀል፣ መንግስት የተኩስ አቁም አውጆ ጦርነቱ ሊቆም ያልቻለው በአማራ ክልል ተስፋፊነትና አማራ ክልል የራሱ ያልሆነ መሬትን ወርሮ በመያዙ መሆኑን በመናገር ግራ አጋቢ ፕሮፓጋንዳ መሥራት ጀምረው ነበረ። እነዚህ የብልጽግና አክቲቪስቶች ከዚህ በኋላ አማራ ብቻውን መዋጋት እንዳለበትና ሌላው ሕዝብ እንደማያገባው ለመቀስቀስም ሞክረዋል። ከነዚህ ቅስቀሳወች አንዱን በ‹የኔታ ቲዩብ› ላይ በቃለ ምልልስ ሽፋን ሲስተጋባ መስማት ይቻላል።

የኦሮምያና የትግራይ ክልሎች ልዩ ኃይል እና ልዩ ኮማንዶ እያሉ በተደጋጋሚ ታጣቂዎችን እያሰለጠኑ ሲያስመርቁ፣ አማራ ክልል ይህን መሰሉን ስልጠና ከኹለትና ከሶሥት ዙር በላይ እንዳያካሂድበት መደረጉ እየተነገረ የቆየ ጉዳይ ነውና የአዲስ አበባ እፎይታ ጥያቄ ላይ የሚወድቅ ነው። ለዚህም ይመስላል አማራ ክልል ገበሬዎችን ያላችሁን ስንቅና ትጥቅ ይዛችሁ ዝመቱ እያለ ብቻውን መወትወቱ አብቅቶ ሌሎች ክልሎች ደግሞ የልዩ ኃይል መዋጮ እንዲያደርጉ በመጠየቅ ላይ ያሉት።

አዎ! ብልጽግና ቡድንና የአማራ ክልልን እመራለሁ የሚለው ቡድን እውነታውን ታሳቢ አድርገው ከመሥራት ይልቅ የጌታና የሎሌ ዓይነት ዝምድና ፈጥረው በደመ ነፍስ የሄዱበት መንገድ ዋጋ የሚያስከፍል የስህተት መንገድ መሆኑ ግልጽ የሆነላቸው ይመስላል። ከሕወሓት ሎሌነት ወደ ብልጽግና ሎሌነት የተሸጋገረ የሚመስለው የአማራው ገዥ ቡድን የክልሉን ታጣቂ ኃይሎች እንዲመሩ የሚመድባቸው ግለሰቦችም የውትድርና መሪነት ልምዳቸውንና ብቃታቸውን መሰረት አድርጎ መሆን ሲገባው አድርባይነታቸውንና ተላላኪነታውን እንደ አዋጭ መመዘኛ አድርጎ ሲሾምና ሲሸልም ቆይቷል። አሁን የብአዴን/ብልጽግና ፀሐይ ግርዶሽ ውስጥ ልትገባ ግብግብ ስትገጥም ደግሞ የትም የተጣሉትን የጦር ሹማምንት ጥሪ ማድረግ የግድ ሆኗል።

የአማራ ሕዝብ በሳልና ለሕዝብ የሚቆሙ መሪዎቹን የተነጠቀ ሕዝብ ከሆነ እጅግ ብዙ ዓመታት አልፈዋል። በተለይ ደግሞ ያለፉት 30 ዓመታት የአማራ ሕዝብ ጭራሽ ጠላቱ ሊሆኑ በተዘጋጁ፣ የክልሉን ሀብት ብቻ ሳይሆን የክልሉን መሬት ለማንም እያሳለፉ በመስጠት የሚጨፍሩ፣ አዲስ አበባ ላይ ለሚቀመጥ ገዥ ነኝ ባይ ሁሉ ተላላኪና ሎሌ ለመሆን በቆረጡ ራስ ወዳድ ግለሰቦች እየተጨፈረበት ነው የኖረው። ባለፉት 30 ዓመታት አማራ የተባለው ሕዝብ ክልልህ ነው ተብሎ በተሰፈረለት መሬት ላይ መብቱንና ሰላሙን ተነፍጎ ሲኖር፣ እንዲሁም አገሬ ነው ብሎ ሰርቶ ለመኖር ሲል በተሰደደበት በሌላው የኢትዮጵያ ክፍልም የጥቃት ኢላማ ሆኖ የመከራ ኑሮን መርቷል።

ብአዴን ከሎሌነትና ከተላላኪነት ወጥቻለሁ፣ አማራውን ሕዝብ በድዬ ለበዳይ አሳልፌ ሰጥቼ የኖርኩበት ጊዜ በቅቶኛል፣ ተጸጽቻለሁ ብሎ ከተናዘዘበት ከ2010 ዓም መገባደጃ ጀምሮ ደግሞ ነገሮች ሊሻሻሉና ሊስተካሉ ሲገባቸው በአዲሰ አበባ፣ በኦሮምያ፣ በደቡብ፣ በቤኒሻንጉል፣ በድሬዳዋና በሐረሪ አንዴ በኃይማኖታዊ አክራሪዎች ሌላ ጊዜ ደግሞ በዘረኝነት በታወሩ ግለሰቦችና ቡድኖች እየተገደለ፣ እየተዘረፈና እየተፈናቀለ የማያባራ ጥቃት ኢላማ ሆኖ በመኖር ላይ ነው። ይህ አልበቃ ብሎ በክልሉ መሪዎች ደካማነትና አድርባይነት ክልሉ ውስጥ የሚኖሩ ሌሎች ግለሰቦችና ቡድኖችም በአቅራቢያቸው የሚኖረውን አማራ የጥቃት ኢላማ ማድረግ ጀምረዋል። በማዕከላዊ ጎንደርና በሰሜን ሸዋ የተከሰቱት ጦርነት አዘል ጥቃቶች በዘመነ ሕወሓት ያልታዩና በዘመነ ብልጽግና የተጀመሩ አዲስ ጸረ-አማራ ዘመቻዎች ናቸው። የአማራ ሕዝብ ወኪል ነን የሚሉት ቀድሞ ሕወሓት/ብአዴን አሁን ብልጽግና/ብአዴን እየተባሉ ክልሉንና የክልሉን ሕዝብ እንመራለን የሚሉት ግለሰቦች ይህን ሰቆቃ እንደ ተራ ጨዋታ እያዩት መኖራቸውን ቀጥለዋል።

ተወደደም ተጠላም አሁን ድክመትን በሰልፎች፣ በፉጨት፣ በጭብጨባ፣ በውሸት፣ ሰበብ በመደርደርና ተጠያቂ በማፈላለግ መሸፋፈን አደገኛ መሆኑ ግልጽ ሊሆን ይገባል። ጊዜው ‘ቦርጭ ከሆነ ይጠፋል፣ ሽልም ከሆነ ይገፋል’ የሚለውን የሐበሻ ተረት ልብ ብሎ ማሰብ የሚገባበት ነው። ማንኛውም ጦርነት የራሱ ቀይ መስመር አለው። ይህ ቀይ መስመር የሐሳብ ወይም የጊዜ ወይም የቦታ መስመር ሊሆን ይችላል። ይህ ቀይ መስመር መታለፉ ግልጽ ሲሆን፣ አንዱ ለሌላው መሰዋቱን እንደ ሞኝነትና ራስን ለኪሳራ እንደ ማዘጋጀት አድርጎ መቁጠርን ያስከትላል።

ይህን የጦርነት ቀይ መስመር በአጉል ብልጠት፣ ውሸቶችን በመደርደር፣ ምድር ላይ ጠብ የሚል ዋጋ የሌላቸውን ቱሪናፋዎችን በየአዳራሹ በመወሽከትና በመሳሰሉት ዘዴዎች ዘሎ ማለፍ አይቻልም። ስለዚህ የብልጽግና ቡድን ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች አማራውን ሕዝብ የእሳት መጨበጫ ጉጠት አድርገው በማየት እሳቱ የእነሱን እጅ እንደማያቃጥል አድርገው ማሰባቸው ሞኝነት ከመሆን አልፎ ሌላ ነገር ሊሆን እንደማይችል ከ34 እና ከ33 ዓመት በፊት በትግራይ ከተከሰተውና የደርግ መንግሥት የአመራር ችግር እንዲከሰት ካደረገው ውደቀት ትምህርት መውሰድ ተገቢ ነው።

ከ34 ዓመታ በፊት ከመጋቢት እስከ ሚያዝያ 1980 ዓም ድረሰ ባሉት ወደ ኹለት ወራት የሚጠጉ ጊዜያት ለመጀመሪያ ጊዜ የትግራይ አብዛኛው ክፍል በሕወሓት እጅ የወደቀበት ጊዜ ነበረ። ይህ ጊዜ ሕወሓት ከተመሰረተበት ከ1967 ዓም ጀምሮ አግኝቶት የማያውቀውን ትልቅ የጦር ሜዳ ድል ያጣጣመበት ጊዜ ነበረ። ቡድኑ ይህን ትልቅ ድሉን ማጣጣም የጀመረው ወደ ዘጠኝ ሰዓታትን የወሰደ ውጊያ አካሂዶ አክሱም ከተማን በመቆጣጠር ነበረ። በዚሁ ዕለት ከአክሱም 25 ኪሎሜትር ብቻ ርቃ የምትገኘውን አድዋን ያለ ጦርነት ሲቆጣጠር ከቀናት በኋላ ደግሞ በመጠነኛ ጦርነት ሽሬ-እንዳስላሰ ከተማን ተቆጣጥሯል። ይህ ከተሞችን የመቆጣጠር ውጊያ ቀጥሎ ዓዲግራት፣ ውቅሮ፣ ዓብይ ዓዲ፣ ሐገረ ሰላም፣ ወዘተ. በሕወሓት ቁጥጥር ስር ገቡ። ደርግ መቀሌንና ማይጨውን ብቻ ይዞ ቀረ። ሕወሓትን የሚደግፉ ተጋሩ ጦርኑ እያጨበጨቡ ሲቀበሉ፣ ሕወሓትን በጸረ-ኢትዮጵያ አቋሙ አምርረው የሚጠሉ፣ መጠጊያ የሚሆን ቤተሰብና ቤተዘመድ ያላቸው ተጋሩ ጓዛቸውን እየጠቀለሉ ቡድኑ ከያዛቸው ከተሞች እየሸሹ ወደ መቀሌና ወደ ደቡባዊ ኤርትራ ከተሞች ተሰደዱ። መቀሌ፣ አስመራና የደቡብ ኤርትራ ከተሞች ከዓቅማቸው በላይ በሆነ የሰው ብዛት ተጥለቀለቁ።

ቀድሞውንም ቢሆን የደርግ-ኢሠፓ መንግሥት በከተሞች ብቻ የተወሰነ ስልጣንና ቁጥጥር ነው የነበረው። ከመሐል አገር ይሁን ከአንዱ የትግራይ ከተማ ወደ ሌላው በወራት ዕድሜ ውስጥ አንድ ጊዜ በሚደረግ የወታደራዊ ቃፍላይ (ኮንቮይ) ጉዞ ነበረ ግንኙነት የሚደረገው። በዚህ የኮንቮይ ጉዞ ነበረ ከጦር መሳሪያዎች ጀምሮ እስከ ጨውና ስኳር፣ አስፈላጊ የሆኑ የፍጆታ እቃዎች ለሕዝቡና ለጦሩ የሚቀርቡት። የከተሞቹ በሕወሓት እጅ መግባት ከ95 ከመቶ በላይ የሚሆነው የትግራይ ምድር በቡድኑ ቁጥጥር ስር እንዲገባ አድርጎ ስለነበረ መጋቢትና ሚያዝያ 1981 ዓም በተደረገው ጦርነት ትግራይ ከደርግ እጅ ልታመልጥ ነው፣ ደርግ ባዶ እጁን ቀረ ተብሎ ነበረ።

ነገር ግን ከኹለት ወይም ከሦስት ወራት በኋላ ከደቡብና ምራስቅ ኢትዮጵያ ወደ ትግራይ መላኩ በተነገረለት ጦር የሕወሓት ወረራ ተቀለበሰ። በሕወሐት እጅ ውስጥ ገብተው የነበሩት ከተሞች በሙሉ ወደ ደርግ ተመለሱ። የኢትዮጵያ ህልውና አስግቷቸው የነበሩ ተጋሩዎች የጦሩን መመለስ በእልልታና በሆታ ተቀበሉ፤ እናቶች የትግርኛ ተናጋሪዎች (የትግራይና የኤርትራ) ባህል በሆነው ፈንድሻ በመርጨት ጦሩን እንኳን መጣህ አሉት። በዚህ ጊዜ በተካሄደው የመልሶ ማጥቃት ጦርነት ወቅት አጀማመሩ ላይ ሕወሓት ጠንካራ የመከላከል ውጊያ ያደረገ ቢሆንም፣ ወደ ትግራይ የገባው ጦር ከፍተኛ ጫና ስላደረገበት የጦሩን ግስጋሴ ለማዘግየት ያህል ብቻ በጥቂት ታጣቂዎች መጠነኛ አሰናካይና የጦሩን ጉዞ ለማዘግየት ብቻ የታሰሰበት ተኩስ እየከፈተ ጓዙንና የሰው ኃይሉን እንዳለ ይዞ ወደ በረሀ ምሽጎቹ ፈረጠጠ። የጦርነቱ ለብለብ መሆንና ብዙ ውጊያ ያልተካሄደበት ግጭት ወደ መሆን መውረዱ፣ የኢትዮጵያ ጦር በተቆጣጠራቸው ከተሞች መንግስታዊ መዋቅሮች ተመልሰው ባለመተከላቸውና ዋናው የኢትዮጵያ ጦር ወደፊት እየገሰገሰ፣ ከተሞቹ ያለ ጠባቂ ኃይል እየተተው፣ በአንዳንዶቹም ጥቂት ወታደራዊ ኃይል ብቻ እንዲቀር እየተደረገ በመታየቱ በኢትዮጵያዊነታቸው የሚያምኑ ተጋሩ ደስታቸው ሙሉ ሳይሆን ቀረ። ከፍተኛ ስጋትም ይገባቸው ጀመረ። እናም ጦር ወደ ከተማቸው ጎራ ባለ ቁጥር ሕዝቡ በነቂስ እየወጣና የአገር ሽማግሌዎችን ተወካይ አድርጎ እየላከ መንግሥት እንደገና ትቷቸው እንዳይሄድ ከፍተኛ ተማጽኖ አደረጉ። የደርግ መንግሥት ዋና ዓላማ ሕወሓትን እስከ ቤዝ አምባዎቹ በማሳደድ ሕልውናውን ለማጥፋት ያለመ ስለነበረ የሕዝቡ ጥያቄ ምላሽ አላገኘም ነበረ።

በክረምት ጥቅጥቅ ባለ ጫካ፣ በወንዞችና በጅረቶች ወደተሞላው በሰሜን ምዕራብ የኢትዮጵያ ክፍል የቀጠለው ጦርነት አልጋ በአልጋ ሊሆን አልቻለም። ክረምቱ የጦሩን ብረት ለበስ ተሸከርካሪዎችን፣ ታንኮችንና ከባድ መሳሪያዎችን ማጓጓዙን አስቸጋሪ ስላደረገው ጦርነቱን በበጋ ለመቀጠል በሚል እሳቤ ጦሩ ወደ ኋላ ተመሰለ። ከፍተኛ ጦር ሰራዊትና የጦር መሳሪያ ሽሬ ላይ ተከማቸ።

1981 ዓም መጥቶ የታሰበው ጦርነት ሳይጀመር ከስድስት ወር በላይ የሚሆን ጊዜ አለፈ። ይህን የጊዜ ክፍተት በመጠቀም ሕወሓትና ሻዕቢያ ተባብረው ሽሬ ከተማን ከበባ ውስጥ በማስገባት ሽሬ ውስጥ በተከማቸው ጦር ላይ ዘመቱበት። ሦስት ቀናትን በወሰደ ከፍተኛ ውጊያ የኢትዮጵያ ጦር ተረታ። በሽሬው ውጊያ የኢትዮጵያ ጦር መረታቱን የሰማው የኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም መንግስት በዚሁ ዕለት ትግራይን ለቆ ለመውጣት ወሰነ።

መቀሌን በጥድፊያ ሲለቅም ታዬ። በሽዎች የሚቆጠር የትግራይ ሕዝብ እና ትግራይ ውስጥ በሥራ ላይ የነበረው ኢትዮጵያዊ ማይጨውን አቋርጦ ወደ ወሎ፣ አዲስ አበባና ወደ ሌሎችም የኢትዮጵያ ክፍላተ-አገሮች ፈለሰ። መራር ሽንፈትን የተጎነጨው የደርግ ኢሠፓ መንግስት መሪ የነበሩት ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለማርያም ሽንፈታቸውን ለመሸፋፈን ትግራይ ለቾክ መግዣ የሚበቃ ገቢ የማይገኝባት ክፍለ-አገር ናት ሲሉ ሽሽቱን ኪሳራ የሌለበት አድርገው ለማሳየት ሞከሩ። የጦሩን በትግራይ ሕዝብ መጠቃት በመናገር ትግራይን መልቀቅ አዋጭና ቀላል አድርገው ለማሳየት ጥረት አደረጉ። ከትግራይ በሚመነጭ ችጋር የፈረንጅ ዕርዳታ ለማኝ ሆነን እየተሰደብን ነው ሲሉም ከአንድ የድኃ አገር መሪ የማይጠበቅ ውንጀላ ሰነዘሩ።

ሕወሓት ዕድሜ ልኩን በኖረበት የገጠሩ የትግራይ ክፍል የሚኖሩ ገበሬዎችን ክብሪት፣ ችቦ እያለ እያደራጀ ከጎኑ ማሰለፉና በኢትዮጵያ ጦር ላይ በጠላትነት እንዲነሳሱ ማድረጉ ሐቅ ቢሆንም፣ በሌላ በኩል ደግሞ የትግራይ ተወላጆች የሆኑ ከገበሬዎች እስከ መንግሥት ሠራተኞች የሚገኙባው ሕወሓትን የሚዋጉ በርካታ የሚሊሻ ቡድኖች፣ ዘንዶ የተባለውን ቡድን የመሳሰሉ ልዩ ተዋጊ ኃይሎች በትግራይ ምድር ሲንቀሳቀሱ እንደነበረ፣ ብዙዎች የሕይወትና አካል መስዋዕትነት መክፈላቸው ሊረሳ የማይገባው ጉዳይ ነው። ብዙ የትግራይ ወጣቶች ስንዴ እየተሰፈረላቸው ብቻ ነበረ ኢትዮጵያዊ ታጠቂዎች ሆነው ሕወሓትን ሲፋለሙ የነበሩት። ስለዚህ ኮሎኔል መንግስቱ ጠቅላላው የትግራይ ሕዝብ በሙሉ ለኢትዮጵያ ጠላት ሆኖ ተሰልፏል ሲሉ መወንጀላቸው ታሪክ ይቅር የማይለው በሕዝብ ላይ የተፈጸመ ወንጀል ነው።

የደርግ መንግስት ውድቀት እየተቃረበ ሲሄድ የኮሎኔል መንግስቱ ውንጀላና ዘለፋ እየሰፋና እየገዘፈ፣ ምስኪኑን ወታደርና ኢትዮጵያዊውን ወጣት ኹሉ የሚያብጠለጥልና የሚያጣጥል እየሆነ መምጣቱም የሚረሳ አይደለም። ለሽንፈቱና ለውድቀቱ ሌላውን ተጠያቂ እያደረጉ የመጨረሻውን ጉዞ ለማድረግ የሞከሩት ኮሎኔል መንግስቱ የመጨረሻው መጨረሻ መድረሱ ሲታያቸው ጉብኝት ሄድኩ ብለው፣ የቅርብ ጓዶቻቸውን አታለው፣ አውሮፕላን አስነስተው ኬንያን አቋርጠው ዙምባቡዌ ገቡ። አዲስ አበባን በቅርብ ርቀት ለማማተር የበቃው ሕወሓት ‘… ቦሌ አየር ማረፊያ በተኩስ ዒላማዬ ርቀት ውስጥ ገብቷል…’ ብሎ አውሮፕላን እንዳይነሳና እንዳያርፍ ሲያስጠነቅቅ ከባነኑት የደርግ ዘመን ባለሥልጣት አንዱ አህያ ጭነውና ባላገር መስለው ከአዲስ አበባ ኬላወች በአንዱ ለማምጥ ሲሞክሩ ተይዘው የደርግ ዘመን ማክተሚያ ሆኗል።

የደርግ መንግሥት በተለይም ኮሎኔል መንግስቱ የጦርነቱን አካሄድ ብቻ ሳይሆን የራሳቸውን መሪነት ብቃት ተገቢ መሆንና አለመሆን ገምግመው አገርንና ሕዝብን ከአደጋ መታደግ ሲገባቸው፣ ሐቁን እየሸፋፈኑ፣ በእጃቸው ውስጥ ባሉ መገናኛ ብዙኃን እሳቸው ሊናገሩት የሚፈልጉትን ዝባዝንኬ ወሬ ብቻ እያወሩና እያስወሩ፣ ለሽንፈታቸውና ለደካማነታቸው ሰበብና ሌላ ተጠያቂ እያፈላለጉ በአገርና በወገን ላይ ቢቀልዱም መጨረሻ ላይ ግን ሐቁ ገሃድ ሆኗል። ‘ቦርጭ ከሆነ ይጠፋል፣ ጽንስ ከሆነ ይገፋል’ ተብሏልና!
ግዛቸው አበበ በኢሜል አድራሻቸው
gizachewabe@gmail.com ማግኘት ይችላሉ።


ቅጽ 3 ቁጥር 143 ሐምሌ 24 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!