የእለት ዜና

ምርጫ ቦርድ እና ሴት አመራሮቹ

ኢምፓቲ ፎር ላይፍ ኢነተግሬትድ ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን(ኤሊዳ) የተቀናጀ የልማት ሥራን በመሥራት ሴቶችን፣ ልጃገረዶችን፣ ወጣቶችን እና ህጻናትን በትምህርት፣ በጤና እና በኢኮኖሚ በመደገፍ እንድሁም በዴሞክራሲ ባህል ግንባታ እና ዘላቂ ሰላም ላይ የሚሠራ እና ማኅበራዊ ኀላፊነታቸውን የሚወጡ ፣ ምርታማ እና አርቆ አሳቢ ዜጎችን ለማፍራት በማለም 2008 (እ.ኤ.አ)ሴቶች የተመሠረተ አገር በቀል የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅት ነው፡፡

በዚህ ገፅ ላይ የተካተቱ የተለያዩ አካላት ሐሳቦች የኤሊዳንም ሆነ የድጋፍ ሰጪ ድርጂቱን አቋም ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡

የኢትዮጵያ የ2013 ስድስተኛ አገራዊ ምርጫ የመጀመሪያ ዙር ተጠናቆ ኹለተኛው ዙር ሊከወን ቀናት እየተጠበቀ ይገኛል። ይህ ምርጫ ከሞላ ጎደል ከዚህ ቀደም ከነበሩት ጋር ሲመሳከርና ኢትዮጵያም አሁን ላይ በተለያየ አቅጣጫ ካለባት ጫና እና ተጽዕኖዎች አንጻር ሲመዘን፣ ከነበረውም ስጋት አኳያ ስኬታማ የተባለለት ነው። በድኅረ ምርጫ ከምርጫ ጋር የተያያዘ አለመረጋጋት አለመፈጠሩም ይበል የሚያሰኝ የምርጫ ሂደት ነበር ተብሎ እንዲመሰከርለት አድርጓል።

ይህ በቀደሙት ጊዜ ያልታየውና አሁን የታየ ለውጥ አንድም በምርጫ ቦርድ ላይ ያደረው ተዓማኒነት የፈጠረው እንደሆኑ የሚስማሙ ጥቂቶች አይደሉም። በተለይም የብርቱካን ሚደቅሳ በምርጫ ቦርድ ኃላፊነት መሰየም ለለውጡ ትልቅ ግብዓት እንደሆነ በተደጋጋሚ ሲነሳ ይደመጣል። ይህንንም ከኹለት ነገር አንጻር የሚጠቅሱት አሉ።

በአንድ ወገን ብርቱካን ሚደቅሳ በቀደመውና በተደጋጋሚ በሚወሳው ምርጫ 97፣ ምርጫ ፍትሐዊ ካልሆነ የሚያስከትለውን ችግር ደርሶባቸው የቀመሱ ናቸው። እናም በምርጫው ሂደት በኩል ‹ይህ ቢሆን!› ሲሉ የነበሩትን ሁሉ ለመተግበር እድል ሰጥቷቸዋልና ነው። ፖለቲከኞችንና የኢትዮጵያን የፖለቲካ መልክ በሚገባ ያውቁታል። ስለዚህም አመራራቸው ውጤታማ ሊሆን እንደሚችል ተጠብቋል።

በእርግጥ ብርቱካን ለአመራርነት ሲሰየሙ እንዲሁም አስቀድሞ ወደ አገር ቤት ሲመለሱ፣ ከጋዜጠኞች ጋር ባደረጉት ቆጥታ አስተያየት ሰጥተው ነበር። በዛም በኢትዮጵያ የታዩ ለውጦች ብርታትና መነሳሳት እንደፈጠረባቸውና መንግሥት እውነተኛ ዴሞክራሲን ለመተግበር ያለውን ቁርጠኝነት የተመለከቱበት እንደሆነ ተናግረው ነበር። እናም ለምርጫ ቦርድ መሰየማቸውንም በሚመለከትም ተቋሙ አጥቶት የቆየውን ተዓማኒነት ለመመለስና እውነተኛና ትክክለኛ ምርጫን የማካሄድ ሥራ ከፊታቸው እንደሚጠብቃቸው ጠቅሰው ነበር።

በሌላ በኩል ደግሞ ነገሩን ከጾታ ጋር የሚያገናኙት አሉ። ሴቶች በተፈጥሮ እንዲሁም በማኅበራዊ ሕይወት ልምድ በውሳኔ ሰጪነት እና አመራር ላይ የታደሉት ፀጋ እንዳለ ይታመናል። በማንኛውም የሥራ መደብ ላይ ግጭትን አለመግባባትን ማስቀረት፣ ችግሮችን በውይይት መፍታት፣ ነገሮችን በትዕግስት ማስተናገድና የመሳሰሉ ተግባራት ቢጠበቁም፣ ቦታው ላይ መገኘት ብቻ እነዛን ያስገኛል ማለት አይቻልም። ልምድ እንዲሁም ብልሃትን ይጠይቃል።

እነዚህ ኹለት ዕይታዎችን እናቆያቸው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በ6ኛው አገራዊ ምርጫ እንደሚታወቀው ከአመራር ጀምሮ በርካታ ሴቶችን አሳትፏል። ብርቱካን ሚደቅሳ በኢትዮጵያ ብሮድካስት ሰርቪስ (EBS) የሰይፉ ፋንታሁን እንግዳ ሆነው በቀረቡበት መድረክ ይህን ነጥብ አንስተዋል።

በንግግራቸው በምርጫ ቦርድ በርካታ ሴቶች ተሳትፎ ማድረጋቸውን አውስተው ቦርዱ የጾታ እኩልነትን እውን ለማድረግ የራሱ ፖሊሲ አለው ብለዋል። ‹‹ፓርቲዎች የሴቶችን ተሳትፎ እንዲያጠናክሩ እየጠየቅን እኛ ያንን ባናደርግ ትክክል አይሆንም›› ሲሉ ነበር አስተያየት የሰጡት። ስለዚህም ቦርዱ በቅጥርም ሆነ በምልመላ ቅድሚያ ለሴቶች ሰጥቷል ሲሉ ነው የተናገሩት።

ይህን ዓይነት ሴቶችን ከአመራር ጀምሮ በየቦታው እንደ አቅምና ችሎታቸው መሰየም ሁሉም መሥሪያ ቤቶችሊተገብሩት የሚገባ እንደሆነ መክረዋልም። በኢትዮጵያ ራሳቸውን የሚያስተምሩ፣ ያላቸውን ክህሎትም በየጊዜው የሚያሳድጉ ብዙ ወጣት ሴቶች እንዳሉ የጠቀሱት የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢዋ ብርቱካን ሚደቅሳ፣ ሥራው እነዚህን ብርቱ ሴቶች ለማየት እድል እንደሰጣቸው ነበር የገለጹት።

በአመራር ላይ ያሉትና ወሳኝ የሥራ ድርሻን የያዙት ሴቶች ውጤታማ ሥራን እንደሠሩም በምርጫው ማግስት ተመስክሮላቸዋል። ክፍተቶች የሉም ማለት ግን አይደለም። ምርጫ ቦርድ መሪዎቹ ሴቶች ባይሆኑና ቁርጠኛና ተዓማኒ ምርጫን ለማካሄድ ጉጉና ቀናዒ የሆነ ማንኛውም ሰው ቢቀመጥበት፣ አሁን ካለው ጋር ተመሳሳይ የምርጫ ሂደት ውጤት ሊገኝ ይችል ይሆናል። ነገር ግን ብዙ ሴቶች ወደ ፖለቲካው ለመግባት ፍላጎት እንዲያድርባቸው፣ ፍላጎት ያላቸውም ገፍተው እንዲሳተፉ ላያደርጋቸው ይችል ነበር።

የተባበሩት መንግሥታት የሴቶች ጉዳይ ምርጫ የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለመደገፍ ወሳኝ ኹነት ነው ይላል። ታድያ ግን የፖለቲካ ባህልም ወሳኝ እንደሆነ ጥናቶች ያመላክታሉ። ታድያ በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ የታየውን ልምድ ማዝለቅ ተችሎ ነገሩን ባህል ማድረግ ከተቻለ፣ በእርግጥም በፖለቲካው የሴቶች የእኩልነት ጥያቄ ታሪክ መሆኑ አይቀርም። ከዛ በኋላ በልምድ፣ በችሎታ የበቁ እንዲሁም ባላቸው አቅም በራስ መተማመንን ይዘው እችላለሁ በሚል መንፈስ የሚተጉ ሴቶችን ማፍራት ይቻላል።


ቅጽ 3 ቁጥር 143 ሐምሌ 24 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!