የእለት ዜና

ስቶክ ማርኬት በኢትዮጵያ ለማቋቋም ዝግጅት እየተደረገ ነው

የሀብት ገበያን (የስቶክ ማርኬት) በኢትዮጵያ ለማስጀመር መሰረታዊ ነው በተባለው “የመጀመሪያ አክሲዮን/ቦንድ ሽያጭ ሂደት” “ኢኒሻል ፐብሊክ ኦፈሪንግ” (IPO) ላይ ትኩረት ያደረገ ሠሚናር በሸራተን አዲስ ተካሂዷል።
የመጀመሪያ አክሲዮን/ቦንድ ሽያጭ ሂደት “ኢኒሻል ፐብሊክ ኦፈሪንግ” ድርጅቶች በኢትዮጵያው ስቶክ ማርኬት ላይ እንዴት መሳተፍ እንደሚገባቸው የሚያብራራ አጀንዳ መሆኑም በመድረኩ ተገልጿል። ሠሚናሩን በዋና አስተባባሪነት ያዘጋጁት ሴሉላር ኮንሰልታንሲ፣ ግራንድ ቶራንተን አማካሪ፣ ቢዲኦ እና ኮርነርስቶን አድቫይዘሪ የተሰኙ የአማካሪ ድርጅቶች ሲሆኑ ጉዳዩ የሚመለከታቸው የመንግስት ባለስልጣናት፣ የግሉ የንግድ ዘርፍ ስራ አስፈፃሚዎች፣ ባለሀብቶችና የሚዲያ አካላትም በመድረኩ ተገኝተዋል።

ድርጅቶች በቦንድ ወይንም በአክሲዮን መልክ ሀብታቸውን ለመሸጥ በስቶክ ማርኬት በኩል ምን ምን አስፈላጊ መስፈርቶችን ማሟላት ይጠበቅባቸዋል፣ የሚያልፉትስ የሽያጭ ሂደት ምን መምሰል አለበት በሚሉ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ማብራሪያና ውይይት ተካሂዷል። የኢትዮጵያ ኦዲተሮችና አካውንታቶች ቦርድ ሀላፊ የሆኑት ሂክመት አብደላ ከኋላ መነሳታችን ሌሎች ሀገራት ከተጓዙበት ጓዳና ብዙ መማር እንደሚያስችለን ገልፀው፤ ለሀብት ገበያ (ስቶክ ማርኬት) የሚያስፈልገውን የሰው ሀይል ለማቅረብ አዲስ ተቋም እየተመሰረተ መሆኑን ተናግረዋል።

በስቶክ ማርኬት ላይ በአሜሪካን ሀገር የረጅም አመታት ልምድን ያካበቱት አቶ ተስፋዬ ሀይለሚካኤል የመጀመሪያ አክሲዮን/ቦንድ ሽያጭ ሂደት ወይንም በካፓታል ገበያው አጠራር “ኢኒሻል ፐብሊክ ኦፈሪንግ” ተሞክሮ በሌሎች አገራት ምን ይመስላል በሚል እርዕስ ሰፉ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል። ተስፋዬ ስቶክ ማርኬት (የሀብት ገበያ) ማለት ሰነዶች ገዝቶ ገንዘብ መስጠት ወይንም አክሲዮን/ቦንድ መግዛት ማለት ሲሆን ይህ የገበያ ስርዓት ከግምት የሽያጭ ስርዓት የምንላቀቅበትን እድል በመፍጠር ኩባንዮች ሰነድ ሸጠው ተቋማቸውን የሚያሳድጉበት አቅም ይፈጥርላቸዋል ብለዋል።

የስቶክ ማርኬት የገበያ ስርዓት በአንድ አገር ውስጥ ሲኖር ብዙ አቅም ያላቸው ኢንቨስተሮችን ወደ አገር ውስጥ የመሳብ እድልን እንደሚፈጥር ተመላክቷል፡፡ በአገር ኢኮኖሚ ላይም አወንታዊ ሚናን መጫወት እንደሚችል አስረድተዋል። በተጨማሪም በካፒታል ገበያ ላይ ልምድና ተሞክሮ ያላቸው የመድረኩ ተሳታፊዎች ልምዳቸውን አካፍለው ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል።

ገበያው ከሚያመጣቸው ልዩ ልዩ ጥቅሞች ውስጥ አንዱ የንግድ ድርጅቶችም ሆኑ የመንግስት ድርጅቶች ለሚያስፈልጋቸው የስራ ማስኬጃና የአቅም ግንባታ ማስፋፊያ አክስዮን ወይም ለቦንድ በመሸጥ ከማህበረሰቡ ገንዘብ የሚያገኙበት መንገድ መሆኑ ይታወቃል።

ስቶክ ማርኬት ማለት መደበኛ ባልሆነ መንገድ የተካሄዱ የአክሲዮን ሽያጮች (በየጊዜው ከፍ እና ዝቅ የሚሉ) መደበኛ የማድረግ ሂደት መሆኑ ይታወቃል። የአክሲዮን ተሳታፊዎች መጠንም በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምር የሚያስችልም ነው።
‹‹ስቶክ›› የሚለው የእንግሊዘኛ ቃል በአንድ ኩባንያ ውስጥ ያለ ድርሻ እንደሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።በአንድ ኩባንያ ውስጥ ስቶክ ወይም አክስዮን አለው ማለት በኩባንያው የተወሰነ ድርሻ አለው ማለት ነው። ስቶክ የሚለው ጽንሰ ሀሳብ በአንድ ኮርፖሬሽን ውስጥ የአክሲዮን ድርሻን የሚያመላክት ሲሆን አንድ አክሲዮን መሸጥም ሆነ መግዛት ይቻላል።

የስኬትና የቢዝነስ መጻሕፍትን በማዘጋጀት የሚታወቁት በፋይናንስ፤ በኢንቨስትመንትና በስቶክ ማርኬት ባለሙየዎች የስቶክ ማርኬት ወይም ካፒታል ማርኬት ማለት ከኢንቨስትመንት ዘርፍ መካከል አንዱ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
ይህ የኢንቨስትመንት ዘርፍም ኢንቨስት የሚደረግበት የተለያዩ መንገዶችና ስልቶች ሲኖሩት ከእነሱም መካከል ስቶክ ወይም አክሲዮን እንዲሁም ቦንድ የሚባል የብድር ሰነድ በዋናነት ይጠቀሳሉ። ስቶክና ቦንድን ለኢንቨስትመንት ማስፋፊያ መሳሪያነት በመጠቀም ሰዎች አክሲዮን በመግዛትና በመሸጥ ገንዘብ እንዲያገኙ የሚያስችል የኢንቨስትመንት አይነት ነው።

ቦንድንና ስቶክን ለህብረተሰቡ የሚሸጡ አካላት ሲኖሩ በተለይም የግል ድርጅቶች ስቶክና ቦንድን መሸጥ ይችላሉ። መንግስት ከሚሸጠው የቦንድ አይነት ታላቁ ህዳሴ ግድብ ቦንድ ለአብነት የሚጠቀስ ነው። ስለዚህ ቦንድና ስቶክስ ለህብረተሰቡና ኢንቨስት ለሚያደርጉ ተቋማት የሚሸጥበት የኢንቨስትመንት ሂደት ነው። ህብረተሰቡና ተቋማትም እንዲሁ ቦንድና ስቶኮችን ከድርጅቶች በመግዛት ልክ እንደ መሬት አቆይተው ዋጋው ሲጨምር በመሸጥ ተጠቃሚ ይሆናሉ።

ከዚህ በፊት ሰዎች ከተለያዩ ድርጅቶች አክሲዮን በመግዛት የትርፍ ክፍፍል ያገኛሉ። ነገር ግን የስቶክ ማርኬት ከትርፍ ክፍፍሉ በተጨማሪ በዋናነት ለሌሎች ሰዎች አትርፎ በመሸጥ ላይ የተመሰረተው የንግድ ሂደት ነው። ቦንድና ስቶክ ገዝቶ መሸጥ ከኢንቨስትመንት ዘርፎች መካካል አንዱ ነው።


ቅጽ 3 ቁጥር 143 ሐምሌ 24 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!