የእለት ዜና

የኮልፌ ወጣቶች ስለሠላም ያላቸው ምልከታ

Views: 127

የሠላምና ልማት ማዕከል ለትርፍ ያልተቋቋም፣ መንግሥታዊ ያልሆነ አገር በቀል ድርጅት ሲሆን፣ ከማንኛውም የፖለቲካም ሆነ የሌላ ወገንተኝነት የጸዳ፣ በአገሪቱ የሠላም ባህል እንዲስፋፋ፣ በውይይት እና በንግግር የሚያምን ማሕበረሰብን ለመፍጠር የሚሰራ ተቋም ነው።
ተቋሙ ከተመሰረተበት 1982 ዓ/ም አነስቶ በተለያዩ የሠላም ግንባታ ሥራዎች ላይ ተሰማርቶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል። በተለይም ደግሞ ግጭትን ለመፍታት እና የሠላም ባህልን ለመገንባት የሚያስችሉ አገር በቀል እውቀቶችን በማዳበር በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ አለመግባባቶች በውይይት እንዲፈቱ ሲያደርግ ቆይቷል። በተለይም ደግሞ በቦታ እና በሁኔታ አለመመቸት ምክንያት ለብዙ ተቋማት ለመድረስ አመቺ አይደሉም የሚባሉ የአገራችን አካባቢዎች ጭምር ሳይቀር በመግባት ከታችኛው የማሕበረሰብ አደረጃጀቶች ጋር ሰፊ የሠላም ግንባታ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል። ተቋሙም በተሰማራበት የሥራ ዘርፍ ምንም እንኳ እንደአገር ያለብን ችግር ዘርፈ ብዙ እና ሰፊ ቢሆንም የአቅሙን በማበርከት ላይ ከመሆኑም በላይ አመርቂ የሚባሉ ውጤቶችን በማስመዝገብ ላይ ይገኛል። ተቋሙም አሁን ያሉ ፕሮጅክቶችን በማስፋት እና ወደተጨማሪ ቦታዎች በመንቀሳቀስ፣ እንዲሁም የተለያዩ ማሕረሰብ አቀፍ የሆኑ የሰላም ጥረቶችን በመደገፍ እንዲሁም አቅማቸውን ጭምር በመገንባት ለችግሮች ተመጣጣኝ የሆነ ምላሽ ለመስጠት የበኩሉን አስተዋፅኦ በማበርከት የሚቀጥል ይሆናል።
ሠላምና ልማት ማዕከል

በስደት የነበሩ የግንቦት ሰባትና ኦነግ አመራሮች ከሦስት አመት በፊት ወደ አገር ውስጥ ሲገቡ በአቀባበሉ ሒደት ላይ በተነሳ አለመግባባት የአዲስ አበባና የቡራዩ ከተማ ወጣቶች ጎራ ለይተው ግጭት ውስጥ መግባታቸው የሚረሳ አይደለም፡፡ የአዲስ አበባ በተለይ የኮልፌ ወረዳ 10 ወጣቶችና የቡራዩ አቻዎቻቸው የፈጠሩት አለመግባባት አድማሱን አስፍቶ ለወራት በመቀጠሉ ለበርካቶች ሕይወት መጥፋትና መሰደድ እንዲሁም ለብዙ ንብረት መውደም ምክንያት ሆኖ ነበር፡፡

የኹለቱ ከተማ ወጣቶችን ጸብ የፀጥታ ኃይሎች ማርገብ ቢችሉም፣ ዕርቅ ማውረድ ግን ሳይቻል ቆይቷል፡፡ ይህን ክፍተት ለመሙላት የተንቀሳቀሰው የሠላምና ልማት ማዕከል ነው፡፡ ማዕከሉ የኹለቱን አካባቢ ወጣቶች ለማቀራረብና በመካከላቸው ዕርቅ እንዲወርድ ለማድረግ በርካታ መርኃ ግብሮችን ነድፎ፣ ወጣቶቹን አገናኝቶ በማወያየት፣ ችግሩ አንዲቀረፍ በማድረጉ በኩል እንደተሳካለት በሒደቱ ላይ ተሳታፊ ሆነው ተጠቅመናል የሚሉት ወጣቶች ይናገራሉ፡፡ ከዚህ ቀደም ስለአጠቃላይ የዕርቀ ሠላሙ ውጤትና የቡራዩ ወጣቶች በሒደቱ ላይ ስላላቸው አመለካከት ተመልክተን የነበረ ሲሆን፣ በዚህ ጽሑፍ ደግሞ የኮልፌዎቹ ወጣቶች በማዕከሉ ስለተዘጋጀው ዕርቀ ሰላም ያላቸውን ምልከታ አቅርበናል፡፡

ከዓመት በፊት ተጀምሮ እስከአሁን በዘለቀው የዕርቀ ሰላም ሒደት ተሳታፊ ከነበሩት የኮልፌ ወጣቶች መካከል ነዋይ በቀለ አንዱ ነው፡፡ ከቤተሰብ ጋር እየኖረ በተመረቀበት የኢንጂነሪንግ ሙያ ሥራ እየፈለገ የሚገኘው ይህ ወጣት፣ በኹለቱ አጎራባች አካባቢዎች የተፈጠረውን ክስተት በደንብ ያውቀዋል፡፡ የፓርቲዎች አቀባበል ወቅት ከተፈጠረው አለመግባባት አንስቶ ሕዝባዊ በዓላት በሚኖሩበት ጊዜ የሚያገረሸው ግጭት፣ ወጣቶችን ለችግር እስከመዳረግና ሰውን እስከማፈናቀል ደርሶ ነበር፡፡ በኹለቱም ከተሞች የሚኖሩ ሥራ ፈላጊዎች እየተንቀሳቀሱ ሥራ መሥራት እስኪያቅታቸው ድረስ አለመግባባቱም ስር ሰዶ መቆየቱን ይናገራል፡፡

ሠላምና ልማት ማዕከል ያሰናዳው የማሕበረሰብ ውይይት በኹለቱ ተጎራባች አካባቢዎች ያሉ ወጣቶች እንዲቀራረቡ ማስቻሉን የሚናገረው ነዋይ፣ ወረዳው ባቀረበለት ጥሪ መሠረት ለውይይት ሲጋበዝ በደስታ መቀበሉን ያስታውሳል፡፡ እርስበርስ እንደሩቅ ሰው ይተያዩ የነበረው እንደሚቀር በማሰብ ሳያመነታ ወደተዘጋጁት መድረኮች መቀላቀሉን ይናገራል፡፡ ውጥረቱ እንዲረግብ ውይይት አስፈላጊ ነው ብሎ ያምን ስለነበረ፣ መድረኩ ላይ በመገኘት አመለካከቱን ለመቀየር መቻሉንም ያስረዳል፡፡ እሱ ብቻ ሳይሆን በኹለቱም በኩል የነበሩ ተሳታፊዎች እንደጠላት ይተያዩ የነበረውን እንዲያስቀሩ የማዕከሉ ሥራ ማገዙን ይመሰክራሉ፡፡

በቡራዩና ኮልፌ ወጣቶች መካከል ያልነበረ ወንድማማችነት እንዲፈጠር ያደረገው ውይይት፣ አንዳችን በአንዳችን ቦታ ሆነን ምን እንደሚሰማን ያስተዋልንበት ስለነበር ማዕከሉ የተጠቀመበት መንገድ ውጤታማ ነበር ሲል ነዋይ ያብራራል፡፡ ተሳታፊዎች ስለሌላው ያላቸውን አመለካከት በግልጽ ማስረዳታቸው ማንነታቸውን እንድናውቅ ከማድረጉ ባሻገር፣ ስለራሳችን አመለካከት መወያየታችን የችግሩን መንስዔ በቀላሉ እንድናውቅ አግዞናል ሲል የኮልፌ ወጣቶችን ሲያስተባብር የነበረው ይህ ወጣት ይገልጻል፡፡

ሠላምና ልማት ማዕከል ያዘጋጃቸው የውይይት መድረኮች አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ተሳታፊዎችን ቢያካትትም የነበረን የግንዛቤ እጥረት የተረዳንበት ነው የሚለው ንዋይ፣ ክፍተታችንን ተረድተን አዲስ እውቀት ያገኘንበት ጠቃሚ መርሃ ግብር ነበር ይላል፡፡ አነስተኛ ቁጥር ባላቸው ተሳታፊዎች ውጤታማ ሥራ ሠርቷል የተባለው ማዕከሉ፣ በቀጣይ ረዘም ላለ ጊዜ አቅዶ በሌሎች ተጎራባች አካባቢዎች ሥራውን ቢያስፋፋ መልካም እንደሆነ ይናገራል፡፡ ግጭቶች በተለያዩ አካባቢዎች የመኖራቸውን ያህል የማዕከሉ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም የኮልፌ ወጣቶች እምነት ነው ብሏል፡፡

ኮልፌን ወክለው የተገኙ ወጣቶች የፖለቲካ ተሳትፎ የነበራቸው ስለሆኑ ከውይይቱ ያገኙትን ዕውቀት ቢያንስ ለ20 ሰዎች በቀላሉ ማድረስ የሚያስችላቸው እንደሆነ ነዋይ ይገልፃል፡፡ ሒደቱ ያለምንም ጭቅጭቅ ውጤታማ ሆኖ ስላለቀ ተሳታፊዎቹ ሌሎች ያልተገኙ ወጣቶችን ለማሳመን እንደሚቀላቸው የሚናገረው ይህ ወጣት፣ ሥራው ወደሌሎች ወረዳዎች መስፋፋት እንዳለበት ያምናል፡፡

በኹለቱም ወገን የነበሩት ወጣቶች የተጣመመ አመለካከት እንደነበራቸው የሚጠቁመው ነዋይ፣ የነበሩ መንሸዋረሮች ተስተካክለው ወደ ትከክለኛ አመለካከት እንዲመጣ ማዕከሉ ያዘጋጀው መድረክ ጠቅሟል፡፡ “ለካ ትክክል አልነበርንም” የሚሉ ሐሳቦች ከውይይቱ በኋላ የተንጸባረቁ ሲሆን፣ ጥሩ የሆነ የመቀራረቢያ መንገድን ማዕከሉ ስለተጠቀመ ሒደቱ በቀላሉ ሊሳካ እንደቻለ ይናገራል፡፡ ወጣቱ የነበረበትን አላዋቂነት በቀላሉ እንዲረዳ አድርጓል የተባለው ውይይት፣ በማያገባ እየተገባ በእልህና በአላዋቂነት ግጭት መነሳቱ አሳዛኝ መሆኑ ወጣቱ የተረዳበት እንደነበርም ጠቁሟል፡፡ በሠላምና ልማት ማዕከል የተዘጋጀው መርሃ ግብር ቀድሞ ተሰርቶበት ቢሆን ኖሮ በኹለቱ ከተማ ወጣቶች መካከል ተፈጥሮ የነበረውን ክስተት ማስቀረት ይቻል እንደነበር የሚናገረው ነዋይ፣ ሌሎችም በተመሳሳይ ሑነት ውስጥ ከማለፋቸው በፊት የማዕከሉ ሥራ ተስፋፍቶ ቢቀጥል መልካም ነው ብሏል፡፡

‹‹ምነው ባላደረግነው›› ያሉ በርካቶች መኖራቸውን የሚናገረው ይህ ወጣት፣ ለወደፊቱ በግሉም ቢሆን ያልተሳተፉ ወጣቶችን ግንዛቤ ለመቀየር እንደሚሠራ ተናግሯል፡፡ ቢያንስ ፊቴ ላይ ያልተገባ አመለካከት ሲያንጸባረቅ ዝም ብዬ እንዳላይ ውይይቱ አስችሎኛል ያለ ሲሆን፣ ሕብረተሰቡ ምክንያታዊ እንዲሆንና ስሜታዊ እንዳይሆን የበኩሉን ኋላፊነት እንደሚወጣ ቃል ገብቷል፡፡ የሠላምና ልማት ማዕከል ተግባር፣ ውይይት ለሠላም ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለው እንድንገነዘብ አድርጎናል የሚለው ነዋይ፣ ማዕከሉ የጀመረውን ሥራ ግጭት ባለባቸው አካባቢዎች ሰፋ አድርጎ እንዲቀጥልና ሕብረተሰቡ ያለውን የባላንጣ አስተሳሰብ አስወግዶ በወዳጅነት እንዲተያይ ቢያደርግ መልካም እንደሚሆን ተናግሯል፡፡

በሠላምና ልማት ማዕከል ታቅዶ ተግባራዊ የሆነው የዕርቀ ሠላም መርሃ-ግብር ውጤታማ እንደነበር የምትናገረው ሌላኛዋ የኮልፌ ክፍለ ከተማ ነዋሪ ኤልሳቤጥ ታምሩ ናት፡፡ በውይይቱ አዲስ ትውልድ እየተገኘ ነው የምትለው ይህች ወጣት፣ እርስበርስ መነጋገር መፍትሄ ለማግኘትና ሠላም ለማምጣት ይጠቅማል፡፡ በኹለቱ አካባቢዎች የነበረ አመለካከት የተዛባና ጥላቻ ላይ የተመሰረተ እንደነበርም ትናገራለች፡፡ አንዳችን ሌላችንን እንደክፉና መጥፎ እናይ ነበር ያለችው ኤልሳቤጥ፣ በማዕከሉ የተዘጋጀው የዕርቅ መድረክ ከማቀራረብ አልፎ ወዳጅ አድርጎናል ትላለች፡፡ እንደጨካኝ እንተያይ የነበረውን ትተን እርስበርሳችን እንደ መልካም ወዳጅ እንድንተያይ ስልጠናው በመጥቀሙ አሁን አንድ ሆነናል ብላ የምታስብ ሲሆን፣ መገናኘታችንና መቀራረባችን ምን አይነት ሰዎች እንደሆን እንድንተዋወቅ አድርጓል ትላለች፡፡

እርስበርስ ያለን ግንኙነት ለማሻሻል ቀርቦ መወያየቱ አስፈላጊ በመሆኑ ከአምና ጀምሮ የተካሄደው የማቀራረብ ሒደት አሁን ፍሬ አፍርቶ ጥሩ ወዳጅ መሆን መቻላቸውንም ትናገራለች፡፡ የተለያዩ ቦታዎች አብሮ በመጓዝ፣ የበጎ አድራጎት ተግባራትም ላይ በጋራ ለመሳተፍ በፍቃደኝነት ላይ የተመሰረተ ማኅበር ለማቋቋም መብቃታቸውን የምትናገረው ይህች የኮልፌ ወጣት፣ የነበረው የወረደ አመለካከት ተወግዶ እዚህ ደረጃ ለመድረስ የማዕከሉ አስተዋፅኦ ከፍተኛ ነበር ትላለች፡፡
ስለቀደመው ግጭት ስታስብ በኹለቱም ወገን የተዛባ አመለካከት ችግር እንደነበር የምትረዳው ይህች ወጣት፣ በመካከል የነበረ አለመግባባት ምን ያህል ችግር ለሁሉም እንዳመጣ ትገነዘባለች፡፡ የወጣቱ አንድ መሆን ለራስ ብቻ ሳይሆን ለአገርም እንደሚጠቅም ያወቅንበት የዕርቀ ሰላም ሒደት፣ መጥፎ አመለካከታችንን እንድናስወግድ ብቻ ሳይሆን የሌላውንም አስተውለን እንዲቀየሩ የምንጥርበት ነው ብላለች፡፡

መጀመሪያ የሠላምና ልማት ማዕከል ሊያወያይ ይመጣል ሲባል እንዲህ ውጤታማ ሥራን ይሠራል ብላ ያልጠበቀችው ኤልሳቤጥ፣ እንኳን አብረን በጎ ሥራን እንሠራለን ብላ ልታስብ ይቅርና የነበረ አመለካከት ይቀየራል ብላ እንዳልጠበቀች ታስታውሳለች፡፡ ለእሷ ብቻ ሳይሆን የኹለቱ አካባቢ ወጣቶች እዚህ ደረጃ እንዲደርሱ ዋናውን በር የከፈተው ማዕከሉ እንደሆነም ትናገራለች፡፡ ለሠራው ሥራም ምስጋና እንደሚገባው የምትናገረው ይህች ወጣት፣ ጥቅም ያገኘችው ለራሷ ብቻ ሳይሆን በእሷ ስር ላለ በጎ አድራጎት ማኅበር አባላትም ጭምር ነው፡፡ የአንድነትን አስፈላጊነት ቀለል ባለ መንገድ ውይይቱ እንዳስተማራቸውና በዚህም ለወደፊት ብዙ መሥራት እንደሚችሉም አሳውቃለች፡፡

የሠላምና ልማት ማዕከል ትኩረቱን በኮልፌና ቡራዩ ወጣቶች ላይ ቢያደርግም፣ ሌሎች ግጭት ያለባቸው ቦታዎችንም ቢያካትትና በስፋት ቢቀጥል መልካም እንደሆነ ጠቁማለች፡፡ እንደ ኤልሳ ዕምነት የወለንኮሚ፣ የአዲስ ኣለምና የአምቦ፣ እንዲሁም ከአዲስ አበባ የአዲስ ከተማና የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወጣቶችም ተመሳሳይ ዕድል ቢያገኙ እነሱ ብቻ ሳይሆኑ አገራችንም ትጠቀማለች፡፡


ቅጽ 3 ቁጥር 143 ሐምሌ 24 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com