የእለት ዜና

የተቋማት ቁርጠኝነት ለቀጣይ አገራዊ ሥራዎች ትምህርት የሚሰጥ መሆኑ ተገለጸ

Views: 96

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሪታሪያት የሚዘጋጀው የአዲስ ወግ የውይይት መድረክ “ዴሞክራሲ አንድ እርምጃ፤ የስድስተኛው ብሔራዊ ምርጫ ምልከታዎች” በሚል ርዕሰ ሐሳብ ውይይት አካሂዷል። የስድስተኛው አገራዊ ምርጫ አጠቃላይ ሒደት የኢትዮጵያን ዴሞክራሲ ግንባታ አንድ እርምጃ ወደ ፊት የወሰደ እና ለቀጣይ አገራዊ ምርጫ ትምህርት የሰጥ ነው መባሉን ኢዜአ ዘግቧል።
በመድረኩም በምርጫው ሒደት ላይ የባለድርሻ ተቋማት፣ የመገናኛ ብዙኅንና የሲቪክ ማኅበራት የነበራቸው ሚና ላይ የውይይት መነሻ ሐሰብ ቀርቧል። የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም ዐቀፍ ግንኙነት መምህሩ ካሳሁን ብርሃኑ(ፕ/ር) በውይይቱ ላይ እንደገለጹት፣ ምርጫውን የሚመለከቱ ሕግና ዐዋጆች ማውጣት እንዲሁም አስፈጻሚ አካላትን የመሰየሙ ሥራ አሳታፊ ነበር ብለዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ተቋቁሞ በሒደቱ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት የሔደበት ርቀት የሚመሰገን እንደሆነም ተነስቷል። ይህም ምርጫው ከዚህ ቀደም ከተካሄዱ ምርጫዎች በብዙ መልኩ የተሻለ እንዲሆን ከማድረጉም ባሻገር ለኢትዮጵያ ቀጣይ የዴሞክራሲ ግንባታ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑ ተገልጿል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ተሰባስበው ችግሮቻቸውን ለመፍታት የሔዱበት ርቀት የዘንድሮውን ምርጫ ከሌሎች ምርጫዎች የተለየ እንዳደረገው የገለጹት ደግሞ የደስትኒ ኢትዮጵያ መስራችና የማይንድ ኢትዮጵያ አባል ንጉሱ አክሊሉ (ዶ/ር) ናቸው። የሰብዓዊ መብት ኮሚሽንና የምርጫ ቦርድ የመሳሰሉ የዴሞክራሲ ተቋማት በአጭር ጊዜ ውስጥ የተገነቡበትን ሒደት አድንቀው፣ በቀጣይ የተቋማት ግንባታ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 143 ሐምሌ 24 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com