የእለት ዜና

የድህረ ምርጫ አገራዊ ግንባታ ኹሉን ዐቀፍ ውይይት ሊዘጋጅ ነው

በድህረ ምርጫ ጊዜያት ውስጥ ባሉ አንኳር የአገር ግንባታና ሌሎች ብሔራዊ አጀንዳዎች ላይ በማተኮር በቅርቡ ኹሉን ዐቀፍና አሳታፊ አገራዊ የምክክር መድረክ እንደሚዘጋጅ “ማይንድ ኢትዮጵያ” አስታወቀ።
ውይይቱም በዋናነት በድህረ ምርጫ ጊዜያት ውስጥ ባሉ አንኳር የአገር ግንባታና ሌሎች ብሔራዊ አጀንዳዎች ላይ ትኩረት እንደሚያደርግም ተጠቅሷል፡፡ “ማይንድ ኢትዮጵያ” የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ “ደስትኒ ኢትዮጵያ” እና ሌሎች ስምንት ባለድርሻ አካላትን የያዘ አገር ዐቀፍ ጥምረት ነው።
ጥምረቱ በተለይ በኢትዮጵያ ኹሉን ዐቀፍ ትብብር እንዲፈጠር የሚሠራ ሲሆን፣ በቅርቡም ከስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ድምጽ መስጫ ዕለት ቀደም ብሎ በምርጫው ለሚሳተፉ ፓርቲዎች የመልካም ምኞት መግለጫ መድረክ ማዘጋጀቱ ይታወሳል። የ “ደስትኒ ኢትዮጵያ” መስራችና የ “ማይንድ ኢትዮጵያ” አባል ንጉሱ አክሊሉ(ዶ/ር) ለኢዜአ እንደተናገሩት፣ ጥምረቱ በቅርቡ ኹሉን አቀፍ አገራዊ የምክክር መድረክ ለማዘጋጀት እንቅስቃሴ መጀመሩን ኢዜአ ዘግቧል።
በመድረኩ አንድ ሺሕ ሰዎች ይሳተፋሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የገለጹት ዶክተር ንጉሱ፣ ማይንድ ኢትዮጵያ መድረኩን ከማመቻቸት ያለፈ ሚና እንደማይኖረው ተናግረዋል። ውይይቱ የመንግሥትም ሆነ የውጭ አገራት ጣልቃ ገብነት እንደሌለውና አገር በቀል ዕሴቱን ጠብቆ እንደሚከናወንም አንስተዋል።
በአገር አቀፍ ደረጃ የሚንቀሳቀሱ ሕጋዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የወጣቶች፣ የሴቶች፡ የአርብቶ አደሮችና የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍል ተወካዮችን ጨምሮ 22 ባለድርሻ አካላት በመድረኩ እንደሚሳተፉም ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅትም ባለድርሻ አካላት ተብለው ከተለዩ አካላት ጋር በመገናኘት የውይይት አጀንዳዎችን መሰብሰብ፣ ተወካይ መቀበልና ሌሎች ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ጠቁመዋል።
“ደስትኒ ኢትዮጵያ” ከዚህ ቀደም 50 የሚሆኑ ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን በመያዝ ባደረገው ምክክር ላይ “ሰባራ ወንበር”፤ “የፉክክር ቤት”፤ “አፄ በጉልበቱ” እና “ንጋት” የሚሉ የቢሆን ዕይታዎች ማስቀመጡን አስታውሰዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 143 ሐምሌ 24 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!