የእለት ዜና

ምርጫ ቦርድ እና ፓርቲዎች በፍርድ ቤት

ኢትዮጵያ ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ስታካሂድ የምርጫው ዋና አሳላፊ በሆነው በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና የምርጫው ዋና ተዋንያና በሆኑት የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል ከውይይትና መግባባት አልፎ በፍርድ ቤት እስከመዳኘት የደረሱ ቅድመ ምርጫና የድህረ ምርጫ ሒደቶች ተስተውለዋል። በቅድመ ምርጫ ወቅት በምርጫ ቦርድና በፓርቲዎች መካከል የነበሩ የፍርድ ቤት ዳኝነቶች አሁንም በድህረ ምርጫ ማግስት ቀጥለዋል።

ቅድመ ምርጫ በፍርድ ቤት
በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ የምርጫው ወና አሳላፊ ምርጫ ቦርድ ምርጫውን ለማካሄድ ቅድመ ዝግጀት ከሚደርግበት ጊዜ ጀምሮ፣ ፖለቲካ ፓርቲዎች ከዚህ ቀደም ባልተለመደ ሁኔታ ቦርዱ ያልተቀበላቸውን ጉዳዮች ወደ ፍርድ ቤት በመውሰድ አሽናፊ የሆኑበት ሒደት ነበር።

በቅድመ ምርጫ ወቅት በምርጫ ቦርድና በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል በነበረው ልዩነት ወደ ፍርድ ቤት ካመሩ ጉዳዮች መካከል፣ የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲ(ባልደራስ) በቀዳሚነት የሚጠቀስ ነው። ባልደራስ በፍርድ ቤት ዳኝነት እልባት እንዲያገኝ ወደ ፍርድ ቤት የወሰደው ጉዳይ፣ በእስር ላይ የሚገኙት የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች እነ እስክንድር ነጋና ስንታየሁ ቸኮል ዕጩ ተወዳዳሪ አድርጎ ማቅረቡና ቦርዱ ዕጩነታቸውን አለመቀበሉን ተከለትሎ ነበር።

ምርጫ ቦርድ እስር ላይ የሚገኙ የባልደራስ የቦርድ አመራሮች በዕጩነት አልመዘግብም ያለው፣ በእስር ላይ ያለ ሰው በዕጩነት መቅረብ አይችልም በማለት ነበር። ይሁን እንጂ ፓርቲው የምርጫ ቦርድን ውሳኔ በመቃወም በፍርድ ቤት ለወራት የቆየ ክርክር ካደረገ በኋላ አሸናፊ መሆኑ የሚታወስ ነው።

በምርጫ ቦርድ ተሸናፊነት የተጠናቀቀው የፍርድ ቤት ክርክር እነ እስክንድር ነጋ በዕጩነት ተመዝግበው በምርጫው ተወዳዳሪ መሆን ችለው ነበር። በምርጫ ቦርድና በባልደራስ መካከል የነበረው የፍርድ ቤት ክርክርና ውሳኔ በፖለቲካ ፓርቲዎች በኩል መነቃቃትን የፈጠረ መሆኑ የሚታወስ ነው።

በሌላ በኩል በምርጫ ቦርድና በሐረሪ ክልል መካከል እንዲሁ በቅድመ ምርጫ ወቅት ፍርድ ቤት ክርክር መነሳቱ የሚታወስ ነው። የሐረሪ ክልል እና ምርጫ ቦርድ የፍርድ ቤት ክርክር መጀመራቸውን ተከትሎ የሐረሪ ክልል ምርጫ ሰኔ 14/2013 በተካሄደው የመጀመሪያ ዙር ምርጫ ሳይካተት ቀርቷል። ቦርድ የሐረሪ ክልል ምርጫ ወደ ጳጉሜ 1/2013 እንዲዛወር የተወሰነው የፍርድ ቤት ክርክሩ ውሳኔ አለማግኘቱን ተከትሎ መሆኑን መግለጹ የሚታወስ ነው።
ከቅድመ ምርጫ ቀጥሎ በነበረው ሒደት ማለትም በምርጫ ዕለት ለምርጫ ተብለው በተቋቋሙ ፍርድ ቤቶች ውሳኔ እንዲያገኙ የተደረገበት ሁኔታ መኖሩ የሚታወስ ነው። በጊዜያዊነት በተቋቋሙት የምርጫ ፍርድ ቤቶች ቀላል የማይባሉ ጉዳዮች ውሳኔ ማግኘታቸውን ምርጫ ቦርድ መግለጹ የሚታወስ ነው።

ድሕረ ምርጫ በፍርድ ቤት
ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በኹለት ዙር ለማካሄድ ቦርዱ መወሰኑን ተከትሎ፣ ሰኔ 14 ከተካሄደው የመጀመሪያው ዙር ምርጫ በኋላ በምርጫው የተሳተፉና በምርጫው ቅሬታ ያላቸው ፖለቲካ ፓርቲዎች የገጠሟቸውን ችግሮች ለቦርዱ አቅርበው፣ ቦርዱ ተገቢውን ምላሽ ካልሰጠ ወደ ፍርድ ቤት እንደሚያመሩ በምርጫ ማግስት መግለጻቸው የሚታወስ ነው።

የመጀመሪያው ዙር ምርጫ በተካሄደ በማግስቱ የገጠሟቸውን ችግሮች ለምርጫ ቦርድ አቅርበው ተገቢ ውሳኔ የማያገኙ ከሆኑ ጉዳዮቹን ይዘው ወደ ፍርድ ቤት እንደሚያመሩ ካስታወቁት ፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ(ኢዜማ) ቀዳሚው ነው። ኢዜማ በተለይም በምርጫው ዕለት በርካታ ችግሮች እንደገጠሙት መግለጹ የሚታወስ ሲሆን፣ የገጠሙትን ችግሮች ምርጫ ቦርድ እልባት እንዲሰጥለት በዝርዝር ጥያቄ ማቅረቡን ገልጾ ነበር።

ኢዜማ በምርጫ ቦርድ እልባት የማያገኙ ጉዳዮችን ወደ ፍርድ ቤት እወስዳለሁ ባለው መሰረት፣ አጋጥመውኛል ያላቸውን ችግሮች ይዞ ወደ ፍረድ ቤት አቅንቷል። ኢዜማ ሰኔ 14/2013 ምርጫ ከተካሄደባቸው ምርጫ ክልሎች ውስጥ በ28 ምርጫ ክልሎች ምርጫ እንዲደገም ለፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት አቤቱታ ማስገባቱን ገልጿል። ኢዜማ ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት ያስገባው፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከፓርቲው የቀረቡለተን ቅሬታዎች እና ማስረጃዎች ሳይገመግም ውሳኔ ማስተላለፉን ተከትሎ መሆኑን ጠቁሟል። ፓርቲው ቦርዱ እልባት የማይሰጣቸውን ጉዳዮች ወደ ፍረድ ቤት እንደሚወስድ መግለጹ የሚታወስ ነው።

ኤዜማ ቅሬታ አለኝ ያላቸውን ጉዳዮች በዝርዝር ማስረጃ አስደግፎ አቤቱታውን ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ያስገባው ሐምሌ14 /2013 መሆኑን በጉዳዩ ላይ በሰጠው መግለጫ መግለጹ የሚታወስ ነው። የኢዜማን ክሶች የተቀበለው ፍርድ ቤቱ ጉዳዮቹን እንደሚመለከት መግልጹን ፓርቲው በመግለጫው ጠቅሷል። ኢዜማ ለፍርድ ቤቱ ያስገባው አቤቱታ “ከበቂ በላይ ማስረጃ አቅርቤባቸዋለሁ ያላቸውን 28 የምርጫ ክልሎች የተመለከተ ይሁን እንጂ፣ ለምርጫ ቦርድ ቅሬታ ያቀረበባቸው አጠቃላይ የምርጫ ክልሎች ብዛት 68 መሆናቸውን ፓርቲው አስታውሷል። ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ሰኔ 14 መካሄዱን ተከትሎ ምርጫ በተካሄደ ሰሞን ፓርቲው ለምርጫ ቦርድ ያቀረበው ቅሬታ፣ የሰው፣ የሰነድ፣ የቪድዮ እና የምስል ማስረጃዎችን ያካተተ እንደሆነ ገልጿል።

ፓርቲው ባቀረበው ቅሬታ በድምጽ አሰጣጥ ሒደት እና በምርጫ ውጤት ላይ እጅግ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳደሩ ተግባራት መፈጸማቸውን ለምርጫ ቦርድ ማሳወቁን ጠቅሷል። ኢዜማ በምርጫው ዕለት ተፈጽመዋል ያላቸው ጉድለቶች የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥትን፣ የምርጫ ዐዋጅን እና ምርጫ ቦርድ ያወጣቸውን መመሪያዎች በቀጥታ የሚጻረሩ መሆናቸውን ገልጿል። የፓርቲው አመራሮች ከመጀመሪያው ዙር ምርጫ በኋላ ለሚዲያዎች በሰጧቸው ቃለ ምልልሶችና በተለያ መድረኮች ባደረጉትን ንግግር ምርጫው በርካታ ጉድለቶች የታዩበት እንደነበር ሲገልጹ ተደምጠዋል።

ፓርቲው ወደ ፍርድ ቤት የወሰዳቸውን ጉዳዮች አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ ተጠያቂ ናቸው ያላቸውን አካላቶች ጠቅሷል። ከተጠቀሱት አካላት መካከል ከቀበሌ እስከ ክልል ያሉ የገዢው ፓርቲ አመራሮች፣ ከቀበሌ ሚሊሺያ እስከ ክልል ልዩ ኃይል ድረስ ያሉ የጸጥታ አስከባሪዎች፣ የምርጫ ጣቢያ የምርጫ አስፈጻሚዎች እና ለጊዜው ማንነታቸውና ሕጋዊ የሥራ ኃላፊነታቸው በግልጽ ያልታወቀ ግለሰቦችን ያካተተ ነው።

ኢዜማ ለፍረድ ቤት ያቀረበው ክስ በፍረድ ቤት መታየት ጀምሯል። በዚሁ መሰረት የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ኢዜማ ያቀረበውን የምርጫ ይደገም የይግባኝ አቤቱታ ተቀብሎ ምርጫ ቦርድ በጉዳዩ ላይ ምላሽ ይዞ እንዲቀርብ አዟል።
ኢዜማ እንዳስታወቀው ከሆነ ፍርድ ቤቱ በፓርቲው የቀረበለትን አቤቱታ የመረመረ ሲሆን፣ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ኹለተኛ የምርጫ ጉዳዮች ችሎት ባሳለፍነው ሐምሌ 22/2013 ኢዜማ ያቀረበውን የይግባኝ አቤቱታ መቀበሉን ፓርቲው አስታውቋል። ፍርድ ቤቱ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ በቀረበበት ክስ ላይ ምላሽ ይዞ እንዲቀርብ ለሐምሌ 30/2013 ቀጠሮ ሰጥቷል ሲል ፓርቲው አስታውቋል።

በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በፖለቲካ ፓርቲዎችና በምርጫ ቦርድ መካከል እስከ ፍርድ ቤት ዳኝነት የሚደርስ ሒደቶች መኖራቸው ዴሞክራሲያዊ ሙከራዎችን የሚያጎለብትና የቦርዱን አቅም የሚያጠናክር እንደሆነ ተገልጿል። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሜደቅሳ በምርጫው ሒደት ላይ በፖለቲካ ፓርቲዎች የቀረቡ የፍርድ ቤት ክሶችና ክርክሮች የቦርዱን አቅም ለማጎልበትና በዴሞክራሲ የዳበረ ምርጫ ለመለማመድ ዕድል እንደሚፈጥሩ መግለጻቸው የሚታወስ ነው።


ቅጽ 3 ቁጥር 143 ሐምሌ 24 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!