የእለት ዜና

የትራንስፖርት ሕጎችን የተላለፉ 96 ሺሕ የሚደርሱ ተሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ ተወሰደ

እርምጃ ከተወሰደባቸው ተሽከርካሪዎች 32 ሚሊዮን ብር ተሰብስቧል

የሕዝብ ትራንስፖርት መመሪያዎችን በመተላለፍ ከታሪፍ በላይ በማስከፈልና አቆራርጦ ከመጫን ጋር በተያያዘ በዘንድሮው የ2013 በጀት ዓመት 96 ሺሕ የሚደርሱ ተሸከርካሪዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።

ቢሮው በ10 ቅርንጫፎች በሕግ ጥሰቶች ላይ የክትትልና ቁጥጥር ሥራ በከፍተኛ ሁኔታ በመሠራቱ፣ በተጠናቀቀው 2013 በጀት ዓመት 96 ሺሕ የሚደርሱ ተሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን የቢሮው የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ አረጋዊ ማሩ ገልጸዋል።

በባለፈው በጀት ዓመት እስከ ሰኔ 30/2012 ከታሪፍ በላይ በሚያስከፍሉ፣ ታፔላ በማይጠቀሙ እንዲሁም አቆራርጠው በሚጭኑ 19 ሺሕ 300 የሚደርሱ አሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ መወሰዱን ዳይሬክተሩ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።

በ2012 በጀት ዓመት የትራንስፖርት ሕጎችን በሚጥሱ አሽከርካሪዎች ላይ የተወሰደው እርምጃ ከዘንድሮው የ2013 በጀት ዓመት ጋር ሲነጻጸር ከፍተኛ ልዩነት አሳይቷል ብለዋል።
በዚህ ዓመት የሕግ እርምጃ የተወሰደባቸው የተሸከርካሪዎች ቁጥር ለመጨመሩ እንደ ዋነኛ ምክንያት የሚወሰደው በተሽከርካሪዎች ላይ የተሠራው የክትትልና ቁጥጥር ሥራ በስፋት መሠራቱ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

ከዚህ ቀደም የክትትልና ቁጥጥር ሥራን የሚያከናውኑ ባለሙያዎች፣ ክትትላቸው አነስተኛ የነበረ በመሆኑ የተፈለገውን ያህል ለውጥ ማምጣት አለመቻሉን አንስተዋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ ከዚህ ቀደም የትራንስፖርት ሕግ የጣሱ ተሸከርካሪዎችም በተቀመጠው የቅጣት መመሪያ የእርከን መጠን መሰረት መቀጣታቸው ተገልጿል።

በሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ላይ ለሚፈጸሙ የሕግ ጥሰቶችን አሸከርካሪዎች ከገንዘብ ጀምሮ እስከ እስር የሚደርስ ቅጣት የሚቀጡበት ሁኔታ አለ።
አሽከርካሪዎች የትራንስፖርት ሕግን የሚተላለፉበት ሁኔታ የሚጨምር ከሆነ ከሦስት እስከ ስድስት ወር፣ ብሎም እስከ አንድ ዓመት ድረስ የመንጃ ፈቃዳቸው የሚታገድ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል።

በዘንድሮው 2013 በጀት ዓመት በአጠቃላይ ከተቀጡ 96 ሺሕ ተሸከርካሪዎች 32 ሚሊዮን ብር የቅጣት ገንዘብ መሰብሰብ መቻሉን አዲስ ማለዳ አውቃለች።
በከተማዋ የሚስተዋሉ አቆራርጦ መጫን፣ ከታሪፍ በላይ ማስከፈል፣ ተሳፋሪዎች ከመዳረሻቸው በፊት እንዲወርዱ ማስገደድ አይነት ጥሰቶች በትራንስፖርት ተጠቃሚዎች ላይ ሲከሰት የትራንስፖርት ክትትልና ቁጥጥር ለሚያከናውኑ ባለሙያዎች ጥቆማ ማድረግ እንደሚቻል ተገልጿል።

ችግሮቹ ከፍ ያሉ ከሆነ ተሳፋሪዎች ባቅራቢያቸው ወደሚገኝ የትራፊክ ፖሊስ በመሄድ ጥቆማ ማድረግ ይችላሉ ብለዋል። የተሳፋሪዎች ቅሬታ ከሕግ አካላት ካለፈ፣ በትራንስፖርት ባለሥልጣኑ መደበኛ የስልክ መስመሮች ደውሎ ጥቆማ ማቅረብ እንደሚቻልና ባለሥልጣኑም ሕግ የጣሱ ተሸከርካሪዎች ላይ የእርምት ሥራ እንደሚሠራ ገልፀዋል።

ከዚህም ጋር በተያያዘ በሕዝብ ትራንስፖርት ላይ የሚከሰቱ ስርቆቶች በዋናነት የሚመለከተው የሕግ አካልን በመሆኑ ፖሊስ ኮሚሽን ባሰማራቸው የሕግ አስከባሪ አካላት ክትተል የሚደረግ መሆኑን ጠቁመዋል።
በሕዝብ ትራንፖርት ላይ የሚከሰቱ ስርቆቶች ስልት በመቀያየር የሚፈጸሙ የወንጀል ጥቃቶች በመሆናቸው ግንዛቤዎችን ለማሕበረሰቡ በአፋጣኝ ማድረስ እንደሚገባ አስቀምጠዋል።
በአጠቃላይ ይህንን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የትራንስፖርት አገልግሎት ከሚሰጡ ባለድርሻ አካላት እና ከማህበረሰቡ ጋር በቅንጅት መሥራት እንደሚገባ ዳይሬክተሩ አሳስበዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 143 ሐምሌ 24 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!