የእለት ዜና

የጎዳና ላይ ውሾች ዘራቸው እንዲመክን ሊደረግ ነው

– በአዲስ አበባ 250 ሺሕ የሚሆኑ ባለቤት አልባ ውሾቸ አሉ

በአዲስ አበባ የሚገኙ 250 ሺሕ በላይ ባለቤት አልባ ውሾችን ከሚቀጥለው ዓመት ጀምሮ ዘራቸውን ለማምከን ማቀዱን የአዲስ አበባ ከተማ አርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን ለአዲስ ማለዳ አስታወቀ።
በአዲስ አበባ ከተማ ብዛት ያላቸውን ባለቤት አልባ ውሾችን መመልከት የተለመደ ሁነት ነው። እነዚህ ባለቤት አልባ ውሾች ለከተማዋ ነዋሪዎችም ስጋት እንደሆኑም በየቀኑ የምንታዘበው ነገር ነው።

ይህን ጉዳይ በተመለከተ የአዲስ አበባ አርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን የእንሰሳ ጤና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ፋሲካ በለጠ (ዶ/ር) ለአዲሰ ማለዳ እንዳስታወቁት፣ በትክክል የቆጠራ ስራ ባይከናወንም እንደ ኮሚሽኑ ግምት ግን ቁጥራቸው እስከ ሁለት መቶ ሃምሳ ሺህ የሚገመት ባለቤት አልባ ውሻዎች በመዲናዋ ይገኛሉ ሲሉ ገልጸዋል።

እነዚህንም ባለቤት አልባ ውሻዎች በተመለከተ ለነዋሪው ስጋት እንዳይሆኑ ከ2011 ጀምሮ ክትባት መስጠት ላይ እንደሚገኙ ዳይሬክተሯ ተናግረዋል። በተጨማሪም በቀጣይ 2014 በጀት ዓመት ታህሳስ ወር ላይ ባለቤት ዐልባ ውሾችን ለመከተብ እቅድ እንዳለ ዳይሬክተሯ አክለዋል።

ክትባቱን ከመስጠት ጎን ለጎን እንደ ሌላ አማራጭ የተያዘውና የባለቤት አልባ ውሾችን ቁጥር ይቀንሳል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት፣ ሴት ውሾችን የማምከን ሂደትን በ2014 በጀት አመት ላይ ለመጀመር መታቀዱንና ለዚህም የሚሆን በጀት መመደቡን የአዲስ አበባ አርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን የእንሰሳ ጤና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አስታውቀዋል።

ኮሚሽኑ ባለቤት አልባ ውሾችን ቁጥራቸው ከመቀነስ አኳያ የማስወገድን ተግባር ለበርካታ ዓመታት ሲከውን እንደቆየ የሚገልጹት ደግሞ የአዲስ አበባ አርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን የእንሰሳ ጤና ቡድን መሪ የሆኑት የሺዳኛ በላይሁን ሲሆኑ፣ አሁን ላይ ግን ውሾቹን ለማስወገድ የሚጠቅመው መድሀኒት በዓለም አቀፍ ደረጃ ጥቅም ላይ እንዳይውል በመታገዱ ሙሉ ትኩረታቸውን በክትባት ሂደት ላይ ማድረጋቸውን ቡድን መሪው ያስረዳሉ።

በዚህ ሂደት ከ2012 ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት የዘመቻ ክትባት መከወናቸውና ይሄም በቀጣይ ዐመት ላይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የሺዳኛ ይናገራሉ። በከተማዋ ውስጥ ባለቤት ኖሯቸው ነገር ግን ያልተከተቡና ያልተመዘገቡ በርካታ ውሾች መኖራውን የሚያነሱት የሺዳኛ፣ እነዚህንም በተመለከተ የአዲስ አበባ አርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን የመመዝገብ ስራ እየሰራ መሆኑንም ያክላሉ።

በአለም ዐቀፍ ደረጃ በተደረገ ጥናት ለተከታታይ አምስት አመታት ለባለቤት አልባ ውሾች ክትባት መስጠት ከተቻለ ከሰባ ከመቶ በላይ የእብድ ውሻ በሽታን መቆጣጠር እንደሚቻል የሚናገሩት የቡድን መሪው፣ ከዚህ በመነሳት ኮሚሽኑ በተደጋጋሚ የዘመቻ ክትባት ማከናወኑንም ያነሳሉ።

ባልተከተቡ ውሾች መነከስ ምክኒያት የእብድ ውሻ በሽታ ተጋልጭ የመሆን እድል ሰፊ ሲሆን ይህ በሽታ ወደ ሰዎች የሚተላለፈው በበሽታው የተያዘ እንሰሳ ሌላ እንሰሳ ወይንም ሰው ሲቧጭር ወይም ሲነክስ በሽታው ሊተላለፍ እንደሚችል የአለም ጤና ድርጅት ይገልጻል።

የእብድ ውሻ በሽታን በክትባት መከላከል እንደሚቻልም ተቋሙ በ2021 ግንቦት ወር ላይ ባወጣው ጽሁፍ ይገልፃል።


ቅጽ 3 ቁጥር 143 ሐምሌ 24 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!