የእለት ዜና

23 ፋብሪካዎችን እና አስመጪዎችን በጥራት ጉድለት ማገዱን ንግድ ሚኒስቴር አስታወቀ

የኢትዮጵያ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የጥራት ደረጃ ባላሟሉና መመሪያን በተላለፉ ተቋማት ላይ የማሸግና እና የማገድ ዕርምጃ መውሰዱን አስታወቀ።

ተቋሙ በአካልም በላብራቶሪም ፍተሻ ባደረገው የድህረ ገበያ ምርመራ 23 የንግድ ድርጅቶችን ማገዱንና ማሸጉን የገበያና ፋብሪካ ኢንስፔክሽን ዳይሬክተር ተከተል ጌቶ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በዚህም 61 ድርጅቶች ላይ የንግድ ፈቃድ ማገድና እና ዕሸጋ የተከናወነ ሲሆን፣ ሌሎች 21 ድርጅቶች የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል። በፋብሪካዎች ላይ በተደረገ የፊዚካል ኢንስፔክሽንና የላብራቶሪ ምርመራ ደግሞ 23ቱን ማሸጉን እና ማገዱን እንዲሁም ለቀሪዎቹ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ መስጠቱን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ በገበያና ፋብሪካ ኢንስፔክሽን በኩል ክትትልና ቁጥጥር ካደረገባቸው ምርቶች መካከል ቆሮቆሮ፣ ጨውና የታሸጉ የምግብ ቅቤዎች ይገኙበታል። ከነዚህ ውስጥ የምርት ጥራት ችግር የተገኘባቸውን ምርቶች ወደ ገበያ እንዳይሰራጩ ከማድረግ ጀምሮ የተሰራጩ ምርቶችም እንዲሰበሰቡ መደረጉን ዳይሬክተሩ ገልጸዋል። እነዚህን እክል ያለባቸውን ምርቶች በሚያስመጡም ሆነ በሚያመርቱ ፋብሪካዎች ላይ ተገቢውን እርምጃም እንደተወሰደም ያስረዳሉ።

የብሔራዊ ደረጃን ምልክት ያላደረጉ፣ የምርት ቦታቸው የማይታወቅ ከሆነና በአጠቃላይ በማሸግና ስያሜን በተመለከተ አስፈላጊውን መረጃ የማያስቀምጡ ሆነው ከተገኙ እነዚህን አሟልተው ወደ እውቅና እንዲመጡ እንደሚደረግና አንዳንድ ክፍተቶችን ባስቸኳይ እንዲያስተካክሉ ማስጠንቀቂያ እንደሚሠጡም ገልጸዋል።

በኹለት መንገድ ምርመራ እንደሚያካሂዱ የሚናገሩት ተከተል፣ በፋብሪካ ደረጃ እና በገበያ ደረጃ ምርመራ እንደሚያካሂዱ ይገልጻሉ። በፋብሪካ ደረጃ ምርመራ የተደረገባቸው 29 ፋብሪካዎች ናቸው ብለዋል። በገበያ ምርመራ ደግሞ ከውጭ መጥቶም ይሁን አገር ውስጥ ተመርቶ በገበያ ላይ የሚገኝ ምርት ላይ በተደረገው ምርመራ 30 ድርጅቶች ላይ ችግር ማግኘታቸውን ዳይሬክተሩ ይናገራሉ።

ከተላለፏቸው መመሪያና ደንብ መካከል የምርት ጥራትን ካለማሟላት በተጨማሪም ንግድ ፍቃድ ሳይኖራቸው መነገድ፣ ከቅርንጫፍ ውጪ መሥራት ፣ ከተሰጣቸው አድራሻ ውጪ መነገድና ንግድ ፍቃድ አለማደስ ሌሎቹ እርምጃ እንዲወሰድ ያደረጉ ምክንያቶች ናቸው ብለዋል።

በ2013 በ1063 ድርጅቶች ላይ በተደረገው ክትትልና ምርመራ 82 ድርጅቶች መመሪያና ደንብ ተላልፈው ስለተገኙ እርምጃ መውሰዱን ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል። ከነዛ ውስጥ በሕግ አግባብ ያለሠሩና የተለያዩ የአዋጅ ጥሰቶች በታዩባቸው 61 ድርጅቶች ላይ በሕግ ንግድ ፍቃዳቸውን አግደናል፤ እሸጋም አድርገናል ይላሉ ተከተል ጌቶ። ማገድ ማለት ሥራውን አስቁሞ ማስተካከያ እንዲያደርጉ ማድረግ ማለት እንደሆነ የሚያስረዱት ዳይሬክተሩ፣ ማስተካከያውን ማድረጋቸው ሲረጋገጥ ወደ ሥራ እንዲገቡ እንደሚደረግም አስታውቀዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 143 ሐምሌ 24 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!