የእለት ዜና

የሲሚንቶ ‹‹ነጻ›› ገበያ የፈጠረው ጫና

Views: 361

ከቅርብ ጊዜ ውድህ በነጻ ገበያ እንዲተዳደር መንገድ የተከፈተለት ሲሚንቶ፣ ዋጋው የማይቀመስ ሆኖ ከግለሰብ ጀምሮ ትላልቅ ኮንትራክተሮችን እያስመረረ ይገኛል።
እንደ አገር የሲሚንቶ ፍጆታችን እጅግ ከፍተኛ እንደመሆኑ መጠን፣ ያሉት የሲሚንቶ አቅራቢዎች ወደ ገበያው የሚያቀርቡት የሲሚንቶ መጠን አለመመጣጠን እንደ አንድ የዘርፉ ችግር ሆኖ መነሳት ከጀመረ ሰነባብቷል።
ከአቅርቦት እና ፍላጎት አለመመጣጠን ባሻገር የግብይት ሰንሠለቱ ላይ ያሉት ተዋንያኖች መብዛት ገበያውን እየረበሸው እንደሚገኝ ምሁራን ያነሳሉ።

የግብይት ሥርዓት፣ አንድ ዕቃ ከተመረተ በኋላ ለተጠቃሚው እስከሚደርስ ድረስ የሚከናወኑ ተግባራትን የሚያካትት ሂደት ነው። በአጭሩ የሚከናወን ዕሴት የመጨመርና የማሰራጨት ሒደት ነው። ይህም ምርት ማሰባሰብ፣ ማከማቸት ፣ ማቀነባበር ፣ ማጓጓዝ እና ሽያጭና ግዢን ማገናኘትን ያካትታል።

በሂደቱም በተቻለ መጠን ገዢና ሻጭ በቀጥታ የሚገናኙበትን ዕድል ስለሚፈጥር ዕሴት የማይጨምሩ አላስፈላጊ ደላሎችን ጣልቃ ገብነት በማስወገድ አጭር የቅብብሎሽ ሰንሠለት ያለው የግብይት ስርአት እንዲኖር ይፈለጋል።
ለአገር ኢኮኖሚ ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ዕድገት መኖር ጠንካራ መሰረት ነው። ለአገር ምርት መጨመር ወይም ለአጠቃላይ ኢኮኖሚ ዕድገት ዋነኛ ማነቃቂያ በሕብረተሰቡና በአምራቹ መካከል ያለው ትስስር መጠናክር ነው::
ከዚህ ቀደም መንግሥት ይህን የግብይት ሰንሠለት ለመቀነስ ፣የዋጋ ንረት እንዳይከሰትና የተረጋጋ ገበያ መፍጠር እችላለው ያለበትን የሲሚንቶ ምርትን መጥኖ የማከፋፈል ሥራ ሲሠራ ቆይቶ ነበር። በዚህም አሠራር የሲሚንቶ ተጠቃሚው ምርት

በሚፈልግበት ወቅት የንግድ ፍቃድ በማሳየት መንግሥት በሚፈቅደው መጠን ከአከፋፋዮች እንዲገዛ ሲያደረግ ቆይቷል።
ይህ አሠራር ያልጣማቸው በርካታ ኮንትራክተሮች በፈለጉት መጠን ያህል ሲሚኒቶ መውሰድ አለመቻላቸው የኮንስትራክሽን ዘርፉን ሲፈትን ከርሟል። ለዚህም ትላልቅ የሥራ ተቋራጮች በሲሚንቶ ድርቅ ተመተው ሥራ እስከማቆም የደረሱ እንደነበሩ ይታወሳል።

ይህንን ችግር ከአሁን በኋላ አታዩትም ያለው የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ አሠራሬን ወደ ቀደመው ነጻ ገበያ ቀይሬአለሁ ማለት ከጀመረ ኹለት ሳምንት ተቆጥሯል።
ይህም አሠራር ሲሚንቶ ፈላጊዎች በቀጥታ ከሲሚንቶ ፋብሪካዎች የፈለጉትን ያህል ሲሚንቶ እንዲገዙ የሚያስችል እና በፈለጉት ዋጋ ምርቱን የሚያገኙበትም ነው ተብሎለታል።

ከዚህ በተጨማሪ አሠራሩን ተግባራዊ እንዲደረግ መንግሥት ያደርጋቸው የነበሩ የቁጥጥር ተግባራትን በማቋረጥ ፋብሪካዎች በቀጥታ ከአከፋፋዮች እና ቸርቻሪዎች ጋር የሚገናኙበትን ሰንሠለት ዳግም በማስተካከል ወደ ሥራ ገብቷል።
መንግሥት ሰንሠለቱን በድጋሚ ወደ ነጻ ገበያ ከቀየረ ወር እንኳን ሳይሞላው፣ በተለያዩ የመሸጫ ቦታዎች ላይ የተለያየ፣ አንዳንድ ቦታ ደግሞ እጅግ የተጋነነ የመሸጫ ዋጋ ሲጠራ ይሰማል።

ፋብሪካዎች የመሸጫ ዋጋቸው ከንግድ እና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በሚታወቅ የዋጋ ልኬት እንዲሆን ተስማምተው የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ያለው እውነታ ግን ገበያውን የሚቆጣጠር አካል እንደሌለ የሚያሳይ ነው ሲሉ ኮንትራክተሮች ቅሬታ እያነሱ ይገኛሉ።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ይህን ቅሬታ መፍታት ያስችለዋል የተባለለትን ከሲሚንቶ ገበያው ራሱን በማስወጣት ለፋብሪካዎች ነጻነት መስጠቱን በመፍትሔነት መውሰዱን በሚኒስቴሩ የንግድ ዕቃዎች ዋጋ ጥናት፣ ክትትልና ቁጥጥር ዳይሬክተር ካሳሁን ሙላት ለአዲስ ማለዳ አስረድተዋል።

መንግሥት እጁን እንዲያወጣ በተደጋጋሚ ከተጠየቀ በኋላ ፋብሪካዎች ያተርፈኛል በሚሉት ዋጋ አውጥተው፣ የመቆጣጠሩንም ኃላፊነት ወስደው፣ ከዋጋ በላይ የሚሸጥ ካገኙም ዕርምጃ የሚወስዱበትን ግልጽ አሠራር እንካችሁ ብለናል ሲሉ ነው የገለጹት።

ይህ አሠራር የተዘረጋውም በክረምት ያለው ግንባታ አነስተኛ እንደመሆኑ መጠን የሲሚንቶ ፍላጎት መቀነስ ስለሚኖር ኹሉም የዘርፉ ተዋንያኖች፣ አምራች ኢንዱስትሪዎች፣ አከፋፋዮችና ቸርቻሪዎች ባልተጋነነ ዋጋ እንዲሸጡ በማሰብ እንደሆነ ካሳሁን ገልጸዋል።

ዮት ኮንስትራክሽን አገሪቷ ላይ ትላልቅ የኮንስትራክሽን ተግባራት ከሚያከናውኑ ድርጅቶች አንዱ ሲሆን፣ ባለፉት 15 ቀናት በተፈቀደው የነጻ ገበያ መሰረት የሲሚንቶ ዋጋ በጣም በመወደዱ ምን ማለት ራሱ እንዳለብን ግራ ገብቶናል ሲሉ የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ዮናስ ሙሉጌታ ተናግረዋል።

እንደ ኮንትራክተር በጣም ፈተና ውስጥ ወድቀናል። ነጻ ገበያ ሲሆን እንደልብ ሲሚኒቶ የማግኘት ዕድል ቢፈጥርልንም፣ አንድ ሲሚኒቶ 720 ብር ገዝተን እየተጠቀምን ነው ብለዋል። አዲስ ማለዳ ዮናስን ባነጋገረችበት ወቅት ዳንጎቴ ሲሚንቶን በ720 ብር እና ሌሎችን ደግሞ በ680 ብር ገዝተው እየተጠቀሙ መሆኑን ነግረዋታል።

ሲሚንቶ ከፋብሪካው ከመጣ በኋላ ወደ ኮንትራክተሩ ሲደርስ ከ300-400 ብር መሸጥ ሲገባው አሁን ላይ በተጋነነ ብር እየገዛን እንገኛለን ሲሉ ቅሬታ አቅርበዋል።
‹‹ኮንትራክተሩ የሚሠራው በጊዜ ነው። ለምሳሌ ለ2 ዓመት የተያዘ ፕሮጀክት ያለን ሲሆን ማቆም አይቻልም፤ ለመጨረስ ደግሞ ውሉን በተዋዋልንበት ወቅት የነበረው የሲሚንቶ ዋጋ እና አሁን ያለው ዋጋ እየተለያየ ለአላስፈላጊ ወጪ ዳርጎናል። ይህ ደግሞ ሥራችንን በመሥራት ማትረፍ ሲገባን ላልተገባ ተጨማሪ ወጪ እየዳረገን ነው›› ብለዋል።

‹‹እንደ ኮንትራክተር ሲሚንቶ ብቻ አይደለም የሚያሳስበን፣ ብረት ከ200 ፐርሰንት በላይ ጨምሮ ነው ያለው። አሁን ደግሞ ሲሚንቶ ሲጨምር ጫና ፈጥሮብናል››ሲሉ ዮናስ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
በፊት የነበረው ነጻ ገበያ ሌሊት መግዛት እና ጥቁር ገበያ የተንሰራፋበት ነበር። የአሁኑ ለየት የሚያደርገው ነገር ፊት ለፊት ሱቅ ላይ ሲሚንቶ ማግኘት ይቻላል። ነገር ግን ዋጋው የሚቀመስ አይደለም።
እንደ ኮንስትራክሽን ድርጅት የመንግሥት ፕሮጀክት በሚሰራበት ወቅት ከፍተኛ ኪሳራ ያጋጥማል። የግል ከሆነ ግን ገበያውን ባማከለ ሁኔታ የዋጋ ማስተካከያ መፍጠር ይቻላል።

ዮት ኮንስትራክሽን ከ6 ፕሮጀክት በላይ እየሠራ ያለ ድርጅት ሲሆን፣ ወሊሶ አጠቃላይ ሆስፒታል፣ የአዲስ አበባ ውኃና ፍሳሽ እንዲሁም አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ከሚጠቀሱ ሥራዎቹ መካከል ናቸው።
የነጻ ገበያ መሰረታዊ ጽንሰ ሐሳብ በመጀመሪያ ደረጃ ግልጽ መሆን ይገባዋል የሚሉት የኢኮኖሚ አማካሪ ደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) ናቸው። ነጻ የሚባል የትኛውም አገር እንደሌለ መገንዘብ ያስፈልጋል። በትምህርት ደረጃ ቲዮሪ ላይ ያለ ሐሳብ እንጂ ወደተግባር ሲቀየር ነጻ የሚባል ኢኮኖሚ የለም ሲሉ ይገልጻሉ።

የትኛውም የዓለም ክፍል ቢታይ ነጻ ገበያ ትግበራ ላይ መንግሥት ጣልቃ መግባት ይኖርበታል። ለምሳሌ አሜሪካኖች በተለያየ የኢኮኖሚ ዘርፍ ላይ ጣልቃ ይገባሉ። ቻይና አሜሪካ ውስጥ በብዛት ዕቃ የምታቀርብ ከሆነ የማይቀበለቡት ሁኔታ ይፈጥራሉ። ምክንያቱም የአገራቸውን ምርት እንዳይጠቀሙ ኢንቨስትመንታቸውን ይዘጉባቸዋል። ያንን ታሳቢ በማድረግ የቻይና ምርቶች ለተጠቃሚው በርካሽ እንዲደርስ ይደረጋል። ይህን የነጻ ገበያ ቁጥጥር ሐሳብ ወደ አገራችን ሲመጣና በሲሚንቶ ገበያ ላይ መንግሥት ጣልቃ ሲገባ አንድ ግብ ይዞ ነበር። አሁን ደግሞ ገበያውን ነጻ አድርገው መልቀቃቸው ትልቅ ተግባር ነው። ነገር ግን፣ በዚህ መሀል አንድ ነገር መጠንቀቅ የሚያስፈልገው ጉዳይ ከመንግሥት ጋር ብቻ ሳይሆን፣ ከተጠቃሚውና ከአምራቹ ጋርም ይገናኛል ሲሉ አብራርተዋል።

በማክሮ-ኢኮኖሚ የኢኮኖሚ ሰንሠለት ሦስት ዋና ተዋያንያን እንዳሉት ይጠቀሳል። እነዚህም ሸማች፣ ግብዓት አቅራቢ እና መንግሥት ናቸው። እነዚህ ሦስቱን የሚያገናኙ የሸቀጥ፣ ፋይናንስ እና የግብዓት ገበያ አሉ። እነዚህ ሦስት ተዋያንያኖች በአንድ መስመር ማስኬድ ካልተቻለ እና ተገቢውን ሚናቸውን ካልተጫወቱ ችግር ይፈጠራል።

በሲሚንቶ ዘርፍም ቢሆን ሲሚንቶውን የሚሸምተው በአቋራጭ መንገድ የሚገዛ ከሆነ የድለላ ሥራዎችን ለማበራከት በር ይከፍታሉ ሲሉ ደምስ ይገልጻሉ።
ሦስቱ ከላይ የተጠቀሱት ተዋንያኖች መናበብ የሚችሉ፣ ለአገር የሚጠቅሙ ጨዋታ መጫወት አለባቸው።

መንግሥት ምርት የሚደብቁትን፣ ከተማ ውስጥ በሌሊት የሚሸጡትን እና ያለአግባብ ትርፍ ፈላጊዎችን መቆጣጠር ይጠበቅበታል። ነጻ ገበያ የሚባለው ሐሳብ በአግባቡ እና በሚፈለገው መንገድ የቅርብ ክትትል እና ቁጥጥር ሊደረግበት ይገባል።
የገበያ ትስስር መርዘም እና የደላሎች መብዛት የሚፈጥረው ጫና በሲሚንቶ ላይ ብቻ ሳይሆን በሽንኩርት እና በመሳሰሉ ሸቀጥ ግብይት ላይ የሚታይ ነው።

ይህን ደግሞ የፈጠረው የ‹ሳቦታጅ› ጉዳይ ነው የሚሉት ደምስ፣ የንግድ ሰንሠለቱ ማለት ከአምራቹ እስከ ተጠቃሚው ድረስ ባሉ ተጫዋቾች የሚደረግ የገበያ ጨዋታ ነው። ይህ ደግሞ በተለምዶው ደላላ የሚበዛበት ትስስር መሆኑን ያስረዳሉ።
‹‹በእኔ አመለካከት ይህን ትስስር የሚያሳልጥ ደላሎች መኖር የለባቸውም ማለት አንችልም። እነሱን እንዴት ሕጋዊ ማድረግ ይቻላል በማለት ሥራቸውን ሕጋዊ የሚያደርግ አካል በትኩረት መሥራት አለበት እንጂ መከላከልና ማስቆም ከባድ ነው›› ሲሉ ደምስ ገልጸዋል።

የድለላ ሥራ በየትኛውም አገር ያለ ስለሆነ “አትደልሉ፣ ኮሚሽን አትቀበሉ” ማለት አይቻልም። እንደውም በሕገ-ወጥ መንገድም ቢሆን ንግዱን እያሳለጡ ያሉት ደላሎች መሆናቸው መታወቅ አለበት። ሕጋዊ እንዲሆኑ ስልጠና መስጠት ይሻላል። ሳቦታጅ ነው የተባለውም መንግሥት መዋቅር ስር ያሉት የፖለቲካ ሥልጣናቸውን ተጠቅመው ለመበለጸግ ስለሚፈልጉ ታች ባሉት ደላሎች ነው የሚጠቀሙት ። ይህ እንዳይፈጠር በገንዘብ የሚደለሉትን በማብቃት እና ሕጋዊ በማድረግ መሥራት ያስፈልጋል ብለዋል።

መንግሥት ደግሞ ነጻ ገበያ አደረኩ ብሎ መተው የለበትም የሚሉት ደምስ፣ ለቁጥጥር የሚመቹ መመሪያዎችን ማውጣት ይጠበቅበታል። መንግሥት ራሱ ሠራተኞቹን ጥሩ የሚሠሩ አድርጎ ማብቃት ይጠበቅበታል። ሥራ ፈጠራ በሚል አወቃቀር ኹሉንም የመንግሥት ሠራተኛ ማግበስበስ የለበትም ሲሉ ጠቅሰዋል።

‹‹ኮንትራክተሩ ተማሯል። ሲሚንቶ በዚህን ያህል ዋጋ እየተገዛ ግንባታ ማካሄድ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ችግር ውስጥ ከቶናል›› የሚሉት ደግሞ ኢንጅነር ግርማ ኃብተማሪያም የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ሥራ ተቋራጮች ማኅበር ፕሬዝዳንት ናቸው።
‹‹ማኅበራችን ባለፉት ጊዜያት ሲሚንቶ ከ800-1000 ብር በሚሸጥበት ወቅት በንግድ ሚኒስቴር ጣልቃ ገብነት ተቆጣጥሮት እስከ 400 ብር ድረስ እየተሸጠ ነበር። ለትንሽ ጊዜያት እፎይታ ሰጥቶ የነበረው ይህ ሂደት ደግሞ የሲሚንቶ እጥረትን እንዲከሰት አደረገ። ሲሚንቶ ማግኘት በጣም ከባድ መሆኑ በሚታይበት ወቅት ደግሞ ገበያውን ልቀቁልን ብለን ቁጥጥሩ ሲቀር እስከ 715 ብር እየገዛን ነው። የሚገዛው ሲሚንቶም ቢሆን ያለደረሰኝ ነው የሚገበያየው። ምን አይነት አገር ውስጥ እንደምንኖር ራሱ አናውቅም›› ብለዋል ፕሬዘዳንቱ።

አምራች ኢንዱስትሪው በተለያየ ጊዜ የሲሚንቶ መያዣ ወረቀት እጥረት ገጥሞኛል፣ ትራንስፖርት እጥረት እንዲሁም የኢንዱስትሪ ማሽኖች ብልሽት ደረሰ እየተባለ ዋጋው ሲንር ቆይቷል።
ይህ የኢኮኖሚ ሳቦታጅ ነው የሚሉት ኢንጅነር ግርማ፣ የሲሚንቶ ዋጋ መናር ከመንግሥት ጋር የተያያዘ ጉዳይ እንጂ የፋብሪካዎች የማምረት አቅም አንሶ አይደለም። ያሉት ፋብሪካዎች ባላቸው አቅም ቢያመርቱ ያለውን ገበያ ማረጋጋት ይችላሉ። መንግሥት ደግሞ ይህን የማምረት አቅማቸውን እንዲያጠናክሩ የመቆጣጠር አቅም እና መዋቅር አለው።

መንግሥት ስርዓቱን ባላስተካከለበት ሁኔታ እንደ እርግማን በሚመስል መልኩ የዋጋ መጨመር በግልጽ እየተደረገ ነው ብለዋል። መንግሥት ምንም ቁጥጥር ያላደረገበት ኮንትራክተሩን የሚጎዳ ሰንሠለት ከአምራቹ ጀምሮ እስከ ሰፈር ደላላ ድረስ ያለ ነው ሲሉም ቅሬታቸውን ያነሳሉ።

ኮንትራክተሩ በሺሕ የሚቆጠር ቋሚና ኮንትራት ሠራተኞች አሉት። ግብር ይከፍላል። መንግሥት ከኮንትራክተሩ የሠራውን ይጠብቃል። የፋብሪካዎች የማምረት አቅማቸውን እጥረት እንዳይገጥማቸው መንግሥት የማይሠራ ከሆነ ችግሩን መቅረፍ አይቻልም። የት ቦታ ችግሩ እንደተፈጠረ ጥቆማ በምንሰጥበት ጊዜ እንኳን ጥቆማችንን ተቀብሎ ዕርምጃ የሚወስድ የለም ብለዋል።
‹‹ኮንትራክተሩ ከዚህ በላይ ጦር ይዞ ዘምቶ ማስቆም አይችልም›› ሲሉ ኢንጅነር ግርማ በምሬት ተናግረዋል።

የሲሚንቶ ፍላጎት ከአመት ዓመት እየጨመረ የመጣ ሲሆን፣ የሲሚንቶ ፍላጎትን መመለስ የሚያስችል ኢንዱስትሪ አለመኖሩ አንዱ ችግር መሆኑን ደግሞ መንግሥት የሚያነሳው መከራከሪያ ነው።
ገበያው ላይ የሲሚንቶ ፍላጎት በሚበዛበት ጊዜ ደላላዎች ገብተው የባሰ ውስብስብ ችግር ይፈጥራሉ።

በሲሚንቶ ዕጥረት እና የዋጋ መወደድ ዋነኛ ተጎጂ የሚሆኑት ደግሞ ሪል እስቴቶች፣ ትላላቅ ግንባታዎች የሚያከናውኑ ድርጅቶች፣ የቴራዞ ምርትን ጨምሮ ሲሚንቶን በግብዓትነት የሚጠቀሙ ፋብሪካዎች ናቸው።


ቅጽ 3 ቁጥር 143 ሐምሌ 24 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com