የእለት ዜና

የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ባልተፈቀደላቸው የደረጃ ስያሜ የሰጡትን የትምህርት ማስረጃ እንዲያስተካክሉ ትዕዛዝ ተሰጠ

ለራሳቸው ያልተፈቀደ የደረጃ ስያሜ የሰጡ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት፣ ከዚህ ቀደም ባስመረቋቸው ተማሪዎች ማስረጃ ላይ ያለውን የተቋማቱን የደረጃ ስያሜ እንዲያስተካክሉ የከፍተኛ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ኤጀንሲ አሳሰበ።
ፈቃድ የሌለው የደረጃ ስያሜ የሰጡና በመገልገል ላይ ያሉ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መኖራውቸን ኤጀንሲው ለአዲስ ማለዳ ገልጿል። ያልተፈቀደ የደረጃ ስያሜ የሚጠቀሙ አንዳንድ ተቋማት ለተገልጋዮች መጉላላትም ምክንያት እየሆኑ ነው ተብሏል። በመሆኑም የትምህርት ተቋማቱ ለተማሪዎቻቸው በሚሠጡት ማስረጃ ላይ የሰጡትን የደረጃ ስያሜ በማስተካከል የተማሪዎችን እንግልት የማስቀረት ግደታ እንዳለባቸው ተገልጿል።

የትምህርት ማስረጃ ማረጋገጫ አገልግሎት ለማግኘት ዜጎች ወደ ኤጀንሲው በሚመጡበት ወቅት፣ በትምህርት ማስረጃቸው ላይ ያለው የደረጃ ስያሜ ያልተፈቀደ ሆኖ ሲገኝ የትምህርት ማስረጃቸው ተቀባይነት እንደሚያጣ ኤጀንሲው ጠቁሟል። ከዚህ ጋር በተያያዘ ተማሪዎች አገልግሎት ሳያገኙ ለተጨማሪ ወጪና መጉላላት የሚዳረጉበት ሁኔታ በተደጋጋሚ መፈጠሩን የኤጀንሲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ታረቀኝ ገረሱ ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።

ለአብነት ያህል ዜጎች ለውጭ አገር ጉዞ የትምህርት ማስረጃ ማረጋገጫ እንዲሰጣቸው ወደ ኤጀንሲው በሚመጡበት ወቅት፣ በማስረጃው ላይ የተማሩባቸው ተቋማት ዩኒቨርስቲ ወይም ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በማለት ፈቃድ ያላገኙበትን የደረጃ ስያሜ ተጠቅመው ስለሚገኙ የትምህርት ማስረጃቸው ሕጋዊ እውቅና የማያገኝ በመሆኑ ለእንግልት ይዳረጋሉ ተብሏል።

በተጨማሪም ኮሌጆች የተሰጣቸው ደረጃ ኮሌጅ ሆኖ ሳለ፣ ራሳቸውን ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ በሚል መጠሪያ የትምህርት ማስረጃ ለተማሪዎቻቸው ስለሚሰጡ በሥራ ቅጥር ወቅት አመልካቾች ላይ ችግር እየተፈጠረ እንደሆነና በሙያ ፈቃድ አሰጣጥም ላይ ተመሳሳይ ችግር እንደሚያጋጥም ታረቀኝ አንስተዋል። በዚህ ምክንያት አስቸኳይ ጉዞ ያላቸው ተገልጋዮች ጉዳያቸው የሚስተጓጎልበት ሁኔታ የተፈጠረበት አጋጣሚ መኖሩን ይጠቅሳሉ።

እያንዳንዱ ተቋም የራሱ የደረጃ ስያሜ እንዳለው ኤጀንሲው ገልጾ፣ በዚሁ መሰረት ተቋማት ዩኒቨርስቲ፣ ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ፣ ኮሌጅ እና ኢንስቲትዩት በሚል የሚገለጽ ሲሆን፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ደረጃ ስያሜ አሰጣጥ የራሱ የሆነ መመሪያ እና ዝረዝር የመመዘኛ መስፈርቶች እንዳሉት ኤጀንሲው አስታውቋል።

በከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ያልተፈቀደ የግል ከፍተኛ ትምህርት ተቋም የደረጃ ስያሜ ተቀባይነት እንደሌለው እና ባልተፈቀደ የደረጃ ስያሜ የተሰጠ የትምህርት ማስረጃም ሕጋዊነት እንደማይኖረው ኤጀንሲው ገልጿል።
ከሦስት ዓመት በፊት ኤጀንሲው በነበረበት የክትትልና ቁጥጥር ክፍተት ምክንያት አንዳንድ ተቋማት ኤጀንሲው ያልሰጣቸውን የደረጃ ስያሜ በመጠቀም ራሳቸውን በኢንተርኔት አውታሮች እና በሚዲያዎች ሲያስተዋውቁ የቆዩ ቢሆንም፣ በአሁኑ ወቅት እነዚህን ተቋማት ወደ ሕጋዊ ሥርዓት ለማስገባት በርካታ ሥራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው ተናግረዋል። በዚህም በአሁኑ ወቅት ጥሩ የሚባል ለውጥ መኖሩን ኃላፊው ጠቅሰው፣ አሁንም ግን ይህን ችግር ያላስተካከሉ አንዳንድ ተቋማት መኖራቸውን ታረቀኝ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ አንስተዋል።

ዩኒቨርሲቲ የደረጃ ስያሜ ያላቸው የግል ተቋማት እስካሁን አምስት ሲሆኑ፣ ዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ፣ ቅድስተ-ማርያም ዩኒቨርሲቲ፣ ሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ፣ ሐራምቤ ዩኒቨርሲቲ እና አድማስ ዩኒቨርሲቲ ናቸው። እንዲሁም ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ ስያሜ ያላቸው የግል ተቋማት እስካሁን አምስት ሲሆኑ፣ አልፋ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ፣ ኒው ጀነሬሽን ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ፣ ሸባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ፣ ሆፕ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ እና ጌጅ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ መሆናቸውን ኤጀንሲው አስታውቋል።
ያልተፈቀደ የደረጃ ስያሜን በመጠቀም በሚዲያ ማስታወቂያ ማሠራት፣ በተለያዩ ሰነዶችና ባነሮች ላይ መጠቀም፣ማኅተም ማሠራት፣ ወዘተ. የተከለከለ መሆኑ ተመላክቷል።

ተቋማት ባልተፈቀደ የደረጃ ስያሜ የሰጡትን የተማሪዎች ማስረጃ የማስተካከልና ለወደፊቱም ለተመራቂዎቻቸው በሚሰጡት የትምህርት ማስረጃ ላይም ሆነ በሚያሠሩት ማስታወቂያ ላይ የተፈቀደላቸውን የደረጃ ስያሜ ብቻ በመጠቀም ሕጋዊ ግዴታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ተገልጿል።

ተማሪዎችም ከዚህ በፊት ባልተፈቀደ የደረጃ ስያሜ የተሰጣቸውን ማስረጃ መመለስ ይኖርባቸዋልም ተብሏል። እንዲሁም በምረቃ ወቅት ከተቋሙ የሚሰጣቸው የትምህርት ማስረጃ ላይ የሚሰፍረው የተቋሙ የደረጃ ስያሜ የተፈቀደ ስለመሆኑ ማረጋገጥ እንደሚኖርባቸው ተጠቁሟል።


ቅጽ 3 ቁጥር 143 ሐምሌ 24 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!