የእለት ዜና

ወታደራዊ ሥነ-ምግባር ትኩረት ይሰጠው!

በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ወታደራዊ ዘመቻ ከተጀመረ ከ9 ወራት ወዲህ በርካታ ዘግናኝ ተግባራት መፈጸማቸው ሲነገር ቆይቷል። ንጹሃንን ከመጨፍጨፍ ጀምሮ ሴቶችን መድፈርና ሕፃናትን ለጦርነት ማስገደድን የመሳሰሉ ተግባራት ለመፈጸማቸው ብዙ ማስረጃዎች ሲቀርቡም ነበር። ተግባሮቹ በየትኛውም ወገን ይፈጸሙ በዓለም ዐቀፍ መድረክ ኢትዮጵያውያኖች ፈጸሙት ተብሎ የነበረችን መልካም ስም በጅምላ እንድናጣ ራሳችን ራሳችንን ስናጋልጥ ቆይተናል።

ከወታደራዊ ሥነ-ምግባር ያፈነገጡ ሕሊና ቢስ በሆኑ ግለሰብ ተዋጊዎች የተፈጸሙት መወገዝ ቢኖርባቸውም፣ እንዲህ አይነት ተግባሮችን አከናውኑ ብሎ የዕዝ ሰንሠለቱን ተጠቅሞ ተግባራዊ ያስደረገ ስለመኖሩ እስካሁን የተረጋገጠ ነገር የለም። እንዲህ አይነት ስሞታ የሚቀርብላቸው የውጭ ዜጎች፣ ተግባሩ እንዲቆም መፍትሄ ከመፈለግና አጥፊውን ለይተው ከማስቀጣት ይልቅ፣ መረጃውን ወስደው ማስፈራሪያና እጅ መጠምዘዣ እንደሚያደርጉት ድርጊቱ የተፈጸመባቸው ሲናገሩ ይሰማል። የራሳቸውን ፍላጎት ለማሳካት የሚማስኑት በርካታ የመሆናቸውን ያህል፣ ለሰው ልጆች ሠላም የቆሙም ጥቂቶች አይጠፉም። እነዚህ ግን ጉልበተኞቹ ፈቅደውላቸው መጠቀሚያ ስለሚያደርጉዋቸው ፍትሐዊ ሆነው በጎ አድራጎት ሥራቸውን ስለመሥራታቸው እንደሚያጠራጥር የሚናገሩ አሉ።

አገር ሠላም እንድትሆን ሁሉም ፍላጎቱ እንደሆነ ቢናገርም፣ ተግባራቸው በተቃራኒው የሚሆንም በርካቶች ናቸው። ጦርነት ጥቅም የሚያስገኝላቸው የመኖራቸውን ያህል ሠላም ከሆነም መኖራቸው የማያስፈልግና ተፈላጊነታቸው የሚቀንስ የሚመስላቸውም ጥቂት አይደሉም። በተለይ በውትድርናው ውስጥ ያሉ ሹመትና እድገትን በተፋጠነ መልኩ እንዲደርሳቸው የሚፈልጉ ጦርነት እንዲቆም እንደማይፈልጉ ይነገራል። ከጥንት ጊዜ አንስቶ የነበረው ይህ የጦርነት ፍላጎት በደርግ ዘመንም ይስተዋል እንደነበር የሚናገሩ አሉ። ሻዕቢያን ናቅፋ ላይ እንዳታንሰራራ አድርጎ ማሸነፍ እየተቻለ፣ ሥልጣን ላይ ያለው ወታደራዊ መንግሥት በሲቪል መንግሥት ይተካ አያስፈልግም የሚል ሐሳብ እንዳይነሳ፣ የሸማቂዎቹ ጦር ሹማምንት እንዲያንሰራሩ በተደጋጋሚ ዕድል እንደተሰጣቸው በርካቶች ይስማማሉ።

አሁን እየተደረገ ያለው ዘመቻም እንዳይቆም የሚፈልጉ አሉ የሚባለውም ከዚሁ ሐሳብ ጋር የተገኛኘ ነው። አንዳንዶች በኹለቱም ወገን የሚያዋጉ፣ እንዲወገድ የፈለጉትን ተሰላፊ እያጋፈጡ ገለል እንዲልላቸው እያደረጉ ነው የሚሉ አሉ። ያም ተባለ ይህ ጦርነቱ እልባት ሳያገኝ ውጊያው እያደር እያገረሸ አልቋል ተብሎ የነበረው እየተባባሰ መምጣቱ ብዙዎችን አሳዝኗል። ይህ አይነት አስተሳሰብ ከሕዝብ ልቦና ውስጥ እንዲወገድ መንግሥት ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንዳለበት አዲስ ማለዳ ማስገንዘብ ትወዳለች።

በሌላ በኩል፣ አሻጥር እየተፈጸመብን ነው የሚሉ ስሞታዎች እያደር በመጠንከራቸው ለጦር መሪዎች መወገድ ምክንያት እየሆነ እንደሆነ እየተነገረ ነው። “ስልታዊ ማፈግፈግ በሚል እሳቤ እያሸነፍን ሳለ ተመለሱ እንባላለን” የሚል የሠራዊቲ ድምፅ መሰማት ከጀመረ የቆየ ቢሆንም፣ ከሠሞኑ አቅጣጫ የሚያስቀይር ዕርምጃ መወሰዱ ተሰምቷል። ባንዳ ነበር የተባለ “ተመለሱ” ብሎ ያዘዘ እንዲመለሱ ባዘዛቸው ሠራዊት “ተላላኪ” ተብሎ እንዳይመለስ ተደርጎ ተሸኝቷል የሚል ወሬ ተሰምቷል። ሌሎችም በተመሳሳይ፣ ሕዝብ በአሉባልታ እንዲዘናጋ፣ እንዲሸበርና ጦሩ እንዲፍረከረክ ያደረጉ አመራሮችም ለእስር መዳረጋቸው ተሰምቷል።

እንዲህ አይነት ተግባሮች ተገቢ ናቸው አይደሉም የሚለውን መተንተኑ ለወታደራዊ ባለሙያ መተው ቢኖርበትም፣ አዲስ ማለዳ ስለወታደራዊ ሥነ-ስርዓት አስፈላጊነት ያላትን ዕምነት ለማሳወቅ ትወዳለች። ተራ ወታደር ወደ ታቀደለት የሞት መሬት እያሳደድኩ ነው በሚል ጠልቆ እንዳይገባ አዛዦች ትልቅ ሚና አላቸው። ሞት ባጠላበት ወቅት እንዲህ አይነት ጉዳይ ላይ ተሰብስቦ ለመወሰን አሊያም የበላይን ለማማከር አስቸጋሪ ሊሆን ስለሚችል ውጊያውን በአካል ተገኝቶ የሚመራው አዛዥ ኃላፊነቱን ይወስዳል። አርቆ ማሰብና በስሩ ላሉት ነፍሳት መቆርቀር ያለበትን ያህል፣ ፍርሃትም ሆነ ሌላ ተልዕኮ ሊኖረው እንደሚችል መገመቱ አይከፋም የሚሉ አሉ። ከውጊያ በፊት መሪን አምኖ መሄድ እንጂ መሀል ላይ ሊገመገምና ክርክር ውስጥ ሊገባ አይገባም የሚሉም መኖራቸው ይታወቃል።

ወታደራዊ የዕዝ ሰንሠለቱ ተጠብቆ ውጊያ መካሄዱ አስፈላጊ መሆኑ ቢታመንም፣ ምርጥ አዋጊና ጀግና በውጊያ እንጂ በትምህርት ብቻ ተፈትኖ አንደማይገኝ በርካቶች ያምናሉ። ሰሞኑን እንደተወሰደው ወታደራዊ ዕርምጃ አይነት ከተለመደ፣ መቧደንን ያስከትልና ትዕዛዝ ለማስተላለፍ አስቸጋሪ ያደርገዋል የሚሉ አሉ። በሌላ በኩል፣ ሌላው አዛዥ ስለራሱ የነበረው የራስ መተማመን እንዲላሽቅና ማፈግፈግ በሚያስፈልግበት ወቅት እንዲያመነታ ያደርገዋል። ይህ አይነት አካሄድም ብዙ ሰው እንዲያልቅ ሊዳርግ ስለሚችል ተዋጊዎችም ሊያስቡበት እንደሚገባ የዘርፉ ምሁራን የሚናገሩት ነው።

በወታደራዊ ሕግ የበታች የበላዩን መገምገም የለበትም ብለው አጥብቀው የሚያምኑ የመኖራቸውን ይህል፣ አምነው ሕይወታቸውን አሳልፈው ሊሰጡለት የሚችሉትን አዛዣቸውን ማንነት ማወቅና መምረጥ እንዳለባቸው የሚወተውቱ አሉ። በመደበኛ ጦርነት ውስጥ መምረጥ የማይታሰብና ተገቢ አለመሆኑ ቢነገርም፣ ከጥንት ጀምሮ ውጤታማ ያደረገን የወዶ ገብ አሰላለፍ ከግምት መግባት እንዳለበት የሚያስረዱ አሉ። በተለይ መደበኛ ተዋጊ ያልሆነውና የራሱን ስንቅና ትጥቅ ይዞ የሚሰለፈው፣ የግዳጅ ቀጠና ተሰጥቶት በመረጠው አለቃ መመራት እንደሚገባው ብዙዎች ይስማማሉ። የክተት አዋጅ ታውጆ የተከተተው ሠራዊት፣ ከሚተዋወቀው ከሚናበበው ጓዱ ጋር በጋራ ቢዘምት፣ እንዲሁም የፈለገው አዛዥ ስር ገብቶ ለአጠቃላይ ዕዙ ተገዢ እንዲሆን ይመከራል።

ጦርነት ጥበብንና ማስተዋልን ከመጠየቁ ባሻገር የጠላትን ፍላጎት፣ እንቅስቃሴና አስተሳሰብ ተረድቶ ቀድሞ ማሰብን እንዲሁም ተዘጋጅቶ መጠበቅን ይጠይቃል። ምን ሊያደርግ ይችላል የሚለው የአዛዦች ትልቁ መፈተኛ ነው። ለዚህ ደግሞ መረጃ ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል። ስለውጊያ ቀጠናው፣ ስለተዋጊው ብቃትና ጉድለት፣ እንዲሁም ስለሥነ-ልቦናው ማወቁ ለውጤቱ አቅጣጫ መሠረት ይጥላል። ወኔና ድፍረት እንዲሁም ብዛትና ትጥቅ ለውጊያ ያግዛሉ እንጂ አሸናፊ እንደማያደርጉ የጦር ጠበብቶች ሲናገሩ ይሰማል።

ሥነ-ልቦናን በተመለከተ፣ አይደለም ወታደር ተማሪም የሚገመገምበት ፈተና ላይ ከመቀመጡ በፊት ሥነ-ልቦናው የአሸናፊነት መሆን አለበት። ወታደር ሲሆን የተበዳይነት መንፈስ እንዲኖረው ካልተደረገና በተቃራነው ከሆነ ሞራሉ ሊላሽቅ እንደሚችል ይነገራል። በሽለላ ከአንዱ ወደ ሌላው ድፍረት የሚተላለፈውን ያህል፣ ፍርሃትም እንደሚጋባ ሊታወቅ ይገባል። ኢትዮጵያ እንዳላት በሚነገር ስለጦርነት በሚያትት፣ የውጊያ ጥበብን በሚገልጽ ጥንታዊ መጽሐፍ ውስጥ አዋጊም ሆነ ተዋጊ ማድረግ የሚጠበቅባቸው ነገሮች አሉ። ወሬን አለመናቅ አንዱ ሲሆን፣ ልቦናን ማደፋፈር ሌላው አስፈላጊ ዝግጅት ነው። ለጠላት ጀርባ አለመስጠትን የሚመክሩ የመኖራቸውን ያህል፣ ፈሪን ጦር ሜዳ ሳይደረስ ማግለል እንደሚስፈልግ ይታመናል።

“ሞት በአጋጣሚ አይሞትም” በሚባልባት አገር “መሞቻ ቀኔ ካልሆነ አልሞትም፣ ከሆነም ብደበቅም አይቀርልኝም” ተበሎ መቅበጥ ባያስፈልግም፣ አለመፍራት ግን ወሳኝ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል። እንደገለልተኛ ወገን ሕዝብ ከየትኛውም ወገን እንዳያልቅ የሚያደርግ አማራጭ፣ ይህ ካልሆነም አንደኛው በቀላሉ አሸንፎ ስርዓት የሚያሲዝበት መንገድ ቢወሰድ መልካም እንደሚሆን አዲስ ማለዳ ማሳሰብ ትወዳለች።


ቅጽ 3 ቁጥር 143 ሐምሌ 24 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!