የእለት ዜና

የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ፈርሶ ቦታው ለሪልስቴት አገልግሎት ሊውል ነው ተባለ

Views: 387

የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ ያለ ተቋሙ ባለሙያዎች ውይይት እና ተሳትፎ በኢንጅነር ታከለ ኡማ በሚመራው የማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ፈርሶ ሪልስቴት ቦታው ላይ ቤቶች ሊገነባበት መሆኑ ተገለጸ።
የአዲስ ማለዳ ምንጮች እንደሚሉት ከሆነ በኢንጅነር ታከለ ኡማ የሚመራው መሥሪያ ቤት፣ በአዲሱ የበጀት ዓመት በጸደቀለት በጀት መሠረት የነበረውን አሰራር በመተው በአዲስ መዋቅር እየተደራጀ እና ሠራተኞችንም ለመቀነስ የሦስት ሰዎችን ሥራ አንድ ሰው እንዲሠራ እያደረገ ነው።

የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይን የማፍረስ ዕቅድ በጣም የተሳሳተ መሆኑንና ተቋሙ ለአገር በጣም አስፈላጊ እንደሆነ በማንሳት የውኃ፣መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ እየተሟገቱ እንደሚገኙም ምንጮቹ ጠቁመዋል።
የአዲስ ማለዳ የውስጥ ምንጮች እንደገለጹት ሚኒስትሩ ወደ ማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ከመጡ ጀምሮ የጂኦሎጂካል ሰርቬይ ተቋም ላይ ትልልቅ ኪሳራዎች እንዲደርሱ ሲደረግ ቆይቷል ነው ያሉት።
ከእነዚህም አንዱ ከምርጫ በኋላ ለተቋሙ የመጣውን የአራት ቢሊዮን ብር የከርሰ ምድር ቁፋሮ ፕሮጀክት ለውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር በማስተላለፍ ተቋሙ ላይ ጫና እየፈጠሩ መሆኑን ምንጩቹ ገልጸዋል።

ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ፣ ለጂኦሎጂካል ሰርቬይ በአዋጅ የተሰጠውን የምርምርና ካርታ ሥራ ኃላፊነት በመንጠቅ፣ በማዕድን እና ነዳጅ ሚኒስቴር ውስጥ እንደ አንድ ቡድን በማድረግ እና የተቋሙን ሕልውና በማሳጣት አገሪቱን በዓለም ላይ ብቸኛዋ የጂኦሎጂካል ሰርቬይ ተቋም የሌላት ያደርጋታልም ነው ያሉት ቅሬታ አቅራቢዎቹ።

የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ በቦሌ ክፍለ ከተማ ጉርድ ሾላ የሚገኝ ተቋም ሲሆን፣ ትልልቅና መካከለኛ የመስክ ተሸከርካሪዎች፣ በየክልሉ የሚገኙ በርካታ ቅርንጫፍ ቢሮዎች፣ 1192 የሥራ መደቦች እና 650 ሠራተኞች ያሉት መሆኑ ታውቋል።

ከእነዚህ ሠራተኞች ውስጥ ከ300 በላይ የሚሆኑት የመስክ ምርምር የሚሰሩ የጂኦሎጂ፣ ጂኦፊዝክስ፣ ሴስሞሎጂ፣ ቮልካኖሎጂ፣ ጂኦተርማል ጂኦሎጂ፣ ጂኦ ኬሚስትሪ፣ ኃይድሮሎጂ፣ ኢንጂነሪንግ ጂኦሎጂ፣ ሪሰርቫየር ኢንጂነሪንግ፣ ላብራቶሪ እና ድሪሊንግ ኢንጂነሪንግ ባለሙያዎች መሆናቸውንም አዲስ ማለዳ ተረድታለች።

ተቋሙ በ1960 በማዕድን፣ ውኃና ኃይል ምንጭ ሚኒስቴር ስር በመምሪያ ደረጃ ከተቋቋመ በኋላ በ1975 ራሱን ችሎ የኢትዮጵያ ጂኦሎጂ ጥናት ኢንስቲትዩት በሚል ስያሜ ለማዕድንና ኢነርጂ ሚኒስቴር በተጠሪነት ተደራጀ።
በመጨረሻም በ1992 በአዋጅ ቁጥር 194/1992 የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ በሚል ስያሜ ለማዕድንና ነዳጅ ሚኒስቴር ተጠሪ ሆኖ እንደገና ተዋቀረ። በ2003 በተደረገው የፌደራል መሥሪያ ቤቶች አደረጃጀት ተቋሙ ቀደም ሲል የያዘውን ስያሜ፣ ተግባርና ኃላፊነት እንደያዘ ለማዕድን ሚኒስቴር ተጠሪ ሆኖ በመሥራት ላይ ይገኛል።

የተቋሙ ዋነኛ ሥራ በሥነ-ምድር ጥናት ዘዴዎች ስለ ምድርና በውስጧ ስለሚገኙ ማዕድናት ምርምር ማካሄድና የማዕድን ሀብት ክምችት መፈለግ፣ መመርመር፣ መገመት እና ማዕድኑ የሚገኝበትን ድንበር ለይቶ ማመልከት ነው።
ተቋሙ ከሚሠራቸው የተለያዩ የቁፋሮ እና የላብራቶሪ መደበኛ ሥራዎች በተጨማሪ፣ ባሉት ትርፍ ማሽኖች በትርፍ ሰዓት ለውጭ ተገልጋዮች የተለያዩ የቁፋሮ፣ የላብራቶሪ ምርመራ፣ የሥነ-ምድር መረጃ አቅርቦት እና ማማከር ሥራ በመሥራት በዓመት እስከ 20 ሚሊዮን ብር ገቢ እንደሚሰበስብ ይገለጻል።

ከዚህ በተጨማሪ በአሉቶ ላንጋኖ 70 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማመንጨት በታቀደው መሰረት፣በመጀመሪያው ምዕራፍ 35 ሜጋ ዋት ለማመንጨት የሚያስችል የጉድጓድ ቁፋሮ ሥራ እያከናወነ ይገኛል።
በተያያዘም በተንዳሆ አካባቢ 12 ሜጋ ዋት ሊያመነጭ የሚያስችል የጉድጓድ ቁፋሮ ሥራ ለማከናወን እየተዘጋጀ መሆኑንም ማወቅ ተችሏል።

የኢትዮጵያ ጂኦሎጂካል ሰርቬይ በዋና ዳይሬክተርና በዋና ጂኦሎጂስት የሚመራ ሲሆን፣ ለዋና ዳይሬክተሩ ተጠሪ የሆኑ አስር ዳይሬክተሮችና ኹለት ጽሕፈት ቤቶችን አቅፏል። ለዋና ጂኦሎጂስት ጽሕፈት ቤት ተጠሪ የሆኑ ስምንት ቴክኒካል ዳይሬክተሮች ሲኖሩ፣ ተቋሙ በድምሩ 18 ዳይሬክቶሬቶችና ኹለት ጽሕፈት ቤቶች እና ድርጅታዊ መዋቅር ያለው መሆኑንም አዲስ ማለዳ ማወቅ ችላለች።


ቅጽ 3 ቁጥር 143 ሐምሌ 24 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com