የእለት ዜና

የብሔራዊ አካል ጉዳተኞች ማኅበር ኦሮሚያ ቅርንጫፍ መዘጋቱ ተገለጸ

የብሔራዊ አካል ጉዳተኞች ማኅበር የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት በኦሮሚያ ክልል ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ መዘጋቱ ተገለጸ።
ማኅበሩ በኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ በመሆን መሥራት እንደማይችል የኦሮሚያ ሠራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ መግለጹን የብሔራዊ አካል ጉዳተኞች ማኅበር የኦሮሚያ ቅርንጫፍ ፕሬዝዳንት ተካልኝ ባይሳ ገልጸዋል።
ከተቋቋመ 22 ዓመት ያስቆጠረው ብሔራዊ የአካል ጉዳተኞች ማኅበር የኦሮሚያ ቅርንጫፍ ቢሮ መዘጋቱ ቅሬታ አስነስቷል። በኦሮሚያ ክልል ጅማ የሚገኘው የብሔራዊ አካል ጉዳተኞች ማኅበር ቅርንጫፍ ቢሮን ሰብሮ በመገባት ቢሮው ለሌላ አካል ተላልፎ መሰጠቱም ተመላክቷል።

የክልሉ ሠራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ በጻፈው ደብዳቤ፣ ማኅበሩን ቢሮ እንዲያስረክብ የተጠየቁ ሲሆን፣ በክልሉ ውስጥ ለመንቀሳቀስም ፍቃድ መውሰድ የሚገባው ከፌደራል መንግሥት አለመሆኑ ተጠቅሷል። ይህ አሠራር ተገቢ አለመሆኑን የሚቃወመው ማኅበሩ፣ የፌደራሉ ፓርላማ ያጸደቀውን አዋጅ በመሻር ነው ቢሮው የተዘጋው ሲሉ ተካልኝ ለአዲስ ማለዳ አብራርተዋል።

የፌደራል ፓርላማ ባጸደቀው የኢትዮጵያ የበጎ አድራጎት ማኅበራትን ለማቋቋም በወጣ አዋጅ ቁጥር 1113/11 መሰረት፣ የፌደራል ምዝገባ ማኅበራት ኤጀንሲ ፌደራል ላይ ተቀምጦ በመላው ኢትዮጵያ ለሚቋቋሙ ማኅበራት መተዳደሪያ ደንብ ማቅረብ እና ማኅተም አስመትቶ ማኅበራት ፍቃድ እንዲያገኙ ማድረግ ይችላል።

ይህንን መሰረት በማድረግ የተቋቋመው ብሔራዊ ማኅበር፣በመላው ኢትዮጵያ ተዋቅሮ እየሠራ ይገኛል። ነገር ግን ይላሉ ተካልኝ ‹‹የማኅበራችን ቢሮ በመዘጋቱ የሥራ እንቅስቃሴዎችን እንዳናደርግ እየተጉላላን ነው›› ሲሉ ጠቁመዋል።
ኤጀንሲው በአስቸኳይ ቢሮዎቹ እንዲከፈቱና በጅማ የተዘረፈው የማኅበሩን ንብረት እንዲመልሱ ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። ለዚህም ደግሞ ሰኔ 2/2013 በተጻፈ ደብዳቤ ማኅበሩ መቋቋሙን ኤጀንሲው በመግለጽ ቢሮው እንዲከፈት ጠይቆ ነበር ሲሉ ተካልኝ ነግረውናል።

ይህ ተግባር የሦስት ሚሊዮን አካል ጉዳተኞችን ሕገ-መንግሥታዊ መብት የጣሰ ተግባር ነውም ብለዋል። የእንባ ጠባቂ ተቋምም የአስተዳደር በደል እንደደረሰባቸው ተገንዝቦ ጥያቄያቸውን እንዲፈታ እንደሚፈልጉ ጠይቀዋል።
ማኅበሩ በዋናነት የዊልቸር ድጋፍ ማሰጠት፣ የአካል ጉዳተኞችን የሥራ ፈጠራ ማበረታት፣ እንዲሁም የመሥሪያ ቦታዎችን ማመቻቸት ተግባር እንዳለው ይታወቃል።

በኦሮሚያ አካል ጉዳተኞችን ለማቋቋም የወጣው አዋጅ አንቀጽ 31፣ የኦሮሚያ ሠራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ለአካል ጉዳተኞች ድጋፍ መስጠት እንደሚገባው ይጠቅሳል።
‹‹ይህን ማድረግ ሲገባው የማኅበሩን ዕቅድ ከቢሮው ጋር በመሆን መሥራት አለባችሁ በማለት ቢሮውን እስከማዘጋት ተደርሷል። ሌሎች ቢሮዎችንም ከፍተን እንዳንሠራ መንገዶች የተዘጉ ሲሆን፣ ዴራ ላይ በሚገኝ ቅርንጫፍ ቢሮ ባለጉዳዮችን እያስተናገድን እንገኛለን›› ሲሉ ተካልኝ ተናግረዋል።

የፌደራል መንግሥት መዋቅር በክልሉ አሠራር ላይ የሚመለከተው አይደለም በማለት ማኅበሩ ክልል ላይ እንዳይሰራ መደረጉን ተካልኝ ገልጸዋል።
አዋጁ የሚፈቅድ ሆኖ እያለና ከክልሉም የሚያባርሩበት አዋጅ እንደሌለ እየታወቀ፣ ፍርድ ቤት በምንሄድበትም ወቅትም ቢሆን ሕገ-ወጥ አለመሆናችንን አረጋግጠው መስማማት እንዳለብን ብቻ እየገለጹልን ይገኛሉ ሲሉ ተካልኝ አስረድተዋል። ማኅበሩ በተለያዩ ክልሎች እየሠራ ያለ ሲሆን በኦሮሚያ ክልል ብቻ መከልከሉ ታውቋል።

የኦሮሚያ ክልል ሠራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ እንደገለጸው፣ ከፌደራል የወሰዱትን ፍቃድ በመመለስ እንደ አዲስ እንዲደራጁ ቢጠየቁም፣ በተባለው መልኩ ለመደራጀት የሚያስችል አዋጅ አለመኖሩን ተካልኝ አብራርተዋል።
በተጨማሪም በክልሉ ፈቃድ የሚሰሩ ከሆነ፣ ፈቃዱ አዲስ አበባ ላይ ከጉምሩክ ቀረጥ ነጻ የሆነ መኪና ለማስገባት እና ዊልቸር ያለ ክፍያ ለማስመጣት መዋዋል አያስችለንም የሚል ስጋት እንዳላቸው ነው ተካልኝ የጠቆሙት።
አዲስ ማለዳ ሐሳባቸውን ለማካተት ለኦሮሚያ ሠራተኛ እና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ በተደጋጋሚ ብትደውልም ምላሽ ማግኘት አልቻለችም።


ቅጽ 3 ቁጥር 143 ሐምሌ 24 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!