የእለት ዜና

አቶ ስብሐት ነጋ እና ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂምን ጨምሮ በሽብር ወንጀል የተከሰሱ 19 ተከሳሾች ዛሬ ፍርድ ቤት ቀረቡ:- የተከሰሱበት የሽብር ወንጀል ክስም በጽሁፍ እንዲደርሳቸው ተደርጓል

በእነ ዶ/ር ደብረፅዮን የክስ መዝገብ ከተከሰሱ 62 ተከሳሾች መካከል አቶ ስብሐት ነጋ እና ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂምን ጨምሮ 19ኙ ተከሳሾች ፍርድ ቤት ቀረበው የተከሰሱበት የሽብር ወንጀል ክስ በጽሁፍ እንዲደርሳቸው ተደረገ።

የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በደብረፅዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) የመዝገብ ስም በስድሳ ሁለት ሰዎች ላይ ክስ መመስረቱን ማስታወቁ የሚታወስ ነው።

የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሕገ-መንግስትና የሽብር ወንጀሎችን የሚያየው አንደኛ ችሎት ክሱን በመዝገብ ቁጥር 27128102 በመቀበል በማረሚያ ቤት የሚገኙ ተከሳሾችን ማረሚያ ቤቱ እንዲያቀርብ ቀሪ ተከሳሾችን የፌዴራል ፖሊስ መጥሪያ አድርሶ እንዲያቀርብ በማዘዘዝ ለዛሬ ሐምሌ 26/2013 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቶ ነበር።

በዚህም መሰረት በዛሬው ዕለት አቶ ስብሐት ነጋ እና ወይዘሮ ኬሪያ ኢብራሂምን ጨምሮ 19 ተከሳሾች ፍርድ ቤት ቀረበው የተከሰሱበት የሽብር ወንጀል ክስ በጽሁፍ እንዲደርሳቸው ተደርጓል።

ዛሬ በችሎቱ ከቀረቡት ከ19ኙ ተከሳሾችም ውስጥ ሁለት ተከሳሾች ለማረሚያ ቤቱ እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ሲተላለፍ ስማቸው ባለመካተቱ ምክንያት ፍርድ ቤት መቅረብ አለመቻላቸው ፖሊስ አስታውቋል፡፡

በተጨማሪም በችሎቱም ዛሬ ያልተገኙት ዶክተር ደብረፅዮንን ጨምሮ ሌሎች 41 ተከሳሾችን ለማቅረብ ወቅታዊው የትግራይ ክልል የጸጥታ ሁኔታ እክል እንደሆነበት ፖሊስ ለችሎቱ አስረድቷል፡፡

ዐቃቤ ሕግ በ62 ሰዎች ላይ ላቀረበው ክስ ሰፊ የሰነድ ማስረጃ ያቀረበ ሲሆን  ፖሊስ ያላቀረበው የተንቀሳቃሽ ምስል ማሰረጃ እንዳለውም ገልጿል።

ፍድር ቤቱ ክሱን ለማንብና ዛሬ በችሎቱ ያልቀረቡት ሁለት ተከሳሾች እንዲቀርቡ ለነሀሴ 11ቀን 2013 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡

 

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!