የእለት ዜና

አፕል የደንበኞቹን ፎቶ አይቶ በሕፃናት ላይ ወሲባዊ ብዝበዛ የሚያደርሱትን ሊለይ ነው

አፕል በሕፃናት ላይ ወሲባዊ ብዝበዛ የሚያደርሱ ደንበኞቹን በአይፎን ስልካቸው አማካይነት መለየት የሚያስችል ቴክኖሎጂ ይፋ አደረገ።

ደንበኞች ፎቷቸውን አይክላውድ ወደተሰኘው ቤተ መዘክር ከመላካቸው በፊት ቴክኖሎጂው ሕፃናት ላይ ወሲባዊ ብዝበዛ ተፈፅሞ ከሆነ እንደሚያጣራ ነው የተገለፀው።

ቴክኖሎጂው ይህን መሰል ምስል ካገኘ በሰዎች እንዲጣራ ይደረግና በኋላ ጉዳዩን ለፖሊስ አሳልፈው እንደሚሰጡም አፕል አስታውቋል።

ነገር ግን ይህ አዲሱ ቴክኖሎጂ ነፃነትን ይጋፋል፣ ያልተፈቀዱ ፋይሎችንና ፖለቲካዊ ጉዳዮችን በስልካቸው ለያዙ ሰዎች አደጋ ነው የሚሉ ቅሬታዎች እየቀረበቡበት እንደሚገኝም ተገልጿል።

ባለሙያዎች ደግሞ አዲሱ የአፕል ቴክኖሎጂን መንግሥታት ሕዝባቸው ላይ ለመሰለል ሊጠቀሙበት ይችላሉ ባይ ናቸው።

ቴክኖሎጂው የሚሠራው ከዚህ በፊት ያሉ የሕፃናት ወሲባዊ ብዝበዛ ፎቶዎችን በመጠቀም መሆኑ ታውቋል።

ካስም የተባለው ቴክኖሎጂ ከጠፉና ጥቃት የደረሰባቸው ልጆች ማዕከል ከሚያገኛቸው ምስሎች እና ከሌሎች ድርጅቶች ያገኛቸውን ፎቶዎችን ይጠቀማል።

ቴክኖሎጂው እኚህን ፎቶዎች በሚገባው መልኩ ወደ ኮድ ይቀይርና በአፕል ምርቶች ላይ ተግባራዊ እንዲሆኑ ይደረጋል።

ግዙፉ ኩባንያ ቴክኖሎጂው የመለየት ኃይሉ መቶ በመቶ ነው ይላል።
ምናልባት ከአንድ ትሪሊዬን ፍለጋዎች አንዱን ቢስት ነው እንጂ ሌሎቹን መንጥሮ የመለየት አቅም አለው ሲል ኩባንያው ይፋ ማድረጉን ቢቢሲ ዘግቧል።

ነገር ግን ቴክኖሎጂው ከለየ በኋላ የሰው ልጅ ድጋሚ ፎቶዎቹን እንደሚያጣራና ከዚያ በኋላ ለሕግ አካል ሪፖርት እንደሚደረግ አፕል አስታውቋል።

አፕል ይህን ይበል እንጂ በቴክኖሎጂ ደህንነት ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች አዲሱን ቴክኖሎጂ ለመቀበል እንዳዳገታቸው እየተገለፀ ነው።

አፕል አዲሱን ቴክኖሎጂ በያዝነው የፈረንጆቹ ዓመት መጨረሻ ይፋ ለማድረግ ማቀዱም ታውቋል።

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!