የእለት ዜና

የሳማንታ ተልዕኮ

ሳማንታ ፓወር የአሜሪካ መንግሥት የውጭ ጉዳይ ባለሥልጣን ሳይሆኑ የአገሪቱ የአንድ ተራድኦ ድርጅት መሪ ናቸው። የሚመሩት ተቋም በስለላ ሥራ ይታማ እንጂ በቀጥታ መንግሥታትን ልዘዝ ሲል የመጀመሪያው እንደሆነ የሚናገሩ አሉ። እኚህ ሴት የምስራቅ አፍሪካ ጉዳይ እንደተነኩ ያህል እያንገበገባቸው መናገር ከጀመሩ የቆዩ ናቸው። የኢትዮጵያ የቀድሞ መንግሥትን በመተቸትም የሚታወቁት እኚህ አወዛጋቢ ፖለቲከኛ፣ ከሠሞኑ ሱዳን ደርሰው ኢትዮጵያ ይመጣሉ ከተባለ አንስቶ መነጋገሪያ ሆነው ነበር።
ሥራቸውን የሚጠሉ ጭራሽ ምድራችንን ሊረግጡ አይገባም፤ መንገድ ዘግተን እንዲመለሱ በማድረግ እሳቸውና መንግሥታቸው የያዘውን አቋም መቃወም አለብን ሲሉ ተሰምተዋል። መንግስት በጉዳዩ ላይ ምንም ሳይል፣ በደፈናው ለሕወሓት የምዕራብ ቀጠና ሊከፈትላቸው እንደማይችል በተለያየ መንገድ ሲያሳውቅ ነበር። ሴትዮዋ ይመጣሉ በተባሉበት ቀን ምን እንደሆነ ባልተገለጸ ምክንያት መዘግየታቸውም መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።
ገና ከመምጣታቸው በፊት በትዊተር የለቀቁት ዛቻ የመሰለ ማስጠንቀቂያን የተመለከቱ፣ የተሰደቡ ያህል ተሰምቷቸው ተደፈርን ሲሉ ሐሳባቸውን አስተጋብተዋል። በውስጥ ጉዳይ መግባታቸው ብቻ ሳይሆን ገለልተኛ መሆን ከሚጠበቅበት የእርዳታ ተቋም መሪ መሰማቱ “እንኳንስ ዘንቦብሽ ድሮውንም እርጥብ ነሽ” አስብሏቸዋል። እርዳታውን እኛ በፈለግነው መንገድ ካልሆነ ተርበው ያልቃሉ እንጂ አይደርስም የሚል ይዘት ያለውን መርዛማ ሐሳባቸውን ማር በመሰለ ለዘብተኛ አነጋገር ለውሰው እንካችሁ ብሉት ብለው ለማጉረስም ሞክረዋል።
ለመቀሌ እርዳታ ለማድረስ ከሱዳን ወደቦች ይልቅ የጅቡቲውም ሆነ የኤርትራዋ ምፅዋ በብዙ እጥፍ እንደሚቀርቡ ግልጽ ነው በሚል ሞኝሽን ፈልጊ ያሉም ነበሩ። ልዑኳን ማን እንደላካቸው ግራ እስኪገባ ድረስ ያዙኝ ልቀቁኝ ማለታቸውን የተቹ፣ መጣላታችን ላይቀር እንዘገጃጅ ማለታቸው አልቀረም። ጠብም ቢሆን በወጉ ይሻላል ሲሉ የነበሩ ደግሞ፣ በዲፕሎማሲ ቢፈታ ይሻላል በማለት ማይካድራን እንድትጎበኝ ቢደረግና አመለካከቷን ለመቀየር ቢሞከር ይሻላል ሲሉ ነበር። በተቃራኒ የግል እምነቷን ይዛ ሳይሆን የመጣችው የላካትን ወገን ፍላጎት ነው የምታራምደው በማለት ቁርጣችንን እንድናውቅ መንግሥትም አቋሙን በግልጽ ይናገር ያሉም ተሰምተዋል።
ነገሩን በዘዴ መያዝ ስለሚሻል አናጩኸው ሲሉ የነበሩት፣ አመለካከቷን አውቀን ቢሆን ኖሮ መጀመሪያውኑም ፊት እንዲሰጣት አቀባበልም እንዲደረግላት ማድረግ አይገባም ብለን እንናገር ነበር በሚል አቋማቸውን ቀይረዋል። አንዳንዶች መምጣቱን ትምጣ ግን እንደጉልበተኛ በለመደችው አይነት ለማስፈራራት ብትሞክር አፄ ቴዎድሮስ እንዳደረጉት ትታሰር ወይም በአፄ ፋሲል ዘመን እንደሆነው ትባረር ማለት ባይቻልም፣ የሚያነጋግራት አጥታ ደጅ ጠንታ ብትመለስ ይሻላል ብለው ነበር። ምንም ነገር ቢመጣ ተነጋግሮ የሚቀየር ነገር ስለማይኖር ይበልጥ መንግሥትን ከሕዝብ የሚያራርቅ እንዳይሆን ይታሰብበት ይላሉ። ከወንዝ የበላይ እየጠጣ አህያን አደፈረሽብኝ ያለውን ጅብ፣ “አያ ጅቦ ሳታማኸኝ ብላኝ” ሳይሆን “ብታመኸኝም አትበላኝም” ሊባል ይገባል።


ቅጽ 3 ቁጥር 144 ነሐሴ 1 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!