የእለት ዜና

የኮቪድ -19 ወረርሽኝ ገጸ በረከቶች

Views: 205

ኮቪድ-19 ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ የገባው መጋቢት 4 ቀን 2012 ላይ ነበር። ‹‹ችግር በቅቤ ያስበላል›› እንዲል አገርኛ ተረት፣ ኮቪድ-19 በመከሰቱ ልናደርጋቸው አስበን የማናውቃቸው ነገር ግን አስፈላጊ የሆኑ ተግባራትን እንድናከናውን አድርጎናል። እጅን በሳሙና ደጋግሞ መታጠብ፣ ሳኒታይዘር መጠቀም እና ርቀትን ጠብቆ መንቀሳቀስ አንዱ የተለወጥንበት ጉዳይ ነው። ከእነዚህ የግል ለውጦች ባሻገር እንደ አገር የጤናው ዘርፍ መሻሻል ትልቅ በረከቶችን ይዞልን መጥቷል።

የወረርሺኙ መከሰት በአገራችን ለጤናው ዘርፍ መሻሻል ያበረከተው አስተዋጽኦ እጅግ በርካታ ነው የሚሉት በኢትዮጵያ የሕክምና ማኅበር ፕሬዝዳንት የሆኑት ተግባር ይግዛው (ዶ/ር) ናቸው።
በጤና ማኅበራት የተመሰረተው የሳይንሳዊ አማካሪ ምክርቤት ሊሠራ ያሰበው ጥናት የሚያመለከተው አንደኛው ጉዳይ፣ አሁንና ወደፊት ከዚህ ወረርሽኝ ምን ተምረናል የሚል መሆኑን ተግባር አንስተዋል።
ይህ ምክር ቤት ከጤና ሚኒስቴር ጋር በመተባበር እና የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በማነጋገር ያለውን ተሞክሮ የሚዳሰስ ጥናት እየሠራ እንደሚገኝ ተግባር ተናግረዋል።
በዚህ ጥናት ቁጥራዊ መረጃዎች የሚካተት ቢሆንም፣ አሁን ያለውን ሁኔታ ብዙ እንደተማርንበት በዝርዝር የሚያስረዱ ሐሳቦችን ይይዛል።
ኮቪድ-19 ይዞልን የመጣው በጎ ነገር መካከል ሆስፒታሎች የበሽታ መመርመሪያና መከላከያ ግብዓቶች ዕጥረት መቅረፍ ነው።

እነዚህ ግብዓቶች በአገር ውስጥ የሚመረቱ ባለመሆናቸው ከውጭ በሚገቡበት ወቅት ዕጥረት ያጋጥማል። በዚህ የግብዓት ዕጥረት ያለበት አገር ላይ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሲከሰት በርካታ መከላከያ እና መመርመሪያ ግብዓቶችን ከውጭ ለማስገባት እንገደዳለን። እነዚህ ከውጭ የሚገቡ ግብዓቶች የሎጂስቲክ መስተጓጎል ሲያጋጥም እና አገሮች የራሳቸውን ፍላጎት ለማሟላት ወደሌሎች አገራት መላካቸውን ሲገድቡ ራሳችን ማምረት እንድንጀምር አበረታተውናል ሲሉ ተግባር ገልጸዋል።

ራስን መጠበቂያ ከምንላቸው አንዱ ማስክ ሲሆን፣ በአገር ውስጥ እንዲመረት መደረጉ ከኮቪድ-19 መከላከል ባሻገር የነበረውን የጤና ባለሙያዎች ፈተና በእጅጉ የቀነሰ ነበር። ለወረርሽኙ ተብለው የተሠሩ ግብዓቶች ለኹሉም የጤና አገልግሎት እንድንጠቀም ረድቶናል ብለዋል።

በዚህም ኢንዱስትሪዎች ሜዲካል ማስክ የማምረት አቅማቸውን እንዲያዳብሩና ገንዘብም የሚያገኙበትን በር የከፈተ ነው ሲሉ ተግባር ያነሳሉ።
ጤና መሰረታዊ የአገር ጉዳይ ነው የሚሉት ተግባር፣ ወረርሽኝ በሚከሰትበት ወቅት ጥንቃቄ ለማድረግ የሚያግዙ ግብዓቶች የማይኖሩ ከሆነ የምንፈልጋቸውን መሪዎች፣ የጤና ባለሙያዎች እና ወታደሮች ልናጣቸው ስለምንችል ራሳችንን በግብዓት አቅርቦት ሙሉ ሆኖ ማዘጋጃት ያስፈልጋል ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪ መሠረታዊ የሆኑ የሕክምና ዕቃዎችን መድኃኒቶች፣ ማስክ እና ሳኒታይዘር ባሻገር የኦክስጅን መጠን ከፍተኛ ሁኔታ ጨምሮ የታየበት መሆኑን ተግባር አስታውሰዋል።
ይህ ከጤና ጋር የተያያዙ ግብዓቶችን አገር ውስጥ የማምረት አቅም የማሳደግ ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱ ተናግረዋል።

በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ወሳኝ እና ሕይወት የሚያድነው ኦክስጅን ሲሆን፣ በርካታ የአለም አገራት ላይም እጥረት በመኖሩ በርካታ ዜጎቻቸውን አጥተዋል። ሕንድ የበርካታ ዜጎቿን ያጣችው አንዱ መንስኤ በኦክስጅን ዕጥረት ነበር። በወረርሽኚ የተጠቃው የሰው ብዛት እና የአገሪቱ የኦክስጅን ግብዓት አለመመጣጠን ነበር ብለዋል ተግባር።

ኢትዮጵያ ባላት አቅም ኦክስጅን የማምረት ሒደት ውስጥ እንድትገባ በማድረግ አቅርቦት እንዲጨምር ተደርጓል። በዚህም እንደ አገር በመንግስትም በግልም በጠቅላላ 500 ይደርስ የነበረውን በእጥፍ በማሳደግ 1000 ማድረስ ተችሏል ሲሉ ተግባር ተናግረዋል።

ይህንን ቁጥር ለማሳደግ የተቻለው ኦክስጅን ማምረት የሚችሉ የብረታ ብረት ኢንዱስትሪዎችን በማበረታታት እና ተበላሽተው የቆዩትን እንዲታደሱ በማድረግ መሆኑን ተናግረዋል።
ከጤናው ዘርፍ ውጭ ያሉ አምራች ድርጅቶችን በመጥቀም የጤናውን ዘርፍ እንዲደገፍ ማድረግ ትልቁ የኮቪድ-19 በረከት መሆኑን የጤና ባለሙያዎች ይስማሙበታል።

ኦክስጅን ለኮቪድ-19 ወረርሽኝ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች በሽታዎች ወሳኝ ግብዓት በመሆኑ መመረቱ እና አቅርቦት ዕጥረት መቅረፉ ሌሎች በሽታዎችን በቀላሉ ማዳን እንዲቻል ያደርጋል ይላሉ ተግባር።
ለጽኑ ሕሙማን ወሳኝ የሆነው ኦክስጅን ከኮቪድ-19 ባሻገር ለልብ፣ ለጉበት፣ ለካንሰር፣ ለድንገተኛ አደጋዎች (እንደ መኪና አደጋ እና በወሊድ ወቅት የሚከሰት ከፍተኛ የደም መፍሰስ) በዚህ መሳሪያ በሽተኛውን ማገዝ የሚቻልባቸው ናቸው።
በኮቪድ-19 ተይዘው በጽኑ ሕሙማን ለሚገኙ ሰዎች ወሳኝ ከሚባሉ ግብዓቶች ሌላኛው ግብዓት ደግሞ የመተንፈሻ መሳሪያ (Medical ventilator) ነው።
አሁን ኢትዮጵያ ባለችበት ሁኔታ ናሙናዎችን በራሷ ለመመርመር የሚያስችላትን የላብራቶሪ ግብዓቶችን በመጨመር ከፍተኛ አቅም ገንብታለች።
እንደ አገር የነበረብንን የግብዓት ዕጥረት ከመቅረፍ በተጨማሪ፣ የጤና ባለሙያዎች እና ማሕበረሰቡ ላይ ትልቅ ለውጥ መጥቷል።

የዚህም ማሳያ የጤና ሙያ ማኅበራት ተደራጅተው የጤና ሚኒስቴርን የማማከር አገልግሎት በመስጠት ለውጥ አምጥቷል። ይህ የማማከር ሥራ በመዋቅር ተደራጅቶ ወደፊት ትልቅ ሥራ መሥራት ይቻላል ብለዋል።
ይህ ተቋማት ከተቋማት ጋር ተናቦ የመሥራት፣ አማካሪዎችን የማሳተፍ እና የጤናው ዘርፍ ከሌሎች አካላት ጋር ጠንካራ ግንኙነት እንዲፈጥር ያደረገው ኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከሰቱ ነው። በጤናው ዘርፍ የሚመለከታቸው አካላት በስተቀር ከውጭ የሚመጡ ሐሳቦች እና ማንኛውም ተግባራት እንዲከናወን የተዘጉ በሮችን መክፈት እንደተቻለ ተግባር ይገልጻሉ።

ይህንን ደግሞ መንግሥት፣ ከጤናው ዘርፍ ውጭ ያሉ አካላት እና ሚዲያዎች ተረድተውት አጠንክረው መቀጠል እንደሚገባቸው ተግባር ገልጸዋል።
የሚዲያ አካላት የፈጠሩት ግንዛቤ ማስጨበጫ የአየር ሰዓት ወይም የጋዜጣ አምድ መፍጠር አንዱ የጤናውን ዘርፍ እንዲመለከቱ እና ለማሕበረሰቡ የጤና መረጃ የማድረስ ኃላፊነት እንዲወጡ ያደረገ ነው።
ይህ የጤናውን ዘርፍ አጠናክሮ ይዞ ለሕብረተሰቡ ስለ ጤና አጠባበቅ መግለጽ የሚቀጥል ከሆነ ጤናችንን በከፍተኛ ሁኔታ ለመጠበቅ አስቻይ ሁኔታ መፍጠር፣ ግንዛቤ ማጎልበት እና የጤና ስርዓት ማሻሻል ይቻላል።
ኮቪድ-19 ይዞ ከመጣው አንዱ በረከት ባለሀብቶች የጤናውን ዘርፍ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲደግፉ ማድረግ ማስቻሉ ነው። የኃይማኖት መሪዎች የሥነ-ልቦና ለውጥ በማምጣት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል። አንደነዚህ አይነት ተቋማዊ እና የግለሰብ አበርክቶዎች ቀጣይነት እንዲኖራቸው በእውቀት የተደገፈ አደረጃጀት መፍጠር ይገባል ብለዋል።

ጤና ተቋማት ላይ የነበረው የሰው ኃይል ዕጥረት፣ የመሳሪያ ግብዓት ዕጥረትና መረጃ የመድረስ ስራ መቀረፉ ማሕበረሰቡ ላይ ትልቅ ለውጥ አምጥቷል።
በመደበኛ ወቅት ያልነበሩ ግብዓቶች ወረርሽኙ ከተከሰተ በኋላ እንዲሟሉ በር ከፍቷል። ጤና ዘርፍ ላይ ያለንን ሀብት መጨመር ያስፈልጋል። ባለሀብቶች የጤና ተቋማትን በማንኛውም ወቅት መደገፍ ቢችሉ መልካም መሆኑንም ተግባር አንስተዋል።


የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል የኮሮና ታማሚዎች የጽኑ ሕሙማን ክፍል መሙላቱ ተገለፀ
በኮቪድ19 ቫይረስ የተያዙ ሰዎች መጨመርን ተከትሎ የኤካ ኮተቤ ሆስፒታል የጽኑ ሕሙማን ክፍሉ ሙሉ በሙሉ መሙላቱ ተገለፀ።
የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ ያሬድ አግደው (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ የጽኑ ሕሙማን ክፍል በመሙላቱ ተጨማሪ ሕሙማንን ሆስፒታሉ የመቀበል አቅም የለውም ብለዋል።
ባለፉት ኹለት ወራት የሕሙማን ቁጥር ቀንሶ እንደነበር እና ወደ ሆስፒታሉ የሚመጡት ሰዎች በቀን ከኹለት የማይበልጡ እንደነበር ሥራ አስኪያጁ አስታውሰዋል።
በአሁኑ ወቅት ግን በየቀኑ 25 የኮቪድ ሕሙማን ወደ ሆስፒታሉ እየገቡ በመሆኑ የቁጥሮቹ ማሻቀብ የሦስተኛው ማዕበል መግባቱን ያሳያል ብለዋል።
በሆስፒታሉ አሁን ላይ ኦክስጅን የሚያስፈልጋቸው 100 ሰዎች ሕክምና እየተደረገላቸው ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 25 በጽኑ ሕክምና ላይ የሚገኙ መሆናቸውንም ነው የተናገሩት።
በአጠቃላይ ሆስፒታሉ 400 የሚደርሱ ሕሙማንን የማስተናገድ አቅም ያለው ሲሆን፥ ከዚህ ውስጥ 25 ፅኑ ሕሙማንን ብቻ ማስተናገድ እንደሚችልም አመላክተዋል።
ከዚህ በኋላ በፀና የታመሙትን ማስተናገድ የሚችለው ክፍሎቹ ሲለቀቁ ብቻ መሆኑን በመረዳት ሕብረተሰቡ ተገቢውን ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል።
እንደጤና ሚኒስቴር መረጃ ከዘጠኝ ቀን በፊት በቫይረሱ ሲያዙ የነበሩ ሰዎች ቁጥር 100 የማይሞላ ሲሆን፥ በዚህ ሳምንት በሚወጡ የምርመራ ውጤቶች በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር 500 የሚጠጋ ሆኗል።
በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ከ280 ሺሕ በላይ ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ መሆናቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያሳያል።


ቅጽ 3 ቁጥር 144 ነሐሴ 1 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com