የእለት ዜና

የተዳከመ የሚመስለው የኢትዮጵያ ዲፕሎማሲ

ዲፕሎማሲ የአንድ አገር መንግሥት ከሌላው የዓለም አገራት ጋር የሚያደርገው ግንኙነትን የሚመሩ ሰፋ ያሉ ግቦችን እና ስትራቴጂዎችን የሚወክል የውጭ ፖሊሲ እና ዓለም ዐቀፋዊ አስተዳደር ዋና መሳሪያ ነው።
ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው ዘርፍ ከሌሎች ዓለም አገራት ጋር የሚኖራትን ግንኙነት ማጠናከር እንዳለባት የዘርፉ ባለሙዎች ብዙ ጊዜ ሲመክሩ ይሰማሉ። ይሁን እንጅ አገሪቱ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በዲፕሎማሲው ዘርፍ የሠራቻቸውና እየሠራቻቸው ያሉ ተግባራት አመርቂ እንዳልሆኑ ብዙሃን የሚስማሙበት ጉዳይ ነው። ለዚህም እንደማሳያ የሚነሱት በታላቁ ሕዳሴ ግድብና በትግራይ ክልል ጉዳይ ላይ አገሪቱ ከምዕራባውያን እየደረሱባት ያሉ ጫናዎች ኛቸው።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት በታላቁ የሕዳሴ ግድብና በትግራይ ክልል ጉዳይ ላይ በአንዳንድ አገራት ጫና እየደረሰባት ነው። ጫና ለመፍጠር የሚጥሩ አገራት የኢትዮጵያን ጥቅምና ሉዓላዊነት ወደ ጎን በመግፋት የራሳቸውን ፍላጎት ለማሟለት የሚጥሩ ሁነው ይታያሉ። አገሪቱ ለዚህ አይነቱ ያልተገባ ጫና እንድትጋለጥ ያደረጋት ደግሞ የዲፕሎማሲ ሥራው በተገቢው መልኩ ባለመሠራቱ እንደሆነ ይገለጻል።

የዘርፉ ባለሙያዎች ኢትዮጵያ የውጭ ጫናዎችን ለመቋቋም የዲፕሎማሲ ሥራ ማጠናከር እንዳለባት ይወተውታሉ። አገሪቱ በውጭ ግንኙነት ላይ ያላትን ተደማጭነት ለማጠንከር በስፋት መሠራት እንዳለበት የሰላም ሚኒስትር አማካሪ ሞገስ ደምሴ(ፕ/ር) ይናገራሉ።

ኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ ታራምደው የነበረው የውጭ ግንኙነት ዲፕሎማሲ በገለልተኝነት፣ በወዳጅነት፣ እንዲሁም በሌሎች አገሮች የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ባለመግባትና የአገራትን ሉዓላዊነት ባከበረ መንገድ የተመሠረተ መሆኑን አማካሪው ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ አንስተዋል።

ከነዚህ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ መርሆዎች መሆናቸውን በማንሳት በተግባር ላይ የመዋላቸው ሁኔታ ግን አጠያያቂ እንደሆነ ይጠቁማሉ። ኢትዮጵያ አሁኑ ባለችበት የፖለቲካ ሽግግር ሒደት ውሰጥ እነዚህን መርሆዎች አጠናክራ ወደ ተግባር እየቀየረች ያለችበት ሁኔታ መፈጠሩን ተናግረዋል።

ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያ ከጎረቤት አገራት ጋር የነበራት የውጭ ግንኙነት አሉታዊ በሚባል መልኩ የተመሰረተ መሆኑን አስታውሰው፣ አሁን ላይ የቀደሙት የውጭ ግንኙነት ዲፕሎማሲ መርሆዎች በተግባር የተቀየሩበት መንገድ መኖሩን ተናግረዋል።

እንደ ምሳሌ ከኤርትራና ሱማሊያ ጋር የነበረውን ግንኙነት በዋናነት ጠቅሰዋል። ከአገራቱ ጋር አዲስ የውጭ ፖሊሲ መርህ በተግባር ላይ ማዋል በመጀመሩ፣ የሻከሩ የውጭ ግንኙነቶችን መቀየር እንደተቻለ ይናገራሉ።
እንደ ፕሮፌሰር ሞገስ ገለጻ፣ ይህ የውጭ ግንኙነት መርህ በአገሪቷ አጎራባች አገራት ብቻ ሳይሆን በውጭ አገራትም የሚንጸባረቅ ነው። ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታትን መስራች ከሆኑ የአፍሪካ አገራት ብቸኛዋ እንደመሆኗ የውጭ ግንኙነት የተጠቀሱት የዲፕሎማሲ መርሆዋቿ በዓለም ዐቀፍ ደረጃ እንዲተገበሩ ጭምር እየሠራች እንደምትገኝ አስረድተዋል። አክለውም በውጭ ጉዳይ ግንኙነት መርሆች ላይ የሚታዩ ክፍተቶችን አሟልቶ ወደ ተሻለ ደረጃ ማድረስ እንደሚቻልም ጠቅሰዋል።

አሁን ላይ ያለው የዓለም አገራት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ በዋነኛነት የሚያተኩረው ብሔራዊ ጥቅም ላይ መሆኑን አስታውሰዋል። ዓለም እንደ ከዚህ ቀደሙ በምዕራብና በምስራቅ የተከፈለች፣ እንዲሁም በኅብረት ላይ ባጠነጠነ መልኩ የተመሰረተ አለመሆኑን አማካሪው ያነሳሉ።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የማንኛውም አገር ተከታይ ወይም ኅብረት አባል አለመሆንዋን ጠቅሰዋል፣ ብሔራዊ ጥቅሞቸን ያስከብሩልኛል ብላ ከምታስባቸው አገራት ጋር የውጭ ግንኙነት መፍጠር እንደምትችል ጠቁመዋል።
ነገር ግን የውጭ ግንኙነት መርሆዎቿን ተጠቅማ ብሔራዊ ጥቅሞቿን ማስከበር መቻልዋ በሌሎች አገራት እንደ ስጋት የሚቆጠርበት ሁኔታ ሊኖር እንደሚችልም አንስተዋል። በዚህም አገሪቷ ላይ ጫና ለማሳደር አገራት እንዲሞክሩ ማድረጉን ጠቅሰዋል። ይህ አይነቱ ድርጊት ከበፊትም ጀምሮ መከሰቱንም ጨምረው አንስተዋል።

ሆኖም ይህን የውጭ አገራት ጣልቃ የመግባት ድርጊት በደረሰባት ወቅት፣ የአገር ሉዓላዊነትን ለማስቀጠል ተገቢውን ሒደት አገሪቱ ማከናወንዋን አንስተዋል። አገሪቷ ያላትን በራስ የመወሰን አቅም ለሌሎች አጎራባች አገሮች ብሎም በዓለም አቀፍ ደረጃ በታሪክ ማሰፈርዋ የሚታወስ ተግባር ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ልታሳካቸው ከሚገቡ የአገር ሉዓላዊነት ጉዳዮች መካከል የውጭ አገራት ጣልቃ ገብነትን መታገል፣ የአገር አንድነትን የከፋፈሉ ኃይሎችን መዋጋት፣ እንዲሁም በውጭ አገር የሚኖሩ ዜጎቹዋን ደህንነት መጠበቅ መቻል እንደሆነ አንስተዋል።

እነዚህን የአገሪቷን ብሔራዊ ጥቅሞችን ለማስከበር ከተለያዩ አገራት ጋር ኅብረት መፍጠር የሚያስችል ፓሊሲ መኖሩንም አዲስ ማለዳ ማወቅ ችላለች።
የአገራችን የውጭ ገፅታ በሌሎች ጠንካራ ወይም ደካማ ተብሎ የሚታየው በአገሪቷ ውስጥ ባለው የፖለቲካ ሁኔታ መሆኑን የሚታወቅ ነው።
ከዚህ ጋር ተያይዞም ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ታሪካዊ ሁነት ላይ እንደምትገኝ በመጥቀስ፣ የአገር አንድነት በተግባር የሚፈተንበት ወቅት መሆኑንም አንስተዋል።

የአገር አንድነትን የሚያጠናክሩ ተግባራት ላይ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በአሁኑ ሰዓት መሥራት መቻል እንደሚገባም ባለሙያው ገልጸዋል። አያይዘውም የአገራችን የውስጥ አቅም ሲጨምር በውጭ አገራት ላይ ያለንን ገፅታ ማሳደግ እንደሚቻል ይናገራሉ።

የውጭ አገራት በአገራችን ውስጥ ያሉትን ሁኔታዎች በመጠቀም የኛን የመከላከል አቅም ገንብተው ጫና ለማድረስ በከፍተኛ ሁኔታ ይንቀሳቀሳሉ። በዚህም በአገራችን ውስጥ ያለው የእርስበእርስ ግንኙነት በሚላላበት ጊዜ፣ ባዕዳን አገራት ክፍተት ይኖራል ብለው ስለሚያስቡ ጫና ማድረስ እንደሚጀምሩ ጠቅሰዋል።

ይህን የውጭ አገራት ጣልቃ ገብነት ለመከላከል የውስጥ አንድነትን ማሳደግ አንዱና ዋነኛው መፍትሔ ሲሆን፣ በአገራዊ ጉዳዮች ላይም ምንም አይነት ልዩነት በዜጎች ላይ ሊኖር እንደማይገባ አንስተዋል።
በዜጎች መካከል በፖለቲካ እንዲሁም በአመለካከት ላይ ልዩነት መኖሩ የተለመደ ቢሆንም፣ በማንኛውም የአገር ጉዳይ እንዲሁም ሉዓላዊነት ላይ ግን የሚኖር ልዩነት አግባብነት የሌለው ነው። ለዚህም እንደ ምክንያት ያነሱት አገር ሲኖር ብቻ ነው በፖለቲካም፣ በማንኛውንም ጉዳይ በሰላም መወያየት፣ ተደራድሮ መመረጥ፣ ስልጣን መያዝ የሚቻለውና ማንኛውንም ችግር ሊፈታ የሚችለው ብለዋል።

እንደ እሳቸው ገለጻ፣ ማንኛውንም ነገር ማከናወን የሚቻለው አገር ሲኖር ብቻ በመሆኑ በአገር ሉዓላዊነት ላይ የሚደራደር የኢትዮጵያ ዜጋ ሊኖር እንደማይገባ ጠቁመዋል። የአገር አንድነትንና ሉዓላዊነትን ሊያጠናክር በሚችሉ ተግባራት ላይ መሳተፍ ከማንኛውም የኢትዮጵያ ዜጎች የሚጠበቅ እንደሆነም እስታውሰዋል።

ከዚህ ጋር አያይዘውም ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት ለአባይ ግድብ ግንባታ መጠናነቅ ማንኛውንም ዓይነት ድጋፍ ማድረግን እንደሚኖርባቸው አንስተዋል።
ኢትዮጵያ እየገነባች ያለችው የአባይ ግድብ፣ ዜጎችዋ ኅብረት በመፍጠር በጋራ ሲያጠናቅቁ ከውጭ አገራት እየደረሱብን ያሉ ጫናዎች ለመመከት የሚያስችልና የመደራደር አቅም እንደሚፈጥር ያነሳሉ።
የውጭ አገራትን ጫና ለመቀነስ ኢትዮጵያዊ ዲሞክራሲን መገንባት፣ የውስጥ አንድነትን ማጠናከርና የአባይ ግድብ ግንባታን መጨረስ፣ እንዲሁም አገራዊ እሴቶችን መንከባከብ በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ደረጃ ልትሠራበት እንደሚገባ ገልፅዋል።
ከሰሞኑ በተሰማው የኤንባሲዎችን ቅነሳ ጋር በተያያዘ ሞገስ ሐሳባቸውን ሲገልጹ፣ ተግባሩ ኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነቷን በተሻለ መንገድ አቀላጥፋ ስኬታማ በሆነ መልኩ ለማስፈፀም የሚያስችላትን መንገድ የሚያመቻች መሆኑን ተናግረዋል። ይህም ማለት ኢትዮጵያ በውጭ አገር የሚገኙ ኤንባሲዎችዋን ሙሉ ለሙሉ ትዘጋለች ማለት እንዳልሆነ አስገንዝበዋል።

የኤንባሲዎችን ቁጥር ቀንሶ ዓለም በደረሰችበት የቴክኖሎጂ ሥልጣኔ በመጠቀም በውጭ ግንኙነት ላይ የተሻለ ውጤት ማምጣት እንደሚቻል አስታውቀዋል። የኤንባሲዎችን ቁጥር መቀነስ አገሪቷን ካላስፈላጊ የኢኮኖሚ ወጪ ሊታደጋት ይችላልም ሲሉ ሐሳባቸውን አካፍለዋል።

በውጭ አገራት የሚኖሩ ዲያስፖራዎችም ከዚህ በፊት በአገራዊ ጉዳዮች ላይ በቋሚነት መሳተፋቸውን አስታውሰው፣ በቀጣይም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ በጠነከረ መልኩ ማድረግ እንዳለባቸው አመልክተዋል።
ዲያስፖራው የአገርን ገጽታ በመገንባት ሒደት፣ እንዲሁም የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅሞች በማጎልበት ረገድ ከፍተኛ በሚባል ደረጃ ሚናውን መወጣት እንደሚገባው አሳስበዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 144 ነሐሴ 1 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!