የእለት ዜና

ኢትዮጵያዊቷ እናት

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

“ኢትዮጵያ “
ከላይ የጠቀሰኩት ለአገር ከተዜሙ ኢትዮጵያን ከሚያወድሱ የዘፈን ርዕሶች መካከል አንዱ ነው ። በክቡር ዶክተር አርቲስት ጥላሁን ገሰሰ የተዜመው እናት አገር ኢትዮጵያ “እያለ አገራችንን የሚያወድስ ግጥም ነው።
አገራችን የምትሰየመው በሴት ነው። ብዙዎች እናት አገር ኢትዮጵያዬ፤ እማማ እያሉ በፍቅርና በስስት ተቀኝተዋል።
ከአገር ርቀው በሰው አገር ላይ የሚኖሩ ልጇቿ ጋራ ሸንተረሯን፣ ለምለም ምድሯን በምናባቸው እያሰቡ አንደበታቸውን በአድናቆት፣ ልቦናቸውንም በትዝታ ይሞላሉ።
ስለ አገር የተዜሙ ዘፈኖችን ያዳመጡ ቀልባቸው ይሰረቃል። ለዚች ገነት ለተባለችው ኢትዮጵያ ሴቶች የከፈሉላት ዋጋ ግን ምን ያህል ይሆን?
ሴቶች በእነሱ ጾታ የምትጠራው አገራቸው ኢትዮጵያ ያሏትን መልካም እሴቶች ጠብቀው ለተተኪው ትውልድ እስተላልፈዋል።
ታሪክ የማይረሳቸው፣ እነሱ ቢያልፉም ሥራቸው ግን ሁሌም ከመቃብር በላይ የሆኑ ባለታሪኮች አሉ። ኢትዮጵያዊ ሴት እናት ስትሆን እሩህሩህ፣ እንስፍስፍ፣ ለተራበ አጉራሽ፣ ለተራቆተ አልባሽ ኹሉንም አቃፊ ደጋፊ ናት። እህት ስትሆን እንክብካቤና ፍቅር ያለገድብ ለጋሽ ትሆናለች።
አገር የከፋት ቀን ግን እንደ አባት ለአገር፣ ለወገን መከታ፣ መከበርያ ሆና ጋሻና ጦሯን ታነሳለች። ለሌላው ማስፈራሪያ ወንድምን ትሆናለች።
ስለዚህ ይህን ሁሉ ያደረገችን ሴት ምን ሊገልፃት ይችላልን? በአገራችን ላይ በሰላምም ይሁን በጦርነት ታሪክ የማይዘነጋቸው ክስተቶች አልፈዋል። እንዚህን ክንዋኔዎች አገር እንድታሳልፍ ሴቶች በር ከፋች ነበሩ።
ለእናት አገር ኢትዮጵያ በየወቅቱ እንደ ፀሐይ ያበሩላት፣ እንደ ሻማ የቀለጡላት፣ አጥንታቸውን የከሰከሱላት የብዙ ሴት ጀግኖች ታሪክ ሁሌም ህያው ሆኖ ይቀጥላል።
የአገር ፍቅር ስሜት በልጦባቸው እራሳቸውን ለአገር አሳልፈው የሰጡ ሴቶች ማወደስ ግድ ይለናል። በሰው ህሊና ሲታወስ የሚከብድ መቼም ሊዘነጋ የማይችል እልፍ ታሪክና ጀብዶችን ፈጽመው አልፈዋል።
የአገር ፍቅር ስሜት ከምን አስከ ምን ድረስ እንደሆነ የምንረዳበት የእነዚህ የአገር መከታዎች ታሪክ ዛሬም ድረስ ይወሳል፤ ስም ከመቃብር በላይ እንዲሉ ።
አገር ቀን በጨለመባት ጊዜ ብርሀን፣ በችግር ውስት መፍትሄ፣ በፍርሀት ጊዜ ወኔ፣ በድካም ጊዜ ብርታት፣ በዝምታም ወቅት ልሳን የሆኑላት እንስት ኢትዮጲያዊያን ባሰበን ጊዜ አንገታችንን በወኔ ቀና የሚያስበሉንን ታሪክ ይቁጠራቸው።
ፋሽስት ጣሊያን ኢትዮጵያን በወረራት ጊዜ አገር አናስደፍርም፤ ለነጭ አንገዛም፤ ብለው ጦር ሜዳ ድረስ በመሔድ ዘምተው ድል አድርገዋል። ከአገራችን ከኹሉም አቅጫጫ የተውጣጡት ሴቶች በጦርነት ላይ የነበራቸው ሚና ቀላል የሚባል አልነበረም።
ለአብነት ያህል በአደዋ ጦርነት ጊዜ እቴጌ ጣይቱ በሺሕዎች የሚቆጠሩ መድፈኞችና ወታደሮችን ይዘው እንደዘመቱ የታሪክ መዛግብት ያስረዳል።
የተጣለባቸውን አደራ በኃላፊነት በመወጣት የዛሬዋን በነጭ ያልተገዛች ብቸኛዋን አገር አስረክበውናል።
በጦርነት ወቅት ስንቅ ሰንቀው በወኔ ከመቀስሰቀስ ባሻገር እስከ ግንበር ድረስ ዘምተው ድል ተቀናጅተዋል።
ይህ አኩሪ ተግባራቸው ለቀጣዮ ትውልድም ተላልፎ ሁሌ ሲዘከሩና ትውልድ ሲያስተምሩ ይኖራሉ።


ቅጽ 3 ቁጥር 144 ነሐሴ 1 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!