የእለት ዜና

“መንግሥት ዕርምጃ መውሰድ የጀመረው በጣም ዘግይቶ ነው”

አርዓያ ተስፋማርያም የሕወሓትን ባለሥልጣናት ሥራ በማጋለጥ የሚታወቁ አንጋፋ ጋዜጠኛ ናቸው። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለውጡን ለማገዝ ወደ አገር ቤት ተመልሰው የተለያዩ ተግባራትን እያከናወኑ ይገኛሉ። በተለያዩ ሚዲያዎች እየቀረቡ ሰው ያልሰማቸውን ታሪኮች በማቅረብ ይታወቃሉ። በትግራይ ጊዜያዊ መስተዳድር ስር የትግራይ ቲቪ ኃላፊ ተደርገው በአጭር ጊዜ ለውጥ ለማምጣት መሥራታቸውን በቅርብ የሚያውቋቸው ይናገራሉ። የአዲስ ማለዳው ቢኒያም ዓሊ ስለወቅታዊው የሰሜኑ የአገራችን ክፍል ነባራዊ ሁኔታ ከእርሳቸው ጋር ቆይታ አድርጓል።

አጠቃላይ የሰሜኑን ወቅታዊ ሁኔታ እንዴት ያዩታል?
በትግራይ ያለው ወቅታዊ ሁኔታ ከ13 ዓመት በላይ የሆኑ ሕፃናት በግድ እየታፈኑ ወደጦርነት የሚሄዱበት ነው። ዶ/ር አረጋዊ ሠሞኑን በአንድ ትልቅ ስብሰባ ወቅት እንደተናገሩት 200 ሺሕ የሚሆኑ ሕፃናት በግድ አፍነው ከመቀሌ በሲኖትራክ እየተወሰዱ ወደማሰልጠኛ ይከቷቸዋል። ዝም ብለው መሳሪያ እያደሏቸው ለጦርነት እየዳረጓቸው ነው።

በኹለተኛ ደረጃ ከፍተኛ የረሀብ ችግር አለ። በተለያየ መንገድ ከትግራይ የሚመጡትን እያገኘሁ አነጋግሬያለሁ። በአፋር፣ በጎንደርና በወሎ የሚወጡ ቢኖሩም፣ ወጣቶችን ግን እንዳይወጡ ከልክለዋቸዋል። ወደሌላ ክልል ብቻ ሳይሆን ከከተማ ከተማ ወጣቱ እንዳይንቀሳቀስ አድርገዋል። የ71 ዓመት አዛውንት ሳይቀር በሕፃናት እየተደበደቡ ወደአልታወቀ ቦታ እንዲወሰዱ ተደርጓል።

ሰውን መግደሉ በስፋት ቀጥሏል። “ለመከላከያ ምግብና ውኃ ታቀርቡ ነበር፤ መረጃም ታቀብሉ ነበር” እየተባለ በጣም ብዙ ሰው እየተገደለ ነው። በዚህ መንገድ ከ450 በላይ ሰዎች ተገድለዋል። በተለይ አክሱም 89 ሰዎች ተገድለዋል። በእስልምና እምነት ተከታዮች ላይ በተለይ በኲሓ አካባቢ የ43 ሼኆች መኖሪያ የመከላከያ ደጋፊ ናችሁ በሚል ተቃጥሎ እንዲወድም ተደርጓል። የተገደሉትን ዝርዝር ለማግኘት ጥረት እያደረግኩ ነው።
ሕግ በማስከበሩ ዘመቻ ወቅት መንግሥት በረሃብ አንድም ሰው አልሞተበትም ነበር። አሁን ግን ሰዎች ተርበው እየሞቱ ነው። በሚዲያም ተደጋግሞ እየተነገረ እንዳለው በትግራይ ከፍተኛ ችግር ነው ያለው።

ከትግራይ ሸሽተው ለሚወጡ ስደተኞች የተዘጋጁ መጠለያ ጣቢያዎች አሉ?
አዲስ አበባ መጥተው ጎዳና ላይ እየወደቁ ናቸው። አፋር ክልልና ወሎ ውስጥም በብዛት አሉ። ተፈናቃዮቹን በተመለከተ መጥፎ ሁኔታ ነው ያለው። ሶሻል ሚዲያና ዩቲዩብ መጠቀም አልቻልኩም እንጂ ማስረጃዎች አሉኝ። ተከዜ ላይ ብዙዎችን አፍነው መግደላቸው ይታወቃል። ልዑል ባሻ የሚባሉ አባትን ከልጃቸው ጋር ገድለው ተከዜ ወንዝ ውስጥ ጥለዋቸዋል። በዚህ መልክ የተገደሉ የ20 ሰዎች አስከሬን ከወንዙ ውስጥ ተገኝቷል። አንድ በጥይት ደብድበው የገደሉትንም ምስሉን ልከውልኛል። እጃቸው ወደኋላ ታስሮ ባሕር ውስጥ የጣሏቸው ሰዎች አስከሬናቸው እየተገኘ ነው። በሚያሰቅቅ ሁኔታ ሰውነታቸው ፈነዳድቶ ሲታይ በሚዘገንን ሁኔታ እንደገደሏቸው ማወቅ ይቻላል (ምስሎቹን ልከውልናል)። ዛሬ ሲታወቅባቸው ታሪኩን ቀይረው በመንግስት የተወሰደ እርምጃ አድርገው ለማቅረብ እየሞከሩ ነው። ይህ ፈፅሞ ስህተት ነው። ሐምሌ 28 ጠዋት ብቻ ወደ 30 አስከሬኖች ወንዙ ውስጥ ተገኝተዋል። “ለአማራ ልዩ ኃይል ስንቅ ታቀብሉ ነበር፣ ትደግፉዋቸዋላችሁ” በሚል እድሜና ፆታ ሳይለዩ ነው የሚገድሉት።

በትግራይ የነበረው ችግር ተባብሶ ቀጥሏል። ገንዘብ በሌለበት ሁኔታ እያንዳንዱ ሰው ስድስት መቶ ብር እንዲያዋጣ አዘዋል። ኹለት እንቁላል ያለው አንዱን ይስጥ ብለዋል። ኹለት ልጅ ያለውም አንዱን አውጥቶ እንዲሰጥ ወስነዋል። እህል ያላቸው ግማሹን እንዲሰጡ ተገደዋል። በተለይ እንደርታ አካባቢ ስቃይና መከራው ቀጥሏል። ሕዝቡን “መከላከያን፣ ብልጽግናንና መንግሥትን ትደግፋላችሁ” በሚል ከፍተኛ ስቃይ ላይ ከተውታል።

ከትግራይ ሸሽተው የሚመጡትን እያስተናገዱ የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች፣ ሕወሓት የላካቸው ሰላይ ሊሆኑ ይችላሉ በሚል ስጋት እንደተፈጠረባቸው ይሰማል። በአንፃሩ ሊሰልሉ የተላኩም መገኘታቸው ይነገራል። በዚህ ጉዳይ ያሎት አስተያየት ምንድን ነው?
በርግጥ እየሆነ ያለው በጣም ያሳዝናል። ሕወሓቶች በመጀመሪያ መከላከያ ላይ እርድ ፈፅመው ይህን ኹሉ መከራ ካመጡ በኋላ ወጣቱንና ታዳጊውንም ዛሬም እያስጨረሱ ነው። በ3 ሳምንት ከደረሰባቸው ሽንፈት ሊማሩ ያልቻሉ ናቸው። እነዚህ የሽፍታ ቡድኖች ምንም የሚማሩ አይደሉም። እነሱ በፈጠሩት ጦስ ነው ይህ ኹሉ የሚደርሰው። ባሳለፍነው ሰኞ ሐምሌ 26 መከላከያን ከድቶ ከእነሱ ጋር አብሮ የነበረና ብዙ የመሥተዳድሩ አባላት ያስገደለ፣ ከስደተኛ ጋር ተቀላቅሎ አፋር ከመግባቱን የሠራውን የሚያውቁ አብረው ከመጡ ሰዎች ጋር እንደደረሰ ጠቁመው መያዙን ሰምቻለሁ። ለእኔም ከነማንነቱ ማስረጃውን ልከውልኛል። እንዲህ አይነት ሰዎች ይገባሉ። ነገር ግን፣ ሕዝቡን በጅምላ እንዳለ መፈረጁ ተገቢ አይሆንም። በእንዲህ አይነት ሰዎች ሳቢያ እውነተኛ ስደተኛው ላይ የሚፈጸም ተጽዕኖ የሚያሳዝን ቢሆንም፣ ኢትዮጵያዊ ሕዝብ አስተዋይ እንደመሆኑ ይስተካከላል ብዬ እገምታለሁ። የመንግሥት የፀጥታ አካላት እነኚህን ሰዎች ለይቶ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው እንዲያገኙ ያደርጋሉ የሚል ዕምነት አለኝ።

ከሕወሓት ጋር ግንኙነት አላቸው በሚል አዲስ አበባ የሚገኙ የንግድ ተቋማት እየታሸጉ ነው መባሉን እንዴት ያዩታል?
በአዲስ አበባ ውስጥ ሕግና ስርዓት አልበኝነት የሰፈነበት፣ እጅግ መረን የለቀቁ አስነዋሪ ድርጊቶች ሲፈፀሙ ነበር። “መቀሌ ተለቀቀ” ተበሎ የኢትዮጵያ ባንዲራ 22 ሲቃጠል ነበር። የሰዎች ስም ዝርዝር እየተጠራ በመሥተዳድሩ ውስጥ ይሠሩ የነበሩ የትግራይ ተወላጆችን “ግደሏቸው! ፍለጧቸው!” እየተባለ ሲዛት፣ የመንግሥት ባለሥልጣናት ስም እየተነሳ ዛቻ ሲሰነዘር፣ የተለያዩ የቅስቀሳ ዘፈኖች እየተከፈቱ ይጨፈር እንደነበር እኔ ራሴ በትክክል ማስረጃ ያገኘሁባቸው ድርጊቶች አሉ። ላለፉት 8 ወራት ከዚህ ድርጊታቸው ሳይቆጠቡ ቆይተዋል። መከላከያ ትግራይን ለቆ ከወጣ በኋላ አሸነፍናቸው በሚል የኢትዮጵያ ባንዲራ ምን አድርጎ ነው የሚቃጠለው? እነዚህ ሰዎች እዚህ ኢትዮጵያ ውስጥ እየኖሩ እንደባዕድ ይህን ማድረግ አልነበረባቸውም። ወይ ጦርነትን መቃወም ሲኖርባቸው ያደረጉት የማይጠበቅ ነገር ነው።

ለ23 አመታት እነሱን ሲጠብቅ የነበረው መከላከያ ላይ የተፈጸመበትን ግፍና እልቂት ማውገዝ ቢሳናቸው እንኳን እንዴት እልል ይላሉ? ሕዝብ ለማረጋጋት የሔዱ 45 የመስተዳድሩ አባላት 8 ቦታ ተቆራርጠው ሲገደሉ መጨፈር በደማቸው መሳለቅ ነው። እነዚህ ሰዎች ላይ በመንግሥት የተወሰደው እርምጃ ተገቢ ነው ብዬ ነው የማምነው። በዚህ አጋጣሚ በስህተት አንዳንድ ሰዎች ላይ ተመሳሰይ ዕርምጃ ሊወሰድ ይችላል። ከአንዳንድ የፖሊስ አባላት የተረዳሁት ነገር በስህተት የግለሰቦች የንግድ ተቋም ሊዘጋና ሊታሰሩ እንደሚችል ነው። ንጹኃንን እየጠቆሙ በስህተት እንዲያዙ የሚያደርጉት የሕወሓት ሰዎች ናቸው። ተገልብጠው ብልጽግና ውስጥ ገብተናል እያሉ ያሉ ኹለት ማልያ ለባሾች አሉ። እነዚህ ሆን ብለው መንግሥት እንዲጠላ የሚያደርጉት ድርጊት መሆኑ ተነግሮኛል።

በአጠቃላይ ግን በማስረጃ የተረጋገጠባቸው ላይ የሚወሰደው እርምጃ ግን ተገቢና ትክክል ነው። ላለፉት 9 ወራት መረን የለቀቀ ድርጊት ሲፈጽሙ የጸጥታ አካላት ካሁን ካሁን ይማራሉ በሚል በትዕግስት ሲያዩዋቸው ነበር የቆዩት። ባለሀብቶች ገንዘብ ይረጫሉ፤ ሽፍታውም ከዚህ በገንዘብ ይረዳ ነበር። ለምሳሌ ለደብረፂዮን 15 ሚሊዮን ብር ቼክ ጽፎ መስጠቱን የካደ አንድ ባለሀብት ነኝ የሚል ግለሰብ የመንግሥት ደጋፊ ለመምሰል 1 ሚሊዮን ብር እያለ እያታለለ ነው የተያዘው። በገንዘብ ብቻ ሳይሆን ሲረዳ የነበረው፣ ኪንዶ ብረት እየተባለ ለትግራይ መሳሪያ እየጫነ ለሽፍታው መድኃኒት ጭምር ሲያስልክ ነበር። ሆቴሉ ውስጥ የመሥተዳድሩን አባላት እንዲገድሉ የተላኩትን በትግርኛ ፈዳይ የሚሏቸውን አሳድሮም ተገኝቷል። ክብሪት የሚሏቸውን ሆቴል ቤቱ ውስጥ አሳድሮ የነበረን በተደጋገሚ በየሚዲያው ሳነሳው የነበረ ነው። በወቅቱ የሰማ ሰው ባይኖርም በኋላ ላይ መንግሥት ይህን ሰው ተከታትሎ ይዟል።
በሌላ በኩል አዲስ አበባ ውስጥ ተደብቀው የኢኮኖሚ አሻጥር በመፈጸም ብረትን የመሳሰሉ ቁሶች ሆን ብለው እንዲወደዱ ያደረጉም አሉበት። እነዚህን ኹሉ ፌደራል ፖሊስ በማስረጃ ይዞ ጉዳዩን ለሕግ አቅርቦታል።

በአዲስ አበባና ውጭ አገራት ሆነው የሚያስፈራሩና የሚዝቱ ላይ ምን መደረግ አለበት ይላሉ?
በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ ስንጮህ ነበር። እዚህ ከተማው ውስጥ ያሉት በሕግ ቁጥጥር ስር እየዋሉ ነው። ዋናው ግን ከውጭ ሆነው የሚዝቱትን ለማስቆም ምን ይደረግ የሚለው ነው። እነዚህ ሰዎች ጦርነቱ እንዲቀጥልና ድሃው የገበሬ ልጅ እንዲሞት ነው የሚፈልጉት። ይህን የሚያደርጉት የባለሥልጣናት ልጆች ናቸው። ከዚህች አገር በተዘረፈ ሀብት የተንደላቀቀ ኑሮ የሚኖሩት ናቸው። ድሃው በሰላም እንዳይኖር የሚያደርጉት። በተለይ እነስዬ አብርሃ በጦር ወንጀለኝነት እንዲጠየቁ መደረግ አለበት። ለምሳሌ ብርሃነ ገብረክርስቶስ ከኤፈርት የወሰደውን 10 ሚሊዮን ገንዘብ ባለቤቱ ከሌላ ሴት ጋር ሲማገጥ አግኝታው ፍቺ በመጠየቋ አምስት አምስት ሚሊዮን ተካፍለውታል። እነሱ በጫሩት ጦርነት የትግራይ ድሃ ገበሬ እያለቀ ነው። ውጭ ሆነው የትግራይ ሕዝብ በጦርነትና በርሃብ እንዲያልቅ የሚያደርጉት በሕግ ይጠየቃሉ የሚል እምነት አለኝ። አሜሪካ ሆነው ሽብርተኛ ቡድንን እየደገፉ ወንጀል የሚሰሩ በአንድ አገር ሕዝብ ላይ እልቂት የሚያስከትል ተግባር እየፈጸሙ መቆየት አይችሉም። በውጭ ያለው ማሕበረሰብም ሆነ የኢትዮጵያ ኤምባሲ የሚመለከታቸው የሕግ አክላት ለፍርድ እንዲያቀርቡ ያደርጋሉ የሚል እምነት አለኝ። መንግሥትም የተጠናከረ ማስረጃ ለአሜሪካን መንግሥት ማቅረብ አለበት።

የትግራይ በጀትን በተመለከተ አዲስ አበባ ያለው ጊዜያዊ አስተዳደር ይለቀቅለት የሚሉ አሉ። ጉዳት ለደረሰባቸው ቤተሰቦችም ሆነ እያገለገሉ ያሉ ባለሥልጣናት እየተቸገሩ ስለሆነ ያሥተዳድሩበት ስለመባሉ ያሎት አስተያየት ምንድን ነው?
ይህ የመንግሥት ውሳኔ ነው። ነገር ግን በጣም የሚያሳዝነው ጊዜያዊ መሥተዳድሩን ለኹለት ከፍዬ ነው የማየው። በቀበሌና በወረዳ የነበረው የበታች አመራር ሲገደል የነበረው ነው። 55ቱ የተገደሉት የበታች አመራሮች ናቸው። በእርግጥ እነእምብዛን ጨምሮ የኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊም አብሮ ነበረ። ለምሳሌ፣ የትግራይ ትምህርት ቢሮ ኃላፊዋ ኢንጂነር አስቴር ሳይነገራት እዛው ቀርታ በጁንታው ታፍና የት እንደደረሰች አይታወቅም። ምን ሊያደርጓት እንደሚችሉ ማሰብ ይከብዳል። ሃገረ ሠላም የሚባል ቦታ ሕሪት ገብረመድህን የተባለች የ9 ወር እርጉዝ ከእግሯ ጀምረው አካሏን ቆራርጠው የገደሉ ናቸው። የማኅበራዊ ጉዳይ ኃላፊ ነበረች። መምህር የሺዓለም ተስፋ ማሪያም የምትባልም በተመሳሳይ አካሏ ተቆራርጦ የተገደለች ናት።

የታችኛው መሥተዳደር ሥራውን በሚገባ ሲሠራ ነበር። አሁን ከሆቴል ወጥተው የተወሰነ ገንዘብ የተለቀቀላቸው ይመስለኛል በየግላቸው ተከራይተው ነው የሚኖሩት። የመንግሥትን ስም ሲያጠፉ የነበሩ የላይኛው አመራሮች ፣ “ሴቶች በብዛት ተደፍረዋል፤ እርዳታ የለም፤ መንግሥት የትግራይን ገበሬ ሊጨርሰው ነው” ሲሉ የነበሩት ባለ5 ኮከብ ሆቴል በተንደላቀቀ ሁኔታ ይኖራሉ። ለበላይ አመራሮቹ መንግሥት የሚያደርገው በጣም ስህተት ነው። ምክንያቱም መከላከያ ላይ ከፍተኛ የስም ማጥፋት ዘመቻ ሲያካሂዱ የነበሩ ናቸው። ዛሬ ሰው በትግራይ በርሃብ እየሞተ አንድ ቃል አውጥተው ተንፍሰው አይናገሩም። አንዱ በዝግ ስብሰባ ላይ የሕወሓት አባል ነበርኩ መልሼ የብልጽግና ሆንኩ ያለ ሰው አለ። ውስጣችን ሆነው ለሽፍታው የሚሰሩ አሉ። ከእኛም ጋር ቆይተው ወደ በረሃ አብረው የገቡ አሉ። ከሕወሓትም መጥተው መሥተዳድሩ ጋር የሚሠሩ ነበሩ። ለምሳሌ፣ መቀሌ ውስጥ አንድ ግለሰብ ጋር 20 ሚሊዮን ብር ተገኝቷል። ይህንን የትግራይ ፖሊስ ኮሚሽነር ቃለመጠይቅ ሳደርገው አምኗል። ምርመራ እየተደረገ ነው ተብሎ በኋላ ላይ ገንዘቡ የት ሄደ ሲባል፣ የት እንዳለ አይታወቅም። የዛሬ 2 ሳምንት የተደረገ የመሥተዳድሩ ዝግ ስብሰባ ላይ አንዱ ተነስቶ አካውንታችሁ ይፈተሸ ብሏል። 18 የሚሆኑት እነዚህ የመሥተዳድሩ የበላይ አባላት ባለፈው ቅዳሜ በነበረው የእምብዛ የሻማ ፕሮግራም ላይ አልተገኙም። መቀሌ አጥንታቸው ተለቅሞ ሲቀበርም አልተገኙም ነበር። ምክንያቱም ለሕወሓት ድጋፍ አላቸው ማለት ነው።

የታችኛው የመሥተዳድሩ አባለት ወጣቶች ናቸው፤ በጣምም ጠንካራ ናቸው። አገራቸውን ኢትዮጵያን የሚወዱና ሕወሓትን አጥብቀው ሲታገሉ የነበሩ ናቸው። ለእነሱ መንግሥት በጀት መድቦ ወደፊት ማድረግ የሚገባውን ያደርጋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። እኛም የተለያዩ ውይይቶችን ለማድረግ ጥረት እያደረግን ነው።

ሕወሓቶች ፈጽመውታል የሚባለውን ግፍ ሕዝብ ማወቅ አለበት ብለው የሚያምኑትን ያህል፣ ግፉን የሚሰሩት ሌላውን አስፈራርቶ እንዳይቃወማቸው ለማድረግ ስለሆነ ወሬውን ማዳረስ የነሱን ዓላማ ማሳካት ነው በሚል የሚቃወሙት አሉ። በዚህ ጉዳይ ላይ ያሎት አስተያየት ምንድን ነው?
የሠሩት ሥራ ለሕዝብ በትክክል መገለጽ አለበት። ምክንያቱም የነዚህ ሰዎች ጭካኔና ጠላትነት ከነተግባራቸው መታወቅ አለበት። የሠሩት ግፍ ብቻ ሳይሆን የዘረፉት ሀብት ይፋ መደረግ አለበት። መንግሥት እኮ አርፍዶ አሁን እኮ ነው ቤት ንብረታቸው እንዲታገድ ያደረገው። መንግሥት እርምጃ መውሰድ የጀመረው በጣም ዘግይቶ ነው። ሽብርተኛው ይህን ያህል ሰው እየገደለ የገንዘብ ምንጩን በፊት ነበር ማድረቅ የነበረበት። በአጠቃላይ የገደሉት፣ የዘረፉት. ያሸሹት ለሕዝብ ምንም ሳይቀር መነገር አለበት።

ራያን በተመለከተ ወጣቱን ከፊት ሆናችሁ ካልተዋጋችሁ ትረሸናላችሁ እያሉ መሆኑ ይነገራል። በአካባቢው የሚፈጸም ግፍም እንደተበራከተ ይሰማል። አካባቢውን በተመለከተ ምን ይላሉ?
ዝርዝር የሆነ ሳይሆን አጠቃላይ መረጃ ነው ያለኝ። በራያ ብቻ ሳይሆን በኹሉም እነሱ ባሉባቸው ቦታዎች ከፍተኛ ግፍ እየተፈጸመ ነው። አንድ እዚህ መንግሥት ሚዲያ ውስጥ የምትሠራ ጋዜጠኛ በፌስቡክ ገጿ ሕወሓት እዚህ ገባ የሚሉ የእነሱን ፕሮፓጋንዳ በመጥቀስ፣ “የትግራይ እናቶች እምባችሁ ታደሰ” እያለች ብዙ ነገር በትግርኛ ትጽፋለች። እንዲህ እያለች ቲቪ ላይ ዜና ታነባለች። ይህች ልጅ አንድ ቀን ቀጥታ ብትገባ “ታጠቅ፣ ዝመት” ልትል እንደምትችል መገመት ይቻላል። አባቷ ሻምበል ነው። ከመከላከያ አባልነቱ ተገልብጦ ዛሬ ወጣት እየሰበሰበ “በፍላጎት የማትዘምት በግድ እናዘምትሀለን፤ እምቢ ካልክም እንረሽንሀለን” እያለ እንደሆነ እናውቃለን። በእንዲህ አይነት ሰዎች ሥራ በአፋር ክልል በአንድ ክፍለጦር ስር ያሉ በርካታ ወጣቶች አልቀዋል።

ፕሮፓጋንዳን በተመለከተ መንግሥት ከተከላካይነት ስላልወጣ እየተሸነፈ ነው የሚሉ አሉ። ወደ አጥቂነት ለምን አይሸጋገርም ለሚሉት ምን አስተያየት አሎት?
ትግራይ ውስጥ 8 ወር በፈጀው የሕግ ማስከበር ዘመቻ ትግራይ ቲቪ የወያኔ ድምጽ ሆኖ ነበር ሲሠራ የነበረው። በመንግሥት አንድም ቀን አንድ ስንዴ እንዳልሰተጠ አድርገውና የትግራይን ሕዝብ እየፈጀው እንደሆነ ሲናገሩ ቆይተዋል። 50 በመቶ የትግራይ ሴቶች ተደፍረዋል ተብሎ እኮ ነው በመንግሥት ሚዲያ የተነገረው። በየቀኑ የማይቀርብ አይነት ክስ አልነበረም። የመከላከያ ሠራዊት በ3 ሳምንት ውስጥ ያገኘውን ድል አስቀርተው በፕሮፓጋንዳ እንድንሸነፍ ተደርጓል። መንግሥት በፕሮፓጋንዳ የተሸነፈው ሚዲያውን መቆጣጠር ስላልቻለ ነው። ፕሮፓጋንዳው ላይ ምንም አልተሰራም።

የሚመለከተው የመንግስት አካል አሁንም ቢሆን መረጃ ለመስጠት ክፍት መሆን አለበት። በየጊዜው እዚህ ደረሱ እየተባለ የሚነገረው የሕፃን ጨዋታ ነው። የሚባለውን ለማድረግ አቅም የላቸውም። እዛ የሚያደርስም ሎጀስቲክስም የላቸውም። ነዳጅ የለም እኮ ትግራይ ውስጥ በምን መኪና ነው አንቀሳቅሰው የሚመጡት። የሚበላ የለም፤ ነዳጅ የለም፤ ገንዘብ የለም። ለምሳሌ፣ በሱዳንና በአንዳንድ አካባቢዎች በኩል ገንዘብ ለማስገባት እየተሞከረ ነው ። ያ እንዳለ ሆኖ ገንዘብ ብቻውን ምንም አያደርግም። ስለዚህ ይሄ በሌለበት ሁኔታ ክላሽ ይዘህ የሽምቅ ተዋግተህ ከተሞችን ልትይዝ አትችልም። ዛሬ ዓለም ሰልጥኗል። ጦርነቱ በቴክኖሎጂ ሆኗል። ጦርነቱ በድሮን ሆኗል። ጦርነቱ በጀት እና በሄሊኮፕተር ሆኗል። የትግራይ ቦታዎች ተራራማ ስለሆኑ ሽፍታው እንደፈለገ ሲንቀሳቀስባቸው ነበር። አሁን ግን አፋር ላይ አንድ ክፍለ ጦር ተደምስሷል። አንድ ኮለኔል ጸጋዬ የሚባል ተገድሏል። አንድም የደህንነት አባል የነበረ ጸጋዬ ገብረመድህን የሚባል አዋጊ የተገደለም አለ። አርዐዶም ልሳን የሚባል የሚሊሺያ አስታጣቂ እና የደህንነት አባል የነበረ፣ ከነአንድ ክፍለ ጦራቸው ሙሉ በሙሉ ተደምስሰዋል። እኔ መረጃዎችን እከታተላለሁ እና ወሎ ተያዘ ምናምን የሚሉት ዝም ብለው ፌዝ ነው።

ውሸት ነው ብሎ ከማስተባበል ሌላ በወሬ ደረጃ የማጥቃቱን ጉዳይ በተመለከተ መንግሥት ምን ማድረግ አለበት ይላሉ?
ይህ በኹለት መንገድ ነው። አሁን መንግሥት በትግራይ ላይ ያን ሁሉ ነገር ፈጸመ እየተባለ ክስ ሲቀርብበት ለቆ መውጣቱን ትክክል ነው ብለናል። እነሱ አጀንዳ በሰጡን ቁጥር መልስ መስጠት የለብንም። ነገር ግን ባለፈው ጄነራል ባጫም ሆኑ ኮለኔል ጌትነት በየሳምንቱ መግለጫ መስጠት እንዳለባቸው አምነው ይሄንንም እንደሚያደርጉ ተናግረው ነበር። መከላከያ ሠራዊት ያለው ግንባታ፣ ያለው ጥንካሬ እና ያለው ኃይል በቂ እና አስተማማኝ ነው። እነዚህ ሰዎች እየተዋጉ ያሉት ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ነው። ስለዚህ ጥቂት እነ ጌታቸው ረዳ በተነፈሱ ቁጥር በተሳደቡ ቁጥር ለእነሱ መልስ መስጠት ሞኝነት ነው።

ቀደም ብዬ እንደተናገርኩት፣ በአፋር በኩል ብዙ ሰው ነው ያለቀው። እነዚህ ሰዎች በጣም ከባድ ምት ስለተመቱ እነዚህን ሕፃናት አስጨርሰው አሁን ያንን ለመሸፈንና ተሸነፍን ላለማለት በዚህ በኩል ጥቃት እየፈጸምን ነው ይላሉ። መቀሌ ተይዞ እኮ ለስትራቴጂ ነው የለቀቅነው ሲሉ ነበር።ተሸነፍን የሚል ነገር እንዴት ከነሱ ይጠበቃል። እነሱ እኮ ውሸታም ናቸው። ነገር ግን ለተለያዩ ሚዲያዎች መረጃ በመስጠት መንግሥት ይሄንን ማጋለጥ ይገባዋል።

የምዕራባውያንን ጫና እንዴት ይመለከቱታል?
እነሱ ሥልጣን ላይ በነበሩበት 27 ዓመታት 23 ቢሊዮን ዶላር ነው ከአገር የሸሸው። ይሄ IMF ያረጋገጠውና መግለጫ ያወጣበት ነው። እኔ አሜሪካ አገር ስኖር ልጆቻቸው በምን አይነት ሁኔታ ውስጥ እንደሚኖሩ አውቃለሁ። የመቶ ሺሕ ዶላር መኪና ነው የሚነዱት። ከአገር በተዘረፈ ገንዘብ የስዩም መስፍን በለው የደብረጺዮን፣ የእነ ጻድቃን የኹሉም ልጆች በተንደላቀቀ ሕይወት ውስጥ ነው የሚኖሩት።

በኃይማኖት ውስጥ ገብተዋል። ቄስ መስለው ግን ካድሬ ናቸው። የትኛውም ኃይማኖት ወንድምህን አትግደል ነው እንጂ የሚለው እነዚህ አደባባይ እየወጡ እኮ ግደሉ እያሉ ነበር። በኹሉም ነገር ላይ ሰዎች አስገብተዋል። ለነጮቹም ገንዘብ ይሰጧቸዋል። ወርቅ ሲሸልሟቸውም አይተናል። ስለዚህ በውሸት በታጀበ ሚዲያ በማገዝ ላይ ናቸው። አሁን እኮ ራሳቸው የገደሏቸውን ሰዎች የዶክተር ዐቢይ መንግሥት ገደላቸው እያሉ እያሳዩ ነው። ተከዜ ላይ እራሳቸው የገደሏቸውን ሰዎች ነው።

አስቀድመን የተናገርነው ነገር ነበር። አሁንም ገና የጅምላ መቃብሮች አሉ ። እነሱን እያወጡ መንግሥት አደረገው፤ መከላከያ አደረገው ይላሉ ስል ነበር። አሁንም ገና ስለሆነ እነሱ ምዕራባዊያንን ያሳመኑበትን መንገድ እኛ አልሰራንበትም። ውጪ ያለው የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ እኮ በራሱ እየታገለ ነው። ሊመሰገን ይገባል። በኤምባሲዎቻችን በኩል በጣም ድክመት አለ። ባለፈው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሲናገሩ 30 ኤምባሲዎችን እንዘጋለን ብለዋል። ምክንያቱም አምባሳደሮቻችን ከአገራቱ መሪዎች ጋር የሚገናኙት በረጅም ጊዜ ስለሆነ፣ ጋዜጣ ሲያነቡ ነው የሚውሉት። ስለዚህ ጋዜጣ ለማንበብ ከሆነ እዚሁ ቢያነቡ ይሻላቸዋል። በዚህም ወጪያችንን እንቀንስበታለን ነው ያሉት። ይሄ ደግሞ ትክክል ነው። አምባሳደሮቻችን ላይ ከጥቂቶቹ በስተቀር በደንብ እየተሠራ አይደለም። ስለዚህ ይሄንን በተደራጀ ሁኔታ መሥራት ያስፈልጋል።

ለመጣችውም የUSAID ኃላፊም ቢሆን ከማይካድራው ጀምሮ የተፈጸመውን ድርጊት፣ጦርነቱን ማን እንደጀመረው እና የተፈጸመውን ነገር መንግሥት በተደራጀ መልኩ በማስረጃ ሊያቀርብላት ይገባል። ከዚሁ ጋር አያይዤ ሳልጠቅስ የማላልፈው ነገር፣ በጣም የሚያሳዝነኝም ነገር የሃምሳ አምስቱን የትግራይ መሥተዳድር አባላት ዝርዝር ኢትዮጵያ ሠብዓዊ መብት ኮሚሽን አቅርበናል። የሠብዓዊ መብት ኮሚሽን ሚዛናዊነት ያልጠበቀ ለአንድ ቡድን ያጋደለ መግለጫ ነው በየጊዜው የሚያወጣው ። በዚህ ጉዳይ ላይ ከዶክተር ዳንኤል ጋር አውርተናል። እናንተ እያወጣችሁት ላለው መግለጫ መረጃ የሚሰጧችሁ ሐኪሞች የሕወሓት አባል ናቸው። የኢትዮጵያ ሠብዓዊ መብት ኮሚሽን እኮ ለማጣራት ወደ ትግራይ ሄዶ ነበር። እነ እምብዛ የተገደሉትና በየጊዜው እየተገደሉ ያሉትን ንጹሀን በተመለከተ እንዴት አንድ መግለጫ አያወጣም። ኹለተኛ እራሳቸው እያመኑ፣ እንደ ትልቅ ጀብድ ምሁሮችን ወጣቶችን ቆራርጠው እየገደሉ፣ ገደልን እያሉም በራሳቸው ሚዲያም መግለጫ እያወጡ እንዴት ነው የኢትዮጵያ ሠብዓዊ መብት ኮሚሽን ዝም የሚለው? እኔ ለዶክተር ዳንኤል ክብር አለኝ። ነገር ግን ለሕወሓት አግዘዋል ብዪ ጭፍን ፍረጃ ውስጥ አልገባም። ይሄንም እንደማያደርጉት አምናለሁ። ነገር ግን ተቋሙ ለምንድነው ሚዛናዊ መሆን ያቃተው? ለምንድነው አሁን እየተፈጸመ ያለውን ነገር የማያወጣው?

ሌላው የትግራይ መሥተዳድር ያልኳቸው ዛሬ በተንደላቀቀ ሁኔታ መንግሥት ያስቀመጣቸው እነሱ ነበሩ መንግሥትን ከጀርባው ሲወጉ የነበሩት። አበበ የሚባል የመሥተዳድሩ ምክትል የነበረ “በአማራ ክልል ምግብ እንዳይገባ ተደርጓል። የትግራይ ገበሬ ማዳበሪያ እና ዘር አጥቶ እንዲሞት ተፈርዶበታል” ብሎ ለውጮች መግለጫ የሰጠ ሰው ነው። ይሄን ሰውዪ እኮ ነው ደሞዝ እየሰጡና እየቀለቡ ቁጭ ያደረጉት።

አበራ ንጉስ የተባለ 1400 ሴቶች ተደፍረዋል አለ። ባለፈው በዝግ ስብሰባ የፖሊስ ኮሚሽነሩ ግርማይ ይሄን ሁሉ ሲሉ እስኪ ማስረጃ ስንል የ100 ሴቶች ድምጽ ያሰሙናል። እነዚህ የጠቀስኳቸው አካላት ናቸው በምዕራባዊያኑ ጫና እንዲደርስብን ያደረጉት።

ሱዳንን የምትሰጠውን ድጋፍ በተመለከተ ድንበራችንንም ስለመያዟ ያለዎት አስተያየት ምን ይመስላል ?
በሱዳን በኩል አንድ ተወልደ ገ/ትንሳይ የሚባል ኮለኔል መከላከያ ውስጥ የነበረና የጥበቃ ድርጅት አቋቁሞ ሀብታም የሆነ በ 50 ሚሊዮን ብር ሽሬ ላይ ያስገነባው አንድ ሆቴል ነበረው። አሁን ማን እንዳወደመው አይታወቅም። እሱ አሁን ሸሽቶ ሱዳን ሆኖ ወታደሮችን እያደራጀ በመተማ በኩል ያስገባቸው ከኹለት ወር በፊት ተደምስሰዋል። በሱዳን በኩል ያለው ጠብ አጫሪነት እና እነሱን የማገዙ ነገር የትም የሚያደርስ አይደለም። ኹለተኛ ኃይላቸውንም እናውቀዋለን። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት የተደራጀ አቋም አለው ስለዚህ እነሱ ብዙም የሚያሳስቡ አይደሉም።

የክልል ልዩ ኃይሎች ዘምተዋል ተብሎ ከተነገረ በኋላ አሁን ላይ የሦስት ክልሎች ወደ ቤኒሻንጉል የአንድ ክልል ደግሞ ወደ አፋር ገብተዋል ተብሏል። ከአማራና አፋር ክልል ልዩ ኃይል ውጪ ወደ ጦር ቀጠናው የተጠጋ የሌላ ክልል ልዩ ኃይል አለ?
እውነት ለመናገር ምንም መረጃው የለኝም።

መከላከያን በተመለከተ ሰሜን ወሎ አካባቢ ሆን ብሎ ቦታ እየለቀቀ መሳሪያም እየተወላቸው ነው የሚል ስሞታ ይቀርባል። መከላከያ ደግሞ በትዕግስት እየጠበኩ ነው የሚል ሀሳብ ማስተላለፉ ይነገራል። አንዳንዶች ደግሞ ስልታዊ በሆነ መንገድ ወደ ውስጥ አስገብቶ ለመምታት ነው የሚሉም አሉ። ይሄን እንዴት ያዩታል?
ምን መሰለህ እንደዚህ አይነት ስትራቴጂዎች ከዚህ በፊትም ጄነራል ብርሐኑም ሆነ ጄነራል ባጫ ሲናገሩት ነበር። እኛ የምንለቃቸው ቦታዎች ለወታደራዊ ስትራቴጂ የማንፈልጋቸው ሆነው ያገኘናቸውን ነው በሚል የለቀቋቸውን ቦታዎች ይፋ አድርገዋል። ከዛ በተረፈ ደግሞ ምን አይነት ርምጃ ሊወስዱ ነው የሚለውን መከላከያው ነው የሚያውቀው። ጥብቅ ወታደራዊ መረጃ ስለሆነ በዚህ ላይ እኔ ብዙም ማለት አልችልም።

መከላከያ የተወው የጦር መሳሪያ የለም። ያለውን ከባድ መሳሪያ በሙሉ ይዞ ነው የወጣው። ሌላው ቀርቶ በተለያዩ ቦታዎች በተከዜ፣ በአድዋ እና አዲግራት አካባቢ ደብቀዋቸው የነበሩ መሳሪያዎች በመከላከያ ተማርከዋል።ጥሎት የወጣው ምንም መሳሪያ የለም።

የኢትዮጵያ መንግሥት በሕጋዊ መንገድ ሱማሊያ ላይ ጥሪ ቀርቦለት እንደገባው ለኤርትራም ቀርቦ በድጋሚ ጦራቸው ቢገባና ቢያግዝ አስተያየትዎ ምን ይሆናል?
የመጀመሪያው አገባብ የመከላከያ ሠራዊት ሲመታ ድንበሩ ባዶ ስለሆነ ነው። ሃያ ሶስት ዓመት ሲጠብቅ የነበረው ድንበር ባዶ ሆነ። እሱ ብቻ ሳይሆን ወደ ኤርትራ እና አማራ ክልል ሮኬቶችን ይተኩሱ ነበር። ይሄ ማለት ጠብ አጫሪነት ነው። አንድ ሰው መጥቶ ቤትህን በድንጋይ እየወገረው ካልገነጠልኩ እያለ ሲደበድብ መቼም ዝም አትልም። እጅህን አጣምረህ አታየውም። እነዚህ ሰዎች እኮ መሳሪያ ያላቸው ናቸው። እንደ አገር ኤርትራ ሉዓላዊ መንግሥት እንድትሆን ራሳቸው ናቸው ሲያጫፍሩ የነበሩት ።

ስለዚህ ሕወሓት ይሄን ሁሉ ሲያደርግ ዝም ሊሉ አይችሉም። በዚህም ምክንያት ገቡ። እንደውም ግብጽና ሌላም አካል አለመግባቱ የሚገርም ነው። ይሄ አንድ ሽፍታ ቡድን ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ለፈጠረው ነገር የኤርትራን መንግሥት ማስገባት እኔ በግሌ አላምንም፤ መንግሥትም አያደርገውም።

ያለን አደረጃጀት በቂ ነው። ነገር ግን፣ ደጋፊዎቻቸው ቆም ብለው እንዲያስቡ ነው የምፈልገው። ከጦርነት የሚገኝ ነገር የለም። በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ጊዜ በኢትዮጵያ ላይ በተፈጸመው ወረራ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆ ብሎ ተነስቶ በኃይል የተያዙትን እነባድመን አስለቅቋል። አሁንም ቢሆን ከክልል ክልል ከጫፍ ጫፍ ሕዝቡ የተነሳው ጸብ አጫሪነቱ እየገፋ ስለሔደ ነው።

ለእነ ጌታቸው ረዳ ስንት ትውልድ መሞት አለበት? ይቺ አገር ካለ እነሱ መሪ እንደሌላት፣ ካለ እነሱ አዋቂ እንደሌላት ተደርጎ የሚታየው ነገር መቆም አለበት። ይሄ የትም አያደርሰንም። ስለዚህ ከእልቂት በስተቀር ምንም የሚያመጡት ነገር የለም። አሁንም እዚህ ላይ ይብቃ የሚል አካል መኖር አለበት። በትግራይ ተወላጅም በኹሉም በኩል መስማት አለባቸው። ይሄ የመጨረሻ እድል ነው። ስለዚህ ሌላ አገር የሚጋበዝበት ምንም ምክንያት አይኖርም።


ቅጽ 3 ቁጥር 144 ነሐሴ 1 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!