የእለት ዜና

የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ በኢትዮጵያ

በሴቶች ላይ የሚፈጸም አድሎ እየቀነሰ መጥቷል ቢባልም የጾታ እኩልነትን ከማስገኘት አኳያ ብዙ ሥራ እንደሚቀር በርካቶች ይናገራሉ። አድሏዊነቱ ስር እንደሰደደ ከሚያምኑትና የኹላችንንም ሥራ ይጠይቃል ከሚሉ ሴቶች መካከል ፍቅር ሽፈራው አንዷ ናቸው። ላለፉት 6 አመታት ሴቶችን ለማብቃት በስርዓተ-ጾታ ዘርፍ ለሚሠሩ አካላት የማማከር አገልግሎት የሰጡት እኚህ ምሁር፣ እስካሁን ድረስ ለ7 አመታት ለትርፍ ባልተቋቋሙ የተለያዩ ግብረሰናይ ተቋማት ውስጥ አገልግለዋል። ኹለተኛ ዲግሪያቸውን (ማስተርሳቸውን) ካጠናቀቁ ወዲህ ሴቶችን በተመለከቱ በርካታ ጉዳዮች ላይ ጥናታዊ ጽሑፎችን ለመጻፍ እና መጻሕፍትን ለማሳተም ችለዋል። የሴቶች ተሳትፎና እኩልነት ተግባራዊ ከማድረግ አኳያ ኹላችንም ይጠበቅብናል ያሉትን እዲህ አስፍረዋል።

ሴቶች በኹሉም ማሕበረሰብ ሊባል በሚችል ደረጃ ለዘመናት አድሏዊ ልዩነት እየተደረገባቸው እና ሰብዓዊ መብቶቻቸው ሳይከበሩላቸው መቆየታቸውን ከታሪክ መመልከት እንችላለን። እነዚህን የመብት አለመከበር እና ፆታን መሰረት ያደረጉ ልዩነቶችን ለማስወገድ በርካታ ዓለም ዐቀፍ ስምምነቶች እና አገር ዐቀፍ ሕጎች በአሁኑ ወቅት በሥራ ላይ ውለው ይገኛሉ። ለኹሉም የሰው ልጆች ሰብዓዊ መብቶች እውቅናን ከሰጡት እንደ ኹሉን አቀፍ የሰብዓዊ መብት መገለጫ(UDHR)፣ ዓለም ዐቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት(ICCPR)፣ ዓለም ዐቀፍ የኢኮኖሚ፣ማኅበራዊና ባህላዊ መብቶች ስምምነት(ICESCR)፣ እንዲሁም በልዩ ሁኔታ ለሴቶች መብት ልዩ ትኩረት ያደረጉት የሴቶች የፖለቲካ መብቶች ስምምነት(CPRW)፣ በሴቶች ላይ የሚደረግ ማንኛውንም ልዩነት ለማስወገድ የተደረገ መግለጫ(Declaration on Elimination All Forms of Discrimination Against Women)የመሳሳሉ ሰነዶች ለሴቶች መብት እውቅና የሰጡ ዓለም ዐቀፍ ስምምነቶች ናቸው።

በኢትዮጵያም የሴቶች መብት ከኢ.ፌ.ድ.ሪ. ሕገ-መንግሥት ጀምሮ በተለያዩ የሕግ ማዕቀፎች ውስጥ እውቅና ተሰጥቶት ይገኛል። እንዲሁም በሕገ-መንግሥቱ አንቀፅ 9/4 መሰረት ኢትዮጵያ ያጸደቀቻቸው ዓለም ዐቀፍ ስምምነቶች የአገሪቱ የሕግ አካል ይሆናሉ በማለት የደነገገ በመሆኑ በስምምነቶቹ የተዘረዘሩትን የሴቶች መብት የማክበር እና የማስከበር ኃላፊነት በመንግሥት ላይ ወድቋል ማለት ነው።

መንግሥት የሴቶችን መብት ለማክበር እና ለማስከበር ከሚወስዳቸው መሠረታዊ እርምጃዎች መካከል ለመብቶቹ በቂ የሕግ ማዕቀፍ መስጠት ይገኝበታል። በዚሁ መሠረት ለሴቶች መብት ሰፊ ሽፋን ከሰጡ ሕጎች የተሻሻለው የኢ.ፌ.ድ.ሪ የቤተሰብ ሕግ ተጠቃሽ ነው። የሕጎች ሁሉ የበላይ ሕግ በሆነው የኢ.ፌ.ድ.ሪ ሕገ-መንግሥት ስለሴቶች መብት የተደነገገውን ድንጋጌ መመልከት ጠቃሚ ነው። በሕግ-መንግሥቱ አንቀፅ 35 ስር ሴቶች ሕገ-መንግሥቱ በአረጋገጣቸው መብቶችና ጥበቃዎች በመጠቀም ረገድ እና በጋብቻ ከወንዶች ጋር እኩል መብት እንዳላቸው፣ በበታችነትና በልዩነት በመታየታቸው የደረሰባቸውን የታሪክ ቅርስ ከግምት ውስጥ በማስገባት ይህ ቅርስ እንዲታረምላቸው በተጨማሪ የድጋፍ እርምጃዎች ተጠቃሚ የመሆን መብት እንዳላቸው፣ ከጎጂ ባህል ተፅዕኖ የመላቀቀ መብታቸውን መንግሥት ማስከበር እንዳለበት፣ በብሔራዊ የልማት ፖሊሲዎች ዕቅድና በፕሮጀክቶች ዝግጅትና አፈጻጸም በተለይ የሴቶችን ጥቅም በሚነኩ ፕሮጀክቶች ሐሳባቸውን በተሟላ ሁኔታ እንዲሰጡ የመጠየቅ መብት እንዳላቸው ተገንግጎ ይገኛል።

ሴቶች በኢትዮጲያ በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚም በፖለቲካ ተሳትፎም ከወንዶቹ አንጻር ሲታይ በአነስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ነገር ግን የኢትዮጲያ ሴቶች በአማካይ በቀን ከ13-17 ሰዓት በስራ ላይ ያሳልፋሉ። 40-60 % በላይ በግብርና የሚሳተፉ ሴቶች ቢሆንም የሚያደርጉት አስተዋጽኦ የማይታይ/invisible/ እና እውቅና /acknowledge/ ያልተሰጠው ሲሆን፣ በተቃራኒው የወንዶቹ ዓመታዊ ገቢ ደግሞ በ 2.7% ከሴቶች ይበልጣል። ይህም አድሎአዊ የሆነው የስርዓተ-ጾታ ነባራዊ ሁኔታ ሴቶች ፍትሐዊ ባልሆነ ዓለም ውስጥ እንዲኖሩ አስገድዶቸዋል። ይህም፡-
አድሎአዊ የሥራ ክፍፍል እንዲኖር አድርጎል/ Gender biased division of labor/
ፍትሐዊ ያልሆነ ገቢ እና ተጠቃሚነት እንዲኖር አድርጎል
አድሎአዊ የሆነ የመረጃ፣ የትምህርት፣ የሀብት የማግኘት እድል እንዲኖር አድርጓል
ፍትሐዊ ያልሆነ ንብረትን የመቆጣጠር፣ ወሳኔ የመስጠት ዕድል እንዲኖር አድርጓል

ይህ ፍትሐዊ ያልሆነ የጾታ-ስርዓትም ለሰብዓዊ መብት ጥሰት(Human right violence)፣ ጾታን መሰረት ላደረጉ ጥቃቶች( GBV)፣ እና ጾታን መሰረት ላደረገ ድህነት/feminist poverty/ ሴቶችን ተጋላጭ እንዲሆኑ አድርጎአቸዋል። እንዲሁም ሴቶች በአገራቸው እድገት ላይ ውስን አስተዋጽኦ /limited contribution for country development/ እንዲኖራቸው አድርጎል ።

በተጨባጭ ሴቶችን ከችግሮቻቸዉ በማላቀቅ፣ የሴቶችን እኩልነት በማረጋገጥ፣ እኩል በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚያዊ እና በፖለቲካው ዘርፍ በማሳተፍ የሴቶችን ተጠቃሚነት በማረጋገጥ እና ተገቢውን አስተዋጽኦ ለአገራቸው እንዲያበርክቱ በማድረግ እኩልነትን፣ ፍትሐዊነትን እና ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን ለማስወገድ እጅግ አስፈላጊ እንደሆነ እሙን ነው።

ብዙ ጥናቶች እንደሚያመላክቱት የሴቶች ተሳትፎ በኹሉም ዘርፎች አናሳ ቢሆንም እንኳ የፖለቲካ ተሳትፎአቸው ከኹሉም ዘርፎች በበለጠ መልኩ አናሳ እንደሆነ ያሳያሉ። ይህ ደግሞ በሴቶች ላይ ያለው የጾታ አድሎአዊነት እንዲቀጥል እና እኩል ተጠቃሚነት እንዳያረጋግጡ፣ በአገራቸው ዕድገት ላይ እኩል ተሳታፊ እንዳይሆኑ እና በአገሪቷ ላይ በሚወጡ እና በሚፈጸሙ ሕጎች ላይ ተጽኖ ፈጣሪ እንዳይሆኑ አድርጓል።

በአጠቃላይ የወንድ የበላይነት የሰፈነበት አባታዊ/Patriarchal culture/ ስርዓት ያለው አገር ስለምንኖር ሴቶች እንዲመሩ፣ በፖለቲካ እንዲሳተፉ የኢትዮጵያ ባህል አያበረታታም:: ከዚህም ጋር ተያይዞ ይህ ባህል በሰዎች አመለካከት ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ በሚያመጡ እና የሴቶችን አቅም በሚወስኑ እና የሴቶችን የመሪነት ችሎታ ጥያቄ ውስጥ በሚያስገቡ አባባሎች እና ብሂሎች ሲደገፍ ኖሯል።

ከነዚህም ወስጥ፡-
“ሴት ወደ ማጀት ወንድ ወደ ሰገነት”
“ሴት ብታውቅ በወንድ ያልቅ”
“ሴት ትመራለች እንጂ አትመራም”

ከዚህም ጋር በማያያዝ የሴቶችን ተሳትፎ በፖለቲካ ዘርፍ ላለፉት 25 ዓመታት በምናይበት ወቅት ሴቶች በመምረጥ፣ በመመረጥ እና በአገራቸው ላይ ባለው የፖለቲካ ስርዓት ላይ ያላቸውን ተሳትፎ ስናይ ከዚህ በታች ባለው ግራፍ ላይ እንደምንመለከተው ሴቶች የሚመሯቸውን በመምረጥ ሂደት ላይ ተሳትፏቸው ከ47.4% እስከ 48.5% በአለፉት አምስት ምርጫዎች ላይ እንዳደገ እንደመጣ ለማየት ይቻላል።

ባለፉት አመታት የሴቶች ውክልና በፖለቲካው ዙሪያ እየጨመረ ቢመጣም፤ የሴቶች የውሳኔ ሰጭነት እና ተጽኖ ፈጣሪነት ግን ጥያቄ ውስጥ ያለ እና መሻሻል ያለበት ቁልፍ ጉዳይ ነው።
በኢትዮጵያ ፖለቲካ ሴቶች ምን ያህል ተሳታፊ ናቸዉ? በተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውስጥስ የሴቶች ተሳትፎ ምን ያህል ነዉ? የሚመሩት የፖለቲካ ፓርቲ አልያም የሴቶችን ሐሳብ የሚያካትት የፖለቲካ ፓርቲስ አለን? እንዲሁም ሴቶች በተወከሉበት ፓርቲ ውስጥ ያላቸው የውሳኔ ሰጭነት ድርሻ እና ተጽኖ ፈጣሪነት ምን ይመስላል? የሚሉት ጥያቄዎች ሊፈተሹ ይገባል። የሴቶችን ድርሻ በሚኒስትርነት ማዕረግ ላለፉት ሶስት አመታት በምናይበት ጊዜ 13.9% ሴቶች በሚኒስትርነት ደረጃ የነበሩ ሲሆኑ በ2011/12 50% ደርሷል።

ከዚህም ጋር በማያያዝ፣ ባለፉት ሦስት አመታት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ ከመጡ በኋላ የካቢኔው ቁጥር ከ34 ወደ 20 የተቀነሰ ሲሆን፣ ከዚህም ውስጥ የሴቶች ተሳትፎ ወደ 50% አድጓል ( ምንም እንኳ ይህ ጽሑፉ በተጠናከረበት ሰዓት 48.2% ቢሆንም)። እንዲሁም ሴቶች የተለያዩ ከፍተኛ የአመራር ቦታዎችን የያዙበት ሁኔታም አለ። የተወሰኑትን ለመጥቀስ ያክል

የአገሪቷ ፕሬዝዳንት፡-
ወ/ሮ ሳህለ ወርቅ ዘውዴ
የአገሪቷ ዋና የፍትህ ስርዓት አመራር፡-
ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ
የአገሪቷ የምርጫ ቦርድ ሊቀመንበር፡-
ወ/ት ብርቱካን ሚዴቅሳ

ስለሆነም የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ባለፍት 25 አመታት በተለይም ባለፉት ሦስት አመታት እየጨመረ ቢመጣም፣ ሴቶች በፖለቲካ ተሳትፏቸው ከቁጥር / ከመወከል ያለፈ ሴቶች በያዙት የአመራር ቦታ ላይ በውሳኔ ሰጭነት ሚና እና የሴቶችን እኩልነት ከማረጋገጥ እና የሴቶችን ችግር ከመፍታት አንጻር ብዙ መሠራት አለበት። በተለይም የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ለማሳደግ ስለ ሴቶች መሪነት ሚና ያለውን ባህላዊ አስተሳሰብ ለመቀየር ብዙ መሠራት አለበት። ሴቶችም ወንዶችም ስለሴቶች ያላቸው የተሳሳተ ግምት እና አመለካከት ሊቀይሩ ይገባል። ይህንንም ለማሻሻል የሚከተሉት ምክረ-ሐሳቦች ሊተገበሩ ይገባል።
የፖለቲካ ምህዳሩ ሴቶችን የሚያካት እና የውሳኔ ሰጭነት አቅምን የሚያገኙበት መሆን አለበት፤
የሚዲያ ተቋማት የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ እና ሚና በማሳደግ ላይ ሊሠሩ ይገባል፤
የመንግሥታዊ ተቋማት ሚና የሴቶችን አቅም ከማሳደግ እና ምቹ ሁኔታ ከመፍጠር አንጻር ሊጎለብት ይገባል፤
የስርዓተ-ጾታን ማካተት ሥራ በተለያዩ በተቋማት ደረጃ ያለበት ሁኔታ ሊፈተሽ እና ሊጠናከር ይገባዋል፤
በፖለቲካ ምርጫ ውክልና ላይ የሴቶችን ተሳትፎ የሚያሳድግ በሕግ የተደገፈ መዋቅር ሊኖር ይገባል፤
ሴቶች በፖለቲካ ምርጫ ተሳትፎ ሒደት ውስጥ የሚያጋጥማቸው እንቅፋት በጥናት ተደገፎ ሊስተካከል ይገባል፤

ባለድርሻ አካላት የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ እና የወሳኔ ሰጭነት ሚና አጠቃላይ ፍትሐዊነትን ከማስፈን፣ የአገሪቱን እድገት ከማሳለጥ አና የሰብዓዊ መብት ጥሰት ከመከላከል አንፃር ያለውን ጉልህ አስተዋጽዖ ተገንዝቦ የበኩሉን ድርሻ መወጣት አለበት።

ብዙ ጥናቶች እንደሚያሳዩት የማሕበረሰብ አንቂ ሚዲያዎች በማሕበረሰቡን ውስጥ ያሉ ያልተገቡ፣ ፍትሐዊ ያልሆኑ የጾታ ስርዓትን ከመቀየር እና ሴቶችን በፖለቲካ ተሳትፎ የሚገባቸውን ጉልህ ሚና ለማሕበረሰቡ ከማሳወቅ እና የሴቶችን ችሎታ ከማውጣት፣ እንዲሁም ከማበረታታት አኳያ ጉልህ ሚና ሊኖራቸው ይገባል። በአገራችን ያሉትን የሚድያ ተቋማትን በምንፈትሽበት ጊዜ ግን አብዛኛዎቹ የሚዲያ ተቋማት ስርዓተ-ጾታን ያላካተቱ እና የሴቶችም ተሳትፎ በተቋማቸው ውስጥ ከ 40% ያነሰ ሁኖ እናገኘዋለን። በአብዛኛው በአገራችን የሚገኙ የሚዲያ ተቋማት ውስጥ ያሉ የአመራር ቦታዎችም የተያዙት በወንዶች ነው። ይህም በመሆኑ ተቋማቱ ላይ ሆነ የሚዘጋጁ እና የሚሰራጩ ፕሮግራሞች ላይ የስርአተ-ጾታን እኩልነት ከማረጋገጥ አንጻር ሚናቸው ውስን ሆኖአል።

አብዛኛዎቹ የሚዲያ ተቋማት ሠራተኞችን በተለይ ሴቶችን የሚቀጥሩበት፣ የሚያበረታቱበት፣ የሚያሳድጉበት አና ወደ አመራር የሚያመጡበት ሆነ በተቋሙ ውስጥ ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶችን የሚከላከሉበት ፖሊሲ እና መመሪያ የላቸውም። እንዲሁም አብዛኛዎቹ የሚዲያ ተቋማት የሚያስተላልፉት ፕሮግራም፣ ድራማ ፣ ፊልም፣ ወዘተ. የነበረውን ፍትሐዊ ያልሆነ የስርዓተ-ጾታ ስርዓት የሚያስቀጥል ማለትም ሴቶች እንደሚደበደቡ፣ እንደሚደፈሩ፣ ሴቶችን የልጅ አሳዳጊነት ፣ የቤት ውስጥ ሠራተኝነት ሚና ብቻ እንዳላቸው፣ እንዲሁም የሴቶችን የበታችነት ስሜት የሚያንጸባርቁ ናቸው እንጅ ስለሴቶች ችሎታ፣ አመራር ሰጭነት ሚና እና አቅም፣ የፖለቲካ ተሳትፎ አስፈላጊነት የሚያንጸባርቁ አይደሉም ።

አብዛኛዎቹ የሚዲያ ተቋማትም ሴቶችን በተመለከተ የሚሰሯቸው ፕሮግራሞች መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት ድጋፍ የሚሰሩ ስለሆኑ ረዘም ባለ መልኩ ላይተላለፉ ይችላሉ። የሚዲያ ተቋማት የስርዓተ-ጾታን እኩልነት ለማረጋገጥ ማኅበራዊ ግዴታቸውን ለመወጣት በፕሮግራሞቻቸው ውስጥ አካተው አይሰሩም፡

ስለሆነም፣ የሚዲያ ተቋማት የስርዓተ-ጾታን እኩልነት እና የሴቶችን ሚና በፖለቲካ ተሳትፎ ማጉላት እና ተጽኖ መፍጠር የሚችሉበት ምህዳር መፍጠር አለባቸው።
በአጠቃላይ የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ላማሳደግ Action For Social Development And Environmental Protection Organization (Asdepo) የተለያዩ የማሕበረሰብ ውይይት በማድረግ/public dialogue/፣ የተለያዩ የሚዲያ ውይይቶችን በማዘጋጀት ማሕበረሰቡ ግንዛቤ እንዲፈጥር ለማድረግ የበኩሉን እየተወጣ ይገኛል።
ፍቅር ሽፈራው በኢሜል አድራሻቸው
fiker2004@gmail.com ማግኘት ይችላሉ።


ቅጽ 3 ቁጥር 144 ነሐሴ 1 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!