የእለት ዜና

ሲቪክ ማኅበራት – በሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ

ኢምፓቲ ፎር ላይፍ ኢነተግሬትድ ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን(ኤሊዳ) የተቀናጀ የልማት ሥራን በመሥራት ሴቶችን፣ ልጃገረዶችን፣ ወጣቶችን እና ህጻናትን በትምህርት፣ በጤና እና በኢኮኖሚ በመደገፍ እንድሁም በዴሞክራሲ ባህል ግንባታ እና ዘላቂ ሰላም ላይ የሚሠራ እና ማኅበራዊ ኀላፊነታቸውን የሚወጡ ፣ ምርታማ እና አርቆ አሳቢ ዜጎችን ለማፍራት በማለም 2008 (እ.ኤ.አ)ሴቶች የተመሠረተ አገር በቀል የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅት ነው።

በዚህ ገፅ ላይ የተካተቱ የተለያዩ አካላት ሐሳቦች የኤሊዳንም ሆነ የድጋፍ ሰጪ ድርጂቱን አቋም ላያንጸባርቁ ይችላሉ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ከመራጩ ሕዝብ እና ከተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ቀጥሎ ትኩረቱ ውስጥ የነበሩት የሲቪክ ማኅበራት ናቸው። የሲቪክ ማኅበራት መራጩን ጨምሮ በምርጫው ሂደት ተሳትፎ የሚያደርጉ ታዛቢዎችን በማሳተፍ፣ ለመራጭ ሕዝብ ተገቢውን ግንዛቤ በመስጠትና የምርጫውን ሂደትም በመከታተል ከፍተኛ ሚና ነበራቸው።
የ2013 ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ሁሉንም ኅብረተሰብ ማሳተፍ እንዲችል እነዚህ ማኅበራት ጥረት አድርገዋል። በተለይም ሴቶች፣ አካል ጉዳተኞችና የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች በምርጫው እንዲሳተፉ ገና ከቅድመ ምርጫ ሂደት ጀምሮ የተለያዩ ቅስቀሳዎችን በማድረግ ሲንቀሳቀሱ ተስተውሏል።
ብዙዎች በዚህ ይስማማሉ፤ ለአንድ ምርጫ ስኬታማነት መንግሥትና የፖለቲካ ፓርቲዎች ከሚያደርጉት ጥረት ባሻገር የሲቪክ ማኅበራት ሚና እና ድርሻ ወሳኝ ነው በሚለው። እንደውም አንድ ምርጫ ምን ዴሞክራሲያዊ ነው ቢባል የሲቪክ ማኅበራት ያልተሳተፉበት ከሆነ ሙሉ እንደማይባል የሚናገሩ አሉ።
በኢትዮጵያ የቀደሙ ምርጫዎች ሲቪክ ማኅበራት እዚህ ግባ የሚባል ትኩረት አግኝተው አያውቁም፣ ተጽእኖ ፈጣሪነታቸውም ከምንም የሚባዛ ነበር። ምንአልባትም ያለፈው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ለሲቪክ ማኅበራት ሰፊ ሜዳ የከፈተ፣ ለእነርሱም እንደ ጥሩ ጅምር በኢትዮጵያ የመልካም አስተዳደርና ፖለቲካ ግንባታ ላይ በጎ አስተዋጽኦ የሚያሳርፉበት መልካም አጋጣሚ ነው።
አንድ ምርጫ ፍጹም ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን የሁሉም ዜጋ ተሳትፎ ያሻል። በዚህኛው ምርጫ እንደታዘብነው ደግሞ ሲቪክ ማኅበራት ሴቶችና አካል ጉዳተኞች እንዲሳተፉ በማነቃቃትና ግንዛቤ በመስጠት ድርሻቸውን ከውነዋል። ይህንንም በአሃዝ አስቀምጠን ልንመለከተው እንችላለን።
ለምሳሌ ምርጫ ቦርድ ራሱ በምርጫው ሂደት እንዲሳተፉ በተለያየ መንገድና በተከታታይ ሂደት አልፈው ፈቃድ ከሰጣቸው 36 ሲቪክ ማኅበራት መካከል ስምንቱ በሴቶች ጉዳይ ላይ የሚሠሩ ነበሩ። እንደሚታወሰው በጠቅላላ ለታዛቢነት ከተሰየሙ 134 ሺሕ በላይ ታዛቢዎችም 61 ሺሕ በላይ የሚሆኑት ሴቶች ነበሩ። ይህ እንዲሆን የተቻለው በሲቪክ ማኅበራት እንቅስቃሴ የተነሳ እንደሆነ እሙን ነው።
ይህ ጉዳይ በአገራችን መልካም ጅምር ያሳየና ቀጣይነቱ የሚያጓጓ ሆኖ ሳለ፣ በዓለማቀፍ ደረጃ ደግሞ የተመሰከረለት ነው። የተባበሩት መንግሥታት ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት፣ የሲቪክ ማኅበራት በማኅበረሰብ ውስጥ የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ እንዲጨምር ጉልህ ሚና ተወጥተዋል። እንደ ምሳሌም በዋናነት የሚጠቅሰው ኢንዶኔዥያ፣ ሃይቲ እና ሜክሲኮን ነው።
ለምሳሌ ይላል፣ ለምሳሌ በኢንዶኔዥያ ማኅበራቱ የሴቶችን ንቅናቄ በመፍጠር ቀዳሚ ነበሩ። ያም እንቅስቃሴ ፍሬ አፍርቶ በምርጫ 30 በመቶ ኮታ ሴቶችን ማሳተፍ ተቋማዊ መልክ እንዲኖረው አስችለዋል። የፖለቲካ ፓርቲዎችም ለፓርቲው ገቢ ከሚደረገው ገንዘብ ውስጥ 2 በመቶ መሉ ለሙሉ ለሴቶች ሥልጠና ሥራዎች እንዲውል እንዲያደርጉ ለማስቻል ያደረጉት እንቅስቃሴ ተሳክቶላቸዋል። ይህም የምርጫ ሂደት ሕግጋትና ድንጋጌ ውስጥ እንዲካተት አድርገዋል።
የትኛውም ሰው ሊረዳው እንደሚችለውና የተባበሩት መንግሥታትም እንደገለጸው፣ ይህ ተግባር የሲቪክ ማኅበራት የሴቶች የፖለቲካ ውክልና ላይ ጠቃሚ ሚና ሊወጣ እንደሚችል፣ አቅምም ያለው እንደሆነ ያሳየበት ነው።
በድኅረ ምርጫ ወቅት የወጡ መግለጫዎችና ትዝብቶችም የዚህ ምስክር ናቸው። ለማሳያነት የሕግ ባለሞያ ሴቶች ማኅበርን ሪፖርት ልናወሳ እንችላለን። በምርጫ ሂደት ምን ዓይነት ጾታዊ ጥቃቶች ሊደርሱ እንደሚችሉና እነዛን አስቀድሞ ማስቀረት ከተቻለ የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ በተሻለ ለውጥ ማየት እንደሚቻል አመላክተዋል።
ከዚህም በላይ ደግሞ እነዚህ ማኅበራት በሚሠሯቸው ሥራዎች፣ በተለይም ከሴቶች እኩልነት ጋር በተያያዘ የሚንቀሳቀሱ ሲቪክ ማኅበራት፣ ሴቶች እንዳይሳተፉ በተለያየ መንገድ ወደኋላ ከሚጎትታቸው ባህል፣ ስርዓትና አስተሳሰቦች ሊያስለቅቁ የሚችሉ ገላጋይ እንደሚሆኑ ይታመናል።


ቅጽ 3 ቁጥር 144 ነሐሴ 1 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com