የእለት ዜና

በበጀት ዓመቱ ለአፋር ክልል ብድር አለመሰራጨቱ ተነገረ

በክልሉ አንድ በመቶ የብድር መመለስ ምጣኔ ነው የተመዘገበው

የፌዴራል የከተሞች የሥራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጄንሲ በ2013 በጀት ዓመት ለአፋር ክልል ምንም አይነት የብድር ስርጭት አለማቅረቡን አስታውቋል። ለብድሩ አለመቅረብ እንደ ዋነኛ ምክንያትነት የቀረበው በክልሉ የብድር አመላለሱ ዝቅተኛ ሆኖ መገኘቱ መሆኑን የኤጀንሲው የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቡድን መሪ የሆኑት አቦዘነች ነጋሽ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል። በአፋር ክልል የብድር አመላለስ ምጣኔ ላይ በታየው ከፍተኛ ችግር ብድር ማሰራጨት አለመቻሉን ጠቅሰዋል።

በ2013 በጀት ዓመት የተሰራጨ ብድር በክልል ደረጃ ኦሮሚያ 1.1 ቢሊዮን፣ አማራ 1.7 ቢሊዮን እና ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር 120 ሚሊዮን ፣ አዲስ አበባ 1.2 ቢሊዮን መካከለኛ አፈጻጸም ያላቸው ሲሆን፣ የሌሎቹ በጣም ዝቅተኛ ነው ተብሏል። ቤኒሻንጉል ጉሙዝ 3.2 ሚሊዮን ፣ ሲዳማ 119.7 ሚሊዮን፣ ጋምቤላ 2.9 ሚሊዮን ፣ ሐረሪ 19.6 ሚሊዮን ፣ ደቡብ 588 ሚሊዮን፣ ሶማሌ 61.1 ሚሊዮን መሆኑን ኤጀንሲው ያወጣው ሪፖርት ያሳያል። ሆኖም የአፋር ክልል ላይ የብድር ስርጭት አለመደረጉን ኤጀንሲው ባወጣው ሪፖርቱ የጠቀሰ ሲሆን፣ በተጨማሪም ሪፖርቱ በአፋር ክልል ከተሰራጨው ብድር ማስመለስ የተቻለው አንድ በመቶውን ብቻ መሆኑን ያሳያል።

የብድር ስርጭት ከብድር አመላለስ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት እንዳለው የሚናገሩት ቡድን መሪዋ፣ በየክልሉ የሚገኙ የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት የብድር አመላለሱ 97 በመቶ ካልደረሰ መልሶ የብድር ስርጭት ላይ ለመግባት አዳጋች እንደሚሆንባቸውም ያስረዳሉ።

ሪፖርቱ እንደሚያሳየው ከተሰራጨው ብድር ውስጥ ለመመለስ ካቀዱት አንጻር ድሬዳዋ 117.6 ሚሊዮን ፣ ሶማሌ 52.2 ሚሊዮን ፣ አዲስ አበባ 996 ሚሊዮን፣ አማራ 1.3 ቢሊዮን እና ኦሮሚያ 1.2 ቢሊዮን የተሻለ አፈፃፀም ያሳዩ ሲሆን፣ የቀሩት ክልሎች ሲዳማ 107.8 ሚሊዮን ፣ ሐረሪ 16.9 ሚሊዮን፣ ደቡብ 440 ሚሊዮን፣ ጋምቤላ 1.9 ሚሊዮን፣ ቤኒሻንጉል 4.4 ሚሊዮን እና አፋር 651ሺ ዝቅተኛ አፈፃፀም ያላቸው ናቸው። አጀንሲው ካለፈው በጀት ዓመት ካሰራጨው የ7.6 ቢሊዮን ብር ጋር ሲነጻጸር የዘንድሮው በ32.8 በመቶ ዝቅ ማለቱንም አስታውቋል።

በመላ አገሪቱ በሚባል ደረጃ የብድር አመላለስ ላይ ችግሮች ይስተዋላሉ። የዚህ ችግር ዋነኛ ምክንያት በብድር ላይ ያለው አመለካከት እንደሆነ የሚያነሱት አቦዘነች፣ በተበዳሪዎች በኩል አንዳንዴም “የዜግነት ድርሻዪን ነው የወሰድኩት” በሚል ብድር ላለመመለስ መሞከርም እንዳለ ይገልጻሉ።

በተጨማሪ እንደምክንያት የሚያነሱት ደግሞ ብድር ተበድሮ መጥፋት እና ብድሩን ተበድረው ወደ ስደት መሔድ ዋነኞቹ ናቸው።

ከዚህ በተጨማሪም ትክክለኛውን የብድር ሒደት ሳይከተሉ የተወሰዱ ብድሮች በማይክሮ ፋይናንሶች ላይ ትልቅ ጫና እየተፈጠሩ መሆኑም ተጠቅሷል። በተለይም ለጊዜያዊ የፖለቲካ ትኩሳት ማብረጃነት በተዘዋዋሪ ፈንድ የሚሰጡ ብድሮችን መልሶ መሰብሰብ አስቸጋሪ እንደሆነም ይነገራል። እነዚህ ብድሮች ትክክለኛው የብድር አካሄድን አሟልተው ስለማይሰጡ መሰብሰቡን አዳጋች ያደርገዋል።

የማይመለሱ ብድሮች ማይክሮ ፋይናንሶችን ሥራ መሥራት የማይችሉበት ደረጃ ያደርሷቸዋል የሚሉት ቡድን መሪዋ፣ በዚህም ምክንያት አመላለሱ ላይ ሰፊ ሥራ መሠራት እንዳለበትም ያነሳሉ።
ከስደት ተመላሾችን ወደ ሥራ ከማስገባት ጋር በተገናኘ ብድር አቅርቦ፣ መስሪያ ቦታ አመቻችቶ ወደ ሥራ ከማስገባት አንጻር በሚፈለገው መጠን አለመሠራቱን የሚያነሱት አቦዘነች፣ በዚህም ምክንያት ከታቀደው ለ 21,925 ከስደት ተመላሽ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጠራ 7,181 ብቻ መሳካቱን ይገልጻሉ።


ቅጽ 3 ቁጥር 144 ነሐሴ 1 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!