የእለት ዜና

ሕወሓት የራያ ወጣቶችን ካልተዋጋችሁ ትረሸናላችሁ በማለት ለጦርነት እያስገደደ ነው ተባለ

በአሸባሪነት የተፈረጀው ሕወሓት በራያ አካባቢ ያሉ ወጣቶችን “ከእኔ ጋር ተሰልፋችሁ ካልተዋጋችሁ ትረሸናላችሁ” በማለት አስገድዶ ለጦርነት እያሰለፈ መሆኑን አዲስ ማለዳ ከአካባቢው ኗሪዎች ሰምታለች።
አሸባሪው የሕወሓት ቡድን የቆቦ፣ ዋጃ እና አላማጣ ወጣቶችን በቆቦ እውቀት ጮራ ትምህርት ቤት በመሰብሰብ፣ “ከእኛ ፊት ተሰልፋችሁ ተዋጉ፤ እኛ ከእናንተ ጎን ነን’’ በማለት ለማሳመን የሞከረ ሲሆን፣ ወጣቶቹ በሐሳቡ ባለመስማማታቸው ምክንያት ካልተሰለፋችሁ ትረሸናላችሁ በማለት እያስገደዳቸው መሆኑን በስብሰባው ላይ የነበሩ የዐይን እማኞች ተናግረዋል።

በሽብርተኝነት የተፈረጀው ሕወሓት በቆቦ ከተማ የራሱን አስተዳደር ለማቋቋም የከተማ አስተዳደርና የከተማ ከንቲባ በመምረጥ ሒደት ላይ እንደሚገኝ የአዲስ ማለዳ ምንጮች ገልጸዋል። አካባቢውን ለቀው ያልወጡ የማኅበረሰብ ክፍሎችን የአማራ ክልልን መታወቂያ ካርድ በመቀየር የትግራይ ክልል መታወቂያ እንዲያወጡ በማስገደድ መታወቂያ እንዲቀይሩ የማድረግ ሥራ ሕወሓት ባደራጃቸው አካላት እየተካሄደ ነው ተብሏል።

አዲስ ማለዳ ካነጋገረቻቸው ምንጮች ወጣት ያሬድ በላይ፣ በዋጃና አላማጣ የሚገኙ የአማራ ተወላጆችን የሕወሓት ሰዎች በመሰብሰብ የትግራይ ክልል መታወቂያ ካርድ ተቀበሉ ማለታቸውን እና ወጣቶችን ደግሞ ከፈለጋችሁ ከእኛ ጋር ትገባላችሁ፣ ካልተስማማችሁ ደግሞ ትረሸናላችሁ እያሉ እንደሚያሰፈራሩ ተናግሯል።

ወጣት ያሬድ አያይዞም የሕወሓት ቡድን በቆቦ ከተማ ቁጥራቸው በግልጽ ያልታወቁ ንጹሀን ዜጎችን የገደለ ሲሆን፣ ከተማዋን እያወደመ፣ ንብረትም እየዘረፈ እንዲሁም የራሱን የከተማ አስተዳደርና ከንቲባ በመምረጥ ሂደት ላይ ነው ብሏል።
በሌላ በኩል ሐምሌ 27/2013 ከራያ አካባቢ ተፈናቅለው አዲስ አበባ የገቡ እና በአዲስ አበባ የሚኖሩ የራያ ተወላጆች ስብሰባ አድርገዋል። በስብሰባውም ላይ እንደገለጹት በራያ ቆቦ፣ በዋጃና በግዳን ቁጥራቸው ያልታወቀ ብዙ ዜጎች በአሸባሪነት በተፈረጀው ሕወሓት ተገድለዋል፤ ሴቶች ተገደው ተደፈረዋል፤ አዛውንቶችም ተንገላተዋል። ከዚህም በተጨማሪ ከተማወቹን በማውደም አሸባሪው በርካታ ንብረቶችን ዘርፏል ሲሉ ተናግረዋል።

በወቅታዊ ጉዳይ ላይ አዲስ አበባ የመከሩት የራያ ተወላጆች፣ “ከራያ አካባቢዎች ተፈናቅለው በወልድያ፣ በመርሳና በደሴ የሚገኙ ዜጎችና ከአካባቢያቸው ሳይወጡ ታፍነው ያሉ ዜጎች እርዳታ ያስፈልጋቸዋልና መንግሥት ፊቱን አዙሮ ሊያያቸዉ ይገባል’’ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።

አያይዘውም አሁንም ቢሆን ሕወሓት በተለያዩ አካባቢዎች(በቆቦ፣ በተኩልሽ፣ በጎብየ፣ በሳንቃ፣ በሙጃ፣ በግዳን፣ በኩል መስክ) ጥቃቱን እያስፋፋ እንደሆነና ቤተሰቦቻቸን በርሀብና በጦርነት እየተሰቃዩ ነው ማለታቸውን አዲስ ማለዳ በስብሰባው ላይ ተግኝታ ሰምታለች።

ተፈናቃዮች ድጋፍ እንደሚያስፈልጋቸው ሀሳባቸውን የገለጹት የራያ አከባቢ ተዋላጆች፣ ከራያ አካባቢ ተፈናቅለው በወልድያ የሚገኙ ዜጎች እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ለአምስት ጊዜ ያህል ከመመዝገባቸዉ በዘለለ እስካሁን በቂ ድጋፍ አላገኙም ብለዋል።

ከራያ ቆቦና አካባቢዋ የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር ከ150 ሺሕ በላይ መድረሱን የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽን መግለጹ የሚታወስ ሲሆን፣ አካባቢውን ለቀው ያልወጡ ዜጎች ችግር ላይ መሆናቸውን ለአዲስ ማለዳ ገልጸዋል።
አዲስ ማለዳ በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ መረጃ ለማካተት የቆቦ የከተማ ከንቲባ መንገሻ አሽብርን በስልክ አነጋግራ፣ “ኔትዎርክ ስለሌለ መረጃ የለኝም” የሚል ምላሽ የሰጡ ሲሆን፣ በድጋሚ ለመጠየቅ በተደጋጋሚ ስልክ ብትደውልም ስልክ ባለመነሳቱ ምላሽ ልታገኝ አልቻለችም።

አዲስ ማለዳ ባለፈው ሳምንት ዕትሟ ይዛው በወጣችው ዘገባ፣ ከቆቦ አካባቢ ተፈናቅለው ከወልድያ አስከ ደሴ የተንቀሳቀሱ ዜጎች የመጠለያና መሠረታዊ ፍጆታ ችግር እንደገጠማቸው መግልጹ ይታወሳል።


ቅጽ 3 ቁጥር 144 ነሐሴ 1 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!