የእለት ዜና

ባንኮች ለ15 ዓመታት ያልተንቀሳቀሰ የግለሰብ ገንዘብን ለብሔራዊ ባንክ ሊያስረክቡ ነው

ባንኮች ሒሳባቸውን ለ15 ዓመታት ሳያንቀሳቅሱ የቆዩ ደንበኞቻቸውን ገንዘባችሁን እስከ ጥቅምት መጨረሻ ድረስ ውሰዱልኝ ያሉ ሲሆን፣ የማይወስዱ ከሆነ ያልተንቀሳቀሱ ገንዘቦችን ለብሔራዊ ባንክ አሳልፈን እንሰጣለን ሲሉ ገለጹ።
የመጀመሪያው ትውልድ ባንኮች የሚባሉት ማለትም የምስረታ ጊዜያቸው ከ15 ዓመታት በላይ የሆኑ አንጋፋ ባንኮች ውስጥ የሚገኙ የማይንቀሳቀሱ ገንዘቦችን ብሔራዊ ባንክ ለልማት አገልግሎት ማዋል እፈልጋለሁ ሲል አዲስ መመሪያ አውጥቷል።

መመሪያውን መሰረት በማድረግ አዋሽ ባንክ፣ አቢሲኒያ ባንክ እና ዳሽን ባንክ ለ15 ዓመታት ያልተንቀሳቀሱትን አካውንቶች ይፋ አድርገዋል።
መመሪያው ባለፈው ዓመት የወጣ ሲሆን፣ ተፈጻሚነቱም ሕጋዊ ማስረጃዎችን በማቅረብ ባለቤቱ ወይንም ተወካይ ሕጉን ተከትለው እንዲወስዱ የሚያደርግ ነው።
እስከ ተጠቀሰው ጊዜ ድረስ ገንዘባቸውን ያልወሰዱ ግለሰቦች አሳማኝ የሆነ ማስረጃ ይዘው በመምጣት ከብሔራዊ ባንክ መውሰድ እንደሚችሉ የአቢሲኒያ ባንክ የፋይናንስ አስተዳደር ምክትል ፕሬዝዳንት ደሳለኝ ይዘንጋው ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በማስታወቂያቸው የተጠቀሱት የግለሰብ አካውንቶች ባለቤት የሌላቸው እንደሆኑ የሚያሳይ እና ለ15 ዓመታት ያህል ምንም አይነት ገቢና ወጪ ያላደረጉ ናቸው ሲሉ ደሳለኝ አስረድተዋል።
ገንዘቡን የመውረስ ሳይሆን ባለቤት አልባ በመሆናቸው በገንዘቡ ለሕብረተሰቡ የሚጠቅም የልማት ሥራ ለማከናወን መንግሥት እንዲወስደው የሚያደርግ አሰራር መሆኑን በመመሪያው ተጠቅሷል።
15 ዓመት ያህል አካውንቱ አልተንቀሳቀሰም ማለት ግለሰቡ ወይ ሞታል ወይ ደግሞ ከአገር መውጣቱን የሚያሳይ ነው ሲሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የቢዝነስ እና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ አሶሼት ዲን፣ የቡና ባንክ ቦርድ ሊቀመንበር እና የኢንቨስትመንትና ፋይናንስ ባለሙያ ሰውአለ አባተ (ዶ/ር) ገልጸዋል።

በባንኮች የደንበኞች የአካውንት ቁጥር ሲሰራ የሚንቀሳቀስ እና የማይንቀሳቀስ ተብሎ እንደሚለይ የጠቆሙት ሰውአለ፣ በዚህ ጊዜ ባንኮች የሚያደርጉት የማስተላለፍ ሥራ የአካውንት ቁጥራቸውን ዝቅ እንዲል ያደርጋል ብለዋል።
ብሔራዊ ባንክ እነዚህን ገንዘቦች በአንድ ላይ የሚሰበሰብበት አንድ ቋት በመክፈት የሚሰበስቡበት አማራጭ ሲፈጠር ባንኮች ጋር ያለው አካውንት ተዘግቶ ወይም ዜሮ ብር እንደሚሆን ገልጸው፣ የማይንቀሳቀሱ አካውንቶች ከሆነ ከባንኮች መዝገብ ይወጣሉ ብለዋል።

ሰዎች በተለያየ አጋጣሚ የተለያዩ አካውንት መክፈት ግዴታቸው ሲሆን፣ ክፈቱ የተባሉበት ቦታ ግንኙነቱን ሲያቋርጡ ደብተሩ ላይ ትንሽ ብር በማስቀረት የሚተወው ሰው ብዙ ነው። በእንደዚህ አይነት ሁኔታ የተከፈቱ ደብተሮች ተጠራቅመው ለብሔራዊ ባንክ ገቢ ይደረጋሉ።

ባንኮች እነዚህን አካውንቶች በመቁጠር ብቻ ይህን ያህል ደረሰን ከማለት፣ የተቀማጭ ገንዘብ መጠንን መጨመር ላይ የበለጠ መሥራት እንደሚገባቸው ሰውአለ ጠቁመዋል።
በየመንገዱ እና በተለያየ መሥሪያ ቤት እየዞሩ የባንክ አካውንት ማስከፈት ባንክ የማይጠቀመውን ሰው የሚያበረታታ መሆኑ ቢታወቅም፣ ከተከፈተ በኋላ በቂ ገንዘብ መቆጠብ እንዲችል ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል።
የአንድ አገር ትልቁ መሰረቱ ቁጠባ ቢሆንም፣ በአገራችን የኑሮ ሁኔታ ደንበኛ ካለው ላይ ቀንሶ መቆጠብ እንዲችል ማድረግ የባንኮችንም አቅም ለመገንባት ያስችላል ሲሉ አንስተዋል።

‹‹ኢትዮጵያውያን ያላቸውን ገንዘብ በግልጽ ላያሳውቁ ይችላሉ። ከቤተሰቦችም ሆነ ከሌሎች ሰዎች ያላቸውን የገንዘብ መጠን በመደበቅ በተለያየ ቦታ አካውንት በመክፈት ያስቀምጣሉ። ይህን ቤተሰብ የማያውቀውን አካውንት ሳይጠቀምበት ግለሰቡ የሆነ ችግር ቢያጋጥመው ገንዘቡ ወራሽ አይኖረውም” ብለውናል።

ብሔራዊ ባንክ ባለሦስት ገጽ መመሪያ ከዓመት በፊት ያወጣ ሲሆን፣ ተፈጻሚነቱ ከ15 ዓመት በላይ በሆናቸው በኹሉንም ባንኮች ይሆናል። ተነባቢ በሆነ ሳምንታዊ ጋዜጣ ማስታወቂያ ማውጣት፣ ከተከፈተበት ቅርንጫፍ ማስታወቂያ ቦርድ ላይ መለጠፍ እንዲሁም በድረ-ገጻቸው (ዌብሳይት) ለ3 ወር ያህል ማስታወቂያ መልቀቅ መመሪያውን ተፈጻሚ የሚያደርጉባቸው መንገዶች መሆናቸውን ይጠቅሳሉ። በነዚህ ጊዜያት ባለቤቱ መጥቶ ካላሳወቀ ባንካቸው ውስጥ ከ5 ብር ጀምሮ ያሉ አካውንቶች ገንዘብ ለብሔራዊ ባንክ እንዲያስተላለፍ ይደርጋል።

በመቀጠልም ብሔራዊ ባንክ እና ባንኮቹ ለ10 ዓመታት ድረ-ገጻቸው (ዌብሳይት) ላይ መልቀቅ እንደሚገባቸውም ይጠቅሳል።


ቅጽ 3 ቁጥር 144 ነሐሴ 1 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!