የእለት ዜና

ባንኮች አግደዋቸው የነበሩ በትግራይ ክልል የተከፈቱ አካውንቶች እየተከፈቱ ነው ተባለ

የኢትዮጵያ ባንኮች እንዳይንቀሳቀሱ አግደዋቸው የነበሩ ትግራይ ክልል የተከፈቱ አካውንቶች በልዩ ሁኔታ እንዲንቀሳቀሱና ደንበኞች አግልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ መሆኑ ተነገረ።
ትግራይ ክልል ግንኙነት መቋረጡን ተከትሎ ባንኮች አግደውት የነበረው የአካውንት እንቅስቀሴ፣ ደንበኞች በተደጋጋሚ ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት በልዩ ሁኔታ አካውንት እንዲንቀሳቀስ መፈቀድ መጀመሩ የተነገረ ሲሆን፣ እገዳው ላልተጠበቀ እንግልትና ችግር ዳርጎ እንደነበር አዲስ ማለዳ አካውንታቸውን ለማስከፈት በሒደት ላይ ከሚገኙ ደንበኞች ሰምታለቸ።

ትግራይ ክልል የተከፈቱ የኹሉም ባንኮች የደንበኞች አካውንቶች በትግራይ ክልል ግንኙነት መቋረጡን ተከትሎ በባንኮቹ ላይ ችግር እንዳይፈጠር በሚል አካውንቶቹን ታግደው መቆየታቸው የሚታወስ ነው። ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ አካውንታቸውን ያንቀሳቀሱ ደንበኞች መኖራቸውን አዲስ ማለዳ አረጋግጣለች።

አካውንታቸውን ለማንቀሳቀስ በሒደት ላይ የሚገኙ የንግድ ባንክ ደንበኞች፣ አዲስ አበባ በሚገኘው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጎተራ ቅርንጫፍ አገልግሎት እያገኙ መሆኑን ገልጸዋል። ደንበኞቹ አካውንታቸውን ለማንቀሳቀስ ባንኩ ያዘጋጀውን የማመልከቻ ፎርም ቅድሚያ መሙላትና ማስገባት ይጠበቅባቸዋል።

በተፈጠረው የግንኙነት መቋረጥ ቀደም ሲል ታግደው የነበሩ ትግራይ ክልል የተከፈቱ አካውንቶችን ለማንቀሳቀስ የተሰየመው ጎተራ ቅርንጫፍ፣ ደንበኞችን ቅድሚያ ፎርም በማስሞላት በአንድ ሳምንት ውስጥ ደንበኞች አካውንታቸውን ማንቀሳቀስ እንዲችሉ እየሠራ ነው ተብሏል። ደንበኞች የታገደባቸውን አካውንት ለማንቀሳቀስ የባንክ ደብተራቸውና መታወቂያቸው ኮፒ ተደርጎ ባንኩ ያዘጋጀውን ፎርም ከሞሉ በኋላ፣ አካውንቱን ለማንቀሳቀስ ከአራት ቀን እስከ አንድ ሳምንት እንዲጠብቁ ተነግሯቸዋል።

አዲስ ማለዳ ጉዳዩን በማስመልከት ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ሱፐርቪዥን ዳይሬክተር ፍሬዘር አያሌው ጋር ቆይታ አድርጋለች። ፍሬዘርም በትግራይ የተከፈቱ አካውንቶች እንዳይንቀሳቀሱ ብሔራዊ ባንክ በጽሑፍም ሆነ በቃል ለባንኮቹ የላከው ውሳኔ አለመኖሩን ገልጸዋል።

ፍሬዘር አያይዘውም በወቅቱ ካለው የፖለቲካ አለመረጋጋት አንጻር የግንኙነት መስመሮች በመቆራረጣቸው ምክንያት ደንበኞች በተለያዩ አካባቢዎች በመዘዋወር በተደጋጋሚ ብር ለማውጣት ቢሞክሩ ማወቅ ስለማይቻል ባንኮች ኪሳራ እንዳይገጥማችሁ ተጠንቅቃችሁ ሥሩ የሚል ምክርን ከመለገስ ውጭ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በትግራይ ክልል የሚገኙ ባንኮችን ዝጉ ወይም አትዝጉ የሚል ምንም አይነት ዕገዳ እንዳላደረገ ነው ለአዲስ ማለዳ የገለጹት።

ዳይሬክተሩ አክለውም በትግራይ ክልል የተከፈቱ አካውንቶች የተዘጉት በሌላ ክልል ከሚገኙ የባንክ ቅርንጫፎች ጋር ያላቸው ግንኙነት በመቋረጡ ምክንያት የሲሰተም ችግር ስለገጠማቸው ነው። ይህን ተከትሎም ደንበኞች ወደ ሌላ የባንክ ቅንጫፍ በመሔድ በድጋሚ በማውጣት ለኪሳራ እንዳይዳርጓቸው በማሰብ በራሳቸው ውሳኔ ባንኮችን እንደዘጉ ነው የተናገሩት።

በትግራይ ክልል ተዘጉ በተባሉ ባንኮች የወጡ አካውንቶችን እንደገና በመክፈት ባንኮች እያደረጉት ያለውን እንቅስቃሴም በራሳቸው ውሳኔ እያስተናገዱ እንጅ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ያስተላለፈው ውሳኔ እንደሌለም ነው አዲስ ማለዳ ለማረጋገጥ የቻለችው።

ባንኮች አግደዋቸው የነበሩ አካውንቶችን ለማንቀሳቀስ የጀመሩት በራሳቸው አሠራር የሚደርስባቸውን የአደጋ ተጋላጭነት መዝነው ሊሆን እንደሚችል ፍሬዘር ጠቁመዋል። ለዚህም ባንኮች በአሠራር ስርዓታቸው ደንበኞቻቸው አካውንታቸውን እንዲያንቀሳቅሱ ሲፈቅዱ የደንበኞቹን ማንነት በማጣራት ለአደጋ የማያጋልጥ መሆኑን የሚያረጋግጡበት ሒደት እንደሚኖር ተጠቁሟል።


ቅጽ 3 ቁጥር 144 ነሐሴ 1 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!