የእለት ዜና

ሴቶችና ውበት!

“ሲቄ” የሚለው የኦሮምኛ ቃል ‹አለንጋ› የሚል ትርጉም አለው። በገዳ ትውፊታዊ አስተዳደር ውስጥ በባሏ ጥቃት የደረሰባት ሚስት፣ ከሌሎች ሴቶች ጋር በመሆን ባሏ ላይ የካሣ ውሳኔ የምታሳልፍበት ስርዓት ሲቄ ይባላል።

የሴት ልጅ ውበት ውስጣዊና ውጫዊ በማለት በኹለት ተከፍሎ ሊገለጽ ይችላል። ውስጣዊ የሚባለው የሴት ልጅ ውበት አመለካከቷን፣ መልካምነቷን፣ ፀባይዋን እንዲሁም እራሷን የምታከብር ሴት መሆንዋን የሚገልጽ ነው።
የሴትን ልጅ ውጫዊ ገፅታዋን አይኗን፣ አፍንጫዋን፣ ጥርሷን፣ ፀጉሯን በአጠቃላይ ተክለ ሰውነቷን በመመልከት መግለጽ የተለመደ ነው።
የሴት ልጅ የውበት ዘውዷ ከሚታይበት መካከል አንዱ ፀጉሯ መሆኑ አያጠያይቅም። የተዘናፈለ ዞማ ፀጉር በማንም አይን ውስጥ ገብቶ አድናቆትን ያሰጣታል።
ይህን የተረዱ ብዛት ያላቸው ሴቶች የተለያዩ መንገዶች በመጠቀም ፀጉራቸውን ያስውባሉ። በሰዎችም ዘንድ ማራኪና ውብ እንደሚያደርጋቸውም ያምናሉ።
በድሮ ጊዜ ሴቶች ቅቤና አደስ እየተቀቡ በባህላዊ መንገድ የራሳቸውን ፀጉር ይንከባከቡ ነበር። እንደ ሴቶቹ ዕድሜ ክልል መሠረት የተለያዩ ሽሩባዎችን በመሠራት ያገቡና ያላገቡ እንደሆኑ የሚለዩበት ባህላዊ የፀጉር አሠራርን ሥርዓትን ይጠቀሙ ነበር።
በርግጥ በአሁኑም ወቅት በገጠሪቱ የአገሪቱ ክፍሎች ፀጉራቸውን ቅቤ እየተቀቡ የሚንከባከቡ ሴቶች ቢኖሩም፣ በከተሞች ውስጥ ግን ከዚህ ቀደም ከነበረው አንፃር ዝቅተኛ የሚባል ቁጠር ያላቸው ናቸው።
አሁን ባለንበት ዘመን ሴቶች የተለያዩ ብልሀቶችን በመጠቀም የፀጉር እድገትን መጨመር እንዲሁም ማስዋብ ጀምረዋል። ዘመን የወለዳቸውን ሰው ሠራሽ ፀጉሮች(ዊጎች)፣ የፀጉር ቅባቶች፣ የፀጉር አሰራሮችን፣ የፀጉር ቀለሞችና የፀጉር እድገት የሚጨምሩ የንጽህና መጠበቂያዎች በመጠቀም ፀጉርን ማስዋብ አሁን አሁን የተለማደ ድርጊት ከሆነ ሰነባብቷል።
ሴቶች የፀጉር ማስዋቢያዎችን መጠቀማቸው የተለመደ ቢሆንም፣ ለማስዋቢያዎቹ የሚያወጡት ዋጋ ግን ኢኮኖሚያቸውን የሚፈታተን ሲሆን ይስተዋላል።
ዘመናዊ በሆነ መንገድ የፀጉራቸውን ውበት የሚጠብቁ አንዳንድ ሴቶች፣ ለፀጉራቸው ውበት መጠበቂያ የሚያወጡት ዋጋ ቀላል የማይባል ጭንቀት ውስጥ እንዲገቡ ምክንያት ሆኗል።
በተቃራኒው በተፈጥሮ ፀጉራቸው የሚዋቡ ሴቶች ዘመን አመጣሽ ማስዋቢያዎችን ባለመጠቀማቸው እራሳቸውን ከከፍተኛ ወጪ ታድገዋል።
በተፈጥሮ በተሰጣቸው ፀጉር የሚዋቡ ሴቶችን ሹሩባ ይሠራሉ፣ የተለያዩ የፀጉር ቅባቶችን እና ንጽህና መጠበቂያዎችን ይጠቀማሉ።
የሰው ሠራሽ ፀጉር (ዊግ) እና የፀጉር ቀለሞችን መጠቀም ተጓዳኝ ችግሮችን ሊያስከትል ስለሚችል አዘውትሮ መጠቀም አይመከረም።
ሴቶች በተቻላቸው አቅም ተፈጥሮ የለገሰቻቸውን ፀጉር በእንክብካቤ በመያዝ ውበታቸውን ቢጠብቁ ተመራጭ ነው። ይህ ሳይሆን ቀርቶ የዘመን ወለድ ማስዋቢያዎችን ሴቶች በሚጠቀሙበት ወቅት ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው።
የሚገዙትን መዋቢያዎች ይዘት፣ ምርቱ የሚያበቃበትን ጊዜ በደነብ መመልከት አስፈላጊ ነው። በሌላ በኩል፣ ሴቶች ለውበት መጠበቂያነት የሚያወጡት ወጪ አቅማቸውን ባገናዘበ መልኩ ሊሆን ይገባዋል።
ውብ ሆኖ መገኘት አንዳንዶች እንደሚሉት ሴትነትን ዝቅ የሚያደርግ ሳይሆን በራስ መተማመንን የሚያጎለብት ነው። አስፈላጊነቱ ላይ ከባህል ባህል የተለያየ አመለካከት ቢኖርም፣ ውብ መሆንን የሚጠላ፣ እንዲሁም የሚያምርን መመልከት የማይወድ ስለማይኖር ክብርን በጠበቀ መልኩ መከናወን ያለበት ጉዳይ ነው።


ቅጽ 3 ቁጥር 145 ነሐሴ 8 2013

Comments: 1

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

  1. ይኼ አምድ የሴቶች መብቶችን እና የስርዓተ ፆታ እኩልነት ጉዳዮችን የሚያቀነቅን ነበር። አሁን እሱ ቀርቶ ሴቶችን ‘ኦብጀክቲፋይ’ የሚያደርጉና ይኼን ጨምሮ በሚሶጂኒ የሚያስወቅሱ ጽሑፎች እየተስተናገዱበት ነው። ብታስቡበት መልካም ነው።

This site is protected by wp-copyrightpro.com