የእለት ዜና

የዓለም የወጣቶች ቀን ከፒ ኤች ኢ ኢትዮጵያ ጋር ሲከበር

ፒ.ኤች.ኢ ኢትዮጵያ ኮንሶርትየም የተቀናጀ አሰራርን ለማስተዋወቅ እና በስፋት እንዲተገበሩ በማድረግ የሰዎች እና የአካባቢ መስተጋብር ተጠጥሞ ዘላቂ ልማትን እውን ርዕይን አንግቦ በ2000 ዓ.ም የተመሰረት ድርጅት ነው።
ድርጅቱ ከተመሰረተበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ድረስ የአካካቢ፣ የሥነ-ሕዝብ፣ የማኅበራዊ፣ የኢኮኖሚ እና የጤና ጉዳዮችን ያቀናጁ የተለያዩ የልማት ሥራዎች ሲያከናውን ቆያቷል።
በዚህ ገጽ ላይ የተካተቱት የተለያዩ አካላት ሐሳቦች የፒኤችኢ ኢትዮጵያን አቋም ላያንጸባርቁ ይችላሉ።

ፒ ኤች ኢ ኢትዮጵያ ኮንሰርቲም ‹‹በኢትዮጵያ የምግብ ሥርዓትን ለመለወጥ የወጣቶች ሚና›› በሚል መሪ ቃል ነሐሴ 12 ዓለም ዐቀፍ የወጣቶች ቀንን አክብሯል። ‹‹የምግብ ስርዓትን በኢትዮጵያ ለመለወጥ የወጣቶች ሚና›› በሚለው ጉዳይ ላይ ቁልፍ ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የግማሽ ቀን ውይይት አዘጋጅቶ ነበር። የውይይት መድረኩ ወጣቶች እና አርሶ አደሮች የምግብ ስርዓቶችን ለሕዝቦች ደኅንነት መለወጥ ላይ በሚደረገው ትግል ውስጥ በተሻለ ሁኔታ እንዲቀመጡ ለመደገፍ በመሳሪያዎች፣ ፖሊሲዎች እንዲሁም የተለያዩ የልምድ ልውውጦች የተደረጉበት ነበር።

በመድረኩ የሕፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ሕይወት ኃይሉ እና የተለያዩ ኃላፊነት ያላቸው አካላት ተገኝተዋል።
Population health and environment consortium (PHE) ባሉት ወጣት ተኮር ፕሮግራሞች መሠረት ዓለም ዐቀፍ የወጣቶች ቀን በአዜማን ሆቴል አክብሯል።
የፒኤችኢ ዋና ዳይሬክተር ነጋሽ ተክሉ በዕለቱ እንደገለጹት፣ PHE ያለውን ኃላፊነት መሠረት በማድረግ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በተገኙበት ቀኑን ውይይት በማካሄድ አክብሮታል ሲሉ ገልጸዋል።
ዓለም ዐቀፍ የወጣቶች ቀን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በወሰነው መሰረት በየዓመቱ ነሐሴ 12 ቀን ይከበራል። የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ በ1999 የውሳኔ ሐሳብ 54/120ን ካጸደቀ በኋላ የመጀመሪያው የወጣቶች ቀን በፈረንጆች 2000 ተከብሮ ነበር። ዓላማውም ግንዛቤን ለመፍጠር እና በዓለም ዙሪያ ላሉት የተለያዩ ማኅበራዊ እና ባህላዊ ተግባራትን በማከናወን የወጣቶች ጉዳይ ትኩረት ለመሳብ በማሰብ ይከበራል። የተባበሩት መንግሥታት በወጣቶች ላይ ያተኮረበት ነጥብ ከወጣት አደረጃጀት እና በወጣቶች ልማት ውስጥ የተባበሩት መንግስታት የኢንተር- ኤጀንሲ አውታር መረብ አባላት ፣ ወጣቶች እና ሲቪል ማሕበረሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን እንዲያደራጁ ለማበረታት ቀኑ ይከበራል።

በኢትዮጵያ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑት ከ30 ዓመት በታች ያሉ ወጣቶች መሆናቸው የሚታወቅ ሲሆን፣ እነዚህ ወጣቶች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚገባ ተረፈ ተከተል የጤና ሚኒስቴርን በመወከል ተናግረዋል።
በዓለም ዐቀፍ ደረጃ የተከበረውን የወጣቶች ቀን ፒኤችኢ ትኩረት ሰጥቶ ማክበሩ መበረታታት ያለበት ነውም ብለዋል። የእናትና ወጣቶች ጤና በሚል ስትራቴጂ በመንደፍ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እየሠራ እንደሚገኝ ተነስቷል።
በጤና ሚኒስቴር የሚዘጋጅ ከ300 ሰዎች በላይ የሚሳተፉበት የወጣቶች ቀንን የሚያመላክት ዝግጅት መኖሩ ተጠቁሟል።

የወጣቶች ጤናን በተመለከተ ግንዛቤን በመፍጠር እና የመከላከል ሥራዎችን በመሥራት የሚታወቀው ጤና ሚኒስትር፣ የአእምሮ ጤናን በመጠበቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ይገኛል ብለዋል።
የሴቶች፣ ሕፃናት እና ወጣቶች ሚኒስትር ዲኤታ የሆኑት ሕይወት ኃይሉ በበኩላቸው፣ የዓለም ዐቀፍ የወጣቶች ቀንን በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ወጣት ተኮር ፖሊሲዎችን በመቅረጽ እና ግንዛቤን በመፍጠር ማክበር እንደሚገባው በማመን መከበሩ ጠቃሚ ነው ብለዋል።
በዘንድሮ ዓመት የሚከበረው የምግብ ስርዓት ጋር በማያያዝ መከበሩ ወጣቶችን ጠቃሚ ማድረግ ያስችላል።

ወጣቶች ለአገር ሠላም የሚያበረክቱትን አስተዋጽኦ በማሰብ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አንድ ወር ሙሉ እያከበረው እንደሚገኝ ሕይወት ጠቁመዋል።
በዕለቱ የተለያዩ ጥናቶች የቀረቡ ሲሆን፣ ጥናቱን ካቀረቡት መካከል ሚሊዮን በላይ የአፍሪካ የምግብ ሉዓላዊነት ጥምረት አስተባባሪ ይገኙበታል። ሚሊዮን እንደገለጹት 80 ከመቶ በላይ አርሶ አደር ባለባት አገር ማምረት የሚገባውን እና ጥራቱን የጠበቀ ምግብ ማምረት ያስፈልጋል።

ይህ ምርት በሚመረትበት ወቅት መሬት እና አካባቢዎች እንዳይጎዱ ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉ ሚሊዮን ገልጸዋል።
ይህንንም ለማድረግ ኬሚካልን፣ የመስኖ እርሻ፣ የተባይ ማጥፊያ እንዲሁም ማዳበሪያ መጠቀም ይገባል ብለዋል። የአፍሪካ ግሪን ሪቮሊሽን አሊያንስ 1 ቢሊዮን ዶላር ፕሮጀክት ኢትዮጵያ ትልቁን ድርሻ ካገኙት መካከል ኹለተኛዋ ናት።
ወጣቱ የሚመገበው ምግብ የስርዓተ ምግብን መዋቅርን የተከተለ ስላልሆነ ይህንን ስርዓት ለመሻሻል ሲሰተም ተቀርጿል።

ፒኤችኢ ኢትዮጵያ ኮንሰርቲየም ለአየር ንብረት ለውጥ በመቋቋም እና የአካባቢን ዘላቂነት በማረጋገጥ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የሕዝብ ጤና እና አካባቢን ውህደት ለዘላቂ ልማት ለማሳደግ የሚፈልግ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት ነው።
አህመድ መሐመድ የፒኤችኢ ኢትዮጵያ ኮንሰርቲም የሥነ-ሕዝብ ፕሮግራም አስተባባሪ እንደገለጹት፣ ወጣቶች የአገር ተረካቢ እንደመሆናቸው መጠን በየዓመቱ የሚከበረው ዓለም ዐቀፍ የወጣቶች ቀን ሐሳብን በመደገፍ ፒኤችኢ ኢትዮጵያ አክብሮታል።
ተቋሙ ወጣቶች ላይ የሚታየውን የሥራ አጥነት ችግር ፣ ከምግብ ስርዓት ጋር በተያያዘ ያለአስፋላጊ ውፍረት ወይም መቀንጨር እንዳይከሰት የግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ በመሥራት ቀኑን አክብሮታል።
ፔኤችኢ ኢትዮጵያ በሴቶች እና ወጣቶች ላይ ትኩረት አድርጎ የሚንቀሳቀስ ተቋም እንደመሆኑ መጠን፣ ለወጣቶች የሥራ እድል በመፍጠር ትልቅ ሥራ መሥራቱን አህመድ ገልጸዋል።

ፒኤችኢ በገጠር የሚገኙ ወጣቶች በአካባቢያቸው ያሉትን መሰረተ ልማት በመጠቀም ሥራ ፈጠራን በማበረታት ይታወቃል። በዚህም በገጠር የሚገኙ ወጣቶች የሚጠቀሙት ማሳ የቤተሰቦቻቸው ስለሆነ የራሳቸውን የሚፈጥሩበት አማራጭ በማሳደግ ደረጃ አስተዋጽኦ ያደርጋል።
ወጣቶቹ የራሳቸው የሆነ መሥሪያ ቦታ በማመቻቸት እንዴት ራሳቸውን ማሳደግ እንደሚችሉ ግንዛቤን በመፍጠር እና አማራጮችን በመጠቆም ትልቅ ሥራዎችን በመስራት ላይ ይገኛል።
ከዚህ በተጨማሪ ገጠር ያሉ ወጣቶች ያላቸውን ሀብት ሳይጠቀሙ ወደ ከተማ መጥተው ሥራ አጥ ሆነው እንዳይቸገሩ እና ስደትን እንዳይመኙ ትልቅ ዓቅም የሚፈጥር መሆኑን አህመድ አንስተዋል። እነዚህ የገጠር ወጣቶች ከተማ መጥተው ሥራ ለመሥራት ከሚያስቡ አቅራቢያቸው የሚገኙትን መሠረተ ልማቶች በመጠቀም ሥራ ፈጣሪ እንዲሆኑ ማስቻል የፒኤችኤ ዋኛ ተግባር መሆኑም ተጠቁሟል።

ደርጅቱ ወጣቶች ላይ እየሠራ ከሚገኘው ሥራ አንዱ ኃይል ቆጣቢ ምድጃዎች በገጠር አካባቢ በጣም አስፈላጊ መሆናቸውን በመገንዘብ ወጣቶች እያመረቱ የሚያቀርቡበትን አማራጭ ማሳየት ነው። ይህ ኃይል ቆጣቢ ምድጃ ባለመኖሩ በገጠር አካባቢ ያሉ እናቶች ሲጎዱ ይስተዋላል። ይህንን ችግር እንዲቀርፉ ኃይል ቆጣቢ ምድጃ በመሥራት ለተጠቃሚ እንዲያቀርቡ ገቢም እንዲያገኙበት በማድረግ ወጣቶች ላይ እየሰራ ይገኛል።

በተጓዳኝም ይህን ማድረግ በአካባቢው ላይ የደን ጭፍጨፋ እና ምንጠራ ይቀንሳል ብለዋል። ባህላዊ ምድጃዎችን መጠቀም የደን ምንጣሮን በማበራከት በገጠር ያለውንም ማኅበረሰብ ለችግር የሚያጋልጥ ነው። ከዚህ በተጨማሪ ከፍተኛ ጭስ ስለሚኖረው ለተለያዩ በሽታዎች የመጋለጥ ዕድል ያሰፋል ሲሉ አህመድ ገልጸዋል።

ይህንን የአካባቢ መራቆት ለመቀነስ እና የጤና ጉዳትን ለመከላከል ለወጣቶች የሚፈጠርላቸው የሥራ ዕድል ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወትም ተጠቁሟል።
ፒኤችኢ ኢትዮጵያ ለእነዚህ ወጣቶች የሚፈጥረው የሥራ ዕድል የችግኝ ማፍላት አንዱ ተጠቃሽ ነው። ችግኞችን በማፍላት ለአካባቢው ማኅበረሰብ በመሸጥ ገቢ እንዲያገኙ የማድረግ ዕድሎችን ድርጅቱ ያመቻቻል ተብሏል።
ይህን ሥራ ወጣቶች ከወላጆቻቸው የተማሩት፣ቀላል እና በአካባቢያቸው የሚተገበር ነው።

ከዚህ በተጨማሪ በአካባቢ የሌሉ የአትክልት ዘር ከሌሎች ቦታዎች በማምጣት እንዲተክሉ እና ለማኅበረሰቡ ጥቅም እንዲሰጥ የማድረግ ሥራ ፒኤችኢ እየሰራ ነው ብለዋል።
በተናጠል ሳይሆን በተቀናጀ የልማት አቅጣጫ የወጣቱን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና የተፈጥሮ ውጤቶች ችግር ለመፍታት እየሠራ እንደሚገኝ ዋና ዳይሬክተሩ አቶ ተክሉ ጠቅሰዋል።
በሥነ ሕዝብ ጤና እና አካባቢ የሚሰራው ፒኤችኢ ኢትዮጵያ ኮነሰርቲም፣ ከተመሠረተ በፈረንጆቹ 2008 ጀምሮ ለሕብረተሰቡ ዘላቂ የልማት አቅጣጫዎች መፍትሄ የማምጣት ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል። ድርጅቱ ከአፍሪካ በሕዝብ ብዛት በ2ኛ ደረጃ የምትገኘው ኢትዮጵያን የሥነ ሕዝብ ሒደት ከልማት ጋር በማስታርቅ ለውጦችን ለማምጣት እየሠራ የሚገኝ ነው።

ፒኤችኢ በብዛት የሚሠራው ጥብቅ የሆኑ ቦታዎችን፣ የተፋሰስ አካባቢዎችን፣ ደረቅ ቦታዎች እና የደን አካባቢዎችን መነሻ በማድረግ ነው።
የአካባቢ ጥበቃ መብትን በተመለከተ ፒኤችኢ ከኮሚሽኑ ጋር በጋራ በመሆን የተለያየ ባለ ድርሻ አካላት አባል የሆኑበት አገር ዐቀፍ መድረክ (ፕላትፎረም) አቋቁሟል።
በአጋርነት እና ትብብር የሚያምነው ፒኤችኢ በሽርክና እና በጥምረት ግንባታ ስኬታማ የሆኑ የብዙ የውህደት ዘርፎችን በመፍጠር ከመንግሥት አካላት ፣ ከአባል ድርጅቶች ፣ ከልማት አጋሮች እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር እየሠራ ይገኛል።


ቅጽ 3 ቁጥር 145 ነሐሴ 8 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com