የእለት ዜና

በግጭት አፈታት ዙሪያ የወጣቶች ሚና

የሠላምና ልማት ማዕከል ለትርፍ ያልተቋቋም፣ መንግሥታዊ ያልሆነ አገር በቀል ድርጅት ሲሆን፣ ከማንኛውም የፖለቲካም ሆነ የሌላ ወገንተኝነት የጸዳ፣ በአገሪቱ የሠላም ባህል እንዲስፋፋ፣ በውይይት እና በንግግር የሚያምን ማሕበረሰብን ለመፍጠር የሚሰራ ተቋም ነው።
ተቋሙ ከተመሰረተበት 1982 ዓ/ም አነስቶ በተለያዩ የሠላም ግንባታ ሥራዎች ላይ ተሰማርቶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል። በተለይም ደግሞ ግጭትን ለመፍታት እና የሠላም ባህልን ለመገንባት የሚያስችሉ አገር በቀል እውቀቶችን በማዳበር በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ አለመግባባቶች በውይይት እንዲፈቱ ሲያደርግ ቆይቷል። በተለይም ደግሞ በቦታ እና በሁኔታ አለመመቸት ምክንያት ለብዙ ተቋማት ለመድረስ አመቺ አይደሉም የሚባሉ የአገራችን አካባቢዎች ጭምር ሳይቀር በመግባት ከታችኛው የማሕበረሰብ አደረጃጀቶች ጋር ሰፊ የሠላም ግንባታ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል። ተቋሙም በተሰማራበት የሥራ ዘርፍ ምንም እንኳ እንደአገር ያለብን ችግር ዘርፈ ብዙ እና ሰፊ ቢሆንም የአቅሙን በማበርከት ላይ ከመሆኑም በላይ አመርቂ የሚባሉ ውጤቶችን በማስመዝገብ ላይ ይገኛል። ተቋሙም አሁን ያሉ ፕሮጅክቶችን በማስፋት እና ወደተጨማሪ ቦታዎች በመንቀሳቀስ፣ እንዲሁም የተለያዩ ማሕረሰብ አቀፍ የሆኑ የሰላም ጥረቶችን በመደገፍ እንዲሁም አቅማቸውን ጭምር በመገንባት ለችግሮች ተመጣጣኝ የሆነ ምላሽ ለመስጠት የበኩሉን አስተዋፅኦ በማበርከት የሚቀጥል ይሆናል።
ሠላምና ልማት ማዕከል

“ወጣት የነብር ጣት” እየተባለ ለብዙ ጉዳዮች ወጣቱ እንደመንስዔም እንደመፍትሄም ይታያል። ፀብ የሚከረው ወጣት በሆነው የሕብረተሰብ ክፍል ነው እንደመባሉ፣ አለመግባባትን ለማርገብም የወጣቱ ሚና ከፍተኛ መሆኑ ይነገራል። ለስራም ሆነ ለውድመት ወጣቱን የሚያክለው ስለማይኖር ብዙ መንግስታትም ሆኑ ተቋማት ትኩረታቸውን ወጣቱ ላይ በማድረግ ይንቀሳቀሳሉ።

ከልጅ እስከአዋቂ የማይጋጭ ባይኖርም፣ ቂም የሚቋጥረውና ብዙ መዘዝ ሊያስከትል የሚችል ተግባር ውስጥ የሚገባው፣ እንዲሁም በቀላሉ የማይበርድ ግጭት የሚያስከትለው ወጣቱ መሆኑን የሚናገሩ በርካቶች ናቸው። ለግጭት ወይም አለመግባባት ብዙ መነሻዎች እንዳሉ ቢታወቅም፣ እነዚህን በየቦታው የሚነሱ ግጭቶችን ለማብረድም ሆነ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የሚወሰዱት የመፍትሄ መንገዶች በዋናነት ወጣቱን ማሳተፍ ይኖርባቸዋል። ጦርነትም ቢሆን በወጣቱ ዘማችነት የሚከናወን እንደመሆኑ በእድሜ የገፉ ይመሩታል አሊያም ያስቆሙታል እንጂ ዋናው ተዋናዮቹ ወጣቶች ናቸው።

ግጭት የሚበዛባቸው የተለያዩ ሐገራት አለመግባባቶችን ለማስወገድና እርቅ ለመፍጠር የሚጠቀሙት ሽማግሌዎችን እንደሆነ ይታወቃል። ሽምግልና በተለይ በአፍሪካ ትልቅ ቦታ ያለው እንደመሆኑ የወጣቶችን ግጭት ለመፍታት እንደዋና መፍትሄ ተደርጎ ሲወሰድና ውጤታማም ሲያደርግ ቆይቷል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የትልቅ ሰው ተደማጭነት እየቀነሰ ሽማግሌዎችም በማሕበረሰቡ ውስጥ ያላቸው ተቀባይነት እያሽቆለቆለ በመምጣቱ እንደበፊቱ ግጭትን ለማርገብና እርቅ ለማውረድ አስቸጋሪ ሆኗል። ይህ ቢሆንም አልፎ አልፎ አሁንም የሽማግሌዎች ሚና ያልተቋረጠበት ቦታ አለ። በቅርቡ የጋሞ ሽማግሌዎች እርጥብ ሳር ነጭተው ይዘው ለጥቃት የተሰለፉ ወጣቶችን ማስቆማቸው ሲነገር ሕብረተሰቡ ያሳየው ደስታ የሚዘነጋ አይደለም።

ከ20 አመታት ገደማ በፊትም የሠፈር ወጣቶች በየቀበሌው እየተቧደኑ እርስ በርስ ያደርጉት የነበረው ግጭት ብዙ ደም ካፈሰሰና ሕይወትም ከጠፋ በኋላ በሽማግሌዎች ጥረት እንዲቀር ተደርጎ ነበር። የ24፣ የሞቢል፣ የቄራ፣ የቅንብቢት… ልጆች እየተባባሉ ባጋጣሚ የተወለዱበትን ሠፈር ይዘው ሕይወት እስከመጠፋፋት የደረሱት ወጣቶች እርቅ ለማውረድም ትልቅ ድርሻ ነበራቸው። “ፈሩ” ላለመባል በራሳቸው ተነሳሽነት ባይጀምሩትም፣ ግጭቱ ያስከተለውን መዘዝ ሁሉም የተረዳበት ወቅት ስለነበር እርቅ ለማውረድና ሰላም ለመፍጠር ጊዜ አልፈጀባቸውም። ድንኳን ተጥሎ ወጣቶቹን ለማቀራረብ እድል ከተፈጠረ በኋላ የነበረው ሂደት በራሳቸው ተነሳሽነት የተከናወነ እንደነበር ይታወሳል።

በግጭት አፈታት ዙሪያ የወጣቶች ተሳትፎ ከፍተኛ እንደሆነ ቢታመንም፣ ብዙዎች ወጣቶችን ግንባር ቀደም ተሰላፊ አድርገው ሲጠቀሙባቸው አይታይም። በአንዳንድ አገራት ግን በራሳቸው በወጣቶች ተቋም ተመስርቶ ግጭት ለመፍታት ብቻ ሳይሆን፣ ወጣቶች ግጭት ላይ እንዳይሳተፉ የሚደርግ የመከላከል ስራም ይሰራል። ለምሳሌ የዩጋንዳን ብንወስድ፣ ወጣቶች የሚመሩትና ወጣቶች የሚሰሩበት ውጤታማ እንደሆነ የሚነገርለት ተቋም አለ። ይህ የወጣቶች ስብስብ፣ ግጭትን ወጣቶች ራሳቸው ያለማንም ጣልቃ ገብነት እንዲፈቱ ብቻ አይደለም የሚሰራው። ወጣቶች ስለግጭት ያላቸውን አስተሳሰብ አስቀድመው እንዲቀይሩ በሰፊው ይሰራል። ምንም አይነት አለመግባባት ሲፈጠር አስቀድመው በውይይት መፍታት እንደሚችሉ የማሳመንን ስራን በጥልቀት ይሰራል። ይህን ተግባሩን ግጭት ሊከሰት ይችላል በሚልባቸው አካባቢዎች ያሉ ወጣቶች ላይ በቅድሚያ በማተኮር ይሰራል። በዩጋንዳ ብቻ ሳይሆን ለግጭት ተጋላጭ ናቸው በሚባሉ የምስራቅ አፍሪካ ጎረቤት ሀገራትም ልምድ በማካፈል ውጤታማ ስራ እየሰራ እንደሆነ ይነገርለታል።

ወጣቶች ሰላምን ለማምጣት ያላቸውን ኃላፊነት ባለማወቅ ባብዛኛው ተግባራቸው በክፉ ሲሳል ይታያል። ወጣቶች ግጭትን ከመፍታት ይልቅ ለግጭት መንስኤ መሆናቸው በተለምዶ ስለሚነገር ሚናቸው እንዲኮስስ ማደረጉን ባለሙያዎች ይናገራሉ። በተለምዶ ስለወጣቶች የሚኖርን አመለካከት የሚገነቡት ትልልቆች በመሆናቸው ትክክለኛው አተያይ እንዳይኖር ማድረጉ ይገመታል። አመለካከቶቹ የሚፈጠሩት ራሳቸውን ወጣቶችን በማናገር ባለመሆኑም የተዛባው አተያይን ለማስተካከል ሳይቻል ተቆይቷል።

ወጣት ለሰላም ያለውን ሚና፣ እንዲሁም ግጭትን ለማስወገድም ሆነ ለመፍታት ሊኖራቸው ስለሚገባ ኃላፊነት ብዙዎች ሲናገሩ ይሰማል። የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ሪዞሉሽን 2250፣ እንዲሁም አፍሪካ ሕብረትም የአፍሪካ ወጣቶች ቻርተርን በፈረንጆቹ 2006 ላይ በጋምቢያ ካፀደቀ ወዲህ በርካታ ስራዎች ተከናውነዋል። የወጣቶችን ሚና በማስተዋል በተለያዩ ሰነዶች ውስጥም በማካተት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግስታት ትኩረት ሰጥተው ለመስራት በእቅዶቻቸው ውስጥ ሲያካትቷቸውም ቆይተዋል። ለወጣቱ ምን ይደረግ የሚሉ ብቻ ሳይሆኑ፣ ወጣቱ ምን ማድረግ ይችላል በሚል ጠቃሚ ውሳኔዎችንና መመሪያዎችን በማውጣት ተግባራዊም ያደርጋሉ።

አፍሪካ ሕብረት በአህጉሪቱ የሚበዙት ወጣቶች እንደመሆናቸው፣ ሚናቸውን በመረዳት ዘግይቶም ቢሆን በ2018 የአፍሪካ ወጣቶች ለሰላም ደህንነት የተባለ ራሱን የቻለ ተቋም በሕብረቱ ስር በመመስረት ጥናትም አስጠንቶ ወደ ስራ አስገብቷል። ስለወጣቶች ያለ አመለካከት በቅድሚያ መቀየር እንደሚገባ የሚያመለክተው ከአመት በፊት በሕብረቱ ይፋ የተደረገው የጥናት ሰነድ፣ ወጣቶችን እንደግጭት መንስኤ ብቻ አድርጎ ማየቱ ትክክል አለመሆኑን ያመላክታል። ለተለያዩ አገር ዜጎች መጠይቅ በማዘጋጀት የወጣቱን አመለካከት ለማወቅም ጥረት ተደርጓል። ወጣቶች ግጭት እንዳይፈጥሩ አስቀድሞ አመለካከታቸው ላይ መሰራት እንዳለበት ትኩረት የተሰጠው ሲሆን፣ አለመግባባት ሲከሰት ምን አይነት መንገዶችን በመጠቀም ያለ ፀብ ልዩነትን መፍታት እንደሚቻል የሚያመላክት ነው።

አንድ ልብስ ለሁሉ ልክ እንደማይሆነው፣ ከቦታ ቦታ እንደአመለካከታቸውና ባህላቸው የተለያየ የመፍትሄ እርምጃ መወሰድ እንዳለበት የተገለጸ ሲሆን፣ ራሳቸውን ወጣቶቹን ቦታ ሰጥቶ ማሳተፉ በዘላቂነት ግጭት እንዳይከሰት፣ ከተፈጠረም እልባት ለመስጠት ጠቃሚ እንደሆነ በጥናቱ ተጠቁሟል። ወጣቶች ሚናቸው ሰፊ እንደመሆኑ እነሱን ተሳታፊ ለማድረግም የተለያዩ አማራጭ መንገዶችን መጠቀም ያስፈልጋል። የወጣቶችን ሚና ለማጎልበት አቅም መፍጠር መቻሉ ወሳኝ እንደሆነም ይታመናል። የኑሮ ውድነት እየጨመረ፣ ወጣቱም በልቶ ለማደር በሚራወጥበት ጊዜ ግጭት ውስጥ እንዳይገባ የሚያስችለውን እውቀት እንዲያገኝ ፕሮግራም ተቀርፆ ሃላፊነት ተወስዶ መሰራት ያለበት ተግባር መሆኑን ብዙዎች ይስማሙበታል።

ወጣቶች በግጭት አፈታት ዙሪያ የሚሰሩትን ስራ ለማሳደግና ኃላፊነትም እንዲሰማቸው ለማድረግ የግብረሰናይ ተቋማት ሚና ከፍተኛ እንደሆነም ይታመናል። በአቅምም ሆነ በዕውቀት ወጣቶች እንዲጎለብቱ ለማድረግ አለም አቀፍም ሆኑ አገር በቀል የእርዳታ ድርጅቶች ትልቁን ድርሻ እንደሚወስዱ ይታወቃል። በተለይ ኢትዮጵያን በመሳሰሉ አቅም በሌላቸው የአፍሪካ አገራት ለትርፍ ያልተቋቋሙ ግብረሰናይ ተቋማት የሚያከናውኑት ተግባር ውጤታማ እንደሆነ ይነገራል።

የኢትዮጵያ ወጣቶች በግጭት አፈታት ዙሪያ የሚኖራቸውን ሚና ለማሳደግ ከሚሰሩ ተቋማት መካከል የሰላምና ልማት ማዕከል አንዱ ነው። የመንግስት ይሁንታን በማግኘት በተለያዩ ግጭት በተከሰተባቸው አካባቢዎች የሚሰራው ይህ ተቋም፣ ወታቶችን ተሳታፊ በማድረግ በርካታ ስራዎችን እንደሰራ ይነገርለታል። በሁሉም ክልሎች ሊባል በሚችል ሁኔታ የተጋጩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተቀራርበው እርቅ እንዲያወርዱ እየሰራ ይገኛል። ከሰሞኑም በቡራዩና በአዲስ አበባ ወጣቶች መካከል ተከስቶ የነበረውን አለመግባባት ተከትሎ የተፈጠረው ግጭት ያስከተለውን መራራቅና መፈራረጅ ለማስቀረት ሲሰራ ቆይቷል። ኹለቱ ተጎራባች ወጣቶች ለአመታት የቆየው ቅርርባቸው በአንድ አጋጣሚ ተወግዶ እንደባላንጣ መተያየት የጀመሩበትን ሂደት በማቆም፣ ወጣቶቹ ራሳቸው ሰላም እንዲወርድ ያደረጉትን ጥረት በማስተባበርም ሆነ አነስተኛ ስልጠና በመስጠት ማእከሉ እገዛ አድርጓል።

ከፍተኛ የገንዘብ አቅም የሚጠይቁ ተመሳሳይ ሂደቶችን የሰላምና ልማት ማዕከል ሲያካሂድ ቢቆይም፣ በቂ እንዳልሆነ ተሳታፊዎቹም ሆኑ ተጠቃሚዎቹ ይናገራሉ። ግጭት ያለባቸው አካባቢዎች በርካታ ከመሆናቸው አንፃር ገና ብዙ መሰራት እንዳለበት ቢታወቅም፣ ለወደፊትም ለግጭት ቅርብ የሆኑ አካባቢዎች ላይ ትኩረት በማድረግ አስቀድሞ ግንዛቤ የመፍጠር ስራ መሰራት እንዳለበት ይታመናል።

ወጣቱ ትኩስ ኃይል እንደመሆኑ ጉልበቱንም ሆነ ትኩረቱን ለሠላም እንዲሰጥ ማድረግ ቀላል ላይሆን ይችላል። ነገር ግን፣ በአንድ አገር እጣ ፋንታ ላይ የመወሰን ኃላፊነታቸውን ለተረዳ አካል እነሱን ሳያሳትፉ መስራት ውሃ እንደመውቀጥ ልፋት ሆኖ እንደሚቀር ያምናሉ። እድሜ ልኩን የሆነ አስተሳሰብ ይዞ ያደገን አዋቂ ለመቀየር ከመሞከር ይልቅ፣ ክፍት አዕምሮ ያላቸው ወጣቶች ላይ ትኩረት ተደርጎ ቢሰራ ውጤታማ እንደሚሆንም ባለሙያዎች ይናገራሉ። ወጣቱ ቀጣይ አገር ተረካቢ ነው ሲባል በተደጋጋሚ እንደምንሰማው፣ የተሻለ አስተሳሰብ ይዞ ካልመጣ ሕብረተሰቡ የባሰ አዘቅት ውስጥ እንደሚገባ ይታወቃል። ለበጎም ሆነ ለክፉ ያለወጣቱ ተሳትፎ የሚሆን ነገር እንደሌለ ሊታመን ይገባል። የትውልድ መልካም ቅብብሎሽ እንዲኖርም፣ “ልጅ ያቦካው ለእራት አይበቃም” እያልን ከአገራዊ ጉዳዮች ከምናገላቸው፣ ለሁላችንም እራት እንዲበቃ አድርገው እንዲያቦኩ ማስተማር የአዋቂዎች ፈንታ እንደሆነ መረዳት ይስፈልጋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 145 ነሐሴ 8 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com