የእለት ዜና

አፍሪካ እና የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ

ኢምፓቲ ፎር ላይፍ ኢነተግሬትድ ዴቨሎፕመንት አሶሴሽን(ኤሊዳ) የተቀናጀ የልማት ሥራን በመሥራት ሴቶችን፣ ልጃገረዶችን፣ ወጣቶችን እና ህጻናትን በትምህርት፣ በጤና እና በኢኮኖሚ በመደገፍ እንድሁም በዴሞክራሲ ባህል ግንባታ እና ዘላቂ ሰላም ላይ የሚሠራ እና ማኅበራዊ ኀላፊነታቸውን የሚወጡ ፣ ምርታማ እና አርቆ አሳቢ ዜጎችን ለማፍራት በማለም 2008 (እ.ኤ.አ)ሴቶች የተመሠረተ አገር በቀል የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅት ነው።

በዚህ ገፅ ላይ የተካተቱ የተለያዩ አካላት ሐሳቦች የኤሊዳንም ሆነ የድጋፍ ሰጪ ድርጂቱን አቋም ላያንጸባርቁ ይችላሉ።

በያዝነው የፈረንጆች ዓመት በአፍሪካ የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ የተመለከተ የዳሰሳ ጥናት ውጤት ይፋ ተደርጓል። ይህ ‹Women Political participation: Africa Barometer 2021› የሚል መጠሪያ ያለው ጥናት በዓለማቀፉ የዴሞክራሲ እና የምርጫ ድጋፍ ተቋም (IIDEA) የታተመ ነው። ጥናቱ እንደሚያመላክተው በመላው በአፍሪካ አገራት ካሉ 12 ሺሕ 113 የፓርላማ አባላት መካከል ሴቶቹ 24 በመቶ ናቸው።
ይህን የዳሰሳ ጥናት መሠረት ያደረገው ዘገባ፣ አፍሪካ ከሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ አንጻር ጥሩ የሚባሉ ስኬቶችን አስመዝግባለች፤ ነገር ግን አሁንም የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ከማሳደግ አንጻር ብዙ የሚጠበቅባት መሆኑን የሚያመላክት ነው ተብሎለታል። በዚሁ ጥናት ውስጥ ሴቶች በፖለቲካው እንዳይሳተፉ መሰናክል ከሆኑ በርካታ ችግሮች መካከል ትልቁን ድርሻ የሚይዘው የገንዘብ ወይም የሀብት እጥረት ነው ተብሏል።
ይኸው ጥናት ታድያ መልሶ አፍሪካውያን የሴቶችን የፖለቲካ ተሳትፎ ማነስ እንደማይፈልጉት አረጋግጫለሁ ብሏል። በአፍሪካ 72 በመቶ የሚሆኑ ሰዎች እንደ ወንድ ሁሉ ሴቶችም እኩል የመመረጥና በፖለቲካ የመሳተፍ እድል ሊኖራቸው ይገባል በሚለው ይስማማሉ። ነገር ግን ይህ ለሁሉም የአፍሪካ አገራት እውነት ነው ማለት አይደለም። አንዳንድ ቦታዎች በዚህ የሴቶች እኩል የፖለቲካና የምርጫ ተሳትፎ መብት አይስማሙም፣ ወይም ሴት አመራሮችን አይቀበሉም።
በምሥራቅ አፍሪካ 74 በመቶ ሰዎች በሴቶች እኩል የምርጫና የፖለቲካ ተሳትፎ ሲያምኑ፤ በደቡብ አፍሪካ 73 በመቶ እንዲሁም በሰሜን አፍሪካ 50 በመቶ የሚሆኑት በዚህ ሐሳብ ይስማማሉ። በአንጻሩ በሱዳን 53 በመቶ ሰዎች እንዲሁም በግብጽ 50 በመቶ ሕዝብ ሴቶችን በአመራርነት መቀበልን አይፈልጉም፣ እኩል እድል ሊሰጥ ይገባል ብለውም አይሞግቱም፤ በጥናቱ መሠረት።
ጥናቱ ላይ የተሳተፉ ባለሞያዎች ሲናገሩ፤ ለአንድ አገር መልካም አስተዳደር የሴቶች ተሳትፎ ቁልፍ የሆነበትን ምክንያት ያነሳሉ። በከፍተኛ አለመረጋጋት ላይ የነበሩ አገራትን ተቀብለው ለውጥ ያመጡ አፍሪካውያት ሴት መሪዎችንም ይጠቅሳሉ። ኤለን ጆንሰን ሰርሊፍን ጨምሮ በዚህ የሚጠቀሱ ሴቶች አሉ ይላሉ። የሚገርመው ሴት መሪዎች የተለየ ለውጥ እንዲያመጡም በዛው መጠን ይፈለጋል፤ ብጥብጡንና አለመረጋጋቱን በአንድ ጀንበር እንዲያበርዱት ይፈለግባቸዋል።
ጥናቱም ለዛ ሳይሆን አይቀርም የሴት መሪዎች ስኬት የማይወራለት ይላል። ያም ሌሎች ሴቶችም ወደ ምርጫ እና ፖለቲካ እንዳይቀርቡ ያደርጋቸዋል። ‹‹[አንዳንድ አገራት] ሴት መሪዎች ከወንዶች በሚገባ የተለዩ ናቸው ብለው አያምኑም። ሴት አመራሮች ያሉባቸው አገራትም መሪዎቻቸውን እንደ ጥሩ ምሳሌና እንደ አረአያ በአደባባይ ሲጠቀሱ አይስተዋልም።›› ይላል።
እንደ አገር አረአያ አድርጎ መጥቀስ ሲገባ በብዛት የማይነሳ ቢሆንም ከአፍሪካ አልፎ ለዓለም አገራት ምሳሌ የሚጠቀስ ሥራን ያሳየች አገር ሩዋንዳ ናት። በሩዋንዳ የትኛውም የዓለማችን አገር ላይ በማይታይ መልኩ 64 በመቶ ወንበሮች በሴቶች የተያዙ ናቸው። በሩዋንዳ ብቻ ሳይሆን በሴኔጋል፣ ሲሺየልስ፣ ደቡብ አፍሪካ ከ40 በመቶ በላይ እንዲሁም በሞዛምቢክ፣ አንጎላ፣ ታንዛንያ እና ኡጋንዳ 35 በመቶ ወንበር በሴቶች የተያዘ ነው።
ይህ ብዙ ጊዜ የሥልጣኔ እና የንቃት ሚዛን ከምናደርጋት አሜሪካ ጋር ሲነጻጸር ትልቅ የሚባል ነው። ምክንያቱም በአሜሪካ ፓርላማ ሴቶች 19 በመቶ ወንበር ያላቸው ሲሆን፣ በምክር ቤት 20 በመቶ ብቻ ናቸው።
ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ በአፍሪካም በነሩዋንዳ መልካም ተሞክሮ ጥላ ስር ገብተው ያልታዩ የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ እዚህ ግባ የማይባልባቸው አገራት አሉ። እነዚህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ሳይቀር የከፋ ቁጥር ያሳዩ ናቸው የተባለላቸው ሲሆኑ፣ ስዋዚላንድ 6.2 በመቶ፣ ናይጄሪያ 6.7 በመቶ እንዲሁም ቤኒን 8.4 በመቶ ናቸው።
እንዲህ ያሉ አገራትን ጨምሮ በዓለማቀፍ ደረጃ የሴቶችን የፖለቲከ ተሳትፎ ለማሳደግ ባለፉት ኹለት ዐስርት ዓመታት ጥረት ሲደረግ እንደነበር ይኸው ጥናት አክሎ ጠቅሷል። የ1995 የተባበሩት መንግሥታት የቤይጂንግ ጉባኤም አገራት ቢያንስ የሴቶችን ተሳትፎ 30 በመቶ እንዲያደርሱ ሥራን ትቶላቸዋል።
ይህን ለማሳከትም ብዙ አገራት ከተጠቀሟቸው መንገዶች መካከል አንደኛው የኮታ አሠራር ነበር። በፓርላማ ውስጥ ተሳታፊ ሊሆኑ የሚገቡ ሴቶችን በቁጥር ካስቀመጡ አገራት መካከልም ጎረቤት አገር ኬንያን ጨምሮ ደቡብ አፍሪካ እና ሞዛምቢክ ይገኙበታል። ይህን የኮታ ስርዓትም የውስጥ ሕጎችን ሳይቀር አውጥተዋል። በእርግጥ በኮታ ስርዓት ውጤታማነት ላይ ጥርጣሬ ያላቸውና የማይቀበሉት አሉ።
ያም ሆነ ይህ ሪፖርቱ የአፍሪካ አገራትን የሚያነቃ ነው ተብሎለታል። ይልቁንም በ2030 የሚጠናቀቀውና ወደዛው እያዘገመ ያለው ዘላቂ የልማት ግብ አስራ አንደኛ ሰዓት ላይ የደረሰ እንደመሆኑ፣ በቀሩ ጥቂት ዓመታት አገራቱ የተለያየ መንገድ በመጠቀም የሴቶችን ተሳትፎ እንዲያሳድጉ ይጠበቅባቸዋል።
በዓለም 46 አገራት ከፓርላማ አባሎቻቸው መካከል ሴቶች አንድ አራተኛ ቦታ አላቸው። ከእነዚህ አገራት መካከል ደግሞ 14ቱ በአፍሪካ የሚገኙ ናቸው። አፍሪካ በሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ እያሳየች ያለችው ለውጥ ገና ያልተዘመረለት መሆኑ ግን እሙን ነው። ሴት መሪዎች ተሰየሙ ማለት ግን የአፍሪካ ችግር በአንድ ጀንበር ታሪክ ይሆናል ማለት አይደለም፤ አዲስ ዕይታና አዲስ ኃይል እንደሚገኝ ግን እሙን ነው።


ቅጽ 3 ቁጥር 145 ነሐሴ 8 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com