የእለት ዜና

“ህወሓቶችን ያጎለመሳቸውና ቦታ የሰጣቸው መንግሥት ነው”

ቴዎድሮስ አያሌው ይባላሉ። ከ1994 ወዲህ ባሉት ዓመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ተሳትፎ ነበራቸው። የ2002ቱን ምርጫ ተከትሎ ለ7 ዓመታት በእስር ላይ ቆይተዋል። ከእስር ከተፈቱ ወዲህ ዲሞክራሲ እውን እንዲሆን የበኩላቸውን ትግል አድርገዋል። ከተለያዩ የኢትዮጵያ ግዛቶች የተፈናቀሉ ስደተኞች እርዳታ እንዲያገኙ በማስተባበርም ይታወቃሉ። ከሠሞኑም በመንግሥት አሸባሪ የተባለው የህወሓት ታጣቂ ወልዲያን ለመያዝ በተደጋጋሚ በሞከረበት ወቅት ሕዝብን በማስተባበርና ተፈናቃዮችን በማስተናገድ ትልቅ ሥራን እንደሠሩ ይነገርላቸዋል። ባለፈው ማክሰኞ ግን ራሳቸው ተፈናቅለው ወደ ደሴ ለመሰደድ ተገደው ነበር። ደሴ በነበሩበት ወቅት ስለአጠቃላይ ወቅታዊው ሁኔታ ያላቸውን ምልከታ እንዲያጋሩ የአዲስ ማለዳው ቢኒያም ዓሊ ጋር ቆይታ አድርገዋል።

ስለእርስዎ ቢያስተዋውቁን?
ስሜ ቴዎድሮስ አያሌው ነው። ተወልጄ ያደግኩት ወልዲያ ነው። ወደፖለቲካው የገባሁት በ1994 በወጣትነቴ ነው። የመኢአዱ ኢንጂነር ኃይሉ ሻወል ወደ አካባቢያችን መጥተው በነበረበት ወቅት በተካሄደው የሕዝባዊ ድጋፍ ትዕይንት ወቅት በመገኘቴ ነበር ወደ ፖለቲካው የገባሁት። ሒደቱ ስለፖለቲካ በተወሰነ ደረጃ እንዳውቅ አድርጎኝ ነበር። ከልጅነት ጀምሮ በአገር ፍቅር እንዳድግ ተደርጌ ነበር። የኢትዮጵያ ባሕር በር የሚመለስበት፣ በብሔርና ቋንቋ ላይ የተመሰረተው ዘረኛ አካሄድ ቀርቶ የኢትዮጵያ አንድነት የሚመጣበት፣ የተበላሸው የሚስተካከልበት፣ ሰው በሰውነቱ የሚከበርበት አገር እንድትሆን ለመታገል የወሰንኩበት ጊዜ ነበር።
በ1997ቱ ምርጫ ወቅት የመኢአድ አባል ሆኜ ቅንጅቱ እንዲያሸንፍ አስተዋፅኦ ባደርግም፣ ምርጫው በነአቶ መለስ ዜናዊና አቶ በረከት ተጭበርብሮ መክኗል። በዛ የተነሳ ብዙ ዋጋ ከፍለናል። ብዙዎች ሲገደሉ ከተሰደድት ውስጥ አንዱ እኔ ነበርኩ። አመራሮቻችን ከተፈቱ በኋላ የ2002ቱ ምርጫ ላይ መሳተፋችንን ቀጥለን ነበር።

ለዓመታት ስለታሰሩበት ሁኔታ ቢያሳውቁን?
በዛን ዘመን ሰው ሲያስሩ ማስረጃ የሚባል ነገር አያስፈልግም ነበር። አንድ ሰው የፖለቲካ አመለካከቱ ከገዢው ፓርቲ በተቃራኒው ከሆነ አንድ ታርጋ ተለጥፎለት ይታሰር ነበር። እኔ ከስደት መልስ ዲሞክራሲያዊ የሆነ መንግሥት እንዲኖር ስታገል ነበር። አሁንም ቢሆን የማምነው በብዕር ፖለቲካ ነው። በመናገር በመጻፍ አምናለሁ። ዲሞክራሲና ሰብዓዊ መብት የሚረጋገጥባትን ኢትዮጵያ ዕውን ለማድረግ ትግል ማድረግ እንዳለብኝ በማመኔ የበኩሌን አስተዋፅኦ አድርጌያለሁ። በ1997 ሞራሉ የተደቆሰው ሕብረተሰብ እንዲነቃቃ ከሌሎች ጋር በመሆን ትልቅ እንቅስቃሴ አድርገን ነበር። አደረጃጀታችንን እስከ ትግራይ ዘርግተን መንቀሳቀሳችንን ያልወደደው የወያኔ መንግሥት ብቻ ሳይሆን ሌሎቹም የእሱ ተቀፅላ የሆኑትም ነበሩ። ሥራችንን ያልወደዱት የወቅቱ አመራሮች ምርጫው ከተጠናቀቀ በኋላ ይዘው “አሸባሪ” ብለው አስረውኛል። በ2003 በአገር መክዳት ተብሎ በጸረ ሽብር አዋጁ መሰረት የ10 ዓመት ፍርድ ተፈርዶብኝ ወህኒ ቤት ገብቼ ነበር። ከ7 ዓመት እስር በኋላ በአቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ከተፈቱት መካከል ሆኜ ከእስር ቤት ልወጣ ችያለሁ።

የመንግሥት ለውጥ ከተባለው ወዲህ በህወሓት ላይ የተወሰደውን ወታደራዊ እርምጃ እንዴት ይገመግሙታል?
ለውጥ መጣ የምንለው በአንጻራዊነት ነው። እርግጥ ነው ከወያኔ ኢሕአዴግ አገዛዝ ነፃ ወጥተናል። ዛሬ በወያኔው ሥርዓት ልክ “ይህን ተናገርክ፣ ይህን አደረግክ” ብሎ የሚያዋክብ የለም። አሁን ምንም የለም ሳይሆን በተወሰነ መልክ ለመኖሩ በእነእስክንድር ላይ የሆነው ምሳሌ ነው። ሙሉ በሙሉ ነፃነት መጥቷል ብለን መናገር የምንችልበት አይደለም።

በህወሓት ወያኔ ላይ ያለው የመንግስት ዕይታ የተንሸዋረረና ትክክል ያልሆነ ነው። አንደኛ አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀን አካል ለድርድርና ለዲፕሎማቲክ ወግ ማብቃት አልነበረበትም። ይህን የሚያደርግ ደካማነቱን ያመነ ነው። ይህን ያደረጉ ሹመኞች ደካማነታቸውን የሚያሳይ ተግባር ነው የተከተሉት። ወያኔ ኢሕአዴግ 27 ዓመት ሙሉ የፈጸመብን ግፍና በደል ቢሰፈር ህልቆ ቢስ ነው። እንጻፈው ቢባል እንኳን የሚያልቅ አይደለም። ይህን ማስረዳት ሲያቅት እነሱ ከወደቁ በኋላ ፕሮፓጋንዳ ስለሠሩብህ መቀየር አያስፈልግም ነበር። እነሱ አሸባሪነታቸውን ለማረጋገጥ በአማራ ሕዝብ ላይ በተለይ በወሎና በጎንደር ሕዝብ ላይ ያወጁት ጦርነት ማሳያ ነው።

የወያኔን አምባገነንነትና ዘር አጥፊነት ለማሳየት የ27 ዓመቱ ድርጊታቸው በቂ ነበር። ስለዚህ መንግሥት እያሳየው ያለው ለዘብተኝነት ተገቢ አይደለም። ወያኔዎች በዲፕሎማሲ የሚያምኑ አይደሉም። ደረቅና ግትር ብለው በጋርዮሽ ሥርዓት ለማሸነፍ የሚሞክሩ ናቸው። አሁንም ቢሆን እየሄዱበት ያለው መንገድ የድሮው አይነት ነው። ማነው አሁን በጠመንጃ አፈሙዝ ተሸንፎ ነገ ሲገዙት ዝም የሚል? ትላንት ከደርግ ይሻላሉ ብሎ ገምቶ ነበር ሕዝቡ 4ኪሎ ሲገቡ ዝም ያላቸው። ዛሬ ግን አልጋ ባልጋ አይሆንላቸውም።

ህወሓቶችን ያጎለመሳቸውና ቦታ የሰጣቸው መንግሥት ነው። እነሱ ቦታ ሊሰጣቸው የማይገባ ምንም ነበሩ። በ15 ቀን የተደመሰሱትን ከ8 ወር ቆይታ በኋላ ከሞት እንዲነሱ ያደረገው የመንግሥት ተግባር ነው። ለእነሱ አሁን ትንሳኤ ነው የሆነላቸው። ሙቶ አብቅቶለት የነበረውን ሥርዓት እንደገና ከመቃብር አስነስቶ እንዲዋጉን ተደርጓል። አሁን የምንዋጋው ከሙት መንፈስ ጋር ነው። ጀሌዎቻቸው ሲመጡ መከላከያ ጥሎ ይወጣል፤ እነሱ መሣሪያውን አንስተው ይታጠቃሉ፤ ከዚያም በአካባቢው ያገኙትን ያጠፋሉ። አሁን የገጠመን ነገር ይህ ነው።

ህወሓቶች ሰሜን ወሎን አልፈው እስከ ደቡብ ወሎ መግቢያ ለመድረስ ያበቃቸው ምንድን ነው ይላሉ?
የህወሓቶች ወረራ የተፈቀደ ነው የሚመስለው። አንደኛ መከላከያ መረጃ አጥቶ ነው ለማለት አይቻልም። መረጃውን እኛም ጭምር እየሰጠን መንገዳቸውን መዝጋት ሲገባው ቦታውን ይለቃል። በዚህ መንገድ ቁልፍ ወታደራዊ ቦታዎችን ህወሓቶች እየያዙ ነው የደረሱበት ለመግባት የበቁት። የተመቻቸላቸውን መልካም አጋጣሚ ተጠቅመው መቄትን ከመሳሰሉ ቦታዎችም አልፈው መሔድ ነበር ሐሳባቸው። በአጠቃላይ ለእኔ ወረራው የተፈቀደ ነው።

እንደወልዲያ ነዋሪነቴ ከሕዝቡ ጋር የቻልነውን ሞክረናል። ከመከላከያው፣ ከልዩ ኃይል፣ ከሚሊሻውም ሆነ ከየትኛውም ሕዝባዊ ሠራዊት ጋር ቆመናል። አሁንም ለኢትዮጵያ ዘብ ከሚቆም ጎን እንቆማለን። አቅማችን ስንቅ የማቀበል ሞራልና ድጋፍ የመስጠት ነው።
ህወሓትን ለመዋጋት የሕዝብ ድጋፍና ደጀን ሳያጣ ሠራዊቱ ለመዋጋት ለምንድን ነው የሚምለሸለሸው? ለምንድን ነው ወደ ኋላ የሚያፈገፍገው? ይህን በመጠየቅ መከላከያው ውስጡን ይፈትሽ እንጂ ሕዝባዊ ደጀንነት እስካሁን አልተነፈገውም። ለእኔ እየሆነ ያለው ፖለቲካዊ አሻጥር ያለው ነው። አንዳንዶች እየሆነ ያለው አልገባኝም ሲሉ ቢሰማም፣ እኔ ተረድቸዋሁ። ለኔ የገባኝ ነገር ቢኖር ቀብድ እንድንያዝ እንደተደረግን ነው። ይህ አይነት ፖለቲካ ያለፈበት ያረጀ ነው። ገና ለገና ነጭ ያምነኛል ተብሎ የገዛ አገርን ዜጋ መክዳት የለበትም።
ለትግራይ ገበሬ ፋታ ይሰጥ በሚል እነሱ እንዲያርሱ ተብሎ፣ እንዲያ ለም የሆነ የራያ መሬት ሳይታረስ መቅረት አልነበረበትም። የትግራይ ገበሬ እንዲያርስ ተብሎ የአማራ ገበሬ መፈናቀል አለበት እንዴ? እውነታው ይህ ነው። ለትግራይ ገበሬ ተብሎ ከሆነ እዚያው ላይ መቆም ነበረበት። ማሳየት የተፈለገውን ነገር እዚያው ትግራይ ላይ ማሳየት ይቻል ነበር። በተሰጠው ተኩስ አቁም ወቅት ገበሬው እንዳያርስ ሲያደርጉት ማሳየትም ይቻል ነበር። እርዳታ እንዳይሰጥ ሲያደርጉ፣ ሕዝብ ላይ እንቅፋት ሲሆኑ ለማሳየት ይቻል ነበር። የእነሱን ግፍ ለምን አማራ ክልል ላይ ለማሳየት ተፈለገ? መከላከያው መቀሌ ላይ ቁጭ ብሎ የዲፕሎማሲ ብልጫውን መያዝ ይችል ነበር። ሌላውን አካባቢ ለቆላቸው የተወሰኑ አካባቢዎች በካምፕ መቆየት ይችል ነበር። ከዚህ ውጭ ስትራቴጂ እያሉ እየሸሹ አላማጣን፣ ቆቦንና መርሳን የመሳሰሉ ቦታዎችን መልቀቅ ለዲፕሎማሲ ነው መባሉን አልቀበለውም።

ጦርነቱ አውዳሚ ነበር። ብዙ ከተሞች ትግራይም አማራ ክልልም ወድመዋል። በአጠቃላይ ተኩስ አቁም ውሳኔው ለእኔ ስህተት ነው። መንግሥት ተጸፅቶ ሕዝብን ይቅርታ ሊጠይቅ ይገባል። አማራ ክልል እንዳይገቡ አድርጎ ለማስቆም አቅሙ ነበረው። ጦሩ ማጥቃት ቢከለከል እንኳን መከላከል ይችላል እኮ። ህወሓትና መከላከያ ያላቸው የጦር መሳሪያ ያለው ልዩነት የትየለሌ ነው። ህወሓት እየጎለበተች የመጣችው መከላከያ መሳሪያውን ጥሎ እየተዝረከረከ ቦታውንም እየተወላት ስለመጣ ነው።

የህወሓት ታጣቂዎች ከንፁሀኑ ጋር እየተቀላቀሉ ስላስቸገሩ ወደ አማራ ክልል ስቦ ለይቶ ለማስቀረት ታስቦ ነው የሚሉ አሉ። በዚህ ላይ ያሎት አስተያየት ምንድን ነው?
ሊያጠቃ የፈለገ አካል ያለህበት ድረስ ስለሚመጣ ነው ከትግራይ መከላከያው መውጣት አልነበረበትም የምለው። ተኩስ አቁሙ ተደርጎ ካምፕ መስርቶ እዛው ቢቀመጥ በሲቪልም ቢመጡበት እርምጃ መውሰድ ይችሉ ነበር። እንደ ኮማንድ ፖስት ትዕዛዝ የተከለከለ ቦታን አልፎ የመጣ ማንኛውም ሰው እናትም ብትሆን እርምጃ ሊወሰድባት ይገባል ተብሎ መቅረት ነበረባቸው። በዚህ አይነት መንገድ እዛው መለየት እየተቻለ ለምንድን ነው አማራ ክልል እንዲገቡ የፈቀዱላቸው። በዚህ መንገድ 4 ኪሎ እስኪገቡ መጠበቅ የለበትም። እዛው ቢጠብቁ ጉጅሌ እየሆኑ ይመጡላቸውና ለይተው ማጥፋት ይችሉ ነበር። የተሰራው ለእኔ ስህተት ነው። ብስለት የሌለው፣ ለሕዝብ የማያስብ ፣ግዴለሽ የሆነና ኃላፊነት የማጎደለው ውሳኔ ነበር።

ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ የሕብረተሰብ ክፍሎች አመለካከት ላይ ውሳኔው ምን ለውጥ አምጥቷል ይላሉ?
ከማንም በላይ የራያ ሕዝብ ነው የተካደው። “ልጅሽን አሞራ እንጂ አይቀብረውም ዘመድ” በሚባልባት አገር፣ የመከላከያውን አባላት ጉድጓድ ቆፍሮ ቀብሮ አርባውን ያወጣለትን ሕብረተሰብ ነው የከዳው። የወታደር ቤተሰብ የሚያምነው ወታደር ቀባሪ እንደማይኖረው ቢሆንም፣ ለአገር ሲሉ የወደቁትን በውጊያ ወቅት ከማንም በማይጠበቅ መልኩ የቀበረ ሕዝብ ነው እንዲህ አይነት ውለታ የተመለሰለት። አስከሬን ፈልጎ ቀብሮ 40ውንና ተስካር ላወጣ የራያ ሕዝብ ይህ አይገባውም ነበር። ሌላውን አካባቢ ትተን በራያ ሕዝብ ላይ የተሰራው ክህደት ሊታሰብም የማይገባ ነበር። በህወሓት ግፍ ደረሰባቸው ብሎ ወታደሮችን እንዲያ ተንከባክቦ ተቀብሎ በእንዲህ አይነት ሁኔታ ለህወሓት መተው አልነበረበትም። ለመከላከያ ብላ የድሃ መቀነቷን ፈታ ከአቅሟ በላይ ስታደርግ የነበረች እናት አሁን ስትንገላታ ማየት ሕሊና ያቆስላል፣ ያደማልም። የራያ ሕዝብ አሁን እየከናወተ ነው የሚገኘው።

ነሐሴ 4 የተኩስ አቁሙ እንደፈረሰ በመንግሥት የተሰጠውን መግለጫ እንዴት ያዩታል?
መጀመሪያ ደረጃ የተኩስ አቁም የተደረገው እስከዚህ እስኪደርስ ነበር ማለት ነው። ሕይወት እንዲጠፋ፣ ንብረት እንዲወድም፣ ሕዝብ እንዲፈናቀል ሲጠበቅ የነበር ነው የሚመስለው። ተኩስ አቁሙን መንግሥት ያቆመበት ራሱ ሽንፈት ነው። ሠራዊቱ ከትግራይ መውጣት ሳይኖርበት በመውጣቱ ብዙ ጉዳት ራሱም ላይ ደርሶበታል። ብዙዎች ተማርከዋል፣ በጥም ያለቁም አሉ፤ የደረሰባቸው እንግልት ብዙ ነው። ከዚህ ሁሉ በኋላ ተኩስ አቁም ሥምምነቱ ፈረሰ ተባለ። ለምን ፈረሰ? ተብሎ መጠየቅ ያለበት መንግሥት ነው። እንደእኔ መንግሥት ካሰበው ውጤት በላይ ኪሳራ ስለደረሰበት ነው። አሁንም ቢሆን እየተንገላቱ ያሉ ሕፃናትና አቅመ-ደካሞች ስላሉ በሚያሳዝን ሁኔታ ትተናቸው የመጣናቸውን እናቶች መንግሥትም ሆነ ዓለም ዐቀፉ ማኅበረሰብ ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል። ተኩስ አቁም ተደረገ አልተደረገ ለእኛ ምናችንም አይደለም። የሞት ሽረት ትግል ልናደርግ ነው። ከዚህ በኋላ ምን እንዳይመጣብን ነው። ተፈናቅለናል፤ ንጹኃን ሞተውብናል፤ እናቶች ተንገላተውብናል፤ እርሻም አልታረሰም። ከዚህ በኋላ በአካባቢያችን ላይ ትልቅ ሰብዓዊ ቀውስ ይደርሳል።

እኛ ከወያኔ አናንስም። ትጥቅ ያለው “እንግባ” ሲል፣ “አትግቡ” ይባላል። ያልታጠቀው ደግሞ ጀሌ ነው፤ ምን እናድርግ? የገጠመን ነገር እኮ ፈተና ነው። ምንም ይሁን ምን እኛ ቆርጠን ተነስተናል። ተኩስ አቁሙ ኖረም አልኖረም፣ የማይቀረውን ትግል ለማድረግ ተዘጋጅተናል። ከነገ ጀምረን ወደአካባቢያችን እንመለሳለን። አሁን በአጋጣሚ እኔና የአካባቢው ነዋሪዎች ተፈናቅለን ደሴ እንገኛለን። የቻለ ያግዘን ያልቻለ ደግሞ ዝም ይበለን።

ከህወሓት ጋር በነበረ ፍልሚያ የስልክ ኔትወርክ መቋረጥ ጉዳት እያደረሰ ነው ስለሚባለው የሚነግሩን አለ?
ህወሓቶች ግንኙነታቸው በሳተላይት ነው። እኛ ግን ያለን አማራጭ መደበኛው ስልካችን ነው። መንግሥት ብዙ ጊዜ የሚሸወደው ጠላት በደረሰበት አካባቢ ኔትወርክ እያቋረጠ ነው። የእነሱን የኢትዮጵያ ቴሌኮም መቆጣጠር አይችልም። በዚህ ምክንያት የእኛ ብቻ ግንኙነት ይቋረጣል። መቋረጡ የሚጎዳው ሕዝቡን ብቻ ስለሆነ ሊታሰብበት ይገባል። በዚህ ምክንያት ስለተጠፋፋን ብዙ ጓደኞቻችንን ጥለን ለመምጣት ተገደናል። ከዚህ በኋላ ጠላት ያቋርጠው እንጂ ራሱ መንግሥት ለምን ያቋርጣል።

ስንቅና ትጥቅን በተመለከተ ለተዋጊው የሚቀርበው አጥሯል ይባላል። ለተፈናቃዮችም በቂ እርዳታ እየቀረበ አይደለም መባሉን እንዴት ያዩታል?
የተፈናቃይ ነገር ቅብብሎሽ ነው የሆነው። በመጀመሪያ ከኦሮሚያ የመጡ ተፈናቃዮችን ተቀብለን ነበር። አሁን ከአላማጣ የመጡ ተፈናቃዮችን ቆቦ ተቀበለ። ከቆቦም ነዋሪውን ጨምረው ሲፈናቀሉ ወልዲያ ተቀበለ። ቀጥሎ ከወልዲያ የተፈናቀልነውን እኛን ጨምሮ ደሴ ተቀበለ። ከዛም አልፎ መገስገሱ አይቀርም ተብሎ ዘመድ ያለው ወደ አዲስ አበባ እየተጠጋ ነው። ደሴ የገቡና ትምህርት ቤት የተጠለሉ ከሰሜን ወሎ ከዋግ፣ ከራያ፣ ከመርሳና ሐራ አካባቢ የመጡ ናቸው። ለማየት እንደሞከርነው የተወሰኑት ትምህርት ቤት ተጠልለዋል። አቅም አለን ያሉት ቤት እየተከራዩም ሆነ በሆቴል ለመቆየት ሞክረዋል። ያልቻሉ ደግሞ በረንዳ ለማደር እየተገደዱ ነው።

ወልዲያ በነበሩበት ሁኔታ ሰው ባለው አቅም እየተረባረበ ሲረዳቸው ነበር። ምግብ ብቻ ሳይሆን አቅሙ እንደፈቀደለት የሚለበስም ሲለግስ ነበር። የደሴው ግን በጣም ያሳዝናሉ። የሚያርፉበት ምንጣፍ እንኳን በሌለበት ሁኔታ ነው ለማረፍ የተገደዱት። ምግብ ሲቀርብ እንኳን መመገቢያ እየጠፋ ፌስታል ተዘርግቶ ሲበሉ ተመልክቻለሁ። ይህ ስሜትን በጣም ይጎዳል።

ወልዲያን በተመለከተ ራሳችን ያዋጣነውን ለሠራዊቱ ከምናቀርበው ኮቾሮ ላይ ነው እንዲዳረስ ስናደርግ የነበረው። የምግብ ዋስትና ኃላፊው መጥተው ስለነበር፣ ከነበረበት እስቴዲየም ዱቄትና ኮቾሮ እንዲወጣ ተደርጎ አከፋፍለናል። ከዚህ ሌላ ማሕበረሰቡ የሚችለውን ያህል አድርጓል።

ደሀ አገር መሆናችን ቢታወቅም፣ ከ2010 ጀምሮ መፈናቀል በዝቶብናል። በሚሊዮን የሚቆጠር ተፈናቅሎ አሁንም እየቀጠለ ነው። ተፈናቃይ ስናስተናግድ እንዳልነበር ራሳችን አሁን ተፈናቃይ ሆነናል። የሚያናድደው መፈናቀላችን ወይም አለመረዳታችን አይደለም፤ ምን እናድርግ ብለው ደውለው ሲጠይቁ ነው። ተፈናቃይ ምንም ስለማይኖረው ልብስም፣ ምግብም፣ መጠለያም፣ መመገቢያ ቁሳቁስና ማብሰያም ይፈልጋል። ከመጠየቅ ከግብረ ሰናይ ተቋማት ጋር ተነጋግሮ የሚቻለውን ጊዜ ሳይሰጡ ማድረግ ነው።

ወልዲያ በነበርኩ ሰዓት ወደ 150 ሺሕ ተፈናቃይ ነበር። አሁን ወልዲያን ጨምሮ መርሳና አካባቢው ሲፈናቀል የሰሜን ወሎው ከ500 ሺሕ በላይ ይሆናል። መፈናቀሉ ያን ያህል አያሳስብም። ድል አድርገን መመለሳችን አይቀርም። ዋናው የሚያሳስበው እርሻው አለመታረሱ ነው። በዚህ ምክንያት ቢያንስ ለአንድ ዓመት ሕብረተሰቡ በረሀብ ችግር ላይ ስለሚወድቅ አስቀድሞ የመከላከል ሥራ መሠራት አለበት።

ደሴ ተፈናቃዮች ከመብዛታቸው አኳያ የሸቀጦችና የአገልግሎት ዋጋዎች በብዙ እጥፍ መጨመራቸውን የሚናገሩ አሉ። እንደ እርሶ አስተያየት ምን መደረግ አለበት?
ደሴ ላይ እኔ ራሴ ያየሁት በጣም አሳዛኝ ነው። ሰው በራሱ የማይደርስ እየመሰለው ተገደው ከተፈናቀሉ ላይ አላግባብ ለመጠቀም ይፈልጋል። ዋጋ ማስናሩን ደሴ ላይ እንጂ ሌላ ቦታ አላየሁም። ሽሮ ከ100 ብር በላይ ተሸጧል። የሆቴል አልጋም ሆነ ቤት ኪራይ አላግባብ ጨምሯል። መቆጣጠር ያለበት ንግድ ቢሮ ነው። እንዲህ በሚያደርጉት ላይ ክትትል አድርጎ እርምጃ መወሰድ አለበት። እነዚህ ሰዎች ተግባራቸው ከህወሓቶች ተለይቶ መታየት የለበትም። ይህ የእነሱ አንዱ የትግል ስልት ነው። ሕዝቡን ማስመረርና ማሰደድ ወይም ያለውን ሲጨርስ በረሀብ መፍጀት የእነሱ ፍላጎት ነው።

በዚህ አጋጣሚ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ትኩረቱን ወረራ ወደተደረገበት አካባቢ እንዲያደርግ እጠይቃለሁ። አቅም የሌላቸው ብዙዎች ሞታቸውን በቤታቸው እየጠበቁ ስለሆነ ለምስኪኖቹ እንድናዝን ጥሪ አቀርባለሁ። እንዲህ አይነት መከራና ስደት በገዛ አገራችን ላይ ነው እየተፈፀመብን ያለው። ይህን ያደረሰብንን አካል በጋራ እናውግዝና ተፋልመን እንጣለው።


ቅጽ 3 ቁጥር 145 ነሐሴ 8 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!