የእለት ዜና

የከሸፈው የተኩስ አቁም እና አዲሱ አቅጣጫ

በፌደራል መንግሥት እና በሽብርተኝነት በተፈረጀው ህወሓት መካከል ለስምንት ወራት የዘለቀው ጦርነት፣ የፌደራል መንግሥት ሰኔ 21/2013 የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ ከትግራይ ክልል መውጣቱን ተከትሎ በብዙዎች ዘንድ ይመጣል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት የሠላም ጭላንጭል በህወሓት በኩል ተኩስ አቁሙ ተቀባይነት ባለማግኘቱ ከሽፏል።
የተናጠል ተኩስ አቁም መታወጁን ተከትሎ መንግሥት የመሠረተውን የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር እና በክልሉ አሰማርቶት የነበረውን የመከላከያ ሠራዊት ከትግራይ አስወጥቷል። ህወሓትም በተኩስ አቁሙ የተገኘውን አጋጣሚ ተጠቅሞ ከ15 ቀን ብኋላ በአማራ እና አፋር ክልል ላይ ጥቃት መጀመሩ የሚታወስ ነው።
በጥቃቱ በአፋር ክልል ከ240 በላይ ሰዎች ሲገደሉ፣ ከኹለቱም ክልሎች ከ300 ሺሕ በላይ ዜጎች ተፈናቅለዋል።በሽብርተኛነት የተፈረጀው ህወሓት ጥቃት በፈጸመባቸው የኹለቱ ክልሎች ቀላል የማይባል የሕይወት መስዋዕትና የንብረት ኪሳራ ድርሷል።
ሽብርተኛ የተባለው ቡድን በኹለቱ ክልሎች የሚደርሰውን ጥቃት አጠናክሮ መቀጠሉን ተከትሎ የፌደራል መንግሥት ባሰላፍነው ሳምንት የአገር መከላከያ ሠራዊት፣ የክልል ልዩ ኃይሎችና ሚሊሻዎች በህወሓት ላይ “የማያዳግም አርምጃ” እንዲወስዱ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
መንግሥት ያስተላለፈው “የማያዳግም እርምጃ” ከዚህ በፊት የተፈጠሩ ስህተቶችን የሚያርም እንዲሆን እና የተራዘመ ጦርነነት እንዳያስከትል በፍጥነት መጠናቀቅ እንዳበለት የወታደራዊና የፖለቲካ ባለሙያዎች ጠቁመዋሉ። የአዲስ ማለዳው መርሻ ጥሩነህ የባለሙያዎችን ሐሳብ አካቶ የሐተታ ዘ ማለደ ርዕሰ ጉዳይ አድርጎታል።

ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት የዜጎቿን ደህንነት ስጋት ላይ በሚጥል ችግር ውስጥ ትገኛለች። ይሄውም በትግራይ ክልል የተጀመረው ጦርነት ከጊዜ ወደ ጊዜ መልኩን እየቀያየረ መስፋፋቱ ነው። በፌደራል መንግሥትና በሽብርተኝነት በተፈረጀው ህወሓት መካከል ጥቅምት 24/2013 የተጀመረው ጦርነት ለስምንት ወራት በትግራይ ክልል ተገድቦ ቢቆይም አሁን ላይ ወደ አማራ እና አፋር ክልል ሰፍቷል።

በፌደራል መንግሥት እና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት በተፈረጀው ህወሓት መካከል በሕግ ማስከበር ዘመቻ ስም ጦርነት የተጀመረው፣ ጥቅምት 24/2013 ሽብርተኛ ቡድኑ መቀመጫውን መቀሌ ባደረገው የኢትዮጵያ መካላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መስንዘሩን ተከትሎ ነበር። በሕግ ማስከበር ዘመቻ ጥቅምት 24 ተጀምሮ ወደ ጦርነት ባደገውና ለስምንት ወራት በዘለቀው የትግራይ ክልል ጦርነት ሒደትም የፌደራል መንግሥት ጊዜያዊ አስተዳደር አቋቁሞ ክልሉን ለተወሰኑ ወራት ለማስተዳደር መሞከሩ የሚታወስ ነው።
ይሁን እንጅ የፌደራል መንግሥት ለስምንት ወራት ከህወሓት ጋር አንድ ጊዜ በሚሞቅ አንድ ጊዜ በሚቀዘቅዝ ጦርነት ውስጥ ካሳለፈ በኋላ፣ የተናጠል የተኩስ አቁም አውጆ የመሠረተውን ጊዜያዊ አስተዳደርና መከላከያ ሠራዊቱን ሰኔ 21/2013 ከትግራይ አስወጥቷል።
በፌደራል መንግሥትና በህወሓት መካከል የኃይል ፍልሚያው በግልጽ ከተጀመረበት ከጥቅምት 24/2013 አንስቶ እስከ ሰኔ 20/2013 ባሉት ጊዜያት ድረስ ውስጥ የተከናወነው ውጊያ ከሰው ሕይወት ህልፈት፣ አካል ጉዳትና ሥነ-ልቦናዊ ቀውስ ባሻገር ከፍተኛ የሀብት ብክነት ያስከተለ እንደነበር መገለጹ የሚታወስ ነው።

የፌደራል መንግሥት ትግራይ በቆየባቸው ስምንት ወራት ወታደራዊ ወጪን ሳይጨምር ለተለያዩ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች እና ለቀለብ ብቻ ከ100 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጉን መግለጹ የሚታወስ ነው።
በፌደራል መንግሥት የታወጀው የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔ፣ በወቅቱ ከአገር ውስጥ አስከ ዓለም ዐቀፍ ባሉ ተቋማት አድናቆት የተቸረውና ለትግራይ ችግር አዲስ የሠላም መንገድ ይከስታል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ነበር። ይሁን እንጅ ተስፋ ተጥሎበት የነበረው የተናጠል ተኩስ አቁም በህወሓት በኩል ተቀባይነት አላገኘም።

በዚህም በሽብርተኝንት የተፈረጀው ህወሓት መንግሥት ክልሉን ለቆ መውጣቱን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም እራሱን አደራጅቶ ተስፋ የተጣለበትን የተናጠል ተኩስ አቁም ውጤት አልባ እንዳደረገው ብዙዎች ይገልጻሉ። ህወሓት የተናጠል ተኩስ አቁሙን እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅሞ ከ15 ቀናት በኋላ በአማራ እና አፋር ክልሎች ላይ ጥቃት መክፈቱ የሚታወስ ነው።

ህወሓት በኹለቱ ክልሎች ላይ ጥቃት እየፈጸመ ባለበት ወቅት፣ በተለይም ለትግራይ አዋሳኝ በሆኑ የአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን አካቢዎች የተጠናከረ ጥቃት ሲፈጽም፣ የፈደራል መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም ላይ ነኝ ማለቱ የሚታወስ ነው።
በአማራ እና በአፋር ክልል በሽብርተኝንት የተፈረጀው ህወሓት ጥቃት መፈጸሙን ተከትሎ የአማራ ክልል መንግሥት “የክተት አዋጅ” ማወጁም የሚታወስ ነው። አፋር ክልል ቢሆንም በክልሉ ልዩ ኃይል ከጥቃቱ እራሱን ለመካከል ሲሞክር ነበር። ይሁን እንጅ የህወሓት ጥቃት በኹለቱም ክልሎች ተጠናክሮ መቀጠሉ ይታወቃል።
የተናጠል ተኩስ አቁም ክሽፈት

የፌደራሉ መንግሥት ሰኔ 21/2013 በትግራይ ክልል ላይ የወሰነው የተናጠል ተኩስ አቁም ብዙ ተስፋ ተጥሎበት የነበረ ቢሆንም፣ የተጠበቀውን ውጤት ሳያመጣ ቀርቷል።
ከዚያ ይልቅ የተናጥል የተኩስ አቁም ውሳኔው እና የመከላከያ ሠራዊት ትግራይን ለቆ መውጣቱ ለህወሓት የዝግጅት ጊዜ እንደሰጠው የመከላከያ ባለሙያዎች ይናገራሉ። ህወሓት ለ15 ቀን ዝግጅት ካደረገ በኋላ በአማራ ክልልና በአፋር ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ጥቃት መፈጸሙን የኹለቱ ክልልና የፌደራሉ መንግሥት መግለጻቸው የሚታወስ ነው።

የአማራ ክልል መንግሥት የክተት አዋጅ ጥሪ ያስተላለፈው ይህንኑ በሽብርተኝንት የተፈረጀውን ህወሓትን ጥቃት ተከትሎ ሲሆን፣ ጥቃቱን ለመመከት የተደራጀ ኃይል እንደሚያስፈልግ በማመኑ መሆኑን መግለጹ የሚታወስ ነው። የክተት አዋጅ ጥሪውን ያስተላለፉት የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አገኘሁ ተሻገር ሲሆኑ፣ በክተት አዋጅ ጥሪያቸው ላይ “በክልሉ ውስጥ ማንኛውም የመንግሥትን መሳሪያ የታጠቀ፣ የግል መሳሪያ የታጠቀ፣ ለግዳጅ ብቁ የሆነ ወጣት ይክተት” ብለው ነበር።

ህወሓት በተለያዩ ግንባሮች በክልሉ ላይ ጥቃት እየፈጸመ መሆኑን በመግለጽ ሕዝቡ ተደራጅቶ እንዲመክት ጥሪ ማስተላለፋቸው የሚታወስ ነው። ርዕሰ መስተዳድሩ በክተት አዋጅ ጥሪያቸው “ከተሠለፈብን ጠላት አኳያ ብዙ ኃይል የምናሰልፍበትና ሎጅስቲክስ የሚያስፈልግበት ወቅት ነው” ማለታቸው የሚታወስ ነው።

የክልሉን የክተት አዋጅ ተከትሎ ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጣ ልዩ ኃይል ወደ ሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ማቅናቱ ይታወሳል። ይሁን እንጅ ህወሓት ከዕለት እለት የማጥቃት ሥራውን በማጠናከር በአፋርና በአማራ ክልል ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል።
በዚህም ሽብርተኛው የህወሓት ቡድን በአፋር ክልል ሕፃናትን ጨምሮ 240 ሰዎችን መግደሉን ዩኒሴፍ ገልጿል። በጤና ጣቢያ ውስጥ ተጠልለው በነበሩ ንጹሐን ላይ የህወሓት ታጣቂዎች በፈጸሙት ጥቃት ከ200 በላይ የሚሆኑት አፋሮች መጨፍጨፋቸውን የገለጸው ዩኒሴፍ፣ ከእነዚህም መከላል ከ100 በላይ የሚሆኑት ሕፃናት ናቸው ብሏል። በክልሉ ከንጹሐን ሰዎች ግድያ በተጨማሪ ህወሓት ለ30 ሺሕ ሰዎች የሚበቃ እርዳታ በከባድ መሳሪያ ማውደሙ ተነግሯል።

ህወሓት ለትግራይ አዋሳኝ በሆኑ የአማራ ክልል ሰሜን ወሎ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች ላይ ጥቃት ፈጽሟል። በዚህም ከፍተኛ የሰብዓዊ ቀውስ የተፈጠረ ሲሆን፣ ሽብርተኛ ቡድኑ በደረሰባቸው እንደ ራያ ቆቦ ባሉ አከባቢ በሚገኙ ኗሪዎች ላይ አስከፊ የሚባል የበቀል ግድያና ንብረት ዘረፋ እንዳካሄደ አዲስ ማለዳ ኗሪዎችን አነጋግራ መዘገቧ የሚታወስ ነው።

በሽብርተኝነት የተፈረጀው ህወሓት፣ በአማራ ክልል በደረሰባቸው አከባቢዎች ካደረሳቸው ጥቃቶችና መፈናቀሎች በተጨማሪ ነሐሴ 2/2013 ወልዲያ ከተማ ላይ የከባድ መሳሪያ ጥቃት መሰንዘሩ የሚታወስ ነው።
ወታደራዊ ባለሙያዎች እንደሚሉት ከሆነ፣ የፌደራል መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም ዐውጆ መልቀቅ የሌለበትን ቦታ መልቀቁ አሁን ለተፈጠረው ችግር መንስኤ እንደሆነ ይናገራሉ። ከአዲስ ማለዳ ጋር ቆይታ ያደረጉት ወታደራዊ ባለሙያው ሻለቃ ታመነ አባተ፣ “መከላከያ መጠበቅ ያለበትን አካባቢ ትቶ መውጣቱ፣ አሁን የሚታየውን መስዋዕትንት እያስከፈለ ነው” ይላሉ።

በወታደራዊ ሳይንስ የተናጠል ተኩስ አቁም ሲደረግ ስለ ወደፊት ኹኔታዎች ቀድሞ ምቹ ኹናቴ መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን የሚገልጹት ሻለቃ ታመነ፣ የፌደራል መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም አድርጎ ከትግራይ ሲወጣ መጠበቅ የሚገባውን አካባቢ ለመጠበቅ በሚያስችለው ቦታ ላይ መቀመጥ እንደነበረበት ተናግረዋል።

ይሁን እንጅ መከላከያ ከትግራይ ክልል ሲወጣ መጠበቅ ያለበትን አካባቢዎች አልፎ መሄዱ በአማራ እና በአፋር ክልል አሁን ህወሓት ላደረሰው ጥቃት በር መክፈቱን ተናግረዋል። “በምንም ኹኔታ መከላከያ ከተሞችን እና መጠበቅ ያለበትን ሕዝብ አልፎ መሔዱ ለህወሓት በር መክፈት ካልሆነ ትክክል አይደለም” ብለዋል።

የፖለቲካ ሰዎች በበኩላቸው፣ የፌደራል መንግሥት መጠበቅ ያለበትን አከባቢዎች ትቶ መንቀሳቀሱ ለህወሓት ድፍረት የሰጠ እንደሆነ ይገልጻሉ። መንግሥት የተናጠል ተኩስ ማድረጉም ዓለም ዐቀፉ ተጽዕኖ ወደ ህወሓት ይገለበጣል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበት እንደነበር የሚታወስ ነው።

መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ ትግራይን ለቆ ሲወጣና ህወሓት ማጥቃት ሲጀምር መከላከያ ምላሽ ባለመስጠቱ በኹለቱ ክልሎች ላይ ጥቃቱ ተጠናክሮ መቀጠሉን የእናት ፓርቲ ዋና ጸሐፊ ጌትነት ወርቁ ከአዲስ ማለዳ ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል።
“መከላከያ በርካታ አካባቢዎችን የማሪያም መንገድ ለህወሓት ሰጥቷል” የሚሉት ፖለቲከኛው፣ ምንም ያክል ዓለም ዐቀፍ ጫና በመንግሥት ላይ ቢኖርም ገና ለገናው ጫናው ወደ ህወሓት ይገለበጣል ተብሎ ሕዝብን መስዋዕት አድርጎ ዋጋ ማስከፈል ተገቢ እንዳልሆነ ጠቁመዋል።
መንግሥት መካለከያን ከትግራይ ሲያስወጣ እና ህወሓት ተዘጋጅቶ በአማራ እና በአፋር ክልል ጥቃት ሲጀምር የሚከላከለው አካል ባለመኖሩ ጥቃቱን በማስፋፋት በየደረሰበት አካባቢ ከፍተኛ የበቀል ጥቃት መፈጸሙን ፖለቲከኛው ይናገራሉ። መንግሥት ህወሓት ክልሎችን ማጥቃት ሲጀምር ዝም ከተባለ ቀላል የማይባል የበቀል ግፍ እንደሚፈጽም እያወቀ እየገፉ ከተሞችን ሲቀጣጠሩ ዝም ያለበት ሁኔታ ስህተት መሆኑን ጌትነት ጠቁመዋል።

አያይዘውም ህወሓት በኹለቱ ክልሎች ላይ የሚያደርሰውን ጥቃት አጠናክሮ ሲቀጥል የፌደራል መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም ላይ ነኝ በማለት ሕዝብ ሲፈናቀልና ሲሞት ዝም ማለቱ፣ ለሽብርተኛው ቡድን ያልተፈለገ ድፍረት የሰጠ መሆኑን ጠቁመዋል።
ወታደራዊ ባለሙያው በበኩላቸው፣ ህወሓት ጥቃቱን አጠናክሮ ሲቀጥል መንግሥት ሕዝቡን ከጥቃት ከመታደግ ይልቅ ሕዝቡን ትቶ ወደ ኋላ በመሸሹ ተገቢ ያልሆነ መስዋዕትነት ዜጎችን አስከፍሏል ይላሉ። ባለሙያው መንግሥት ሕዝብን ለጥቃት አጋልጦ የተናጠል ተኩስ አቁም አውጃለሁ ብሎ ከተቀመጠ መጀመሪያውኑ የጀመረው የሕግ ማሰከበር እርምጃ አስፈላጊ አልነበረም ይላሉ።

“የማያዳግም እርምጃ” እና ከስህተት መማር
ህወሓት በኹለቱ ክልሎች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት አጠናክሮ መቀጠሉን ተከትሎ የፌደራል መንግሥት ባሳለፍነው ሳምንት የአገር መከላከያ፣ የክልል ልዩ ኃይልሎች እና ሚሊሻዎች በቡድኑ ላይ የማያዳግም እርምጃ እንዲወስዱ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
መንግሥት የሰጠው የትዕዛዝ መግለጫ ዕድሜያቸውና ዓቅማቸው የሚፈቅድላቸው ኢትዮጵያውያን ኹሉ በአገር መከላከል ዘመቻው እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርቧል። ህወሓት በኹለቱ ክልሎች ባደረሰው ጥቃት ከ300 ሺሕ በላይ ዜጎች እንደተፈናቀሉም ጠቅሷል።
አዲስ ማለዳ ያነጋገረቻቸው ወታደራዊ እና ፖለቲካዊ ባለሙያዎች የፌደራል መንግሥት በትግራይ ክልል ለስምንት ወራት በዘለቀው ቆይታው እንዲሁ አሁን ከስህተቱ መማር እንዳለበት ጠቁመዋል።

ወታደራዊ ባለሙያው ሻለቃ ታመነ እንደሚሉት ከሆነ፣ መንግሥት ከዚህ በፊት ከፈጸማቸው ስህተቶች በመማር፣ ዳግም የጀመረውን የሕግ ማስከበር ዕርምጃ በተቀላጠፈ መልኩ በፍጥነት ማጠናቀቅ አለበት። መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁሙን አንስቶ ዳግም ወደ ማጥቃት ከገባ በተቃራኒ ለቆመው ኃይል ፋታ ሊሰጥ የማይችል ተደጋጋሚ ጥቃት በማድረግ በአጭር ጊዜ ማጠናቀቅ አለበት ብለዋል።

ከተማ ማስለቀቀ ወታደራዊ ግብ አይደለም የሚሉት ወታደራዊ ባለሙያው፣ መንግሥት የገባበትን ጦርነት ሊፋጽም በሚያስችል ጥቃት ካላጠናቀቀ በተቃራኒ ለቆመው ኃይል ሌላ ተጨማሪ ዕድል ሊፈጥር እንደሚችል ጠቁመዋል።
ፖለቲከኛው ጌትነት በበኩላቸው፣ መንግሥት አሁን የጀመረውን “የማያዳግም” ያለውን ዕርምጃ ከባለፈው ስህተቱ በመማር የተራዘመ ጦርንት እንዳይሆን ማድረግ እንዳለበት ጠቁመዋል። በሽብርተኝንት የተፈረጀው ህወሓት ከውጭ ኃይሎች ጋር የሚገናኝበት ቀዳዳ ካገኘ ኢትዮጵያን ሊያፈርሳት ይችላል የሚሉት ፖለቲከኛው፣ መንግሥት ለውጭ ኃይሎች በር የሚከፍቱ ኹኔታዎችን በጥንቃቄ መመልከት እንዳለበትም አክለዋል።

የፌደራል መንግሥት ህወሓት ላይ “የማያዳግም እርምጃ” እንዲወሰድ ትዕዛዝ በሰጠበት ማግስት በሕዝብ ተወካዮች በሽብርተኝንት የተፈረጀው ሌላው “ኦነግ ሸኔ” ተብሎ የሚጠራው ታጣቂ ኃይል በጥምረት ከመንግሥት ጋር ለመዋጋት ከህወሓት ጋር መስማማቱን ገልጿል።
በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን ለአዲስ ማለዳ የሰጡት ሻለቃ ታመነ፣ የህወሓትና የኦነግ ሸኔ ግንኙነት አሁን የተጀመረ እንዳልሆነ ይናገራሉ። ከሰሞኑ ጥምረት መፍጠራቸውን የገለጹት በሕዝቡ ዘንድ ስጋት ለመፍጠርና ለፕሮፖጋንዳ ትርፍ ነው የሚሉት ባለሙያው፣ ከመንግሥት እስከ ሕዝብ ድረስ ኹሉም የድርሻውን ከተወጣ ችግሩን ማለፍ እንደሚቻል ጠቁመዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 145 ነሐሴ 8 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!