የእለት ዜና

በምርጫው ተፎካክረን ኢትዮጵያ አሸንፋለች፤ አገር ለማዳን ሳንፎካከር በጋራ ቆመን እንመክታለን

በምርጫው ተፎካክረን ኢትዮጵያ አሸንፋለች። አገር ለማዳን ሳንፎካከር በጋራ ቆመን እንመክታለን ሲሉ የተፎካካሪ ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ተናገሩ።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) እና የእናት ፓርቲ ከፍተኛ ኃላፊዎች እንደገለጹት፣ በ6ኛው ጠቅላላ ምርጫ የነበረው ፉክክር ኢትዮጵያን አሸናፊ አድርጓል።
ኢትዮጵያን አሁን ለገጠማት የሕልውና አደጋ ደግሞ ውድድርና ፉክክር ሳይሆን የሚያስፈልገው በምክክር ጠላትን መመከት መሆኑን ገልጸዋል። በዚህም የየፓርቲያቸው አመራሮችና ደጋፊዎች አገር ለማዳን በጋራ በመቆም ለመመከት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል። የእናት ፓርቲ ዋና ጸሐፊ አቶ ጌትነት ወርቁ፣ ፓርቲያቸው አገርና ሕዝብን በማስቀደም ለምርጫው ሠላማዊነት መሥራቱን አስታውሰዋል።
በመሆኑም በቅድመ-ምርጫ፣ በምርጫና በድህረ-ምርጫ የጎላ ችግር አለመከሰቱ እንደ አገር መልካም የዴሞክራሲ ጅማሮ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም በድህረ-ምርጫ ከምርጫው ጋር በተገናኘ የተከሰተ ችግር ለአለመኖሩ ሕዝቡና የፖለቲካ ፓርቲዎች ትልቁን ድርሻ እንደሚወስዱ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያውያን ለአገራቸው ሠላም፣ ቀጣይነት፣ አንድነትና ሉዓላዊነት መከበር ኹሌም በአንድ የሚቆሙ በመሆናቸው፣ አገር በችግር ውስጥ ሆና በአንድ ሐሳብ ምርጫውን በሠላም ማከናወን መቻሉን ተናግረዋል።
በአጠቃላይ ምርጫው የኢትዮጵያ ጉዳይ በመሆኑ በሠላም ተጠናቆ አገር እንድታሸንፍ በጋራ በመሠራቱ በሠላም ተጠናቆ “ኢትዮጵያ አሸንፋለች!” ብለዋል።
የተከናወነው ምርጫ ለአፍሪካውያን ትምህርት ለቀጣይ ትውልድ ደግሞ ታሪክ ጥሎ ያለፈ መሆኑን ጠቅሰው፣ ከፖለቲካና ምርጫ በላይ ኢትዮጵያን በማስቀደም አሁን የገጠማትን ችግር ለመመከት ዝግጁ መሆናቸውንም አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያን አሁን ለገጠማት የሕልውና አደጋ ደግሞ ከመንግሥት ጎን በመሆን አስፈላጊውን እገዛና ድጋፍ እንደሚያደርጉም ገልጸዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 145 ነሐሴ 8 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com