የእለት ዜና

የሰኔ 14ቱ ምርጫና የዓለም ዐቀፍ ታዛቢዎች ሪፖርት

Views: 229

ሰኔ 14 ቀን 2013 የተደረገውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫን በተመለከተ ኢንተርናሽናል ሪፐብሊካን ኢንስቲትዩት (IRI) እና ናሽናል ዴሞክራቲክ ኢንስቲትዩት (NDI) የጋራ ሪፖርታቸውን አውጥተዋል። ሪፖርቱ የምርጫ ምህዳሩን የተመለከተ መጠነ ሠፊ ትንታኔ የሚያቀርብ ከመሆኑም በላይ፣ የኢትዮጵያን ምርጫ የመታዘብ ውስን ተልዕኮውን ከሚያዝያ ወር ጀምሮ ከርቀት ሲያከናውን የቆየውን ትንተና እና በአገር ውስጥ ያለውን ውስን የቴክኒክ ድጋፍ ግብዓት ያደረገ መሆኑን ገልጿል።

ኢትዮጵያ ሰኔ 14 ያደረገችው ምርጫ ወሳኝ ማሻሻያዎችን ተከትሎ የተደረገ ቢሆንም፣ ሠፊ የጸጥታ ችግሮች፣ ግልጽ ግጭቶች እና በምርጫው ምህዳር ውስጥ ሌሎች ከባድ ውስንነቶች የነበሩ በመሆኑ የነበረው ፖለቲካ ምህዳር፣ ተሳትፎ እና ፉክክር በከፍተኛ ሁኔታ የተገደበ ነበር በማለት ኹለቱ ተቋማት በጋራ ባወጡት ሪፖርቱ ላይ ጠቅሰዋል ።

የናሽናል ዴሞክራቲክ ኢንስቲትዩት ፕሬዝዳንት ዴሬክ ሚቼል፣ “ምንም እንኳን ከዚህ ቀደም ከነበሩት ምርጫዎች ጋር ሲነጻጸር፣ በተለይም ደግሞ ከብሔራዊው የምርጫ አካል እና በፖለቲካ ፓርቲዎች እና በሲቪሉ ማኅበረሰብ ከሚደረግ የምርጫ ክትትል ጋር በተያያዘ፣ ወሳኝ መሻሻሎች የነበሩበት ቢሆንም፣ ምህዳሩ ሲቪል ነጻነቶችን፣ ዕኩልነት የሰፈነባቸው የምርጫ ቅስቀሳ ኹኔታዎችን እና ጸጥታን የተመለከቱ አስፈላጊ ደረጃዎችን ያሟላ አልነበረም” ሲሉ በምርጫው ላይ አስተያታቸውን ሰጥተዋል። በተጨማሪም የኢንተርናሽናል ሪፐብሊካን ኢንስቲትዩት ፕሬዝዳንት የሆኑት ዳንኤል ትዋይኒንግ በበኩላቸው፣ “ምንም እንኳን በምርጫው ሒደት ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ያሳደሩ በርካታ ችግሮች የነበሩ ቢሆንም፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ቀጣዩ ጊዜ ጠንካራ በሆነ ዲሞክራሲያዊ አስተዳደር የሚመራበት እንዲሆን እንደሚፈልግ በግልጽ ያሳየበት ነበር” ብለዋል። በተጨማሪም “ኢትዮጵያዊያን አሁን ብሔራዊ ዕርቅን ለማምጣት እና ተጨማሪ ዲሞክራሲያዊ ማሻሻያዎችን ለማድረግ ተግተው መሥራት አለባቸው፤ ያለበለዚያ አሁን ያሉባቸው ተግዳሮቶች እንዳሉ ይቀጥላሉ” ብለዋል።
ሪፖርቱ በምርጫ ሒደቱ ላይ የተደረጉት ማሻሻያዎች ሲቪሉ ማኅበረሰብ እና የፖለቲካ ፓርቲዎች በምርጫው ሒደት ውስጥ ተዋንያን ሆነው ብቅ እንዲሉ ያስቻሉ ናቸው በማለት አወድሷል።

በዋነኛነት የተደረጉት ማሻሻያዎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይበልጥ ነጻ እንዲሆን፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን እና የዜጋ የምርጫ ክትትል እና የመራጮች ሥልጠና የሚያከናውኑ ቡድኖችን ጨምሮ በኢትዮጵያ የሚገኙ ግለሰቦች እና ተቋማት አዎንታዊ ሥራዎችን እንዲሠሩ ያስቻሉ እንደነበሩ ሪፖርቱ ያነሳል። ሆኖም ግን ለረጅም ጊዜ የቆዩ የብሔር እና የቋንቋ እንዲሁም የፖለቲካ ኃይል ክፍፍሎችን መሠረት ያደረጉ በስፋት የሚስተዋሉ የጸጥታ ችግሮች እና ግልጽ ግጭቶች፣ በምርጫ የመጫወቻ ሜዳው ላይ ያለው የሚዛን መዛባት፣ የፖለቲካ ሐሳብን ከመግለጽ አንጻር ወደኋላ ሸርተት የማለት ኹኔታዎች መከሰታቸው፣ ከሎጂስቲክስ ጋር የተያያዙ ተግዳሮቶች እና የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ያስከተላቸው ውጤቶች የፖለቲካ ምህዳሩ፣ ተሳትፎው እና ፉክክሩ ውሱን እንዲሆን እንዳደረጉ ሪፖርቱ ገልጿል።

ሪፖርቱን ለማውጣት የተሠራው ትንተና ከሚያዝያ 1 ጀምሮ እስከ ሐምሌ 8 ቀን 2013 ዓ.ም. ድረስ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከፍተኛ ተወካዮችን፣ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶችን፣ ሚዲያውን፣ የዜጋ የምርጫ ታዛቢዎችን እና የዲፕሎማሲውን ማኅበረሰብ ጨምሮ ከተለያዩ የምርጫ እና የፖለቲካ ባለድርሻ አካላት ጋር የተደረጉ ጥልቅ የበይነ መረብ ቃለ መጠይቆችን ግብዓት ያደረገ፣ እንዲሁም ኹለቱም ኢንስቲትዩቶች በኢትዮጵያ ላይ ያላቸውን ዕውቀት እና ግንኙነቶች መሠረት ያደረገ መሆኑ ተጠቅሷል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የጤና ቀውስ በፈጠራቸው ውሱንነቶች የተነሳ የኢትዮጵያን ምርጫ የመታዘብ ውሱን ተልዕኮው የተከናወነው ከዓለም ዐቀፍ ምርጫ የመታዘብ መርሆዎች (Declaration of Principles for International Election Observation) እና ከኢትዮጵያ ሕግ ጋር በሚጣጣም መልኩ ቀጣይነት ያለውና ከርቀት የሚከናወን ስልታዊ ትንተናን በመጠቀም ነው ተብሏል።

በበይነ መረብ የቅድመ-ምርጫ ግምገማ ልዑካን ቡድን እና በምርጫው ቀን በቦታው በነበረ አነስተኛ የቴክኒክ ቡድን የተደገፈና የኢትዮጵያን ምርጫ የመታዘብ ውሱን ተልዕኮው ከርቀት ሆኖ ሥራውን በሚያከናውን በአንጻሩ አነስ ያለ ቡድን አማካይነት ጳጉሜ 1 የሚደረገውን ምርጫ በመገምገም በምርጫ 2013 ላይ የሚሠራውን የግምገማ ሥራ የሚቀጥል ይሆናል ሲል ጠቁሟል።

ሪፖርቱን ያወጡት ኹለቱ ተቋማት ምርጫን በመታዘብ እና በመግምገም ብዙ ልምድ ያላቸው ተቋማት እንደሆኑ የተጠቀሰ ሲሆን፣ ኢንተርናሽናል ሪፐብሊካን ኢንስቲትዩት (IRI) የፖለቲካ ፓርቲዎች ይበልጥ ምላሽ ሰጪ እንዲሆኑ በማገዝ፣ ግልጽነት እና ተጠያቂነት ያለበት አስተዳደርን በማጠናከር እና ሴቶችን እና ወጣቶችን ጨምሮ የተገለሉ የሕብረተሰብ ክፍሎች በፖለቲካ ሒደት ውስጥ የሚጫወቱትን ሚና በማሳደግ በዓለም ዙሪያ ነጻነትን እና ዴሞክራሲን የሚያራምድ ለትርፍ ያልተቋቋመ፣ ከፓርቲ ወገንተኝነት ነጻ የሆነ ድርጅት ነው። ከ1983 ጀምሮ ኢንተርናሽናል ሪፐብሊካን ኢንስቲትዩት በዓለም ዐቀፍ የመታዘብ ተልዕኮዎች እና በግምገማዎች አማካይነት በ60 አገራት ውስጥ ከ200 በላይ ምርጫዎችን ተከታትሏል።

በአንጻሩ ናሽናል ዴሞክራቲክ ኢንስቲትዩት የዴሞክራሲ ተቋማትን፣ ሒደቶችን፣ ልማዶችን እና ዕሴቶችን በማጠናከር እና በመጠበቅ ኹሉም ሰው የተሻለ ጥራት ያለው ሕይወት እንደዲኖር ለማድረግ በዓለም ዙሪያ በአጋርነት የሚሠራ ለትርፍ ያልተቋቋመ፣ ከፓርቲ ወገንተኝነት ነጻ የሆነ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት እንደሆነና ርዕዩ ዴሞክራሲ እና ነጻነት የሰፈነበት እና ኹሉም ሰው ሰብዓዊ ክብሩ የተጠበቀበት ዓለም ተፈጥሮ ማየት መሆኑ ተነግሯል። በተጨማሪም ተቋሙ ባለፉት 35 ዓመታት ከ250 በላይ ምርጫ የመታዘብ ተልዕኮዎችን በ70 አገራት ያከናወነ መሆኑ በሪፖርቱ ላይ ተጠቅሷል።

የአፍሪካ ሕብረትን ጨምሮ የሲቪል ተቋማት በኢትዮጵያ የተደረገውን ምርጫ ለመታዘብ አባሎቻቸውን ማሰመራታቸው ይታወሳል። የአፍሪካ ሕብረት ምርጫ ታዛቢ ቡድን ታዛቢዎቹን ወደ አምስት ክልሎች እና ኹለት የከተማ አስተዳደሮች ልኮ ምርጫውን መታዘቡ አይዘነጋም። በዚህም ታዛቢ ቡድኑ በተሰማራባቸው ስፍራዎች ምርጫ ጣቢያዎች ሲከፈቱ፣ የድምጽ ሲሰጥ፣ ምርጫ ጣቢያዎች ሲዘጉና እና ድምጽ ሲቆጠር መታዘቡ የተገለጸ ሲሆን፣ የሕብረቱ ምርጫ ታዛቢ ቡድን 22 ምርጫ ጣቢያዎች ሲከፈቱ መታዘቡን ገልጾ ከእነዚህ መካከል 13 የሚሆኑት በጊዜ አለመከፈታቸውን ማስታወቁ አይዘነጋም። ምርጫ ጣቢያዎች በጊዜ ሳይከፈቱ የቀሩት የምርጫ ታዛቢዎች እና ቁሳቁሶች መዘግየት እንዲሁም ለምርጫ ቀን የተደረገው ደካማ ቅድመ ዝግጅት ዋና ዋና ምክንያት እንደሆኑም አስቀምጧል።

የድምጽ መስጫ ወረቀቶች ዕጥረት ተከስቶም እንደነበር ሕብረቱ መግለጹ ይታወሳል። ሆኖም የድምጽ መስጫ ሳጥኖች በትክክል ታሽገው እንደነበርም ታዛቢዎቹን ዋቢ አድርጎ አስፍሯል። በቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዝደንት እየተመራ ምርጫውን የታዘበው የአፍሪካ ሕብረት ታዛቢ ቡድን፣ በኢትዮጵያ የተደረገውን ምርጫ የምርጫ ቁሳቁስ አቅርቦት ዕጥረት ባለበትና የኮቪድ 19 ወረርሽኝ እና ደህንነት ስጋት በተጋረጠበት ወቅት የተከናወነ ቢሆንም፣ ሥርዓቱን የጠበቀ፣ ተዓማኒና ሠላማዊ እንደነበር ሪፖርት ማድረጉ አየዘነጋም።

ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ በኹለት ዙር ለማካሄድ የተገደደው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ ሙሉ በሙሉ ምርጫ ባልተካሄደባቸው የሱማሌ፣ ሐረሪ እና ሌሎች ክልሎች እንዲሁም ተቆርጠው በቀሩ ሌሎች አከባቢዎች ጳጉሜ 1/2013 ምርጫ ለማካሄድ ቀነ ቀጠሮ ይዟል። ይሁን እንጅ ከጥቅምት 24/2013 ጀምሮ እስካሁን ድረስ የዘለቀ ችግር ያለበት ትግራይ ክልል ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ ስለማካሄዱ እስካሁን የተባለ ነገር የለም።

ሰኔ 14/2013 የተካሄደውን የመጀመሪያ ዙር አገራዊ ምርጫ ውጤት ከግማሽ ወር በኋላ ባሳለፍነው ሐምሌ ወር ላይ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ መሆኑ የሚታወስ ሲሆን፣ ቦርዱ ይፋ ባደረገው የምርጫ ውጤት 547 መቀመጫዎች ካሉት ኢትዮጵያ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመጀመሪያው ዙር ምርጫ 465 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች ተካተዋል። ይህም ማለት ከመጀመሪያው ዙር ምርጫ ተቆርጠው የቀሩ የሕዝበ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች ብዛት 82 ናቸው ማለት ነው።

ሰኔ 14 በተካሄደው የመጀመሪያ ዙር አገራዊ ምርጫ፣ በአዲስ አበባ ለመምረጥ ከተመዘገቡት አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊየን መራጮች 99 በመቶ ሲመርጡ፣ በአፋር ከተመዘገቡ አንድ ነጥብ ሰባት መራጮች 97 በመቶ፣ አማራ ክልል ከተመዘገቡት ሰባት ነጥብ አንድ ሚሊየን መራጮች 94 በመቶ፣ ቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ከተመዘገቡ 162 ሺሕ መራጮች የመረጡት 55 በመቶ ያክሉ ብቻ ናቸው።

ድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ከተመዘገቡ 208 ሺሕ መራጮች 95 በመቶ ያክሉ ሲመርጡ፣ ጋምቤላ ክልል ከተመዘገቡ 415 ሺሕ መራጮች 89 በመቶ፣ ኦሮሚያ ከተመዘገቡ 15 ሚሊዮን መራጮች 96 በመቶ፣ ደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል ከተመዘገቡ አምስት ነጥብ ሶስት ሚሊዮን መራጮች 91 በመቶ ሲመርጡ፣ ሲዳማ ክልል አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን መራጮች ተመዝግበው 100 በመቶ መምረጣቸውን ቦርዱ ማስታወቁ አይዘነጋም።

ምርጫ ባልተካሄደባቸው ክልሎች የሚደረገው ኹለተኛ ዙር ምርጫ ለጳጉሜ 1/2013 ቀነ ቀጠሮ የተሰጠው ሲሆን፣ ይህም ምርጫ አንዳንድ የፖለቲካ ፓርቲዎች በመጠኑም ቢሆን በምክር ቤት መቀመጫ ለማግኘት እንደ ተስፋ የሚያዩት ሆኖ እየተጠበቀ ይገኛል።


ቅጽ 3 ቁጥር 145 ነሐሴ 8 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com