የእለት ዜና

በአማራ ክልል አርሶ አደሮችን የሚደግፍ ፕሮጀክት ወደሥራ መግባቱ ተገለጸ

በአማራ ክልል አርሶ አደሮችን በኢንቨስትመንት የሚያሳድግ ፕሮጀክት ተጀምሮ ወደ ሥራ መግባቱ ተገለጸ።
‹ፕሮጀክት መርሲ› የተሰኘው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት፣ የተሻሻሉ የእንስሳት ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ ተደራሽ በማደረግ ተጠቃሚነታቸውን ለመሳደግ እየሠራ መሆኑን የድርጅቱ ፕሬዘዳንት ቤቴ ደመቀ ገልጸዋል።
ጀርሲ ከተባለ የእንስሳት ዝርያ የተዳቀሉ የ6ወር እርጉዝ ጊደሮችን ለአርሶ አደሮች በመስጠት ‹‹ወተት ለልጆች፤ ገቢ ለአርሶአደር›› በሚል ድርጅቱ እየሠራ ይገኛል ተብሏል።

ዘርፉን ለማሳደግ መንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር እየሠራ የሚገኘው ግብርና ሚኒስቴር በእንስሳት ዘርፍ ያለውን ሀብት ለመጠቀም የሚያስችል ፕሮጀክት መንደፉን አስታውቋል።
መርሲ ፕሮጀክት ለአርሶ አደሮች የሚያደርገው የ6ወር እርጉዝ ላም ድጋፍ ላሟ በአማካይ 7ሊትር ወተት ሊትሰጥ እንደምትችል በመገመት ነው።

ፕሮጀክቱ 306 ላሞችን ለ153 አርሶ አደሮች ያበረከ ሲሆን፣ ድጋፉም በሰሜን ሸዋ ዞን አንጎለላ እና ጠራ ወረዳ ለሚገኙ 14 ቀበሌ ነዋሪዎች የተሰጠ መሆኑም ቤቴ ገልጸዋል።
መርሲ ፕሮጀክት ይህንን ሥራ ከመሥራቱ አስቀድሞ ስልጠናዎችን የሰጠ ሲሆን፣ በቀጣይ የንግድ ሥራዎችን በማስፋት ከብሔራዊ የእንስሳት ጄኔቲክስ ማሻሻያ ኢንስቲትዩት ጋር በጋራ እየሠራ መሆኑን ለአዲስ ማለዳ አስታውቋል።

የኢንስቲትዩቱ ዋና ዓላማ የእንስሳትን ምርት እና ምርታማነት ማሳደግ፣ የእንስሳት ዝርያዎችን ማሻሻል እና ቀጣይነት ባለው የተሻሻለ የእንስሳት አቅርቦት የአርሶ አደሩን ገቢ እና ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ማስጠበቅ ነው።
ይህ ፕሮጀክት እድገት እንዲኖረው ለአርሶ አደሩ የተሰጡት ላሞች ወተት ተቀነባብሮ፣ በግለሰብ ተቋማት የማስፋፋት ሥራ ተሠርቶ፣ ለአገር እንዲጠቅም የማድረግ ተግባር እንደሚከናወን ቤቴ ገልጸዋል።

በዚህም በአካባቢው የሚገኝ በግል የተቋቋመ ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ጋር ለመሥራት በዕቅድ የተያዘ ሲሆን፣ ተቋሙ አርሶ አደሮችን በመጥቀም ኢንዱስትሪውንም የሚያሳድግ ዕቅድ እንዳለው በቴ አንስተዋል።
መርሲ ፕሮጀክት ከ44 ዓመት በፊት በአሜሪካ የተመሰረተ ድርጅት ሲሆን፣ በርካታ ግብረሰናይ ተግባራት አከናውኗል።

በኢትዮጵያ ያለው የወተት አቅርቦት በሚፈለገው ጥራትና መጠንም ለሕብረተሰቡ እየቀረበ ባለመሆኑ አገሪቱ ምርቱን ከውጪ እያስገባች ሲሆን፣ አመታዊ የወተት ምርት ፍጆታዋ 4.1 ቢሊዮን ሊትር ብቻ ነው። በቀጣይ ወደ 11.7 ቢሊዮን ሊትር በዓመት ለማሳደግ ዕቅድ ተይዟል።
አጠቃላይ አመታዊ የወተት ምርት መጠን ከላሞች 3.8 ቢሊዮን ሊትር፣ ከግሞሎች 165.12 ሚሊዮን ሊትር ብቻ እደሆነና አንድ ላም በአማካይ የምትታለበው የወተት መጠንም ከ1.42 ሊትር እንደማይበልጥ የኢትዮጵያ ማዕከላዊ ሰታትስቲክስ (CSA 2004) ገምቷል።

አንድ ኢትዮጵያዊ በዓመት በአማካይ 19 ሊትር ወተት ብቻ እንደሚጠጣ የሚታወቅ ሲሆን፣ ይህም ከምስራቅ አፍሪካ አገራት እጅጉን ያነሰ ሆኖ ተመዝግቧል።
የምግብና የእርሻ ተቋም ፋኦ እና የዓለም የጤና ድርጅት አንድ ሰው በአማካይ በዓመት 200ሊትር ወተት ሊጠጣ ይገባል ቢሉም የኢትዮጵያ እጅግ አነስተኛ ሆኖ ተቀምጧል። በቀንድ ከብት ሀብት በአፍሪካ አንደኛ በዓለም አስረኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ ከወተት ሀብቷ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም አላገኘችም።


ቅጽ 3 ቁጥር 145 ነሐሴ 8 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!