የእለት ዜና

በአግባቡ ሀብታቸውን ባለማስመዘገባቸው ወደ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የተላኩ ሰዎች ጉዳይ መዘግየቱ ተገለጸ

የፌደራል ሥነ-ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ከዚህ በፊት ንብረታቸውን በአግባቡ ባላስመዘገቡ፣ ዘግይተው ባስመዘገቡና ባላቸውና ባስመዘገቡት መካከል ከፍተኛ ልዩነት ተገኝቶባቸው ጉዳያቸው ወደ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የተላኩ ሰዎች ጉዳይ በሚፈለገው ደረጃ እየሄደ እንዳልሆነ የሀብት ማሳወቅ እና ምዝገባ ዳይሬክተር የሆኑት መስፍን በላይነህ ለአዲስ ማለዳ ተናግረዋል።

በፌደራል ሥነ-ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ጉዳያቸው እንዲመረመር እና ክስ እንዲመሰረት ለጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የተላኩ ፋይሎች ቢኖሩም ሒደቱ ግን ፈጣን እንዳልሆነ የሚናገሩት ዳይሬክተሩ፣ የምርመራ እና ክስ ሒደቱ ከእኛ ሥራ ክፍፍል ውጪ በመሆኑ ምንም ማድረግ እንደማይችሉ አክለው ገልጸዋል። በሀብት ማሳወቅና ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 668/2002 አንቀጽ 11 መሠረት የፌደራል የሥነ-ምግባር እና የጸረ-ሙስና ኮሚሽን የተመዘገበን ሀብት መረጃ ትክክለኛነት የማረጋግጥ ሥልጣን እንደተሠጠው የተናገሩት ዳይሬክተሩ፣ ከዛ ውጪ ያለው ግን በፖሊስና በዐቃቤ ሕግ የሚሠራ እንደሆነ ያስረዳሉ።

በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እና በፌደራል ሥነምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን መካከል ይሄን ጉዳይ አስመልክቶ የመግባቢያ ሥምምነት መኖሩን ጠቅሰው፣ ሒደቶቹ እንዲፋጠኑም እየተሠራ ነው ብለዋል።
በ2013 በጀት ዓመት በፌደራል ደረጃ ንብረታቸውን በአግባቡ ማስመዝገባቸውን ለማረጋገጥ 386 ግለሰቦች ላይ በተደረገው ምርመራ እና ማጣራት 47 በመቶ ያህሉ የተሳሳተ መረጃ ሰጥተው መገኘታቸው ተረጋግጧል። ከነዚህም ውስጥ አብዛኞቹ ባስመዘገቡት እና በምርመራ በተረጋገጠው ሀብት ላይ መጠነኛ ልዩነት የተስተዋለባቸው በመሆኑ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷቸዋል የተባለ ሲሆን፣ ንብረታቸውንም በድጋሚ እንዲያስመዘግቡ ታውቋል። ባላቸውና ባስመዘገቡት መካከል ከፍተኛ ልዩነት የተገኘባቸው ግን ጉዳያቸው ለመርማሪው አካል የሚተላለፍ ሲሆን፣ ይህም በሒደት ላይ እንደሆነ መስፍን በላይነህ ተናግረዋል።

የምዝገባው ሒደት በከፍተኛ ሁኔታ እየተከናወነ ቢሆንም፣ የማረጋገጡ ሥራ በጣም በርካታ ሒደት እንዳለው የሚያነሱት ዳይሬክተሩ፣ ሥራው ሀብት በሚያስመዘግበው ግለሰብ ዙሪያ ያሉ ቤተሰቦችንም ጭምር የሚያካትት በመሆኑ ረጅም ጊዜ እና ሀብት የሚጠይቅ ነው ይላሉ።
አሁን ላይ ተቋሙ የማረጋገጡን ሥራ እያከናወነ ያለው በራሱ ጥናት ላይ ተመርኩዞ እና ለሙስና እና ብልሹ አሠራር ተጋላጭ ይሆናሉ ተብለው በሚታሰቡ ቦታዎች ላይ በመሆኑ፣ ንብረታቸውን በትክክል ያስመዘገቡትን ለማረጋገጥ ባለው ሒደት ላይ መዘግየት ለመፈጠሩ እና የታሰበውን ያህል ለማረጋገጥ አለመቻሉ ላይ የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ እንዳለው ይጠቀሳል።

የማረጋገጡን ሥራ ፈጣንን እና ውጤታማ ለማድረግ የሕዝብ ተሳትፎ በከፍተኛ መጠን የሚያስፈልግ መሆኑን የሚጠቅሱት የሀብት ማሳወቅ እና ምዝገባ ዳይሬክተር የሆኑት መስፍን በላይነህ ናቸው። በሕዝብ ጥቆማ ላይ ተመስርቶ ማጣራቱን ማካሄድ የሚፈጀው ጊዜም ሆነ የሚፈልገው ሀብት አነስተኛ ከመሆኑ በላይ ውጤታማነቱ ከፍ ያለ እንደሆነም ያስረዳሉ።

በአጠቃላይ በሕጉ መሰረት ሀብት አስመዝጋቢዎች የሚያስመዘግቡት ሀብት ትክክለኛ እና እውነተኛ ሊሆን ይገባል። ነገር ግን የሀብት መጠንን በመደበቅ ወይም የተሳሳተ የሀብት ምዝገባ መረጃ የማስመዝገብ ውጤቱ ምንጩ እንዳልታወቅ ሀብት ተቆጥሮ በሕግ የሚያስጠይቅና ሀብቱን የሚያስወርስ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል ሲል የፌደራል ሥነ-ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን አስታውቋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 145 ነሐሴ 8 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!