የእለት ዜና

የመልቲ ሞዳል አገልግሎትን በግሉ ዘርፍ እንዲቀርብ የሚያስችል መመሪያ እየተዘጋጀ ነው ተባለ

የኢትዮጵያ ማሪታይም ባለሥልጣን የግል መልቲ ሞዳል አገልግሎት ሰጪዎችን ወደ ሥራ ለማስገባት መመሪያ እያዘጋጀ እንደሆነ ገለጸ።
የመልቲ ሞዳል ትራንስፖርት ስርዓት ለግል ዘርፉ ክፍት እንዲሆን ለረጅም ጊዜ በተደጋጋሚ ሲጠየቅ የቆየ ጉዳይ ነው። አሁን ላይ ይህን ሥርዓት ክፍት ለማድረግ እና የግሉ ዘርፍ ተሳትፎ እንዲኖረው የሚረዳ መመሪያ በባለሥልጣኑ በኩል እየተዘጋጀ ነው ተብሏል።
የመልቲ ሞዳል የትራንስፖርት ሥርዓት ዕቃዎችን ከተጫኑበት ወደብ እስከ ደረቅ ወደብ ድረስ በአንድ ሰነድ ማጓጓዝ የሚያስችል አሠራር ሲሆን፣ የተለያዩ የሎጀስቲክስ ተቋማት በዘርፉ ለመሰማራት ጥያቄ ማቅረባቸው ታውቋል። የመጀመሪያውን የግል መልቲ ሞዳል ሥራ ለሚከውን ተቋም ፈቃድ ለመስጠት ሒደቶች ተጀምረዋል ።

የግል መልቲ ሞዳል አገልግሎት አቅራቢዎች የራሳቸው ደረቅ ወደብ የሚያስፈልጋቸው ሲሆን፣ የደረቅ ወደብ ሰፋ ያለ መሬት የሚፈልግ ዘርፍ ከመሆኑ አንጻር በአሠራሩ ላይ እንቅፋት ሊፈጥር ይችላልም ተብሎ ይጠበቃል።
አብዛኞቹ ወደ ዘርፉ ለመግባት ፍላጎት ያላቸው የግል ተቋማት ሠፊ የሚባል መሬት የሚፈልጉ ሲሆን፣ መሬቱም ለአዲስ አበባ ቅርብ ርቀት ላይ በሆኑ አካባቢዎች ቢሆን ምርጫቸው እንደሆነ ታውቋል። ሆኖም እስከኹለት ሔክታር ባሉ መሬቶች ላይ የደረቅ ወደቡን መገንባት እና ቀስ በቀስም ማስፋፋት እንደሚቻል ተነግሯል።

የመልቲ ሞዳል የትራንስፖርት ሥርዓት ደንበኞች ዕቃዎቻቸውን ከጅቡቲም ሆነ ከተለያዩ ወደቦች ለማንሳት ዋናውን የማስጫኛ ሠነድ ማቅረብና የባሕር ትራንስፖርት ዋጋ መክፈል ሳያስፈልጋቸው፣ ንብረቶቻቸውን በአጓጓዥ ድረጅቶች ሙሉ ኃላፊነት አማካይነት ወደ አገር ውስጥ በአንድ ሠነድ ብቻ ማስገባት የሚያስችል ነው። በአንጻሩ ዩኒ ሞዳል ተብሎ የሚታወቀው የትራንስፖርት አይነት ዕቃዎች ወደ ኢትዮጵያ ከመግባታቸው በፊት የጉምሩክ ቀረጥና ታክስ ሊከፈልባቸው እንደሚገባ ግዴታ ያደርጋል።

ከዚህም በተጨማሪም፣ የትራንዚት ፈቃድ ከማግኘታቸው በፊት አስመጪዎች ኦሪጅናል የማስጫኛ ሠነድ ከባንኮች ለማስለቀቅ የአገልግሎት ዋጋ መክፈላቸው ግዴታ ነበር። በመቀጠል ደግሞ የጉምሩክ ቀረጥና ታክስ መክፈል ስለሚጠበቅባቸው ዕቃዎች በጅቡቲ ወደብ ላይ እንዲቆዩ፣ እንዲከማቹ የሚያደረግ እና አላስፈላጊ ለሆነ ወጪና የጊዜ ብክነት የሚዳርግ አሠራር ነው።

ከዐስር ዓመት በፊት ኢትዮጵያ ከዩኒ ሞዳል ወደ መልቲ ሞዳል የትራንስፖርት ስርዓት ስትገባ አገልግሎቱን መንግሥታዊ የሆነው የኢትዮጵያ የባሕርና ትራንስፖርት ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በብቸኝነት ሲሰጠው ቆይቷል። አሁን ላይ በመዘጋጀት ያለው መመሪያ የመልቲ ሞዳል ትራንስፖርት ሥርዓቱ ላይ ተጨማሪ የግል ተቋማትን በማምጣት በዘርፉ ላይ የተለየ አማራጭ ከማምጣቱ በተጨማሪ፣ ሒደቱን እንደሚያፋጥነውም ይጠበቃል። ከዚህም ሌላ ሞጆ እና ወረታን ጨምሮ ያሉትን ሰባት የደረቅ ወደቦች በማሳደግ በወደብ ዕቃዎች እንዳይከማቹ በማድረግ የራሱ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።


ቅጽ 3 ቁጥር 145 ነሐሴ 8 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!