የእለት ዜና

ከ4 ሚሊዮን 7 መቶ ሺህ ብር በላይ ግምት ያላቸው 6 መቶ 38 ሳጥን ቢራ የጫኑ ተሽከርካሪዎችን ሰርቀው ሊሰወሩ የነበሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

ከ4 ሚሊዮን 7 መቶ ሺህ ብር በላይ ግምት ያላቸው 6 መቶ 38 ሳጥን ቢራን ከጫኑት ተሽከርካሪዎች ጋር ሰርቀው ሊሰወሩ የነበሩ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር አውሎ ምርመራ እያጣራ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡

ተጠርጣሪዎቹ ወንጀሉን የፈፀሙት በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 ልዩ ቦታው አዲሱ ሚካኤል ገነት ህንፃ ተብሎ በሚጠራው፤ የቢጂ. አይ ኢትዮጵያ ምርቶች ወኪል አከፋፋይ አልታድ ኢትዮጽያ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ ከሚባል ድርጅት ውስጥ ነው፡፡

እንደ ፖሊስ መረጃ ግለሰቦቹ አባሪ ተባባሪ ሆነው ወንጀሉን ከመፈፀማቸው ባሻገር አንደኛው ተከሳሽ በድርጅቱ ውስጥ በጥበቃ ሥራ ተቀጥሮ የሚሰራ ሲሆን፤ ሌላኛው ተባባሪ በዚሁ ድርጅት በጥበቃ ሥራ እየሰራ በሥነ ምግባር ችግር የተሰናበተ ሆኖ ሳለ ኮድ-3-A-75489 A.A እና ኮድ-3-A 98 779 A.A የሆኑ 2 አይሱዙ የጭነት ተሸከርካሪዎችን ከነጭነታቸው እየተመላለሰ ከድርጅቱ በማውጣት የተባበረ ግለሰብ ሲሆን ሶስተኛው ተከሣሽ ወንጀሉ በተሳካ ሁኔታ እንዲፈፀም ድርጅቱ ድረስ በመምጣት እና መረጃ በመስጠት ፍፃሜ እንዲገኝ የተባባረ መሆኑን ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል፡፡

ንብረቱን በ1 ሚሊዮን 9 መቶ ሺህ እንደሚሸጡት እና ገዥ እያፈላለጉ ስለመሆኑ ፖሊስ ከህዝብ በደረሰውን ጥቆማ እና ባደረገው ክትትል ግለሰቦቹን ከጫኑት ቢራ ጋር በቁጥጥር ሥር እንዳዋለ ታውቋል፡፡

በተጠርጣሪዎቹ ላይ የሚደረገው የምርመራ ሂደት ሲጠናቀቅ ለሚመለከተው የፍትህ አካል እንደሚቀርብ ከአዲስ አበባ ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!