የእለት ዜና

በሐረሪ በ77 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው ዘመናዊ ቄራ ለአገልግሎት ክፍት ሆነ

በሐረር ከተማ ማዘጋጃ ቤት በከተማ ተቋማዊና መሠረተ ልማት ማስፋፊያ ፕሮግራም ማስተባበሪያ ጽ/ቤት፣ በሐረሪ ክልል ሶፊ ወረዳ በ77 ሚሊዮን ብር የተገነባው ዘመናዊ የቄራ አገልግሎት መስጫ ሕንፃ ተመርቋል። በመርሃ ግብሩ የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሐመድ ተገኝተዋል።
ኢንጂነር አይሻ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር፣ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በከተሞች ማስፋፊያና ፕሮግራም የከተሞችን አቅም ከማሳደግ አኳያ በ117 ከተሞች እየተተገበረ መሆኑን አንስተዋል።
በጥንታዊቷ ሐረር ከተማ ከቄራ አገልግሎት ጋር ተያይዞ ይስተዋል የነበረውን ችግር ለመፍታት ዘመናዊ የቄራ አገልግሎት መስጫው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ብለዋል።
የሐረሪ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በበኩላቸው፣ የክልሉን ሕዝብ መሠረታዊ ችግሮችን ለመፍታትና ድሃ ተኮር የሆኑ የመሠረተ ልማት ማስፋፋት ላይ ትኩረት በመስጠት እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለያዩ ውስብስብ ችግሮች ሳቢያ ግንባታውን ለማጠናቀቅ ረዥም ጊዜ የወሰደ ቢሆንም በቀጣይ የቄራውን ውስጣዊ አደረጃጀት በማስተካከል ሥራውን በተሟላ መልኩ እንዲያከናውን እንደሚደረግ ርዕሰ መሥተዳድሩ አስታውቀዋል።
ይህ ዘመናዊ የቄራ አገልግሎት መስጫ ሕንፃ ጥራቱና ጤናው የተጠበቀ ሥጋ ለሕብረተሰቡ እንዲደርስ ያስችላል ያሉት ደግሞ የሐረር ከተማ ማዘጋጃ ቤት ሥራ አስኪያጅ አቶ በቀለ ተመስገን ናቸው።
በተጨማሪም ቄራው በሰዓት 40፣ በቀን ደግሞ 980 በሬዎችን አርዶ እንደሚያወጣ ገልፀዋል።
ቄራው ለበርካታ የአካባቢው ወጣቶች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥርና ተረፈ ምርቶቹም ተመልሰው አገልግሎት ላይ እንዲውሉ የሚያስችል አሠራር እንደተዘረጋ በምረቃ ሥነ-ስርዓቱ ወቅት ተገልጿል። በሥነ-ስርዓቱ ላይ የተሳተፉ እንግዶች በቄራው ቅጥር ግቢ ውስጥ ችግኞችን በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 146 ነሐሴ 15 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!