የእለት ዜና

የኮቪድ 19 ሕሙማን ቁጥር በዕጥፍ መጨመሩ ተገለጸ

ባለፉት ኹለት ወራት ከነበረው የኮቪድ 19 ሕሙማን ቁጥር አንጻር አሁን ላይ ቁጥሩ በዕጥፍ እየጨመረ መሆኑን የኮቪድ 19 ሕክምና ማዕከል የሥራ ኃላፊዎች ገለጹ።
በሚሊኒየም የኮቪድ 19 ሕክምና ማዕከል ኃላፊ ዶክተር ውለታው ጫኔ እንደተናገሩት፣ በአሁኑ ጊዜ የጽኑ ሕሙማን ክፍል ሞልቷል ብለዋል። ከአንድ ወር በፊት ከነበረው አንጻርም በቫይረሱ በጽኑ የታመሙ ሰዎች መጠን በአስር ዕጥፍ መጨመሩን ነው የተናገሩት።
በኤካ ኮተቤ የኮቪድ 19 ሕክምና ማዕከል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ናትናኤል በክረጺዮን ከግንቦት እስከ ሐምሌ የነበረው ቁጥር አነስተኛ መሆኑን ገልፀው፣ አሁን ግን በሚያስደነግጥ ሁኔታ የሕሙማን ቁጥር እየጨመረ መሆኑን አስረድተዋል።
በዚህም በአንድ ጊዜ እስከ 30 የሚደርሱ በጽኑ ሕሙማን ክፍል የሚገቡበት ሁኔታ መኖሩን የጠቆሙ ሲሆን፣ የኦክስጅን ዕጥረትም አልፎ አልፎ እየገጠማቸው መሆኑን ነው የተናገሩት። የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት ኤጀንሲም በበኩሉ አሁን ላይ የእጅ ጓንት እጥረት መኖሩን ጠቅሶ ለኮቪድ 19 ሕክምና የሚያገለግሉ ግብዓት እጥረት እንዳይገጥም ከተለያዩ ዓለም ዐቀፍ ተቋማት ጋር ሥራዎች እየሠሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በተወሰኑ ቦታ ብቻ የሚሰጠውን የሕክምና አገልግሎት 180 በሚደርሱ ሆስፒታሎች እና ጤና ጣቢያዎች ለማዳረስ እየሠሩ መሆኑንም አስታውቀዋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 146 ነሐሴ 15 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!