የእለት ዜና

በ2014 በጀት ዓመት 552 ተሽከርካሪዎች ለተለያዩ ተቋማት እንደሚገዙ ተገለጸ

የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት በቀጣይ 2014 በጀት ዓመት፣ 552 ተሸከርካሪዎችና 60 ሞተር ሳይክሎችን ለተለያዩ የፌደራል ተቋማትና ለዩኒቨርስቲዎች ግዥ ለመፈጸም በዕቅድ ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል።
የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት ለአዲስ ማለዳ እንደገለጸው ከሆነ፣ በገንዘብ ሚኒስቴር ትእዛዝ መሰረት ለ187 የፌደራል ተቋማት እና ለ45 ዩኒቨርስቲዎች አገልግሎት የሚውሉ፣ እንዲሁም በተደረገ የቴክኒክ ግምገማ ምክንያት የተሸከርካሪዎች ግዥ ላልፈጸሙ፣ በድምሩ 552 የተለያዩ አይነት ተሽከርካሪዎችን እና 60 ሞተር ሳይክሎችን በተሻሻለው የተሽከርካሪዎችና ሞተር ሳይክል ዝርዝር መግለጫ(ስፔሲፊኬሽን) መሠረት ግዥ ለመፈጸም ዕቅድ ይዟል።
የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት በተለያዩ የፌደራል ተቋማት ውስጥ ለሚሠሩ ሠራተኞችና የተቋማቱ ኃላፊዎች የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ተሽከርካሪዎች ግዥ እንደሚያከናውን ገልጿል።
በተጨማሪም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ቀልጣፋ የሆነ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችላቸውንና ለሠራተኞቻቸው መጓጓዣነት የሚያገለግሉ ተሸከርካራዎችን እና አንቡላንሶችን ለ45 ዩኒቨርስቲዎች ለመግዛት ዕቅድ እንደተያዘ አዲስ ማለዳ ማወቅ ችላለች።
በመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት አማካይነት ለተለያዩ የፌደራል እና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚገዙት 552 የተለያዩ አይነት ተሸከርካሪዎች፣ ተቋማቱ በሚሰጡት አሠራር ላይ በተሽከርካሪዎች ዕጥረት ምክንያት የሚከሰቱ ችግሮችን ለመቅረፍ እንደሚያስችል ተጠቅሷል።
የመንግሥት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት የሚፈጽመው የተሸከርካሪዎች ግዥ በግልጽ ጨረታ መሰረት ተግባራዊ የሚደረግ ሲሆን፣ የሚከናወነው የተሸከርካሪዎችም ግዥ የፌደራል ተቋማት እና ዩኒቨርስቲዎች ሥራቸውን በተመቻቸ ሁኔታ እንዲያከናውኑ አስፈላጊነታቸው የተረጋገጡ ብቻ እንደሚሆን ተጠቅሷል።
በ2013 በጀት ዓመት በኤጀንሲው ለፌደራል ተቋማት እና ለዩኒቨርስቲዎች የተሽከርካሪ ግዥ ለመፈጸም የታቀደ ቢሆንም፣ በትራንስፖርት ባለሥልጣን አማካይነት በሚወጣው የተሽከርካሪዎች እና ሞተር ሳይክል ዝርዝር መግለጫ(ስፔሲፊኬሽን) መስፈርት ግዥው በታቀደለት የጊዜ ገደብ ባለመጠናቀቁ ምክንያት ዕቅዱ በተያዘለት በጀት ዓመት ተግባራዊ ሳይደረግ ቆይቷል።
የመንግስት ግዥና ንብረት ማስወገድ አገልግሎት በቀጣይ 2014 በጀት ዓመት በትራንስፖርት ሚኒስቴር በተሻሻለው የተሽከርካሪዎችና ሞተር ሳይክል ዝርዝር መግለጫ መሰረት፣ ለ187 የፌደራል ተቋማት እንዲሁም ለ45 ዩንቨርስቲዎች በድምሩ 552 ተሽከርካሪዎችን እና 60 ሞተር ሳይክሎችን የመግዛት ዕቅድ እንዳለው አሳውቋል።


ቅጽ 3 ቁጥር 146 ነሐሴ 15 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!