የእለት ዜና

የዳግማዊ አጤ ምኒልክ እና የእቴጌ ጣይቱ ልደት

የጥቁር ሕዝቦችን ድል እና የነጻነት ብርኃንን ብልጭታ ላሳዩን፣ አገርን ጠብቀዉ ላቆዩን ጀግኖች አባቶቻችና እናቶቻችን ምስጋና ይሁንና በነጻነት ለመኖር በቃን። እኛ ኢትዮጵያውያን ነን፤ ከዓለም በፊት በጀግኖች አባቶቻችን ሥልጣኔን የቀመስን፤ አብሮ መኖርን ያዳበርን።
የጥቁር ሕዝቦች ኹሉ የኩራት ምንጭና የመላዉ አፍሪካ የሉዓላዊነት መሠረት የሆነችው አገራችን ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ገናና ታሪክ ያላት መሆኗ የታወቀ ዕውነት ነዉ። አንድ አገር በራሷ አስተዳደር እና ሉዓላዊነት ትኖር ዘንድ ኹሉም ዜጋ የበኩሉን ድርሻ መወጣት ያለበት ጉዳይ መሆኑም መዘንጋትም የለበትም።

ስለ አንድ አገር ነጻነት እና ሉዓላዊነት ሲወሳ በኢትዮጵያ ታሪክ ዉስጥ ቀድሞ የሚነሳ ታሪክ አለ። አድዋ!

ስለ አድዋ ኹነት እና ስለ ጀግኖች ኢትዮጵያውያን የድል ጮራ ሲነገር ቀድሞ ፊት ደራሽ የሆኑ የዚህ ድል ፊታውራሪዎችና ትዉልድ የማይሽራቸዉ የአገር ባለዉለታዎች አሉ። ውድ አንባብያን ይህ ተራ ታሪክ አይደለም፤ ይልቁንም ለአገር ነጻነት የተዋደቁ፣ ክብራቸዉን ከአገራቸዉ መኖር ያሳነሱ፣ ደረታቸዉን ለጦር፣ እግራቸዉን ለጠጠር፣ ግንባራቸዉን ለጥይት የሰጡ፤ ለእናት አገራቸዉ የተሰዉ የእነዛ ጀግኖች አርበኞች እና የአገር መሪዎች ዕንቁ ታሪክ ነው እንጂ።

ነሐሴ 12 1836 ዓ.ም. የዚህ ድንቅ ታሪክ መሪ ተዋናይ ደጉ ንጉሠ ነገስት ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ተወለዱ። ኢትዮጵያም የቁርጥ ቀን ልጇን በደስታ ተቀበለች። ለአፍሪካ ኩራት ለዓለም ጥቁር ሕዝቦች ኹሉ የነጻነት ተምሳሌት የሆኑት እምዬ ምኒልክም ተወለዱ።
ጊዜዉ የነጮች የበላይነት ጎልቶ የሚታይበት በአንጻሩ ደግሞ የጥቁሮች ባርነት የታወጀበት ነበር። ምንም እንኳን የሰዉ ዘር ኹሉ አንድ የአምላክ ፍጥረት የሆነ እና ወደ እዚህ ምድር በእንግድነት የመጣ ቢሆንም ቅሉ፣ ይህን ዕውነታ የዘነጉ ግን በቆዳ ቀለማቸዉ ብቻ እኛ ነን የዓለም ኃያላን ብለዉ የሚያስቡ ቅኝ ሊገዙ ተነሱ።

አሁን ያ ሁሉ ተቀይሮ ታሪክ ሆኖ ቀርቷል፤ አንድ መቶ ሰባ ሰባት ዓመት ወደ ኋላ ተመልሰን ማለትም 1836 ይህ ዓለም ሁሉ ያወቀዉን ዕውነት ይቀይር እና ብሎም ያጠፋ ዘንድ አንጎለላ በምትባል መንደር አንኮበር ላይ፣ ከደጋጎቹ ሐበሾች አብራክ ከንጉስ ሳህለሥላሴ ቤተ መንግሥት ግርጌ፣ ከታላላቆቹ ኢትዮጵያውያን መንደር ዐፄ ምኒልክ ተወለዱ። አዲስ ማለዳም የዚህ ታሪካዊ ቀን መታሰቢያ ዝግጅት ላይ በመገኘት የታሪክ ተካፋይ ለመሆን በቅታለች።

በባህሪያቸዉ ደግ ፤ሐሳባቸዉም የቀና፤ ልባቸዉ በፍቅር እጅግ የተሞላ ትሁት እና ሰዉን አብዝቶ ወዳጅ ናቸዉ። የአድዋን የድል ጮራ ፈንጣቂ፣ የሥልጣኔ ፋና ወጊ የሆነ እና የጥቁር ሕዝቦች ኹሉ ነጻነት እና ድል ተምሳሌቶቹ ጥንዶች፣ የእምዬ ምኒልክ እና እቴጌ ጣይቱ ብጡል የልደት መታሰቢያ በዓል በዋቢ ሸበሌ ሆቴል ነሐሴ 11 ቀን 2013 ዓ.ም. ተከብሯል። ከወጣቶች ልብ ያልጠፋዉ የእነዚህ ደጋግ ነገስታት ፍቅር እንዲሁም አገር ወዳድነት አስገድዷቸው ብዙዎች በፕሮግራሙ ላይ ታድመው ነበር።
በዚህ የመታሰቢያ ዝግጅት ብዙ ታላላቅ ሰዎች ተገኝተዋል። ዶ/ር ዘካርያስ የእምዬ ምኒልክ መጽሐፍ ደራሲ ፤ ተጓዡ ጋዜጠኛ ሔኖክ ስዩም፤ ገጣሚ በላይ በቀለ ወያ ፤ ጋዜጠኛ ጥበቡ በቀለ እና ለሎችም ታዋቂ ሰዎች ታድመዉበታል።

በዚህ መድረክ በተለይም ለጥቁር አፍሪካዉያን እና ለመላዉ ዓለም የነጻነት መነሻ እና ብስራት የሆነዉ የአድዋ ድል ተዘክራል። መላዉ አፍሪካ በቅኝ ግዛት ስር ወድቆ በባርነት ሲማቅቅ፣ ነጮች በጥቁሮች ላይ የበላይነታቸዉን ሲያሳዩ፣ የባርነት በትራቸዉን ሲያሳርፉ እና የቅኝ ግዛት ቀንበራቸዉን በጥቁሮች ትክሻ ላይ ሲጭኑ፣ በእዚህ የአፍሪካ ምድር ይልቁንም ኢትዮጵያ በምትባል ሉዓላዊ አገር የባርነት ቀንበር ለመጨረሻ ጊዘ ሊሰብሩ እምዬ ተወለዱ።

ብላቴን ጌታ ሕሩይ ወልደሥላሴ ባሰፈሩት ጽሑፋቸዉ ላይ፣ ዳግማዊ አጼ ምኒልክ አባታቸዉ ኃይለ መለኮት ንጉሰ ሸዋ በ1848 ሲሞቱ 11 አመታቸዉ ነበር። ያኔ በአጤ ቴዎድሮስ አማካይነት ወደ መቅደላ ተወስደዉ ለ10 ዓመት ያህል ከቆዩ በኋላ በ1857 ወደ አንኮበር ተመልሰዉ እስከ 1882 ዓ.ም. ንጉሰ ሸዋ ተብለዉ ነግሰዉ ቆይተዋል። ከ1882 እስከ 1906 ንጉሰ ነገስት በመባል ኢትዮጵያን አንድ አድርገዉ እንዳስተዳደሩ ይናገራሉ።

በአጠቃላይ የሸዋ ንጉስ ሆነዉ 24 ዓመት ከ 3 ወር፤ የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት ሆነዉ 24 ዓመት ከ 3 ወር በንግስና የቆዩ ሲሆን፣ አጠቃላይ የንግስና ዘመናቸዉም 48 ዓመት ከ 6 ወራት ነበር።

እስከ አድዋ ድል ድረስ መላዉ አፍሪካ ጭንቅ ውስጥ ነበር። ደቡብ አፍሪካ እስከ 1980 ድረስ ለ ኹለት መቶ አመታት በባርነት ትወገር ነበር። ይህ የነጮችን የበላይነት የደመሰሰ የጥቁር ሕዝቦችን ነጻነት በመላዉ ዓለም ያወጀ በአፍሪካ የሥነ-ጽሑፍ ታሪክ ውስጥ ዘርፈ ብዙ ለውጥ ያመጣ የጥቁር ሕዝብ ድል ነዉ።

ዛሬ ለዚህ ትዉልድ በተለይም ለወጣቱ ይህንን ቀን ማክበር ቀላል አይደለም። ይልቁንም ከአያቶቹ እና ከአባቶቹ፣ ፍቅር እና አልሸነፍ ባይነት እንዲሁም አገር ወዳድነትን መማሪያ ጭምር ነዉ እንጂ። አፍሪካ እራሷን ችላ እንድትቆም ያደረገ የፓን አፍሪካኒዝም ጽንሰ ሐሰብ መፈጠሪያ፣ የዘመናዊ ስልጣኔ መጀመሪያ ነዉ።

ከመንገድ እስከ መብራት፤ ከዘመናዊ ትምህርት ቤት እስከ ሆስፒታል ግንባታ ፤ ከባቡር ትራንስፖርት እስከ ስልክ አገልግሎት ጅማሮዎች በዚያን ጊዜ በነበሩት በእምዬ ምኒልክ እና መንግሥታቸዉ የተበረከቱ ናቸዉ። ኢትዮጵያ በራሷ ቋንቋ፣ባህል፣ ኃይማኖት፣ ትዉፊት እንዲሁም ነጻነት እንድትኖር ያደረጉ የአገር ባለውለታዎችን መዘከር የዚህ ትዉልድ ተቀዳሚ ተግባር ሊሆን እንደሚገባ በዝግጅቱ ከተነሱ ሐሳቦች መካከል አንዱ ነው።

ለዚህም ማሳያ ይሆን ዘንድ ነሐሴ 11 ቀን 2013 ዓ.ም. ከተከበረዉ የእምዬ ምኒልክ እና የእቴጌ ጣይቱ የልደት በዓል መታሰቢያ ጋር ተያይዞ ለልደታቸዉ መታሰቢያ እንዲሆን ታስቦ በእንጦጦ እና በትውልድ አገራቸዉ አንጎለላ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ተካሂዷል።

አገራችን ኢትዮጵያ ምንም እንኳን እጅግ የበዙ የጦርነት ታሪኮች ያላት አገር ብትሆንም፣ በዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት የነበረዉ በተለይም የውስጥ ጦርነቱ በጣም ከባድ ነበር። ለዚህም ዋነኛ ምክንያቱ ደግሞ ከራስ ሰዉ ጋር መዋጋት የከፋ እና ከባድ ስለሆነ ነበር። በዚህም አገራችን ኢትዮጵያ ከገጠሟት ጦርነቶች ዉስጥ በዳግማዊ ምኒልክ ዘመነ መንግሥት የነበረዉ ጦርነት ለየት የሚያደርገዉ እምዬ ምኒልክ በታሪካቸዉ አንድም ጦርነት ላይ ሽንፈትን አይተው አለማወቃቸው ነው። ይልቁንም በድል እና በስኬት አጠናቀዋል እንጂ።

ቁጥራቸዉ የበዛ የአገር ዉስጥ እና የዉጭ አገር ጸሐፍት፣ ደራስያን እና ታሪክ ተመራማሪዎች እንደሚሉት፣ ዳግማዊ ምኒልክ ኢትዮጵያን በንጉሠ ነገሥትነት ከመሩ እና ካስተዳደሩት መካከል ደግ እና በፍቅር የተሞላ ልብ ያላቸዉ ነበሩ። ለዚህም አሁንም ድረስ ፍቅራቸዉ እና አገር ወዳድነታቸዉ በኢትዮጵያዉያን ሁሉ ልብ ውስጥ ሞልቶ ሲኖር ይታያል።

ዓለም ዐቀፉ የታሪክ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ሔነሪ ሊዊስ ጌትስ ባሰፈረዉ ጽሑፉ ላይ፣ ኢትዮጵያ አድዋ ላይ ጣልያንን ድል ስታደርግ የነበራት የሕዝብ ቁትር 5 ሚሊዮን ያነሰ እንደነበር ያትታል። ይህ ግን ኢትዮጵያንና መላዉ የጥቁር ሕዝብን ከነጻነት ድል እንዳላቆማቸዉ ይናገራሉ። በአገራችን ደራስያን ከተጻፉቱ መካከል የወቅቱ ዕዉቅ ጋዜጠኛ (ተጓዡ) ሔኖክ ስዩም ከጻፈዉ ‹ሃገሬ› ከተሰኘዉ መጽሐፍ መልክዐ ምኒልክ ለአብነት ያህል፤
ጥቁር ነኝ፤

ለጥቁር ሁሉ ኩራት የኾኑ ንጉሠ ነገሥቴ የተወለዱበትን ቀን አከብራለሁ። ስላከበሩኝ መወለዳቸዉን አወድሳለሁ።

ዘመነ መሳፍንት ባበቃ፤ ዓለም አንዷ ሀገር አስር ቦታ ኾና በተሳለቀበት ዘመን ማብቂያ፤ ሁለቱን ታላላቅ ነገስታት ተከትለው ስለነገሱት ንጉሳችን ልደት ደስታችን ወደር የለዉም።
ምኒልክ ከእናታቸዉ ከኢትዮጵያ ከአባታቸዉ ከጥቁሮች ምድር አፈር የተወለዱ እንጂ እንዲያዉ በቀላሉ የእከሌ እና የእከሊት ልጅ የሚባሉ ተራ አፍሪቃዊ አይደሉም።
ይልቁንም አፍሪቃ አዉሮፓ ጠረጴዛ ላይ መነጋገሪያ ትሆን ዘንድ የቀደመችዋን ገናና ሀገር ዳግም እንድትታፈር ያደረጉ ናቸዉ።

እምዬ ምኒልክ በአገራቸዉ የተወደዱ በሕዝባቸዉ የተከበሩ ከመሆናቸዉም በላይ እጅግ ታሪክ ወዳጅ እና ለዘመናዊ ሥልጣኔ ቅርብ እንደነበሩ ታሪካቸዉ ሕያዉ ሆኖ ሲመሰክር ይገኛል።
ለዚህም ማሳያ ይሆን ዘንድ የአዲስ አበባ ከተማን አመሰራረት ማየቱ ተገቢ ነዉ። ዳግማዊ አጤ ምኒልክ የአዲስ አበባ ከተማን ሲመሰርቱ ዙሪያ ገባዉን አይተዉ መልክዓ ምድሩን አስጠንተዉ የጥንት የአባቶቻቸዉ መሠረት ያለዉ መሆኑን አረጋግጠዉ እንደመሠረቷት ይነገራል። በዚህም ንጉሱ ታሪክ ወዳጅ ብቻ ሳይሆኑ ታሪክ ሠሪም ጭምር እንደነበሩ የሚታወቅ ነዉ።

ዓለማችን በተለያየ ጊዜ ብዙ አስከፊ የሚባሉ የጦርነት ታሪኮችን አስተናግዳለች። አሁንም ይሄዉ አልቀረላትም። ቀደም ባሉት ዘመናት በተለይም በቅኝ ግዛት ዘመን ዓለም በተለያየ ጎራ ተከፍላ ለቅኝ ግዛት ስትዘምት አፍሪካ ደግሞ ዋነኛ ዒላማዋ ነበረች። መላዉ አዉሮፓ አፍሪካን እንደ ቅርጫ ሥጋ ሲከፋፈል የምስራቅ ፀሐይ በሆነችዉ በአፍሪካ ምድር አንድ የተለየ ሰብዕና የተላበሱ መልካቸው በተስፋ እና በነጻነት ብርሐን ብልጭታ የተሞላ ባለ ግርማ ሞገስ አፍሪካዊ መሪ ብቅ አሉ። እኚህ ሰዉ መላዉ ዓለም መነጋገሪያ ያደረጋቸዉ በተግባራቸው ነው። የዓለም ታላላቅ ጋዜጦች፣ መጽሔቶች፣ ኹሉ መነጋገሪያቸዉ ብሎም የፊት ገፃቸዉ እምዬ ምኒልክ ሆኑ።

አገራችን ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ ታዋቂ እና የተከበረች ሉዓላዊ አገር ሆና ለመኖሯ እምዬ ምኒልክን እና የባለቤታቸው እቴጌ ጣይቱ እንዲሁም ፊታውራሪ ገበየሁን የመሳሰሉ በግብር የሚመስሏቸዉን ታላላቅ ሰዎች መዘከር የዚህ ትዉልድ ድርሻ መሆኑም መዘንጋት የለበትም። ታሪክን ካልጠበቁት እና ካልተንከባከቡት መጥፋቱ አይቀሬ ስለሆነ የዚህ ዘመን ትውልድ ታሪኩን የመጠበቅ እና የመንከባከብ እንዲሁም የአባቶቹን ገድል የመፈጸም ትልቅ ኃላፊነት እና ትጋት ሊኖረዉ ይገባል።


ቅጽ 3 ቁጥር 146 ነሐሴ 15 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!