የእለት ዜና

ዴልታ ቫይረስ፡- የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሦስተኛው ማዕበል

Views: 206

ኮቪድ-19 ደረጃውን ከአልፋ ጀምሮ ዴልታ ወደ ተባለው ዝርያ እያሳደገ መጥቷል የሚሉት በጤና ሚኒስቴር የኮቪድ ወረርሽኝ ምላሽ ግብረ-ኃይል አስተባባሪ መብራቱ ማሴቦ ናቸው። ዴልታ ቫይረስ ከዚህ በፊት ከሚታወቀው የኮቪድ-19 የማጥቃት ደረጃው ከፍ ያለ ሲሆን፣ ባሕሪውን በሚቀይርበት ጊዜ የተሰጠ ስያሜ ነው። ይህ ቫይረስ ከመጀመሪያው ቫይረስ የማጥቃት ደረጃው በጣም ከፍተኛ ነው ሲሉ መብራቱ ገልጸዋል። ይህ ራሱን የቀየረው የኮቪድ-19 ቫይረስ ዝርያ በተለያዩ የዓለም አገራት እየተሠራጨ ሲሆን፣ በተለይ ግን በሕንድ ከፍተኛ የሆነ የሥርጭት መጠን አሳይቶ ነበር። ይህ ዝርያ በሕንድ ከጀመረ በኋላ በአሁኑ ሰዓት በ135 አገራት ላይ ተገኝቷል። የኮቪድ ዝርያ የሆነው ዴልታ ቫይረስ ራሱን ችሎ የመጣ አዲስ ቫይረስ ሳይሆን ኮቪድ-19 ደረጃውን አሳድጎ መምጣቱን ግንዛቤ ሊኖር ይገባል ብለዋል።

ማንኛውም ቫይረስ ራሱን ከአካባቢው ጋር በማመሳሰል የመቀየር ተፈጥሯዊ መንገድ ስላለው ባህሪውን በሚቀይርበት ጊዜ ይዞት የመጣው ባህሪ ቀድሞ ከሚታወቀው በጣም አደገኛ ነው። ኮቪድ-19 በብዛት የሚያጠቃቸው ተያያዥ ችግር ያለባቸው እና ዕድሜያቸው ከፍ ባለ ደረጃ የሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ነበር። ይህ ዴልታ የተባለው ግን በተለይ ከ25-40 የዕድሜ ክልል ላይ ያሉትን በከፍተኛ ደረጃ እያጠቃ የሚገኝ ነው። የመግደል አቅሙም ቢሆን ከኮቪድ-19 በእጥፍ ጨምሮ የመጣ ነው ሲሉ መብራቱ ተናግረዋል።

ይህ ቫይረስ ወደ ሰዎች የሚተላለፍበት ፍጥነትም ቢሆን ከተለመደው የበለጠ በመሆኑ በቀን ከ 4ሺሕ እስከ 5ሺሕ ሰዎችን እየገደለ እና በቀን እስከ 100ሺሕ የሚደርሱ ሰዎች በቫይረሱ እየተያዙ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ። ይህንን ቫይረስ በቅድሚያ ለመከላከል የሚያስችለው ክትባት በመሆኑ የክትባቱን ሥርጭት በማስፋት በተወሰነ ደረጃ እንዳይስፋፋ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል። በኢንዶኔዥያ እና ሕንድ ስርጭቱ በጣም ከፍተኛ በመሆኑ ክትባት እንዲያገኙ እየተደረገ እንደሚገኝም መብራቱ ያስረዳሉ።

ኮቪድ-19 ላይ የሚታዩ ምልክቶች በጠቅላላ ማለትም የመተንፈሻ አካላት ላይ ያሉ ሕመሞች ናቸው። ከኮቪድ-19 የሚለየውም ጉንፋን በሚመስል መልኩ ቢሆንም የራስ ምታት የሌለው በመሆኑ ነው ያሉት አስተባባሪው፣ በጤና ሚኒስቴር እየተጣሩ ያሉ ምርመራዎች መኖራቸውን ጠቁመዋል። እየታየ ያለው ምልክት በአብዛኛው ጉንፋን የሚመስል ነው ብለዋል። አብዛኛውን ጊዜ ሰዎች ጉንፋን ነው የያዘኝ በማለት ወደ ምርመራ የማይመጡ ሲሆን፣ ጉንፋን የሚመስለው ዴልታ ቫይረስ ከአፍንጫ ፈሳሽ የማውጣት ባሕሪ አለውም ተብሏል።

በርካታ ተመሳሳይ የሆኑ የሕመም ምልክቶች ቢኖሩትም የጉዳቱ መጠን በጣም በፍጥነት ስለሚሠራጭ ሰዎች በሽታው በጀመራቸው ከሦስት እስከ አራት ባለው ቀን ውስጥ ወደ ማቆያ ይገባሉ። የኮቪድ-19 እስከ አንድ ሳምንት ጊዜ የሚሰጥ ሲሆን፣ ይህ ቫይረስ ግን ሕሙማን በፍጥነት ወደ ጽኑ ማቆያ እንዲገቡ ያደርጋቸዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ ዴልታ ቫይረስ መግባት አለመግባቱ አልተረጋገጠም የሚሉት መብራቱ፣ በርግጥ በኮቪድ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በጣም እየጨመረ መጥቷል። ዴልታ ቫይረስ ያለበትን ሰው ለማወቅ የጅን ምርመራ ስለሚያስፈልግ የሱ ውጤት እየተጠበቀ ይገኛል ብለዋል። በጤና ሚኒስቴር እየተሠራ ያለው ሥራ የዴልታ ቫይረስ ኢትዮጵያ ውስጥ መኖር አለመኖሩን ለማረጋገጥ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ ይህ ቫይረስ ተገኘም አልተገኘም ሕብረተሰቡ የነበረውን የጥንቃቄ አካሄድ እና የመከላከያ መንገዶች ማቆም የለበትም። ማስክ ማድረግ፣ ሳኒታይዘር መጠቀም፣ ተራርቆ መቀመጥ እና እጅን በተደጋጋሚ መታጠብ ኹልጊዜም መረሳት የሌለባቸው ናቸው።

የዚህን ቫይረስ ሥርጭት ለመከላከል መፍትሄው ለኮቪድ-19 ስናደርግ የነበረውን ጥንቃቄዎች በሙሉ መተግበር መሆኑን አንስተዋል። ትልልቅ ስብሰባዎች፣ ሰርጎች እና ብዙ ሕዝብ የሚታደምባቸው ፕሮግራሞችን ስንገኝ ጥንቃቄ በተሞላበት መልኩ መሆን እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ወቅቱ ክረምት እንደመሆኑ መጠን ቤት ውስጥ በርና መስኮት ዘግቶ መቀመጥ ይዘወተራል። በዚህ መሀል አየር የመግባት ዕድል ስለማይኖር ቫይረሱ ታፍኖ በመቆየት የሥርጭት መጠኑ እንዲስፋፋ ያደርጋል። መስኮትን እና በሮችን በመክፈት አየር እንዲገባ ማድረግ ተገቢ ነው ብለዋል። በተለይ አሁን ሰዉ እንደነዚህ ያሉ የጥንቃቄ መንገዶችን ለመተግበር እየተሰላቸ እና ችላ እያለ መጥቷል። ይህ መዘናጋት ደግሞ ለሥርጭት መጠኑ መጨመር ምክንያት ይሆናል።

ጤና ሚኒስቴር ቫይረሱን በሳይንስ እስከሚያረጋግጥ ድረስ ሕብረተሰቡ ጥንቃቄዎችን ማድረግ እንዳለበት ጠቁመዋል። በተቻለ መጠን ክትባቶችን የማሰራጨት እና ቅድሚያ ማግኘት ለሚገባቸው በማዳረስ የቅድመ መከላከል ሥራ እየተሠራ ነው። የክትባት ዘመቻዎችን ለማድረግ የሚያስችሉ በርካታ ክትባቶች እየገቡ ይገኛሉ። እነዚህን ክትባቶች በጣም በአጭር ጊዜ ውስጥ ለበርካታ ሕዝብ ለማዳረስ ታስቧል።

የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ባለፈው ሳምንት ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በከፍተኛ ሁኔታ እየጨመረ መሆኑን አስታውቋል።
የወረርሽኙ መጠን መጨመር ሕብረተሰቡ ጋር ባለው መዘናጋት የተፈጠረ መሆኑን የተናገረው ኢንስቲትዩቱ፣ ሥርጭቱ እንዲቀንስ ማስጠንቀቂዎችን እያስተላለፈ እንደሚገኝ ገለጿል።
በአሁኑ ሰዓት በአጠቃላይ 3.1 ሚሊዮን የላብራቶሪ ምርመራ የተደረገ ሲሆን፣ በቫይረሱ የተያዙት ሰዎች ቁጥር 291ሺሕ መድረሱን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በየቀኑ ከ6ሺሕ እስከ 8ሺሕ የላብራቶሪ ናሙና ምርመራ እየተደረገ ሲሆን፣ እስከ አንድ ሺሕ የሚደርሱ ሰዎች በየቀኑ ቫይረሱ እየተገኘባቸው መሆኑን ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አስታውቋል።
ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ የኃይማኖት ተቋማት ፣ ሲቪክ ማኅበራት፣ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ፣ የጤና ባለሙያዎች ፣ መምህራንና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የከፋ ችግር እንዳያስከትል በጋራ የኮቪድ-19 መከላከያ መንገዶችን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚገባቸው ኢንስቲትዩቱ አሳስቧል።


ቅጽ 3 ቁጥር 146 ነሐሴ 15 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com