የእለት ዜና

የማይቀለድበት ጎርፍ

ከሠሞኑ መነጋገሪያ ከሆኑ አጀንዳዎች መካከል በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱ የጎርፍ አደጋዎች ይጠቀሳሉ። የአንድ ቤተሰብ አባላትን ጨምሮ 7 ሰዎችን የቀጠፈው ይህ ያልታሰበ የጎርፍ አደጋ ብዙዎችን ያሳዘነ ነበር። በፍሳሽ መተላለፊያ መደፈን ምክንያት መከላከል ይቻል የነበረ አደጋ ነው በሚል ብዙዎች አስተያታቸውን ሰንዝረዋል። አሁንም ቢሆን እንማርበት የሚል መልዕክትን ያስተላለፉትም ይበዛሉ።
የሠው ሕይወትን ከነጠቀው የአንድ አካባቢው ጎርፍ ቀደም ብለው ባሉ ቀናቶች ቦሌ አየር ማረፊያ ፊትለፊት ወደ መገናኛ በሚወስደው መንገድ ለሰዓታት መንገድ የዘጋ ጎርፍ ያስከተለው የውኃ መጥለቅለቅ ተከስቶ ነበር። ሕፃናት ሲዋኙበት የነበረው ይህ ክስተት እንደ አደጋ ሳይታይ እንደመዝናኛ ተቆጥሮ በማኅበራዊ ሚዲያ ሲዘዋወር ነበር።
በሱዳን ተመሳሳይ ክስተት ተፈጥሮ ሲቀልድና እሰይ ሲል የከረመ ወጣት፣ በራሱ ሲደርስ በማዘንና እንዳይደገም ተባብሮ ከመሥራት ይልቅ ለቀልድ ምክንያት አድርጎት ነበር። በቀጣይ ቀናት በተለያየ የአዲስ አበባ ጎዳናዎች ላይ ጎርፍ ሲከሰት መኪና ማለፍ ሲቸገር ቆሞ የሚያይ በሰውም የሚቀልድ በተበላሸ መኪናም የሚሳለቅ ይታይ ነበር።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ኤርትራና ቱርክ መሔዳቸውን ተከትሎ የደመና ማዝነቢያውን መቆጣጠሪያ ሪሞት ይዘውት ሔደው ነው፣ አሊያም አጠቃቀሙን ሌሎች ሳያሳዩ በመሔዳቸው የተከሰተ ጎርፍ እንደሆነ አድርገው የተፈጥሮ ክስተቱን ሲሳለቁበት፣ ሰምተውም ሲስቁ የነበሩትን ቤታቸው ይቁጠራቸው። ሳይንሱ የማይዘንብን ደመና ለማዘነብ ተብሎ ቢነገርም፣ የተሰበሰበውን እንዳይዘንብ አልፎ እንዲሄድ ወይም እንዲበተን ማስደረጊያ ቴክኖሎጂውን ለምን ጥቅም ላይ አላደረጉም የሚል ይዘት የነበረው ሓሳብ ቢሆን የተሻለ መልዕክት ይኖረው ነበር።
ያም ሆነ ይህ ከክስተቱ ሕዝብም ሆነ መንግሥት ሳይማር ድጋሚ ተፈጥሮ ባስከተለው አደጋ ጥንቃቄ ማድረግ ያልቻሉ ሕይወታቸው እንዲያልፍ ምክንያት ሆነ። አሁንም ቢሆን ክስተቱ የትም ቦታ ሊደርስ እንደሚችል ተገንዝበን ፍሳሾችን ማጽዳት የመንግሥት ሥራ ብቻ ሳይሆን የኹላችንም መሆኑን መገንዘብ አለብን። እንደችግኝ ተከላውም ሆነ እንደድጋፍ ሠልፎቹ ሕዝቡ በዘመቻ መልክ እየወጣ በየተወሰነ ጊዜ ክረምቱ እስኪያልፍ ለራሱ ሲል በራሱ ተነሳሺነት ሊሠራ ይገባል።


ቅጽ 3 ቁጥር 146 ነሐሴ 15 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

error: Content is protected !!