የእለት ዜና

የቡራዩና አዲስ አበባ ወጣቶች ግጭት አፈታት በአስተባባሪዎች ዕይታ

 የሠላምና ልማት ማዕከል ለትርፍ ያልተቋቋም፣ መንግሥታዊ ያልሆነ አገር በቀል ድርጅት ሲሆን፣ ከማንኛውም የፖለቲካም ሆነ የሌላ ወገንተኝነት የጸዳ፣ በአገሪቱ የሠላም ባህል እንዲስፋፋ፣ በውይይት እና በንግግር የሚያምን ማሕበረሰብን ለመፍጠር የሚሰራ ተቋም ነው።
ተቋሙ ከተመሰረተበት 1982 ዓ/ም አነስቶ በተለያዩ የሠላም ግንባታ ሥራዎች ላይ ተሰማርቶ በመንቀሳቀስ ላይ ይገኛል። በተለይም ደግሞ ግጭትን ለመፍታት እና የሠላም ባህልን ለመገንባት የሚያስችሉ አገር በቀል እውቀቶችን በማዳበር በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ አለመግባባቶች በውይይት እንዲፈቱ ሲያደርግ ቆይቷል። በተለይም ደግሞ በቦታ እና በሁኔታ አለመመቸት ምክንያት ለብዙ ተቋማት ለመድረስ አመቺ አይደሉም የሚባሉ የአገራችን አካባቢዎች ጭምር ሳይቀር በመግባት ከታችኛው የማሕበረሰብ አደረጃጀቶች ጋር ሰፊ የሠላም ግንባታ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል። ተቋሙም በተሰማራበት የሥራ ዘርፍ ምንም እንኳ እንደአገር ያለብን ችግር ዘርፈ ብዙ እና ሰፊ ቢሆንም የአቅሙን በማበርከት ላይ ከመሆኑም በላይ አመርቂ የሚባሉ ውጤቶችን በማስመዝገብ ላይ ይገኛል። ተቋሙም አሁን ያሉ ፕሮጅክቶችን በማስፋት እና ወደተጨማሪ ቦታዎች በመንቀሳቀስ፣ እንዲሁም የተለያዩ ማሕረሰብ አቀፍ የሆኑ የሰላም ጥረቶችን በመደገፍ እንዲሁም አቅማቸውን ጭምር በመገንባት ለችግሮች ተመጣጣኝ የሆነ ምላሽ ለመስጠት የበኩሉን አስተዋፅኦ በማበርከት የሚቀጥል ይሆናል።
ሠላምና ልማት ማዕከል

በአዲስ አበባና ቡራዩ ወጣቶች መካከል የነበረ አለመግባባት ስር ሰዶ ደም እስከማፋሰስ ከዘለቀ ሦስት ዓመት ተቆጥሯል። ብዙዎች በፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች አቀባበል ምክንያት የተነሳ ይመስላቸው የነበረው ግጭት ከዛም ቀደም ብሎ የነበረ እንደሆነ የሚናገሩ አሉ። ለዓመታት የቆየው ግጭትና አለመግባባት ሳይሻሻል ቆይቶ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተጀመረ እንቅስቃሴ፣ የኹለቱ ከተማ ወጣቶችን ለማቀራረብና በመካከላቸው ዕርቅ ለማውረድ ተችሏል። ይህን ውጤት ለማምጣት የአንበሳውን ድርሻ የሚወስደው የሠላምና ልማት ማዕከል ሲሆን፣ ሌሎች አጋዥ አካላትና የመንግሥት ኃላፊዎች ትብብርም ነበረበት። ስለማዕከሉ እንቅስቃሴም ሆነ ስለተሳታፊዎቹ ከዚህ ቀደም ያቀረብንላችሁ ሲሆን፣ ለአሁን ውይይቱን ያስተባብሩ የነበሩትን የኹለቱን ከተማ ወጣቶች አነጋግረናል።

የአዲስ አበባ የኮልፌ ክፍለ ከተማ ወጣቶችን ወክላ ስታስተባብር የነበረችው ሠላማዊት ቸርነት ናት። 18 ማዞሪያ አካባቢ በተለምዶ መብራት ኃይል የሚባለው አካባቢ የምትኖር ሲሆን፣ በግል ንግድ የምትተዳደር የ32 ዓመት ወጣት ናት። ከመጀመሪያው ውይይት ጀምሮ ተሳታፊ የነበረችው ይህች ወጣት፣ በኹለቱ ከተሞች ወጣቶች መካከል በርካታ ችግሮች እንደነበሩ ታስታውሳለች። ካለፉት 3 ዓመታት ወዲህ ችግሮቹ ተባብሰው ታወቁ እንጂ ጎልተው የማይታዩ የውስጥ ችግሮች እንደነበሩ ትናገራለች። በዓላትን ለማክበር ወጣቶች በሚጓዙበት ጊዜ ባንዲራ ጋር በተገናኘ ችግር ይፈጠራል የምትለው ሠላማዊት፣ ያን ያህል እንደጠላት የሚያስተያይ አመለካከት አልነበረም ብላለች።

ከሦስት ዓመት ወዲህ ፀቡ እየከረረ መጥቷል የምትለው ይህች ወጣት፣ በፊት በቡድን የነበረው ተቀይሮ ወደ አካባቢ አድጓል ትላለች። የአንድ አካባቢ ወጣቶች ወደሌላው መሔድ እስኪፈሩ ድረስ ግጭቱ ከሮ እንደነበር ታስታውሳለች። ግጭት ውስጥ ለመግባት ፍላጎት ያለው ወጣት የመኖሩን ያህል ራሱንም ለመከላከል የሚጥር እንደነበር የተመለከተች ሲሆን፣ በጅምላ ጥላቻ አለ የሚለውን እንደማትቀበል ታስረዳለች። የአዲስ አበባ ወጣት ለተለያየ በዓል ወደ ከተማው የሚገቡ የቡራዩንም ሆነ የሌሎች ከተሞችን ነዋሪዎች የሚጠጣና የሚበላ እያቀረበ ማስተናገዱ የሕብረተሰቡን አመለካከት አመላካች ነው ትላለች።

በፊት የነበረው መቀራረብ ተበላሽቶ ወደ ፀብ ሊገባ የቻለው ከውስጥ ሆነው የሚገፋፉ በመኖራቸው ነው ብላ የምታምነው ሠላማዊት፣ በተለምዶ የማሕበረሰብ አንቂ በመባል የሚታወቁት ጫና ስለሚያሳድሩ ነው እንጂ ወጣቱ ያለምንም ምክንያት እንዲህ አይነት ግጭት ውስጥ እንደማይገባ ታስረዳለች። አሁን አሁን የተለያየ ብሔር ያላቸው ኹለት ሰዎች ቢጣሉ የብሔር ግጭት ተደርጎ ይወሰዳል የምትለው ይህች ወጣት፣ በእንዲህ አይነት ሁኔታ ግጭት የሚፈጠረው በጥቂት ግለሰቦች ቀስቃሽነት እንደሆነ ታምናለች።

የሠላምና ልማት ማዕከል የነበረውን አለመግባባት ለመፍታትና ወደ እርቅ እንድናመራ ለማድረግ ሲመጣ ከጥቅሙ ጉዳቱ ሊያመዝን ይችል ይሆናል ብላ ገምታ የነበረችው ይህች የአዲስ አበባ ወጣቶች አስተባባሪ፣ ወጣቶቹ ሲገናኙና ሲነጋገሩ ግጭቱ ሊባባስና ማቆም ሊያስቸግር ይችል ይሆናል ብላ ነበር። እያደር እያየችው ስትሄድ ግን እንዳሰበችው ሳይሆን አስተሳሰቧን ጭምር የቀየረ ሆኗል። ለውጥ በአጭር ጊዜ እንዲህ ይመጣል ብዬ አልገምትም ነበር ያለችን ይህች ወጣት፣ ስልጠናው በጣም ጠቃሚ ነበር ትላለች። በፊት የሚታሰበው ሽብርና ጥፋት ብቻ እንደነበር የምታስታውስ ሲሆን፣ ከማዕከሉ ሥራ በኋላ ግን የእርስበርስ ግንኙነታችን እስኪሻሻል ድረስ ውጤታማ ነበር ብላለች።

እኛ የተጠቀምነውን ለሌሎች እናስተላልፋለን የምትለው ሠላማዊት፣ የሌሎችን አመለካከት ለመቀየር እየሠራን ቢሆንም ገና ብዙ ይቀራል ትላለች። የሠላምና ልማት ማዕከል ሥራውን በኹለቱ ከተሞች ወጣት ላይ ብቻ ሳይሆን በሌሎችም አስፋፍቶ መቀጠል ስላለበት ሊታገዝ ይገባል ብላለች። ማዕከሉ እስካሁን የሠራው የሚያስመሰግነው ቢሆንም፣ ከችግሩ አኳያ መፍትሄው ገና መጀመሩ ስለሆነ በሌሎች መንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት ሊደገፍ እንደሚገባ ትናገራለች።

በሌላ በኩል፣ የቡራዩ ወጣቶችን ሲያስተባብር የነበረው ከበደ ደምሴ ጣባ ይባላል። ለቡራዩና አዲስ አበባ አዋሳኝ በሆነችው የቡራዩዋ ከታ ልዩ ቀበሌ ነዋሪ ሲሆን፣ ተወልዶ ባደገባት ከተማ በንግድ ሥራ የሚተዳደር የ36 ዓመት ወጣት ነው። ከበደ በቡራዩና አዲስ አበባ ወጣቶች መካከል የነበረውን አለመግባባት ከልጅነቱ ጀምሮ ያውቀዋል። የቡራዩ ልጆች በከተማቸው ኹለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እስከቅርብ ጊዜ ስላልነበር፣ እሱና ሌላው የቡራዩ ተማሪ አዲስ አበባ ውስጥ ባሉ ትምህርት ቤቶች ለመማር ይገደዱ ነበር። በተለይ መድኃኒዓለም ትምህርት ቤት ተማሪው ገና ሲገባ በመጣበት አካባቢ ተቦዳድኖ ለአነስተኛ ግጭት ይዳረግ ነበር የሚለው ይህ ወጣት፣ ውስጥ ለውስጥ ሲብላላ የኖረው ልዩነት ስር ሰዶ በይዘትም ጨምሮ ገሐድ የወጣው ከ3 አመት ወዲህ እንደሆነ ይናገራል።

ከበፊት ጀምሮ ግጭት ውስጥ ነበርን የሚለው ከበደ፣ የተለያዩ አካላት መጠቀሚያ ሆነን ነው የኖርነው ይላል። ማንም እየተነሳ የፍላጎቱ መጠቀሚያ ያደርገን ነበር ያለ ሲሆን፣ በተለይ ፖለቲከኞች፣ ባለሥልጣናትና ባለሀብቶች የወጣቱን ችግር መሠረት አድርገው እንደፈለጉ በማድረግ ያጋጩት ነበር ብሏል። ጥቅማቸው እንዳይቀርባቸው የሚፈልጉ፣ ሠላም ከሆነም የማይፈለጉ የሚመስላቸው፣ እንዲሁም የሠሩትን ሙስና በግርግሩ ለመሸፈን የሚፈልጉ አካላት ወጣቱን በመቀስቀስ የግል አጀንዳቸውን አስፈፃሚ በማድረጋቸው ግጭቶች የተለመዱ ነበሩ ይላል።
በቡራዩና በአዲስ አበባ ወጣቶች መካከል የነበረው ግጭት በሰፈር ወጣቶች መካከል አካባቢን መሠረት አድርጎ እንደሚከሰተው የነበረ ቢሆንም፣ እየቆየ ሲሄድ ግን ብሔርን መሰረት ያደረገ መሆኑን ብዙዎች ሲዘግቡት አንዳንዶችም ይበልጥ ሲያራግቡት የነበረ ክስተት እንደነበር ከበደ ያስታውሳል። ወጣቱ በማያውቀው ነገር፣ “ተበድለሃል” እየተባለ የጥቂቶች መጠቀሚያ መሣሪያ በመደረጉ የአንድ ቤተሰብና የዘር ሐረግ አባል የሆኑ ጭምር ጎራ ለይተው እንዲጋጩ አድርጎ ነበር።

ሠላምና ልማት ማዕከል በኹለቱ ከተማዎች መካከል የነበረውን ግጭት ለማርገብና ወጣቱን አቀራርቦ ለማስታረቅ ያደረገውን ተግባር የሚያደንቀው ከበደ፣ የመጀመሪያ ዙር ተወያይ እንደመሆኑ ሒደቱን ከመነሻው አንስቶ ያስታውሰዋል። ማዕከሉ ለማነጋገር ሲመጣ እንደተለመዱት ፖለቲከኞችና ባለሀብቶች ስለራሳቸው አውርቶ ወጣቱን ሊጠቀምበት የፈለገ ቢመስላቸውም፣ ኹለት ሦስቴ አገናኝቶ ሲያወያያቸው ዓላማውን ተረድተው በጉጉት ይጠብቁ እንደነበር አስተባባሪው ይናገራል።

በማዕከሉ ተግባር ከተለወጡ የቡራዩ ወጣቶች አንዱ እኔ ነኝ የሚለው ከበደ፣ እስከዛሬ ይጠቀሙብን የነበረውን ተረድተን ወገናችን በሆነ የሠው ልጅ ላይ መቼም እንደማንነሳ ያወቅንበት ነው ይላል። የማዕከሉ ውይይት እኛን ተሳታፊዎችን ብቻ ሳይሆን የቀየረው፣ እኛም እያገኘን የለወጥናቸውን ጭምር ነው በማለት ይናገራል። በተለያየ መንገድ ከመንግሥት አካላት ጋር በመሆን 300 ሶስት መቶ ወጣቶችን እሱና መሰሎቹ በመሰብሰብ የአመለካከት ለውጥ እንዲያመጡ እየሠሩ መሆናቸውንም አሳውቋል። በተለያየ መስክ ሥራ ፈላጊና ትምህርት እየፈለገ ያላገኘን በማደራጀት ተጠቃሚ እንዲሆኑ የማድረግ ሥራን እያከናወኑ እንደሆኑም ያስረዳል።

የሠላምና ልማት ማዕከል በኹለት ዓበይት ነገሮች ቀይሮኛል የሚለው ከበደ፣ ሰው በሰውነቱ እንዲከበር፣ ኹሉም ሰው እኩል እንደሆነና ተመሳሳይ መብት እንዳለው እንዲረዳ አድርጎታል። በፊት “ተጨቁነናል” በሚል የሚደረግ ስብሰባ ቀርቶ፣ ወጣቱን ወደሥራ የሚያስገባ፣ ሰላም የሚፈጥርና የሚያስተጋግዝ መድረክ እንዲሆን ለመቀየር እንድንሠራ አድርጓል ይላል። ከእንግዲህ ወዲያ ከተማቸው ምንም አይነት መድሎ እንዳይፈጸምባት፣ ሞትና መፈናቀልም እንዳይከሰትባት ወጣቱ በትብብር እንዲሠራ የማዕከሉ እንቅስቃሴ መጥቀሙን ይናገራል።

የበፊቱን ሳስታውስ ቁጭት ይሰማኛል የሚለው ይህ የቡራዩ ወጣቶች አስተባበሪ፣ በእጃችን ያጠፋናቸው ሲያጠፉ ያየናቸውን ስናስታውስ፣ እንዲሁም ከጎናችን የነበሩ ጓደኞቻችንን ማጣታችንን ስናስብ ከፍተኛ ቁጭት ያድርብናል ብሏል። ካለማወቅ የተሠራውን መመለስ ባንችልም ለወደፊት በምንም መንገድ እንዳይደገም፣ በቡራዩ 6ቱ ቀበሌዎች ተወካዮች ኖረውን መደራጀታችን ይጠቅማል ይላል። “ያ ሁሉ በከንቱ መሆኑ ሲታወሰኝ በጣም ይቆጫል” የሚለው ከበደ፣ የከተማው ሠላም ቀጣይነት እንዲኖረው ከዚህም በላይ ሥራው መቀጠል እንዳለበት ያምናል።

የሠላምና ልማት ማዕከል ተግባርን ሲመለከተው ከቀርቅሃ አበቃቀል ጋር ያገናኘዋል። አምስት ዓመት ሙሉ ተቀብሮ ምንም ሳያድግ እንክብካቤ የሚፈልገው ስሩ፣ በስድስተኛው ዓመት በአጭር ጊዜ ከ25 ሜትር በላይ ያድጋል። የማዕከሉንም ሥራ ሲያነጻጽረው በወጣቱ አእምሮ ውስጥ ዕውቀት ቁጭ እንደማድረግ ነው። የልፋታቸው ውጤትም ቆይቶ የሚታይ እንደሆነ ያምናል። ይህ ተግባራቸው በቂ እንዳልሆነ የሚናገረው ከበደ፣ ለወደፊት በቡራዩ ሥራቸውን አጠናክረው መቀጠል ብቻ ሳይሆን አቅማቸውን አዳብረው በሌሎች አካባቢዎችም ማዳረስ እንደሚገባቸው ይናገራል።

ማዕከሉ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ብቻውን ይወጣል ማለት ስህተት ነው የሚለው ይህ ወጣት፣ ሠላም ሚኒስቴር እንዲህ አይነት ተግባራትን ካላገዘ ምን ይሰራል ሲል ይጠይቃል። በቡራዩና አዲስ አበባ ወጣቶች መካከል ተከስቶ የነበረውን ግጭት እየተረባረቡ ሲዘግቡ የነበሩ ሚዲያዎች፣ ዕርቁን በዛው ፍጥነትና ጉጉት ለመዘገብ አለመፈለጋቸው ግርምትን እንደፈጠረበትም ይናገራል። ክፉ ነገርን ብቻ ሳይሆን መልካም ነገርንም ማስተላለፍ የሁሉም ግዴታ ስለሆነ ከተፈጠረው ክስተት መማማር እንዳሚገባ ምክሩን ይለግሳል።


ቅጽ 3 ቁጥር 146 ነሐሴ 15 2013

Comments: 0

Your email address will not be published. Required fields are marked with *

This site is protected by wp-copyrightpro.com